ታላቋን አገር ኢትዮጵያ ከመሩ ነገስታት መካከል አንዱ ናቸው። ከ1542 ዓ.ም እስከ መስከረም 1590 ዓ.ም ድረስ የንግስና ዘውድ ደፍተው ኢትዮጵያን መርተዋል። ብዙዎች በዙፋን ስማቸው “መልአክ ሰገድ” በሚለው ያውቋቸዋል። በዛሬው የሳምንቱ በታሪክ ገፃችን የምንዘክራቸው አፄ ሰርፀ ድንግል ናቸው። እኚህ ኢትዮጵያን ለ48 ዓመታት በንግስና ያስተዳደሩ ንጉስ 1590 ዓ.ም መስከረም 24 ነበር ሕይወታቸው ያለፈው።
እርሳቸው ከመንገሳቸው በፊት አገሪቱ ላይ የነበረው አለመረጋጋት እጅጉን የከበደ ነበር። በተለይም ከግራኝ አህመድ ጀምሮ እስከ አባታቸው አፄ ሚናስ ያለው ዘመን ኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነት የበረከተበትና አለመረጋጋት የሰፈነበት ነበር። አፄ ሰርፀ ድንግል በሰሩት ጠንካራ ስራና ሰላምን የማስፈን ጥረት ይህን መፍታትና አንፃራዊ ሰላም በኢትዮጵያ ምድር ማስፈን ችለው ነበር።
አባታቸው አፄ ሚናስ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ እቴጌ አድማስ ሞገስ የሚባሉ ሴት ነበሩ። እኚህ ንጉስ ከአባታቸው አፄ ሚናስ ቀጥሎና ከአፄ ዘርያዕቆብ በፊት ኢትዮጵያን መምራታቸውን የታሪክ ድርሳናት ያመለክታሉ። ንጉሱ ከቅድመ ንግስናቸው ጀምሮ የንግስናቸው መጨረሻ ድረስ በብዙ ፈተና ያለፉ ነበሩ።
ቅድመ ንግስና
አፄ ሰርፀ ድንግል ከመንገሳቸው በፊት አባታቸው አፄ ሚናስ ኢትዮጵያን በሚመሩበት ወቅት ኢትዮጵያ እጅግ የበዙ ጦርነቶችን እና የተለያየ ግጭት ያስተናገደችበት ወቅት ነው። የስልጣን ዘመናቸውን በተለያዩ ጦርነቶ ያሳለፉት የአፄ
ሰርፀ ድንግል አባት አፄ ሚናስ ከፖርቱጋል ካቶሊኮች ጋር አለመስማማታቸው ሲሆን ካቶሊኮቹም አንድ ጊዜ ከባህር ንጉስ ይስሐቅ ጋር በማበር ሌላ ጊዜ ደግሞ ባህር ንጉሱ ከቱርኮች ጋር በመተጋገዝ በሚናስ ላይ አመጽና ዘመቻ ይፈፅሙባቸው ነበር።
በወቅቱ የአዳል ግዛት ኃይሉ እምብዛም ያልተዳከመ ስለነበር በመካከለኛው መንግስት ላይ ጦር የመክፈት ልማዱ አልተገታም ነበር። ሦስተኛው፤ በዘመኑ የአገሪቱ የአስተዳደር ማዕከል የነበረው የሸዋ እና የተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ግጭቶችም ነበሩ። የአፄ ሰርፀ ድንግል አባት አፄ ሚናስ አብዛኛው የስልጣን ዘመናቸውን በተለያዩ ጦርነቶች ነበር ያሳለፉት።
አባት አፄ ሚናስ ካረፉ በኋላ በዚህ ሁኔታ የነበረችው ኢትዮጵያን የተረከቡት አፄ ሰርፀ ድንግል ከአባታቸው ሚናስ የተረከበውን ግዛት አስፍቶና አጠናክሮ ለቀጣዩ መሪ የማስረከብ ትልቁ ሀላፊነት ሊረከቡ ተቃረበ።
የንግስና ትንቅንቅ
የአፄ ሰርፀ ድንግል ወላጅ አባት አፄ ሚናስ በ1555 ዓ.ም ሲሞቱ ቀጣዩን ንጉስ ለመምረጥ የአገሪቱ መሳፍንቶች በሸዋ ተሰበሰቡ። ነገር ግን ንጉስ ማን ይሁን የሚለው ምርጫው ቀላል አልነበረም። በእርግጥ ሠረፀ ድንግል የአፄ ሚናስ ታላቁ ልጅ ቢሆንም ለመንገስ የሚመኙና ንግስናን ለመውረስ የቋመጡ ብዙ ተቀናቃኞች ነበሩት። በተለይም የአፄ ልብነ ድንግል እህት የወይዘሮ ሮማንወርቅ ልጅ የነበረው ሐመልማል ዋና ሲሆን ሌሎችም እንደ ሐርቦ፣ አቤቶ ፋሲል እና ይስሐቅ ያሉ ተገዳዳሪዎች የአገሪቱ መሳፍንቶች ንጉስ ማን ይሁን የሚለው ምርጫ ለማድረግ ያደረጉት ስብሰባ በሙግት የተሞላ ነበር ።
