አዲስ አበባ:- በአገራችን እየተገነቡ ከሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮች እስከ የካቲት ወር 2011 ዓ.ም ድረስ የተጠናቀቁት አምስት ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለ 43ሺህ 653 ዜጎች የሥራ እድል ማስገኘታቸውን የፓርኮቹ የልማት ኮርፖሬሽን አስታውቋል፡፡ ፓርኮቹ በየካቲት ወር ብቻ ከዘጠኝ ሚሊዮን ዶላር በላይ ምርት ወደ ውጭ መላክ እንዳስቻሉም ተጠቅሷል፡፡
የኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ፕላኒንግና ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ገመቹ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ መንግሥት ከፍተኛ ወጪን በመመደብ ይህን ዘርፍ ወደ ማልማት ሲገባ ሰፊ የሥራ እድል ከማስገኘት፣ የኤክስፖርት ምርትን በማሳደግ የውጭ ምንዛሪ ከመምጣት እንዲሁም የቴክኖሎጂና እውቀት ሽግግር ከማስገኘት አንጻር የሚኖረውን የአዋጭነት ጥናት አድርጎ ሲሆን በዚሁ መሰረትም ውጤት በማስገኘት ላይ ይገኛል።
እንደ አቶ ጥላሁን ማብራሪያ እስከ የካቲት 2011ዓ.ም ድረስ በተጠናቀቁት አምስት የኢንዱስትሪ ፓርኮች (ሀዋሳ፣ ቦሌ ለሚ፣ መቀሌ፣ ኮምቦልቻ እና አዳማ) በአጠቃላይ 43ሺህ 653 ዜጎች የሥራ እድል አግኝተው በመሥራት ላይ ሲሆኑ ሁሉም መንደሮች ተጠናቅቀው ወደ ሥራ ሲገቡ ለበርካታ ዜጎች ሰፊ የሥራ እድሎች ይፈጠራሉ።
የውጭ ምንዛሪን በተመለከተም አገሪቱ ከዘርፉ ገቢ ማግኘት ጀምራለች የሚሉት አቶ ጥላሁን በየካቲት ወር 2011 ዓ.ም ብቻ ከአምስቱ ፓርኮች 9 ሚሊዮን 27ሺህ 70 ነጥብ 28 ዶላር (የእቅዱን 44 በመቶ) የሚያወጣ ምርት ወደ ውጪ መላክ የተቻለ ሲሆን፣ ይህም የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ አቅም እየጎለበተ ሲሄድ ምርታቸው እያደገ እንደሚመጣና የአገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ፍላጎት እጥረት እንደሚያቃልል ተናግረዋል፡፡ ለስኬታማነቱም በርትቶ መሥራት እንደሚገባ አስታውቀዋል።
ቀሪዎቹና ያልተጠናቀቁት ስድስት የኢንዱ ስትሪ ፓርኮች (አዳማ፣ ድሬ ዳዋ፣ ቂሊንጦ፣ ቦሌ ለሚ ምእራፍ ሁለት፣ ባህር ዳር እና ደብረ ብርሃን) ግንባታ የማጠናቀቅና ወደ ሥራ የማስገባቱ ሥራ በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እየተከናወነ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ አማካይ አፈፃፀማቸውም ከ76 በመቶ በላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡ ዝርዝሩን በተመለከተም አዳማ 86 በመቶ፣ ድሬዳዋ 94.5 በመቶ፣ ጅማ 100 በመቶ፣ ቂሊንጦ 86.43 በመቶ፣ ቦሌ ለሚ II 92.35 በመቶ፣ ባህር ዳር 76.86 በመቶ እንዲሁም ደብረ ብርሃን 90.35 በመቶ መጠናቀቃቸውንና ወደ ኦፐሬሽን ለማስገባት የሚያስችል ደረጃ ላይ መድረሳቸውንም አስረድተዋል።
ኮርፖሬሽኑ የያዛቸውን ከማጠናቀቅ ውጪ አሁን ሌሎች ፕሮጀክቶችን የመጀመር እቅድ የለውም የሚሉት አቶ ጥላሁን «ለጊዜው ትኩረታችን የተጀመሩትን ማጠናቀቅ ላይ ሲሆን እግረ መንገዳችንንም ወደፊት ሊገነቡ ስለሚገቡ ፕሮጀክቶች ጥናት እያካሄድን እንገኛለን» ብለዋል፡፡
በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችን በተመለከትም ወደ ሥራው ከገቡት ባለሀብቶች አብዛኛዎቹ የውጭ ዜጎች ናቸው። የሚጠበቀው እና የሚፈለገው ግን የሀገር ውስጥ ባለ ሀብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩና ዘርፉ በአብዛኛው በአገር ውስጥ ባለሀብቶች እንዲያዝ ነበር። ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች ይህ ሊሆን አልቻለም። ወደፊት የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በመደገፍም ሆነ ግንዛቤን በማስጨበጥ ወደ ዘርፉ እንዲመጡ ከማድረግ አኳያ ብዙ መሠራት አለበት። በተለይ ከኢንቨስትመንት ፅህፈት ቤት ጋር በመተባበር ሊሠሩ የሚገባቸው ሥራዎችን ጠንክሮ መሥራት ለነገ የማይባል ነው።
ከኮርፖሬሽኑም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተጨማሪ መገናኛ ብዙኃንም የየድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል የሚሉት ዳይሬክተሩ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ እንዲመጡም ሆነ የኢንዱስትሪ ፓርኮቹ አጠቃላይ ያሉበትን ሁኔታ ለህዝብ ከማሳወቅ አኳያ የሀገራችን መገናኛ ብዙኃን የሚጠበቅባቸውን ተወጥተዋል ማለት አስቸጋሪ መሆኑን፤ ወደፊት ከኮርፖሬሽኑ ጋር አብሮ መሥራትና ለህዝቡ ትክክለኛ መረጃን መስጠት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ ከሠራተኛ መብትና ጥቅም ጋር ያሉ ችግርች፣ በሠራተኞች በኩል የተወዳዳሪነትና ምርታማነት አቅም፣ ከኩባንያዎች የፋብሪካ ሼዶችን የመጠቀም፣ የተገነቡ የፋብሪካ ሼዶችን በአፋጣኝ በባለሀብቶች በማስያዝ የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥን የማቀላጠፍ፣ ሰፊ ቁጥር የሚይዘውን የሴት ሠራተኞችን ችግር ሊቀርፍ የሚችል የቤት አቅርቦት እጥረት እና የመሳሰሉት በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶች ናቸው የሚሉት አቶ ጥላሁን እነዚህ ከተፈቱ ፓርኩቹ ምርታቸውን በማሳደግ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚገመት አይሆንም በማለት የሚመለከተው ሁሉ የጋራ ርብርብ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
በፌዴራል መንግስት አማካኝነት አስራ አንድ የኢንዱስትሪ ፓርኮች በመልማት ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ አምስቱ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቀው ወደ ሥራ መግባታቸውና ቀሪዎቹም በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸው ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 30 /2011
ግርማ መንግስቴ