ልጅ ሆና ጥልቅ የሆነ የኪነጥበብ ፍቅር ነበራት:: ትምህርት ቤት ሳለች በኪነጥበብ ክበቦች ንቁ ተሳታፊ ነበረች:: የኪነጥበብ ፍቅር ሙያዊ ጉዳዮችን ለመመልከትና ወደወደደችው አንድ ሙያ ለመሳብ ምክንያት ሆኗታል:: ይህም በሆሊውድ የሚቀርቡ የተለያየ ዘውግ ያላቸው ፊልሞችን መከታተል ልማዷ እንዲሆን አድርጓል። ይህ ደግሞ አንድ ነገር ላይ ልቧን አሳረፈው። በፊልሞቹ ውስጥ የሚታዩ የሜካፕ ስራዎች:: በምታያቸው ፊልሞች ላይ በሜካፕ ስራዎች መማረክና እሷም ያንን የሜካፕ ሙያ የማወቅ ጥረት አሳደረባት። የሜካፕ ባለሙያዋ ሰዓዳ አበበ::
በፊልሞች ላይ ገጸ ባህሪያት የሌላ ሰው መልክ አልያም የሚፈለገውን ገጸ ባህሪ የማስመሰል የሜካፕ ጥበብ (prosthetic makeup) በተለየ ይማርካትና ስራው ምን እንደሆነ መመርመር ጀመረች:: እዚያ ውስጥ የምታያቸው የሜካፕ ጥበቦችን በተለያየ መንገድ መማርም ስራዋ ሆነ::
ይህ ሙያው ላይ ከፍተኛ ፍላጎት አሳደረባትና በራሷ እንድትሞክር መንገድ ሆናት:: ቤት ውስጥ የተለያዩ የመዋቢያ ቁሳቁሶችን በመጠቀም በራሷና አቅራቢያዋ ባሉ ቤተሰቦቿ ላይ መስራት ጀመረች:: ቤተሰቦቿም የምትሰራውን አይተው ሲያደንቁላት ደግሞ የበለጠ መነሳሳት ተፈጠረባት:: ገንዘብ ስታገኝ ወደ መዋቢያ እቃዎች መሸጫ ሱቆች መሄድ አዘወተረች:: እዚያ የገዛችውን እቤት ካለው ጋር እያቀላቀለች አዳዲስ የሜካፕ ስራዎችን በመሞከር ራሷን ማስተማር ላይ ትኩረት አደረገች::
ይህ ቤት ውስጥ የምታደርገው ጥረት ከፍ ወዳለ ደረጃ የሚያደርስ አንድ አጋጣሚ ፈጠረላት:: የሜካፕ ሙያ ትምህርት ቤት ገብታ የመማር ፍላጎት ቢኖራትም አጋጣሚውን ማግኘት ሳትችል ቀረች:: በሌላ በኩል ግን ከልጅነቷ ጀምሮ ትወደው የነበረው የፊልም ሙያ ጥበብ ለመማር አንድ ትምህርት ቤት ገባች:: በዚያም ከፊልም ሙያተኞች ጋር የመገናኘትና ያላትን የሜካፕ ስራ ክህሎት እንዲሁም የመስራት ፍላጎት ለመናገር እድል ሲገጥማትም ስራዎቿን ማሳየት ጀመረች:: የፊልም ባለሙያዎችም የምትሰራቸውን የሜካፕ ስራዎች ይወዱላትና ያበረታቷት ጀመር:: ይህም መስራት እንደምትችል አረጋገጠላት።
በሂደትም እየተማረች ባለችበት የፊልም ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም ውስጥ የሚሰሩ የተለያዩ አጫጭር ፊልሞች ላይ በሜካፕ ስራ መሳተፍ ጀመረች:: ይህም ብዙዎች ስራዋን አጠንክራ እንድትይዝ ገንቢ አስተያየት እንዲሰጧትና ከፊልም ሰሪዎች ጋር በመገናኘት ወደ ስራ መግባት አስቻላት። ሁሌም እራሷን በሙያው የተሻለ ቦታ ማድረስ የምትፈልገው ሰዓዳ አዳዲስ ነገሮችን መሞከርና በሜካፕ ስራው የተለየ ነገር ለመስራት ጥረቷን ቀጠለችና ተወዳጅ ባለሙያ ለመሆን በቃች::
አሁን ላይ አገራችን ላይ ከተመረጡ የሜካፕ ባለሙያዎች መካከል የምትመደበውና በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ የምትገኘው የሜካፕ አርቲስቷ ሰዓዳ፣ የተለያዩ የሜካፕ አይነቶችን በመስራት በሙያው ላይ ያላት ክህሎት ጥልቅ መሆኑን አሳይታለች:: በስራዋ ውስጥ የተለያዩ ጉዳዮችን በሜካፕ ለማሳየትም ትሞክራለች:: የሴት ልጅ ጥቃት፣ የዓለም የአየር ፀባይ ለውጥ፣ ስለ ሰላም፣ ስለ አገር፣ ስለ ዘረኝነትና ወቅታዊ ጉዳዮችን በተሰጣት ሙያ ማንፀባረቅ ያስደስታታል::
