አዲስ አበባ፦ የአፍሪካ ዓይነ ስውርነት ፎረም እኤአ በ1996 የተጀመረና በተለያዩ አፍሪካ ሀገራት አዘጋጅነት በየአራት ዓመቱ የሚዘጋጅ ፎረም ነው።
የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ወሰን አለሙ እንደገለፁት፤ ፎረሙ በአፍሪካ ውስጥ ለዓይነ ስውራን አገልግሎት ለሚሰጡ ግለሰቦችና ኤጀንሲዎች የተለያዩ መረጃዎችን፣ ተሞክ ሮዎችንና የዳበሩ ልምዶችን በመለዋወጥ ለአፍሪካውያን ዓይነ ስውራን ህይወት መሻሻል አስተዋፅኦ ለማበርከት ተብሎ የተቋቋመ መሆኑን አብራርተዋል።
ፎረሙ ባለፉት ዓመታት በኡጋንዳ ሁለት ጊዜ፣ በጋና ሁለት ጊዜ፣ በኬንያ አንድ ጊዜና በደቡብ አፍሪካ አንድ ጊዜ በድምሩ ለስድስት ተከታታይ ጊዜያት የተካሄደ ሲሆን፤ በዋነኝነት በዘርፉ ለተሰማሩ ሰዎች የዕውቀትና የመረጃ ምንጭ ሆኖ ማገልገሉን ተናግረዋል።
«በተደራሽነት በፈጠራና በህይወት ዘመን ትምህርት ዘላቂ የልማት ግብን ዕውን ማድረግ» በሚል መሪ ቃል ለ7ኛ ጊዜ የሚከበረውን የአፍሪካ ዓይነ ስውራን ፎረም ኢትዮጵያ፤ በቀጣይ ዓመት ከመስከረም 26 እስከ መስከረም 30 ቀን 2012 ዓ.ም ታካሂዳለች። ይህም ኢትዮጵያ፤ ባቀረበችው ጥያቄ መሰረት ከሌሎች አፍሪካ ሀገራት ጋር ተወዳድራ ዕድሉን ያገኘች ሲሆን፤ በመድረኩም ከ400 እስከ 500 የሚደርሱ የተለያዩ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ ይጠበቃል።
በፎረሙ ከሚካሄዱ ዋና ዋና ተግባራት መካከልም ቴክኖሎጂ ሼር የተባለ ኤግዚቢሽን አንዱና ዋነኛው ሲሆን፤ ለዓይነ ስውራን ጠቃሚ የሆኑ ምርቶችን ቴክኖሎጂዎችን
ከሁሉም የዓለም ክፍል በማሰባሰብ በአንድ ቦታ ላይ ለዕይታ የሚቀርብበት መርሃ ግብር ነው። በፕሮግራሙ ላይም ማንኛውም ፍላጎት ያለው ግለሰብ መካፈል የሚችልና ለሀገር ውስጥ ተሳታፊዎች 200 ዶላር እንዲሁም ከሀገር ውጭ ላሉ ተሳታፊዎች 400 ዶላር ለምዝገባ እንደሚያስፈልግ አቶ ወሰን ጨምረው ገልፀዋል።
ወይዘሮ የትነበርሽ ንጉሴ፤ በኢትዮጵያ ለሚዘጋጀው 7ኛው የአፍሪካ ዓይነ ስውርነት ፎረም ከተዋቀሩት ኮሚቴዎች መካከል አንዷ ሲሆኑ፤ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያ እያራመደች ካለችው የለውጥ አቅጣጫ አንፃር አጓጊ ሀገር መሆኗን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በጣም ጠንካራና የተማሩ ዓይነ ስውራን ግለሰቦች ያሉባት መሆኗን አስታውሰዋል። ይሁን እንጂ በዓይነ ስውራን መብት ረገድ ተገቢ የሆነ የህግ ማዕቀፎችን አስቀምጣ ያልጨረሰችና የቤት ሥራዋ ያላለቀ ሀገር መሆኗን በመግለፅ፤ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የምታዘጋጀው 7ኛው የአፍሪካ ዓይነ ስውራን ፎረም ከፎረሙ ውጤት ባለፈ ጠንካራ የዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበርን ለማስቀጠል በጋራ የምንሰራበት ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን እምነቴ ነው ብለዋል።
በመጨረሻም ማንኛውም ፍላጎት ያለው ግለሰብ፣ መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጨምሮ በፎረሙ ተሳታፊ በመሆን የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ ሲል የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ጥሪውን ያቀርባል። የኢትዮጵያ ዓይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር በ1952 ዓ.ም የተቋቋመ አንጋፋ ማህበር ነው።
አዲስ ዘመን መጋቢት 29 /2011
ፍሬህይወት አወቀ