ተስፋ መቁረጥን መቼም ቢሆን ሞክራው አታውቅም:: በብዙ ፈታኝ ችግሮች ውስጥ እያለፈች እንኳን ነገን በተስፋ አሻግራ ትመለከታለች:: ለዛውም ደማቅ ተስፋ:: ዛሬን ከነገ የሚያሻግር ብሩህ ተስፋ:: እሷ የዘወትር ጥንካሬዋ ካሰበችው ያደርሳታል:: በእርግጥ እርምጃዋ ሁሉ ሰውን የሚያስቀድም ነው:: በተለይ በሕጻናት ላይ ያላት ልዩ ፍላጎት የማይታሰበውን ተራራ እንድትንደው አድርጓታል:: ዮሀና ረታን::
ዮሀና ይሁን ብላ ካመነች የራሷን መልካም እድሎች ጭምር እርግፍ አድርጋ ትተዋለች:: ለምን ካሉ እርሷ ለበጎነት ስትል የምትሰስተው የላትምና:: ይህንን ውሳኔ የተማረችው ደግሞ ከወታደሩ አባቷ ነው:: ወታደሩ አባቷ ለውድ አገራቸው ሕይወታቸውን ሰውተዋል:: ከዚያ አስቀድሞ ግን ልጆቻቸው አገር ወዳድ ሆነው እንዲያድጉ ቀርጸዋቸዋል:: ዛሬ ዮሐናም ይህን ፈለግ ተከትላ ለአገርና ለወገኗ የማትከፍለው የለም::
ትውልድና እድገቷ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ከምትገኘው ለምለሟ ስፍራ ቢሾፍቱ ነው:: ብዙውን የልጅነት ጊዜዋን በዚህች ውብ ከተማ አሳልፋለች:: አባቷን ሰባት ዓመቷ ላይ በማጣቷ ብቻቸውን ባሳደጓት እናቷ እቅፍ ውስጥ ሆና ትምህርቷን እስከ ሁለተኛ ደረጃ ተከታትላለች::
የወታደር ልጅነት በረከት
አባቷ ለአገር ብለው ቢሰዉም ብዙ መልካም እሴቶች እንደሰጧት ታምናለች:: የመጀመሪያውና ቅድሚያ የሚሰጠው ደግሞ ሰውን አብዝቶ መውደድን ነው:: እሷ በሰው መውደድ ውስጥ አገር መውደድን አይታለች:: አባቷ ስለ አገር ፍቅር መስበክ የሁልጊዜ ልምዳቸው ነበር::
ዮሀና አባቷን ማጣቷ ቢሰማትም ዓላማ ያላት ልጅ ሆናለች:: ይህ እውነታም ስለሀገሯ የምትከፍለው ዋጋ እንዲኖርና እንዲሰማት አድርጓል:: ከአባቷ ማንነት ለአገር ብሎ መሰዋት ትልቅ ክብር እንዳለው ተረድታለች:: አባቷ በሕይወት በነበሩ ጊዜ ከእርሷ ጋር ቅርብ ቁርኝት ነበራቸውና የወታደር ሕይወትን በደንብ አስተምረዋታል:: ሀገርን ለማስረከብ ሕይወታቸውን እንደገበሩም ታውቃለች:: እናም ወታደርነትን አጥብቃ ትወዳለች::
እርሷ ወታደር ባትሆንም ውትድርናን ኖረዋለች:: የወታደር ልጅ በመሆኗ በስነምግባር መኖርን ታውቃለች:: በራስ መተማመንን አዳብራለች:: ራሷን እንደሴት ብቻ ሳይሆን እንደጀግና አይታ እንድትጓዝም ሆናበታለች:: ተስፋ መቁረጥን እንዳታስብ ፤ በተለይ ደግሞ ‹‹አልችለውም›› ይሉትን ዕንቅፋት እንዳታስብ ወስናለች::