ከምትሰራቸው ዘርፍ ብዙ የሜካፕ ስራዎች በተጨማሪ በፊልም ደረጃ ወደ 32 ፊልሞች ላይ ተሳትፎ አድርጋለች:: ከሜካፕ ሙያ በተጨማሪ አንዳንዶቹ ፊልሞች ላይ በትወናም ተሳትፎ አድረጋለች:: ከተሳተፈችባቸው ፊልሞች መካከል ኪያ፣ ክሱት፣ መላ፣ የተረት ሎሚ፣ ዶቃ (ዶቃ በቅርቡ የሚወጣ)፣ የሴት ልጅ ዝምታ፣ ሞት እምቢ፣ ልዋጭ፣ ጥቁር እና ነጭ 2፣ ሲሳይ ነው፣ ሚስት ጨርሰናል እና በ4 ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ ተሳትፋ ችሎታዋን አስመስክራለች::
በሙዚቃ ክሊፕ ከነ ወንድሙ ጂራ፣ ሀሊማ አብዱራህማን፣ አብነት ግርማ፣ ኮሜዲያን ቶማስ፣ ሚኪያስ ወልዴ እና ሌሎችም ጋር ሰርታለች:: በአጫጭር ፊልሞች ደግሞ “Love and the Brain” እና “The Trip” በተባሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለውድድር በቀረቡ ፊልሞች ላይ በመሳተፍ ከቡድን አጋሮቿ ጋር ሽልማትን አግኝታለች::
ሙያው አሁን ላይ ያለበት ደረጃ ሙሉ ለሙሉ መልካም ነው ማለት እንደማይቻል የምትናገረው ሰአዳ፣ አንዳንድ የሙያውን ኃያልነት የሚያውቁ እና ሙያውን ከልባቸው የሚያከብሩት ደራሲያን፣ ዳይሬክተሮች እና ፕሮውዲሰሮች በደንብ እየተጠቀሙበት መሆኑን በስራ አጋጣሚ የተመለከተችውን ታስረዳለች:: ነገር ግን ይህን ያልተረዱ ሰዎች ስራውንም አጣጥለው ሙያተኛው የሚፈልገውን ሳይሰራ የሚገባውን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ክብርና ልምድ ሳያገኝ የሚያልፍበት ጊዜ እንዳለ ታስረዳለች። የሙያው ክብር የሚገባቸውና ጥቅሙን የሚረዱ ሰዎች ሲበረክቱ አንድ ቀን የኢትዮጵያን የፊልም ኢንዱስትሪ በሜካፕ ሙያ ከፍ ወዳለ ደረጃ ማድረስ እንደሚቻል ግን ያላትን ተስፋ ትናገራለች።
በውጭው ዓለም የሜካፕ ሙያ እጅጉን ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን የምታስረዳው ሰዓዳ፤ ከሀሳብ ጀምሮ በቁሳቁስ አቅርቦት፣ የባለሙያው ነፃነት፣ የባለሙያው ክፍያ ለሙያው የሚሰጠው ክብርና በጋራ የመስራት ፍላጎት ከእኛ አገር አሰራር ጋር ትልቅ ልዩነት እንዳለው ትገልፃለች::
“በፊት ላይ በአንዳንድ ማህበረሰብ ዘንድ በሙያው ላይ ያለው አመለካከት ከባድ ነበር” የምትለው ሰዓዳ፣ የምትሰራቸውን አንዳንድ ስራዎች በማህበራዊ ሚዲያ በምትለቅበት ጊዜ በአስተያየት መልክ “የሴይጣን ስራ ነው የምትሰሪው” ትባል እንደነበር ትናገራለች:: ነገር ግን አሁን ላይ ሜካፕ ትልቅ ሙያ መሆኑን ሰው እየተረዳው መሆኑን ትናገራለች:: ሙሉ ለሙሉ ነቀፌታው ባይጠፋም ሰው ማበረታታ እየለመደ መሆኑንም ታብራራለች::
“ለሙያው እድገት እኛ ባለሙያዎች በራሳችን ማድረግ ያለብን አስተዋጽኦ እንዳለ ሆኖ የፊልም ደራሲያን፣ ዳይሬክተሮች፣ ፕሮውዲሰሮች የሚሰሩት ስራ ላይ የሜካፕ ባለሙያዎችን በደንብ ሊያሰሩ የሚችሉትን ታሪኮች መፃፍ ከለመዱ፣ የፊልም ዘውግ ደግሞ ወጣ ብሎ (science fiction .. thriller .. horror.. action) ፊልሞችን መስራት ይገባቸዋል:: ማህበረሰቡም የሙያውን ትልቅነት ተረድቶ ቢያከብረው እንዲሁም የሚሰሩ ሰዎችን ማበረታታት ቢቻል መልካም ውጤት ላይ መድረስ” ይቻላል ትላለች።
“ሙያውን ለሚፈልግ ሰው ደራሽ መሆን እፈልጋለሁ” የምትለው ሰአዳ፣ ሙያተኞች የትም ሳይለፉ አጠገባቸው የመሆን ሃሳብ እንዳላት ታብራራለች። “አላህ ከረዳኝ ማሰልጠኛ ተቋም ከፍቼ ሙያውን ማወቅ የሚፈልጉ ሰዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ ማለት እፈልጋለሁ:: ኢንሻአላህ ሌሎችም ብዙ እቅዶች አሉኝ ሁሉም እንደሚሳኩ ተስፋ አረጋለሁ” በማለትም ምኞትና የወደፊት እቅዷን ትገልፃለች።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2015