የፋሽን ኢንዱስትሪው ዕድገት ለአገራዊ ኢኮኖሚ ያለው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው። በዓለማችን እጅግ ትኩረት ከሚሰጣቸው መስኮች መካከል አንዱ የሆነው ፋሽን፤ አገራት በየዓመቱ ቢሊዮን ዶላሮች ያፍሱበታል። በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በዓመት ከ 1 ነጥብ 4 ትሪሊዮን ዶላር በላይ የሚደርስ እጅግ ከፍተኛ የሆነ መዋዕለ ነዋይ የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህም ዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ ከተሠራበት ትልቅ ገቢ የሚያስገኝ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
በመሆኑም ፋይዳውን ቀድመው የተረዱት አገራት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው በመሥራታቸው በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ለኢኮኖሚ እድገታቸውም ትልቅ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል። አገራችን ኢትዮጵያም ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ ብትሠራ በተመሳሳይ ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል ሰፊ ነው። ኢንዱስትሪው ሊፈጥረው ከሚችለው ሰፊ የሥራ ዕድል በተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ ችግርን በመቅረፍ በኩል የሚኖረው ሚናም ትልቅ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የፋሽን ኢንዱስትሪው በየዓመቱ ከፍተኛ እድገት ከሚያስመዘግቡ ዘርፎች መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀስ በመሆኑ ሰፊ የሆነ የገበያ ዕድል የሚፈጥር ነው። ይህንን ለመጠቀም ደግሞ እንደ አገር ትኩረት ሰጥቶ መሥራት የሚገባ መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። ፋሽን የዓለማችን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ በመቆጣጠር ላይ የሚገኝ ዘርፍ መሆኑን የምትናገረው ዲዛይነር ብርቱካን ፋንታሁን፣ አገራችንም ለዚህ መስክ ትኩረት ሰጥታ ብትሠራ በከፍተኛ ደረጃ ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል መኖሩን ታመላክታለች።
«ፋሽን የአገራችን ኢኮኖሚያዊ አቅም መገንቢያ በመሆን እያገለገለ ይገኛል» የምትለው ባለሙያዋ ብርቱካን፤ የፋሽን ውጤቶችን በብዛትና በጥራት በማምረት ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ማሳደግ የሚቻል መሆኑን ትናገራለች። ከዚህ በተጨማሪም ፋሽን ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከሚያበረክተው የላቀ አስተዋጽኦ ባሻገር ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚፈልግ ዘርፍ በመሆኑ ሰፊ የሥራ ዕድልን ለመፍጠርና ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ፋይዳው ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ነው ባለሙያዋ የምታመላክተው።
በመሆኑም ኢትዮጵያም ለዘርፉ ትኩረት ሰጥታ መሥራት እንደሚገባት ባለሙያዋ ትጠቁማለች። ለፋሽን ግብዓት የሚሆን አገራዊ እንዲሁም አህጉራዊና ዓለምአቀፋዊ ሰፊ ገበያ መኖሩን የምትናገረው ባለሙያዋ፤ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባትና አገራዊ የፋሽን ምርት በማሳደግ ተወዳዳሪ መሆን የሚቻል መሆኑንም ታመላክታለች።
አሁን ላይ በገበያ የሚገኙ የፋሽን ምርቶች በአብዛኛው ከውጭ የሚገቡ መሆናቸውን የምትገልፀው ዲዛይነር ብርቱካን ምርቶቹ የሚመጡት በውጭ ምንዛሬ ስለሆነ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ትናገራለች። በራሷ አንዳንድ በአገር ውስጥ የተመረቱ ጨርቆችን ተጠቅማ አዳዲስ ዲዛይኖችን በመሥራት የምትሸጠው ብርቱካን፣ አንዳንድ ሰዎች ካልሆኑ በቀር በአገር ውስጥ የተዘጋጁ አልባሳት በብዙዎች ትኩረት እንዳላገኙ ገልፃለች።
