የኤች አይቪ ኤድስ በጤና፣ በኢኮኖሚ እንዲሁም በማህበራዊ ህይወት ላይ እያደረሰ ያለው ችግር ይታወቃል፡፡ በተለይ በወጣትነትና አምራች ዕድሜ ክልል ውስጥ ባለ የህብረተሰብ ክፍል ላይ የሚያደርሰው ችግር ውስብስብ ከመሆኑም በላይ ለመጪው ትውልድም ጠባሳ የሚያሳርፍ ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ችግሩ እንደገና እያገረሸ ይገኛል፡፡ ስለሆነም ሁኔታውን ለመቅረፍ ቀደም ሲል ሲሠራበት ከነበረው አካሄድ በመውጣት በላቀ መልኩ መረባረብና መሥራት እንደ አንድ ታላቅ የሀገር ጥሪ መወሰድ ይገባል፡፡
እንደ አቶ ባይሳ ጫላ ከቫይረሱ ጋር አብረው የሚኖሩ ወገኖች ብሄራዊ ማህበር ዋና አስፈጻሚ ገለጻ በፍጥነት እየተለዋወጠ በሚሄደው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አኗኗር የተነሳ በከተማ ያለው ወጣት ፈንጠዝያን በመውደዱ ራሱን ለቫይረሱ ተጋላጭ አድርጓል፡፡ ከራሱ አልፎም ህብረተሰቡን እየጎዳ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ የሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ግንዛቤ ማስጨበጡንም ሆነ ወጣቱን ከመገሰጽ አንጻር ሥራቸው እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ በመሆኑም እንደገና ወደ ራሳቸው ተመልሰው የበኩላቸውን ጥረት ሊያደርጉ ግድ ይላል፡፡
የህክምና ባለሞያዎች እንደሚገልጹት ከሆነ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ከሚያስችሉት ዘዴዎች ውስጥ አንዱ ሰዎች ተመርምረው ራሳቸውን እንዲያውቁ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን በከተማ ውስጥ በአብዛኛው ለመመርመር ያለው ፍላጎት እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ከሁለት ጊዜ በላይ የተመረመሩ አንዳንዶችም ደግሞ ቫይረሱ በደማቸው እንዳለ እያወቁ እንደገና እየተጠራጠሩ የሚመረመሩ ናቸው፡፡ ይህም ስርጭቱን ከመግታት አንጻር ምንም ፋይዳ አላስገኘም፡፡
በሌላም በኩል አንዳንድ ሰዎች ከክልል ወይም ከሌላ አካባቢ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ተመርምረው ቫይረሱ በደማቸው መኖሩን ካወቁ በኋላ ተመልሰው ወደ አካባቢያቸው ስለሚመለሱና አድራሻቸውን ስለሚያጠፉ መድሃኒት መጀመር አለመጀመራቸው፤ ምን እንደሚሠሩና ከማን ጋር እንደሚገናኙ ስለማይታወቅ ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ነው፡፡
እንደ አቶ ባይሳ ብዙ ሰዎች ምርመራን እንደ ስጋት ነው የሚመለከቱት የምርመራው ዓላማ ግን ሰው ራሱን ካወቀ በኋላ ቫይረሱ በደሙ ከተገኘበት ወዲያው ወደ መድሀኒት መውሰድ ይገባል ነው፡፡ ነገር ግን ሰው ተጠራጣሪና ለመመርመር ካልፈለገ እንዴት ዓላማው ይሳካል፣ በሌላም በኩል አንዳንድ ሰው መድሃኒቱን በመተው ወደ ጠበል መጠመቅ ያመራል ውጤቱ ግን በይፋ አይታወቅም ስለሆነም የስርጭት መጠኑ እንዲቀንስ ብዙ ልፋትን የሚጠይቅ ሥራ መሠራት አለበት፡፡
