አዲስ አበባ፡- በቅርቡ ተመርቆ ለዕይታ ክፍት የተደረገው የሳይንስ ሙዚየም በተለያዩ ደረጃዎች የሚፈጠሩ የፈጠራ ስራዎች በፍጥነት ወደ ቴክኖሎጂ እንዲቀየሩ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንዳለው በፈጠራ ስራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ተናገሩ።
ድሮን ፈጠራ ስራ ላይ የተሰማሩት የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ መምህር አማኑኤል ባልቻ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ ሳይንስ ሙዚየም በፈጠራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ስራ በፍጥነት ተቀባይነት አግኝቶ ወደ ቴክኖሎጂ እንዲቀየር ያደርጋል። ቴክኖሎጂን ያለፈጠራ እውን ማድረግ አይቻልም፣ ሀገር የምትፈልገውን ቴክኖሎጂ ለማስገኘት ፈጠራ ስራ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
እንደ መምህር አማኑኤል ገለጻ፤ ዓለም በሰው አእምሮ የተፈጠሩ ነገሮችን በማበልጸግ የማህበረሰቡን ችግሮች መፍታት ወደሚያስችል ቴክኖሎጂ በማሸጋገር ላይ ትገኛለች። እንደ ሀገር የሚያስፈልጉንን ቴክኖሎጂዎች ለማሳደግም እሳቸው ከዘመኑ ቴክሎጂዎች አንዱ በሆነው የድሮን ቴክኖሎጂ ላይ ተሰማርተዋል። እስከ አሁን ድረስ በሰሩት የፈጠራ ስራ ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ዘጠኝ ድሮኖች መፍጠራቸውንም ገልጸዋል።
በፈጠራ ስራቸው ከተሰሩ ድሮኖች በአብዛኛው በግብርና ዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያገለግሉ ናቸው ያሉት መምህር አማኑኤል፣ 500 ሚሊ ሊትር ኬሚካል ይዞ መብረር የሚችል ድሮን መፍጠር እንደቻሉ ገልጸዋል።
በጤና ዘርፍ የደም እጥረት ባለበት ቦታ በፍጥነት በመድረስ፣ ትላልቅ ህንጻዎች በሚገኙበት አካባቢ በእሳት አደጋ ማጥፊያ ኬሚካሎችን በፍጥነት በማድረስ አደጋን ለመቀነስ የሚያስችሉ ድሮኖች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
ኮምፒውተር ኢንጅነሪግ ምሩቅና ያለ ክፍያ አገልግሎት የሚሰጥ ስልክ ፈጠራ ባለቤት የሆኑት ኤስራኤል ቤለማ በበኩላቸው ሳይንስ ሙዚየም በፈጠራ ስራ ላይ ተሰማርተው በመስራት ላይ ለሚገኙ የፈጠራ ባለሙያዎች ስራቸው በፍጥነት እንዲታወቅ በማድረግ ወደ ቴክኖሎጂ የሚደረገውን ጉዞ ያፋጥናል ብለዋል።
ያለ ክፍያ አገልግሎት የሚሰጥ ስልክ ከፈጠሩ በኋላ ባለችበት ቦታ መረጃ መስጠት የሚያስችል የመኪና ደህንነት ፈጠራን መፍጠራቸውን ገልጸው እስከአሁን ድረስ በሰሩት ፈጠራ ስራ ሦስት የአዕምሮ ፈጠራ ባለቤትነት መብት (patente right ) እና 36 ዓለም አቀፋዊ ምስክር ወረቀት በማግኘት ‘Young gneiss Ethiopian the first Africa ‘’ በመባል ዕውቅና አገኝቷል።
በአገኙት እውቅና የተለያዩ ልምዶችን በመቅሰም ከዩኒቨርሲቲ የወጡ ስራ ለሌላቸው ወጣቶች በኮምፒዩተር ጥገና ፣ በሶፍትዌር ስራ እና በተያያዙ ፈጠራ ስራ ፕሮጀክቶች ስልጠና በመስጠት ለ10 ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጥረዋል።
በተመሳሳይም ከተሞችን ስማርት በማድረግ በሱሉልታ በጣፎ ከተማ ወደ ስማርት ከተማ ለማስቀየር የሚያስችሉ ድጋፎችን በመስጠት ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው በፈጠራ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች በትኩረት በሳይንስ ሙዚየሙ እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በፈጠራ ስራ ላይ ተሰማርቶ በመስራት ላይ የሚገኙት አቶ ሐምባ አብዲሳ ዓለማችን በሰው ጉልበት የሚሰሩ ስራዎችን ወደ ዲጅታል ለመቀየር እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ጠቅሰዉ እንደ ሀገር ወደ ዲጅታል የሚደረገውን ጉዞ ለመቀላቀል ሳይንስ ሙዚየሙ በፈጠራ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን የሚያበረታታ ነው ብለዋል።
ቀጣይ ትውልድ በቲዮሪ የሰማውን በተግባር በማየት ወደ ተክኖሎጂ የሚያደርሰውን ፈጠራ ስራ በማጠናከር ለሀገሪቱ የሚያስፈልጉ ቴክኖሎጂዎች ለመፍጠር በር የሚከፍት ጅማሮ ነው በማለት ገልጸዋል።
ገመቹ ከድር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2015 ዓ.ም