በመሆኑም አገራዊ የፋሽን ምርቶችን ማሳደግ ላይ መሥራትና በብዛትና በጥራት አምርቶ ለአገር ውስጥ ፍጆታ ማዋል እንዲሁም ለውጭ ገበያ በማቅረብ ትልቅ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ መጎናፀፍ ይቻላል ትላለች። ይህም ለማኅበረሰቡ ሠፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራል በማለትም ሀሳቧን ታስረዳለች።
ባለሙያዋ ከውጭ የሚመጡ አልባሳትና ልዩ ልዩ የፋሽን መገልገያዎች ለመቀነስ ኅብረተሰቡ አገራዊ ምርቶች እንዲጠቀምና በአገራዊ ምርት እንዲኮራ ሥራዎችን መሥራትም እንደሚገባ ትጠቁማለች። ለአገራዊ የፋሽን ምርቶች ገበያው ላይ በስፋትና በጥራት አለመገኘት ዋነኛ ምክንያት የጥራትና የምርት እጥረት መሆኑን የምትገልፀው ባለሙያዋ፤ ይህ ጠቀሜታው የጎላው ዘርፍ ቢሠራበት ለአገር ጠቃሚ መሆኑን ታስረዳለች። አገራችን ያላት ሰፊ የሰው ኃይልና የፋሽን ግብአቶች ከፍተኛ ፍላጎትና ሰፊ ገበያ አንፃር ገና ብዙ እንደሚቀረውም ትናገራለች።
ዲዛይነር ሚሊዮን ተፈራ በበኩሏ በአገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶችን በገበያው ላይ ቀዳሚ ምርጫ እንዲሆኑ በጥራትና በብዛት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ትናገራለች። እርሷም የተለያዩ የአገር ባህል ልብሶችን በአዳዲስ ዲዛይን በመሠራት ትተዳደራለች። እንደ ሚሊዮን ገለፃ፣ ገበያው ላይ ያሉ የአገር ውስጥ የፋሽን ምርቶች ከውጭ ከሚመጡት ጋር ሲወዳደሩ በቁጥር እጅግ በጣም አነስተኛ ናቸው።
የአገር ውስጥ የፋሽን ምርት ማስፋፋትና የተመረቱት በኅብረተሰቡ ቀዳሚ ምርጫ እንዲሆኑ ብዙ ሥራ የሚጠብቅ መሆኑ የፋሽን ዲዛይን ባለሙያዎቹ ይገልፃሉ። ለዚህም በፋሽን ገበያ ላይ ያሉ የውጭ ምርቶች በመቀነስ አገራዊ ምርቶች ማሳደግና ኅብረተሰቡ አገራዊ የፋሽን ምርቶች እንዲጠቀም ማበረታታት የሚገባ መሆኑን ሚሊዮን ታነሳለች።
ማህበረሰባችን አገራዊ ምርት ለአገር የሚሰጠው የጎላ ጠቀሜታ ግንዛቤ የለውም። ይህ ደግሞ አንድ የፋሽን ምርት ሲገዛ ወይም ሲገበያይ አልባሳቱ ወይም መገልገያ ዕቃዎቹን በሚመርጥበት ጊዜ አገራዊ ምርቶች የመጀመሪያ ምርጫው እንዳይሆን አድርጎታል።
‹‹ዘርፉ አሁን ላይ ከበፊቱ የተሻለ ትኩረት ተሰጥቶታል›› የሚለው ደግሞ የልብስ ዲዛይነር ደሴ ፀጋዬ ነው። ከኢንዱስትሪው ፈጣን እድገትና ካለው ሰፊ ገበያ አኳያ ግን እንደ አገር ብዙ መሥራት የሚጠበቅ መሆኑን ያስረዳል። የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በፋሽን መስክ እያሰለጠኑ ያሉ ባለሙያዎች ለዘርፉ እድገት የራሳቸው አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ መሆናቸውን የሚገልፀው ዲዛይነር ደሴ፣ መስኩ ከሚፈልገው አኳያ ብዙ ሙያተኛና የዘርፉ ተዋናዮች እንደሚያስፈልጉ ያስረዳል። የፋሽን ምርት አምራች ድርጅቶች በብዛት ሊኖሩ እንደሚገባም ይጠቁማል።
በፋሽን የልብስና ጨርቃ ጨርቅ ማምረቻ ኢንዱስትሪዎች፣ የውበት መጠበቂያ ቁሳቁስ፣ የቆዳና ሌዘር አምራቾችና የመሳሰሉት የሚሳተፉበት ግዙፍ ዘርፍ ነው። በዚህ ዘርፈ ብዙ ኢንዱስትሪ የሚሳተፈው የሰው ኃይል በርካታ በመሆኑ የሥራ ዕድልም ይፈጥራል።
‹‹ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በመሥራት በተለይ አገራዊ ምርትን በማሳደግ የውጭ ምንዛሬ አቅምን ማጠንከርና የገቢ ምንጭ ማድረግ ይቻላል›› የሚለው ባለሙያው በተለይ ኅብረተሰቡ አገራዊ ምርት የመጠቀም ልምዱን እንዲያዳብር ጠንካራ ሥራ መሠራት እንዳለበት ተመሳሳይ አስተያየት ይሰጣል።
ገበያ ላይ አገራዊ ምርቶች በብዛት እንደሌሉ የሚገልፀው ዲዛይነር ደሴ፤ ይህ ልምድ መቀየር እንዳለበትና አገራዊ ምርቶች የማምረትና ከውጭ የሚገቡ የፋሽን ምርቶች መቀነስ እንደሚገባ ያስረዳል። በተለይ ኢትዮጵያን በመሰሉ አገራት ሰፊ የሕዝብ ቁጥራቸውን በፋሽን ገበያው ውስጥ ያለን ዕድል በመጠቀም ኢኮኖሚያቸውን መደጎምና ሰፊ የሰው ኃይል ማሳተፍ እንደሚችሉ ባለሙያዎቹ ይገልፃሉ።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2015 ዓ.ም