ያኔ ምርጫው ሲካሄድ ገና የ13 ዓመት ወጣት የነበረው ሰርፀ ድንግል ንግስናውን ካረጋገጠም በኋላ ተገዳዳሪዎቹ ቀላል አልሆኑለትም ነበር። በተለይም የወይዘሮ ሮማንወርቅ ልጅ ሐመልማል ይህን ውጤት ባለመቀበል የጎጃም እና ደምቢያ መሳፍንቶችን በማስተባበር በወጣቱ ንጉስ ላይ ዘመቻ ከፈተ፤ ጦርነትም አደረገ። በዚህም በመጀመሪያ አካባቢ ድል ተቀዳጅቶ ንጉስ ሰርፀ ድንግልን ለመገዳዳር ሞክሮ ነበር።
በመሳፍንቱ አብላጫ ድምፅ ለንጉስነት ተመርጠው የነበሩት አፄ ሰርፀ ድንግል የቀሳውስቱን እና እንዲሁም እቴጌ ሰብለ ወንጌልን ድጋፍ በማግኘት ንግስናውን ማስጠበቅ ቻሉ። ለሰርፀ ድንግል ስልጣን መጠበቅና ለንግስናው መፅናት ይሰሩ የነበሩት መሳፍንት ቁጥራቸው እየጨመረ መሄዱ ሐመልማልን ከፍቶ የነበረው ጦርነት ተሸናፊ እንዲሆን አደረገው። በኋላ ላይም ንጉስ ሰርፀ ድንግል የጎጃም ክፍለ ግዛትን ስልጣኑን ለሚገዳደረው ጦርነት ገጥሞ ለረታው ሐመልማል እንደ ግዛት በመስጠት ሰላም ማስፈን ቻለ።
ከዚያም ባህረ ንጉስ ይስሀቅ የተባለ የኤርትራ ገዢና የአጎታቸው ልጅ የነበረው አምፀውባቸው ጦርነት ከፍተውባቸውም ነበር። በመጨረሻም አፄ ሰርፀ ድንግል ጦርነቶቹን በማሸነፍ አመፁን መቆጣጠር ችለዋል።
በጦር ስልታቸው እጅግ አስደናቂ እንደነበሩ የሚነገርላቸው አፄ ሰርፀ ድንግል በ1569 ዓ.ም ከቱርኮች ጋር በተደረገው ጦርነት ለመጀመሪያ ጊዜ ቱርኮችን አሸነፉ። ወደ ሰሜንም በመዝለቅ በወገራ እና በአይባ ሌሎች ቤተ መንግስቶችን አሰርተዋል። የተለያዩ ቤተ ክርስቲያናትንም ማሰረታቸው ይነገራል።
ቀድሞ የተሸነፈው የኤርትራው ባህር ንጉስ ይስሐቅ በድጋሚ በኦቶማን ቱርኮችና በአዳል ሰራዊት ታግዞ አመጽ ማስነሳቱ አልቀረም። በዚህ ጊዜ ንጉሱ ወደ ትግራይ በመዝመት በ1578 ባህረ ነጋሽንና አብሮ መጥቶ የነበረው ኦቶማኑን ኦዝደሚር ፓሻንና የአዳል መሪ የነበረውን ሱልጣን መሐመድ አራተኛ ጋር ጦርነት ገጥመው ማሸነፍና መሪዎቹን መግደል ቻሉ።
ኤርትራ ውስጥ በምትገኝ በድባርዋ የተባለች ከተማ የነበሩት ቱርኮችም ያለምንም ተኩስ እጃቸውን ለአፄ ሰርፀ ድንግል ሰጡ። ንጉሱም በአክሱም ስርዓተ ተክሊልን ፈጸሙ። መልአክ ሰገድ የሚለውንም ስም ያገኙት በዚህ ጊዜ ነበር። ከ10 አመት በኋላ፣ በ1588 ኦቶማን ቱርኮች፣ ከተባረሩበት ድባርዋ መልሰው ሊቆጣጠሩ ሲሞክሩ በመሸነፋቸው አርቂቆ ላይ የነበረውን ግዛታቸውን ሰርጸ ድንግል አፈረሰባቸው። በዚህ ምክንያት የቱርኩ መሪ በወርቅ ያጌጠ ፈረስ እስከ ሳዱላው በመላክ ከንጉሱ ዘንድ ሰላም እንደሚሻ አስታወቀ።
ሰርፀ ድንግል የኖረበት ዘመን ከግራኝ አህመድ ጦርነት ጥቂት ዘመን አሳልፎ ስለነበር የህዝቦች ፍልሰት በዚሁ ዘመን ይታይ ነበር። በዚህ መልኩ ኢትዮጵያን ሲመሩ የቆዩት ሰርፀ ድንግል መስከረም 24 ቀን 1590 ዓ.ም በጸና ታመሙና ሞቱ። በጣና ሃይቅ ሬማ ደሴት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ተቀበሩ። የሰርጸ ድንግል መንግስት ረጅምና ከመጀመሪያው ጀምሮ ብዙ ጦርነት የበዛበት ቢሆንም ንጉሱ ለልጁ ዘረ ያዕቆብ ያስረከቡት ግዛት ግን ሰላማዊና ያልተከፋፈለ ታላቅ አገር ነበር።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን መስከረመ 29/2015