በፈቃደኝነት የደም ምርመራ ለማድረግ ሰዎች ውጤቱ አውንታዊም ይሁን አሉታዊ ሊሆን ስለሚችል የሚመጣውን ለመቀበል መዘጋጀት ግድ ይላል፡፡ ነገር ግን እንደ አቶ ባይሳ አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ከቫይረሱ ጋር አብረው የሚኖሩ ወገኖችን ማግለልና መድልኦ እንደቀጠለ ነው፡፡ ማግለሉ የሚከናወነውም በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ ነው፡፡ ቤት አከራዮች በተከራዮቻቸው ላይ አላንዳች ምክንያት የተጋነነ የኪራይ ጭማሪ በማድረግ እንዲለቁ ያደርጓቸዋል፡፡ አንዳንድ ቫይረሱ በደማቸው ያለባቸው ወገኖችም ራሳቸውን ከማህበረሰቡ በራሳቸው ፍላጎት ያገላሉ ይህን የሚያደርጉትም በራሳቸው ላይ በሚፈጠር ስነ ልቡናዊ ቀውስ የተነሳ «በቃ ህብረተሰቡ አይቀበለኝም» በሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ ሲሆን እንደገና ህብረተሰቡም በፊናው ያገላቸዋል:: በዚህም የተነሳም ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ሄደው መማር ያቅታቸዋል፡፡ ይህን የሚመለከት ሰው ደግሞ ነገሩ እንዲህ ከሆነ ለምን እመረመራለሁ ወደ ማለት አስተሳሰብ በመምጣት ለመመርመር ያለው ፍላጎቱ ይቀንሳል፡፡ ነገር ግን አግላዮቹ ራሳቸው ያልተመረመሩ ሆነው ነው ይህን የሚያደርጉት ምናልባትም ቢመረመሩ ነፃ ስለመሆናቸው እርግጠኛ አይደሉም፡፡ ስለሆነም አሁንም ህብረተሰቡ የማግለልን አስተሳሰብ የግድ ካልቀየረ ከችግሩ አዙሪት ለመውጣት ሊያስቸግር ይችላል፡፡
ኤች አይ ቪ በደም ውስጥ መኖር ምንም ማለት እንዳልሆነ ልክ እንደ ስኳርና ሌሎች ህመሞች በመድሀኒት በመታገዝ ለረጅም ጊዜ መኖር እንደሚቻል በመገንዘብ አስተሳሰብን መቀየር ግድ ይላል፡፡
በአሁኑ ወቅት የህብረተሰቡን አኗኗር እየቀየረ ያለው የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ነው፡፡ መረጃዎች በቅጽበት ዓለምን ያደርሳሉ ሰዎችን ያቀራርባሉ፤ የተለያዩ ባህሎችን ይቀይጣሉ በዚህ አጋጣሚም መጥፎም ሆኑ ጥሩ ነገሮች ይወረሳሉ፡፡ ወጣቶችን ከተቃራኒ ጾታ ጋር በማገናኘት ቴክኖሎጂው የላቀ ሚና እየተጫወተ ሲሆን፤ ልቅ የወሲብ ፊልሞችም በዚህ አጋጣሚ ይለቀቃሉ ይህም ተጋላጭነትን እያሰፋ ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ ምን መደረግ እንደሚገባ የተጠየቁት አቶ ባይሳ ጫላ ሲገልጹ ቴክኖሎጂን መቀበል በልማት መገስገስ ያስችላል ጥሩ ነው፡፡ ስለሆነም መጠቀም ግድ ይላል፡፡ ነገር ግን ወሳኙ ነገር ቴክኖሎጂውን ለመልካም ነገር ለመጠቀም በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መስጠት መቻል ነው፡፡
ቴክኖሎጂውን ከሕፃን እስከ አዋቂና አዛውንቱ ድረስ ያለው የህብረተሰብ ክፍል እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ነገር ግን ቤተሰብ ውስጥ ስለ ወሲብና ጾታዊ ግንኙነት እንዲሁም ስለ ስነ ተዋልዶ አለመወያየት በባህላችን የቴክኖሎጂውን ያህል አለመራመዳችንን ያመለክታል፡፡ የውይይቱ ባህል ቢዳብር ኖሮ ቴክኖሎጂው ለጥፋት እንዳይውል ማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ቴክኖሎጂው በተቃራኒው ልጆችንና ቤተሰብን እያራራቀ ነው፡፡ ልጆች በሞባይል ስልኮቻቸው የራሳቸውን ዓለም ፈጥረው የሚኖሩ ሲሆን፤ በዚህ የተነሳም ከቤተሰብ ሊያገኙት የነበረውን የህይወት ክህሎት እያጡ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ወጣቶች ከዚያ አልፈው አደንዛዥ ዕጽ በመውሰድ በየፓርቲና ምሽት ቤቶች ልቅ ወሲብ በመፈጸም ራሳቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ይገኛሉ፡፡
