ልጆች በዚህ ሳምንት አስገራሚ ስለሆኑ እውነታዎች እንነግራችኋለን። ለዛሬ የመረጥንላችሁ ጉዳይ አለ። ልጆች ምድራችን ላይ በርካታ እውነታዎች እንዳሉ ታውቃላችሁ አይደል?። መልካም፤ እኛም በዚህ አምድ ላይ ዓለማችን ላይ ስላሉ በርከት ያሉ አዝናኝ እና አስተማሪ እውነታዎችን በየሳምንቱ ይዘንላችሁ ለመቅረብ እንሞክራለን። ዛሬ ስለ ፕላኔት ጁፒተር ነው እምንነግራችሁ። እስቲ ለትንሽ ጊዜ ስለ ጁፒተር አስቡ። የምታውቁትን እውነታዎችን እኛ የምንነግራችሁን ከማንበባችሁ በፊት ለጥቂት ሴኮንዶች ለማሰብ መሞከራችሁ እራሳችሁ ምን ደረጃ ላይ እንዳላችሁ ለማወቅ ይረዳችኋል።
ልጆች በዓለማችን ላይ ስላሉ አንዳንድ ፕላኔቶች ምን ያህል ታውቃላችሁ? በህዋ ላይ ትላልቅ ፕላኔቶች ይገኛሉ ከነዚህ ውስጥ ደግሞ «ጁፒተር» የምትባለዋ አንዷ መሆኗን የሳይንስ ተመራማሪዎች በተለያየ አጋጣሚ ይነገራሉ። በዓይን ሊታይ የሚችል መረጃዎችንም በየጊዜው ያቀርባሉ። ለዛሬ በእውነታዎች ገፅ ላይ ስለ ጁፒተር አፈጣጠር ጥቂት ነገሮችን ለመመልከት እንሞክር።
1. ጁፒተር በፀሐይ ዙሪያ ካሉት ስምንት ፕላኔቶች እና ጨረቃ ጋር ወይም «የሶላር ሲስተም» ውስጥ ትልቋ ፕላኔት ናት። በዙሪያዋ እጅግ የተጠጋጉ ቀለማማ፣መርዛማ እንዲሁም ገዳይ በሆኑ የጋዝ መርዞች የተከበበች ነች።
2. ፕላኔቷ በጥቁር ጭጋጎች ወይም ደመናዎች ትንፋሽ በሚያሳጥሩ አየሮች ብሎም ምቾት በሚነሱ ሞቃታማ አፈጣጠሯ ትታወቃለች።
3. በጁፒተር የመካከለኛው ክፍል ላይ ድንጋያማ ስፍራ ይገኛል። ይሄ ስፍራ ከምድር በትንሹ የሚተልቅ ቢሆንም በክብደት ከመሬት 20 እጥፍ እንደሚበልጥ ሳይንቲስቶች በምርምራቸው ላይ አረጋግጠዋል። ይህ ስፍራ በእንግሊዝኛው «ኮር» በመባል ይታወቃል።
4. በጁፒተር ኮር ዙሪያ ሰፊ ውቅያኖስ የሆነ ፈሳሽ የሀይድሮጅን ኬሚካል ይገኛል። ሀይድሮጅን ከኬሚካል ንጥረ ነገር ወይም «ኢለመንቶች» ቀላሉ እንደሆነም ይታወቃል። ከዚህ በተጨማሪ የጁፒተር የስበት ወይም «ማግኔቲክ ፊልድ» ኃይል ከፍተኛ መሆኑን ተመራማሪዎች ይጠቁማሉ። ጁፒተር በዙሪያዋ ያለው ከባቢ አየር ምክንያትም አንድ ሰው በምድር ካለው ክብደት በግማሽ ያህል እንዲቀንስ ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ ጁፒተርን የሚዞሩ በርካታ ጨረቃዎች ሲኖሩ ከነዚህ ውስጥ አራቱ ፕሉቶ ከተሰኘችው ፕላኔት በግዝፈታቸው ይበልጣሉ።