
በቅርቡ በዩጋንዳ ዳግም የተቀሰቀሰው የኢቦላ ወረርሽኝ በአጭር ጊዜ ውስጥ የ19 ሰዎች ሕይወት በመቅጠፉ በአገሪቱ ላይ ትልቅ ሥጋት ደቅኗል።
ዩጋንዳ የወረርሽኙ ፍጥነት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ በአንዳንድ አካባቢዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ተገዳለች። በአገሪቱ በሙቤንዴና በካሳንዳ ወረዳዎች ሆቴሎች፣ የዳንስ ምሽት ክበቦች፣ የአምልኮና የሕዝብ መዝናኛ ቦታዎች እንዲዘጉ ከመደረጋቸው በተጨማሪ ሰው ከቤቱ እንዳይወጣ የጊዜ ገደብ ለመጣል እንቅስቃሴ ላይ መሆኑ ተገልጿል።
የበሽታውን ስርጭት በተቻለ መጠን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመግታት በታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሁለቱ ወረዳዎች ከጭነት መኪናዎች ውጭ ምንም ዓይነት የትራንስፖርት እንቅስቃሴ አለመኖሩን ተነግሯል።
የዩጋንዳው ፕሬዚዳንት ዩዌሪ መሴቬኒ ቀደም ሲል በሽታው እንደ ኮሮና ወረርሽኝ በአየር የሚተላለፍ ባለመሆኑ በወረርሽኙ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ሌሎች ገደቦች ማስቀመጥ አላስፈላጊ መሆኑን ቢገልጹም፣ በሽታው በአጭር ጊዜ ውስጥ ካጠቃቸው 58 ሰዎች 19 ላይ የሞት አደጋ በማድረሱ በፕሬዚዳንቱ ዘንድ በተፈጠረው ድንጋጤ የአቋም ለውጥ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል።
በወረርሽኙ የተጠረጠረና ወደ ሕሙማን ማቆያ መግባት ፍቃደኛ ያልሆነው ማንኛውም የአገሪቱ ዜጎች ላይ ፖሊስ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ ትእዛዝ ማስተላለፋቸውንም ቢቢሲ አክሎ ዘግቧል።
ቀደም ሲል በባህላዊ መንገድ ወረርሽኙን ለማከም የተደረገዉ ጥረት ለበሽታው መስፋፋት ሞቹ ሁኔታን በመፍጠሩ በባህላዊ ዘዴ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲቆምም ፕሬዚዳንቱ ትእዛዝ ሰጥተዋል።
አሁን ላይ ይፋ የተደረገው የሟቾች ቁጥር 19 ይባል እንጂ ቁጥሩ ከዚያ በላይ ሊሆን እንደሚችል የተነገረ ሲሆን ወረረሽኙ በስፋት የተከሰተባቸው አካባቢዎች ከአገሪቱ ርዕሰ መዲና ከካምፓላ በቅርብ ርቀት ላይ መሆናቸው ደግሞ ሌላ ሥጋት ፈጥሯል።
ኢቦላ ወረርሽኝ እ.ኤ.አ ከ2013 እስከ 2016 በምዕራብ አፍሪካ ብቻ የ11 ሺህ ሰዎች ሕይወት በመቅጠፍ ትልቅ ጠባሳን ጥሎ አልፏል።
ወረርሽኙ የሚተላለፈው ከሰውነት የሚወጡ ፈሳሾች ጋር ንኪኪ በማድረግ እንዲሁም በተበከሉ ቀሳቁሶች ጋር በሚደረግ ንኪኪ ሲሆን ምልክቶቹም ትውከት፣ ተቅማጥ፣ ከፍተኛ ትኩሳት፣ የሰውነት መዛል፣ የጡንቻዎች ህመም፣ የአፍ ምሬት እና የውስጥና የውጭ አካል ክፍሎች መድማት ናቸው። በሽታው ከወባና ከታይፎይድ ጋር ግንኙነት እንዳለውም ተገልጿል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8/ 2015 ዓ.ም