አዲስ አበባ፡- መንግሥት በተቆጣጠራቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሰብዓዊ አቅርቦቶችን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) አስታውቋል።
በኢትዮጵያ የማስተባበሪያ ቢሮው ዳይሬክተር ሚሼል ሳድ እንደገለጹት፤ መንግሥት በተቆጣጠራቸው አካባቢዎች የሰብዓዊ አቅርቦቶችን ተደራሽ ለማድረግ የጀመረው ጥረትና ለሰብዓዊ ድርጅቶች ያቀረበው ጥሪ
የሚደነቅ ነው። ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ወደቀያቸው መመለስ መጀመራቸው የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ የተሻለ መደላድል ይፈጥራል።
ኦቻ እና ሌሎች የሰብዓዊ ድርጅቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ማዕከላት ባሉባቸው ከተሞች ተደራሽነትን ለማሳላጥ በአፋርና በትግራይ ክልል በስፋት እየሰሩ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
በመሆኑም መንግሥት የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲዳረስ የጀመረውን ጥረት በመደገፍ አብረን እንሰራለን ነው ያሉት።
ለዚህም የሰብዓዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ቢሮው ከፌዴራል መንግሥትና ከሌሎች በተዋረድ ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር ድጋፉን ማሳለጥ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ሲመክር መቆየቱን ጠቅሰዋል።
ሚሼል ሳድ አያይዘውም በየክልሉ ያሉ ሰራተኞች ድጋፉን በፍጥነት ለማድረስ ሲጥሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ ድርጅቶች ከሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ስለእንቅስቃሴያቸው መረጃ የሚለዋወጡበት አግባብ መኖር እንዳለበት ገልጸው፤ ኦቻ በዓመታዊ እቅዱ መሰረት መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመገምገምና የድጋፍ ፍላጎትን በማጤን ወደ ተግባር ለመግባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጠቁመዋል።
መንግሥት ከአሸባሪው ሕወሓት ነጻ በወጡ የትግራይ ክልል ከተሞች የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።
አሸባሪው ቡድን ከሕዝብ ጉሮሮ ነጥቆ ለታጣቂዎቹ ለመስጠት ደብቆት የነበረውን የእርዳታ እህል ለሕዝቡ ማከፋፈሉም የሚታወስ ነው።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም