አሁን አሁን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የምናያቸው አንዳንድ ሃሳቦች ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርጉን ናቸው፡፡ በተለይ ከጥላቻ ጋር የተያያዙ አንዳንድ “መረጃዎች” ሆን ተብለው ግጭትን ለመፍጠር የተቀነባበሩ መሆናቸውን መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ አልፎ አልፎም በድምጽና በምስል ተቀነባብረው የሚቀርቡ የጥላቻ መረጃዎችን ስንመለከት እውን እነዚህ መረጃዎች በኢትዮጵያውያን የሚፃፉ ናቸው? የሚል ጥያቄንም ያጭራል::
በርግጥ የጥላቻ ንግግሮችና ሃሳቦች የራሳቸው መንስኤ እንዳላቸው ምሁራን ይገልጻሉ:: ከነዚህም ውስጥ የግለኝነትና ራስ ወዳድነት ባህል እያደገ መምጣት፣ ኃላፊነት የሚሰማው ማህበረሰብ አለመፈጠር፣ በአቋራጭ ስልጣን ወይም ሃብት የመፈለግ ስግብግብነት መንገስ፣ በልብ የሰረፀ ጥላቻና ቂም በቀል እንዲሁም የተሳሳቱ የኋላ ትርክቶች ይጠቀሳሉ፡፡
እነዚህ የጥላቻ ንግሮች ደግሞ አሁን አሁን ከማህራዊ ሚዲያውም አልፈው በተለያዩ የክልልና የግል ሚዲያዎችም ጭምር የሚንፀባረቁበት አዝማሚያ ይታያል፡፡ በራሳችን ቋንቋ ከውጭ የሚሰራጩ አንዳንድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ደግሞ እንደፈሪ ዱላ ሩቅ ሆነው የሚማቱ ፤ ከማስተማር ይልቅ በተሳሳተ መንገድ መስበክን የመረጡ ናቸው፡፡ “የሚዲያ ነጻነት” የሚለውን አጠቃላይ የዴሞክራሲ ትልቅ አውድ ሽፋን በማድረግም በተሳሳተ መንገድ ላልተገባ የጥላቻ ሃሳብ ማራመጃነት ሲውሉ ይስተዋላል፡፡
በሌላ በኩል የህብረተሰቡም የሚዲያ አጠቃቀም ገና ኋላ ቀር እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል:: በተለይ ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚለቀቁ መረጃዎችን የሚወስድበትና የሚመልስበት መንገድ መስተካከል አለበት፡፡ ለምሳሌ በፌስ ቡክ የሚለቀቁ መረጃዎችን ስንመለከት አብዛኛውን ጊዜ በጥላቻና ስድብ ላይ ያተኮሩ እና ስሜታዊነትን የሚያንፀባርቁ መረጃዎች ከጠቃሚ መረጃዎች በበለጠ ሲነበቡና ለሌላው አካልም “ሼር” ሲደረጉ ይስተዋላል:: ይህ ደግሞ መረጃዎቹ በስፋት እንዲሰራጩ እድል ይፈጥራል፡፡
ጥቂት አካላት በተመቻቸ ቦታ ላይ ተቀምጠው በሚነዙት የጥላቻ ንግግር ለጉዳት የሚዳረገው ግን በጉዳዩ ላይ ምንም አስተዋፅኦ የሌለውና ደሃው ማህበረሰብ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳን ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ተፈናቅለው በስራ የዳበረ እጃቸው ስራ ፈትቶ ለእርዳታ የተዳረጉበትን ሁኔታ ስንመለከት ጥላቻ የሚያስከትለው አደጋ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡
በሌላ በኩል የአገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለከት የወቅቱ መሰረታዊ ጥያቄ ልማት ነው፡፡ በየዓመቱም አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ስራ ፈላጊ ወጣት እየተፈጠረ ባለበት ነባራዊ ሁኔታም ስራን ፈጥሮ ድህነትን መቅረፍ ከመንግስት ብቻ ሳይሆን ከእያንዳንዱ ህብረተሰብ የሚጠበቅ ወቅታዊ ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ ረገድም መንግስት ባለው አቅም ልክ ደፋ ቀና ማለቱን ተያይዞታል፡፡ ለዚህም በየቦታው እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎችን መመልከቱ በቂ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአገራችን አምስት የኢንዱስሪ ፓርኮች ተገንብተው ወደ ስራ ገብተዋል:: በሂደት ላይ የሚገኙ ስድስት ፓርኮችም በቅርቡ ተጠናቀው ወደ ተግባር ይሸጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እነዚህ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በማህበራዊ ሚዲያው ላይ ተጥደን ከምናራግበው የጥላቻም ሆነ የግጭት አጀንዳ የበለጠ ትልቅ ፋይዳና ትርጉም እንዳላቸው ልንገነዘብና ልንጠቀምባቸው ይገባል፡፡ ርስ በርስ በተበላላንና ለግጭት በር በከፈትን ቁጥር በነዚህ የኢንዱስሪ ፓርኮች የሚጠቀም አንድም ባለሃብት ሊኖር አይችልም፡፡ በዚያው ልክም የስራ እድሎች እንደሚዘጉ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
ባለፉት ሶስት አመታት በተለያዩ አገራችን ክፍሎች በተፈጠሩ ግጭቶች የኢንቨስትመንት ዘርፉ ምን ያህል ለጉዳት እንደተዳረገ የተለያዩ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በተለይ የውጭ ባለሃብቶች በአንድ አገር ኢንቨስት ለማድረግ ቅድሚያ የሚያሰጡት ጉዳይ በአገሪቱ ያለው የሰላም ሁኔታ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ልማት የምንፈልግ ሁሉ ሰላምን ዋጋ ሰጥተን ልንከባከበው ይገባል፡፡ ምክንያቱም የልማት ዋነኛ ግብዓት ሰላም ነውና፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በድህነት ውስጥ የኖርን ህዝቦች ነን፡፡ ከዚህ በኋላ የሚከሰት ተጨማሪ ድህነት ደግሞ አጥፊያችን መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡ የጥላቻ ንግግሮችም ከግጭት ሌላ ምንም አይነት ፋይዳ እንደማይኖራቸው ተረድተን ለሰላምና ለፍቅር ዘብ ልንቆም ይገባል፡፡ በቅርቡ በአንዳንድ የአፍሪካ እና የአረብ አገራት ከተከሰቱት የርስ በርስ ግጭቶችም ትምህርት ወስደን ከግጭት መንስኤዎች በብዙ እጥፍ ልንርቅ ይገባል፡፡ ለፍቅር እንጂ ለጥላቻ ቦታ ሊኖረን አይገባም፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2011