በየትምህርት ቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች ዙሪያ የተኮለኮሉት ጫት ቤቶች፤ሺሻና መጠጥ ቤቶች ወጣቱን በቀላሉ ተገዢያቸው እያደረጉ ከዓላማው እያዘናጉት ነው፡፡ ከዚያ ወጥተው ወጣቶች ጥንቃቄ የጎደለው የወሲብ ግንኙነት እየፈጸሙ የሚገኙ ሲሆን፤ በአብዛኛው ኮንዶምን አይጠቀሙም፡፡ በአንድ ያለመወሰን ባህርያቸው ደግሞ ስርጭቱን የበለጠ አስከፊ እያደረገው ነው፡፡ ስለ ሆነም ስለ ቴክኖሎጂው አጠቃቀምም ሆነ ስለ የተቃራኒ ጾታ ግንኙነታቸው በተመለከተ ተከታታይነት ያለው ትምህርት መስጠት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ አቶ ባይሳ አስረድተዋል፡፡
ተጋላጭ ናቸው ተብለው ከሚጠቀሱ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ሴተኛ አዳሪዎች አንደኛው ሲሆኑ የስርጭት መጠናቸውም ከፍተኛ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ወጣቱ፤ የመንግሥት ሠራተኛው እንዲሁም የቤተሰብ ኃላፊዎች ጭምር የሴተኛ አዳሪዎች ደንበኛ እንደሆኑ ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት የሰጡት አቶ ባይሳ የሴተኛ አዳሪዎችን ሁኔታ በሁለት ከፍሎ ማየት እንደሚገባ በአንድ በኩል ምንም አማራጭ የህይወት መስመር አጥተው የዕለት እንጀራቸውን ለማግኘት ብለው ወደ ወሲብ ሥራ የሚሰማሩት አንዳንዴ የተሻለ ገንዘብ እሰጣችኋለሁ ለሚላቸው ያለ ኮንዶም እንደሚወጡ በዚህ ረገድ ሀብታም ወጣቶች እንደሚጠቀሱ ገልጸው፤ ይህም ችግሩን እያወቁት በንህዝላል የሚፈጸም ነው ብለዋል፡፡ ከወጣቶች በዘለለም አዋቂና አዛውንቶች ይህንን እንደሚፈጽሙ ጠቅሰዋል፡፡ በሌላም በኩል የተሻለ ኑሮ እያላቸው ሴተኛ አዳሪነትን እንደ ቢዝነስ ተመልክተው በዚያ ሥራ የሚሰማሩ እንዳሉ ፤ እነኚህ ወገኖች በትላልቅ ሆቴሎች የሚዝናኑና ከፍተኛ ወጪ የሚያወጡ ሲሆን፤ ምንም ዓይነት ችግር አይመጣብንም በሚል መንፈስም ምርመራ እንደማያደርጉ ወደ እነርሱ ዘንድ የሚሄዱት ደንበኞቻቸውም ስለማይ ጠነቀቁ በራሳቸው ላይ ችግር እያስከተሉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ወቅት በየ ሸረንቆው እየተስፋፉ የሚገኙት ማሳጅ ቤቶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የወሲብ ንግድን እያስፋፉ ይገኛሉ፡፡ እነኚህን ንግድ ቤቶች የሚከፍቱ ወገኖች ቀደም ሲል ለረጅም ዘመን ህይወታቸውን በሴተኛ አዳሪነት የገፉ ሲሆን፤ የንግድ ፈቃዳቸው ሌላ ሆኖ የሚሠሩት ግን የወሲብ መዳራትን ነው፡፡ ወደዚህ ስፍራ የሚሄዱ ወገኖችም በኑሯቸው የደረጁና ሌላ ህይወት እየመሩ መገኘታቸው ተጋላጭነትን ይበልጥ ከማስፋፋት በተጨማሪ ሁኔታውን እያወሳሰበው ይገኛል፡፡
የቫይረሰን ስርጭት ከመግታት አኳያ ከመንግሥትና ከመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጥረት ጎን ለጎን ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች የሚሰጡት የገንዘብ ድጋፍ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በተለይ መድሃኒቱን ከውጭ ለመሸመት እንዲቻል ከፍተኛ እገዛ አድርጓል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ለጋሽ ሀገሮች በአብዛኛው የሚሰጡትን ድጋፍ እየቀነሱ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም ይህን ከሀገር ውስጥ ሀብት ለመተካት ግድ ስለሚል ህብረተሰቡ ከመንግሥት ጎን በመሆን የበኩሉን እገዛ ሊያደርግ ይገባል፡፡
አበበ ወልደ ጊዮርጊስ
原來用微信和電腦訂都可以,在這兒訂過機票去大陸玩,付款岀票過程都很快很順利。下次都會在HOPEGOO繼續訂機票!
假期带小孩岀行,要提前的行程和車票都儘量安排好,發現这里订票很方便,服務也不錯。HOPEGOO這個訂票的系統很贊!期待下次。