ሰልፍ መያዝና ወረፋ መጠበቅ የእለት ከእለት አንዱ ተግባራችን ከሆነ ቆይቷል። ቢያንስ በቀን አንዴ ለሆነ ነገር እንሰለፋለን ወይም ረጅም ሰዓት ወረፋ እንጠብቃለን። በተለይም በመዲናችን አዲስ አበባ የማንሰለፍበት ወይም ወረፋ የማንጠብቅበትን ጉዳይ አውጥተን አውርደን አናገኝም ቢባል አልተጋነነም። ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ፣ ስራ ለመግባትና ከስራ ወደ ቤት ለመሄድ ረጃጅም የታክሲ ሰልፎችን እግራችን እስኪቀጥን ቆመን መጠበቅ እንደ አንድ የስራ አካል ሆኖ ስለተለመደ ወደ ጎን እንተወው። ዳቦ ለመግዛት ሰልፍ፣ ወደ ተቋማት ጎራ ብሎ የፈለጉትን አገልግሎት ለማግኘት ወረፋ፣ የመብራትና ውሃ ክፍያ ለመፈጸምም እንደዛው። ብቻ ምን አለፋን አልተሰላም እንጂ በእለት ከእለት እንቅስቃሴያችን ለስራ ከምናውለው ሰዓት በሰልፍና በወረፋ የምናቃጥለው ሰዓት ጆሮን ጭው ሊያደርግ ይችላል።
በታክሲ፣ በዳቦ፣ በዘይትና ስኳር መሰለፍ የተለመደ ብርቅም ያልሆነ የሕይወታችን አንዱ አካል በመሆኑ ወደ ዋናው ጉዳይ እንግባ። የባንኮች ጉዳይ። እነ ታክሲና ዳቦስ አማራጭ ስለሌለን ተሰለፍን። እንደ አሸን እየፈሉ የሚገኙ ባንኮቻችን የገዛ ገንዘባችንን ለማንቀሳቀስ የሚያሰልፉንና ረጅም ሰዓት ወረፋ የሚያስጠብቁን ነገር ግን ያበሳጫል።
ባንኮች አካውንት ካልከፈታችሁ ብለው በየመንገዱ ብቻ አይደለም የሚያስቸግሩን። በየቢሮውም እየሄዱ ፍጹም ትህትናና ያገልጋይነት መንፈስ ተሞልተው ከሌለን ላይ ጭምር እንድንቆጥብ ማሳመን አይሳናቸውም። አገልግሎታቸውን ፈልገን ደጃቸው በጠናን ወቅት ግን የቀድሞ ትህትናቸው እምጥ ይግባ ስምጥ እነሱ ብቻ ናቸው የሚያውቁት።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባንኮችም እንደ ታክሲና ዳቦ ቤቶች ተገልጋዮችን ረጅም ሰልፍ ካላሰለፉ የአገልግሎት ሰጪነት ፍላጎታቸው አልከፈት እያለ ነው። ባንኮችን ከታክሲዎችና ዳቦ ቤቶች የሚለያቸው ሃብታም ድሃ፣ ወንድ ሴት ብለው ሳይለዩ ሁሉንም ለሰልፍና ወረፋ መዳረጋቸው ነው። ሃብታም ሲባል ግን ግዙፎቹን ከበርቴዎች እንዳልሆነ ግልጽ ነው። በግል ስራ የሚንቀሳቀሱ ነገር ግን በየእለቱ ከተቀጣሪ ሰራተኞች የተሻለ ገንዘብ የሚያንቀሳቅሱትን ለማለት ያህል ነው። መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ማለት ሳይቀል አይቀርም። ከቤተሰቡ የተላከለትን ሁለት መቶ ብር ከሚያወጣ ተማሪ ጀምሮ የታሰሩ ረብጣ ብሮችን እስከሚያስገባ ነጋዴ ድረስ ሁሉም በባንኮቻችን ወረፋ ጠባቂ ነው።
በተለይም ባንኮች በሰልፍና ወረፋ ተጨናንቀው የታክሲ ተራ የሚመስሉበት የደመወዝና የበዓላት ወቅቶች ያላማረሩት ሰው የለም። በእርግጥ ባንኮች ሲባል ሁሉንም መኮነን እንዳይሆን ብዙዎቹ የግል ባንኮች ላይ ይህ ችግር ጎልቶ አይታይም። የመንግስት ባንኮች ግን እንኳን የደመወዝ ወቅት ወትሮውንም እንዳንገላቱን ነው። እንግልት መፈጠሩ ሳይሆን የሚፈጠርበት ምክንያት ደግሞ ከሁሉም አናዳጅ ነው። ከተገልጋዮች ብዛት አኳያ መጨናነቆች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ በቀናነት ልናስብ እንችላለን። ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አይነት ብዙ የባንክ ቅርንጫፎች ያላቸው የፋይናንስ ተቋማት በርከት ያሉ የአገልግሎት መስጫ መስኮቶች ይዘው ለአገልግሎት ክፍት ሆነው የምናገኛቸው በጣት የሚቆጠሩትን ብቻ መሆኑ ልንወቅሳቸው ከበቂ በላይ ምክንያት ነው። እግር ጥሎን ወደ አንዱ ባንክ ቅርንጫፍ ጎራ ካልን አንዳንድ የባንክ ሰራተኞች አገልግሎት የሚሰጡበትን መስኮት ጥለው በሌላ ስራም ይሁን በግል ወሬ ተጠምደው ልናገኛቸው እንችላለን። ተገልጋይ ተሰልፎ እያዩ እንኳን አይሞቃቸውም አይበርዳቸውም።
ብዙ ጊዜ በደመወዝ መቀበያ ወቅት በተለይም የኤቲኤም ካርድ የማንጠቀም ወይም በካርድ ማውጣት ከሚፈቀደው የገንዘብ መጠን የበለጠ ለማውጣት የምንፈልግ ሰዎች በቡክ አገልግሎት ለማግኘት ጎራ እንላለን። ወረፋ መጠበቂያ ቁጥራችን ያረፈባት ብጫቂ ወረቀት ይዘን ረዘም ላለ ደቂቃ ጠብቀን አገልግሎት ወደምናገኝበት መስኮት እናመራለን። ከዚያም የባንክ ባለሙያዎች ደመወዝ በኤቲኤም ካርድ ለምን አታወጡም በሚል የራሳችንን ሳይሆን የእነሱን ገንዘብ እንዲሰጡን የጠየቅን በሚመስል ቁጣና ግልምጫ ሊመልሱን ይችላሉ። እሺ በካርድ መጠቀም ስልጣኔ ነው ብለን እንቀበል።
ካርዱን የምንጠቀምባቸው የኤቲኤም ማሽኖች በየባንኮቹ ቅርጫፎች በብዛት ተገትረው አገልግሎት የሚሰጡት ግን እጅግ ጥቂቶቹ የመሆናቸው ጉዳይስ?። እንዲያውም በደመወዝ ወቅት አገልግሎት የሚሰጡ ማሽኖችን ከረጅም ሰልፍና ወረፋ ጋር በአቅራቢያችን ፈልገን ካገኘን እድለኛ ነን ማለት ነው። የኤቲኤም ማሽኖች እዚያው ባንኩ በር ላይ ቆመው ለረጅም ጊዜ ወይ አገልግሎት አይሰጥም ወይም ብር የለውም ወይ ደግሞ በጥገና ላይ ነው የሚሉት ነገር ይበልጥ ያበሳጫል። እዚያው የባንኩ ቅርንጫፎች ጋር የቆሙ ማሽኖች በሲስተምም ይሁን በሌላ ችግር ላይሰሩ ይችሉ ይሆናል። ግን ለረጅም ጊዜ እዚያው አጠገባቸው ቆመው መላ የሚፈጥርላቸው ጠፍቶ ደመወዛችንን ለመውሰድ ወረፋ ሲያስጠብቁን ማየት ግዴለሽነት እንጂ ሌላ ምን ይባላል።
የባንኮችን ብቻ ሃጢያት ማብዛት እንዳይሆንብን የእኛ ተጠቃሚዎችንም ችግር ማንሳት ተገቢ ነው። በተለይም ከኤቲኤም አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ብዙ ጊዜ አንድ ችግር አለብን። የያዝነውን የኤቲኤም ካርድ መጠቀም የምንፈልገው ካርዱን ካወጣንበት ባንክ ማሽን ብቻ ነው። አገልግሎት መስጠት የሚችሉ የሌሎች ባንኮች ማሽኖች አጠገባችን እያሉ ካርዱን ያወጣንበት ባንክ ማሽን ካልሆነ ብለን ረጅም ሰልፍ መጠበቅን የምንመርጠው ነገር አለ። አንዳንዶቻችን ይሄን የምናደርገው ካለማወቅ ነው። አንዳንዶቻችን ደግሞ ካርዱን የሰጠን ባንክ ማሽን ለአገልግሎት ከሚቆርጥብን ገንዘብ በላይ በሌላ ማሽን ስንጠቀም የሚቆርጥብንን ገንዘብ አስልተን ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከምንጠብቀው ወረፋና ሰልፍ አኳያ የያዝነውን ካርድ ባገኘነው ማሽን ብንጠቀም ልዩነቱ ያን ያህል የጎላ አይደለም። እዚህ ጋር ያለውም የሲስተም ችግር መዘንጋት የለበትም። እናም ባንኮች ሆይ ወደ ዘመናዊ(ዲጂታል) አሰራር ለመሸጋገር ከምታደርጉት ጥረት ጎን ለጎን ደንበኞቻችሁ በጥቃቅን ክፍተቶች የሚጉላሉበትን ነገርም አስቡበት።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2015