ከራስ ፍላጎት አልፎ ለሌላው መቆምና መሥራት የሚለውንም ያገኘችው የወታደር ልጅ በመሆኗ ነው:: ከዚያ ባሻገር የወታደር ልጅ በመሆን ውስጥ ጽናትን ተላብሶ መኖርን አውቃለች:: ‹‹ወደፊት እንጂ ወደኋላ እንዳታይ›› የሚለውን እውነታ አረጋግጣለች:: ዮሀና ከዚህ በተያያዘ አንድ እውነታ ታነሳለች:: ‹‹ወታደር ቤተሰብ ሲኖረን ሞትን አንፈራም:: ይልቁንም በዚህ ውስጥ ያለውን መሥራትና ታሪካዊ አሻራን ማኖርን እናስባለን እንጂ:: ›› የሚለውን ሀቅ ::
ይህ ብቻ አይደለም ‹‹ሕልም ሁሉ ዓላማ ያለው እንደሆነ አምነን ለጊዜ ዋጋ እንሰጣለንም:: ዛሬ፤ ነገ ወይም ከነገወዲያ እሞታለሁ የሚለው ውስጣችን ስለሚኖር ከፍርሃት ሳይሆን ከትጋት አንጻር ደቂቃዎችን መጠቀም እንጀምራለን:: በዚህ ውስጥ ስናልፍ ደግሞ እያንዳንዱ ቀን የሥራና የውጤት ይሆንልናል›› ትላለች::
የወታደር ልጅ መሆን ድፍረትን ለራስ መስጠት ነው:: ችግር ሳይሆን በችግር ውስጥ ድል እንዳለ ማሰብም ነው:: ቀናትን የታሪክ መተኪያም እያደረጉ ማለፍ ነው:: ለዚህ ደግሞ በእነርሱ ቤተሰብ ውስጥ ያለው የወንድና የሴት ሥራ አለመለያየት ትልቅ አስተዋፅዖ እንደነበረው ታነሳለች:: ሁሉም ለሁሉም መሥራትና መለወጥን:: በዚህ ውስጥም ሰው ገንዘብና ውርስ ባይኖረው እንኳን ንጹህ ልብ ካለውና የመሥራት ፍላጎትን ካነገበ ስኬቱ ላይ ይደርሳል የሚለውን አረጋግጦላታል::
ትምህርት ከሥራ ጋር
በትምህርቷ ቤተሰቧ ተስፋ የሚጥልባት ልጅ ነበረች:: ለእህቶቿም ሆነ ለወንድሞቿ ከእርሷ በላይ አርኣያ የሚሆን እንደሌለ ሲተማመኑባት ቆይተዋል:: እሷም 12ኛ ክፍል እስክትደርስ ጉብዝናዋን አረጋግጣለች:: የደረጃ ተማሪ በመሆኗም ቤተሰቧን አስመሰግናለች:: በመምህራኖቿ ዘንድም ቢሆን ምስጉንና ተወዳጅ ተማሪ ነበረች:: ማትሪክ ከወሰደች በኋላ ግን ነገሮች ተቀየሩ:: ተስፋ አስቆራጭ ችግር ገጠማት:: ውጤቷ የታሰበውን ያህል ሊሆን አልቻለም:: ለዩኒቨርስቲ የተጠበቀችዋ ልጅ ከቤቷ ቀረች:: የዚህን ጊዜ ሰማዩ በላይዋ የተደፋ አስኪመስላት ነገሮች ከበዷት:: ምን ማድረግ እንዳለባት ግራ ተጋባች::
ዮሀና ጭንቀትና ሀፍረት ውስጧን አደማው:: በተለይ አጋጣሚዎች የአባቷን ቃል እንዳሳጠፏት ባሰበች ጊዜ ሕመሟን ባሰባት:: ስማቸውን በአገር ብቻ ሳይሆን በዓለም አደባባይ አስጠረዋለሁ የምትለው ልጅ የዩኒቨርስቲ ውጤት ማምጣት አለመቻሏ በእጅጉ አበሳጫት:: እናም በቶሎ ትምህርት ቤት ላለመግባት ወስና ራሷን ለማረጋጋት ትጣጣር ጀመር::
እናቷና ወንድም እህቶቿ በብዙ ጎዶሎዎቿ ከጎኗ እየተገኙ ደገፏት:: ችግሩንም እንድትረሳው፣እንዳታስበው አደረጓት:: ከቤተሰብ ሳትርቅ ቢሾፍቱ ከተማ ሆና ለመማር ወሰነች :: በዲፕሎማ አካውንቲንግ ለመማርም ተመዘገበች:: የዲፕሎማ ትምህርቱንም በቁምነገር ያዘችው:: ትኩረት ሳትነፍግ አጥብቃ እየተከታተለች መማሯን ቀጠለች:: በዚህ ጥረቷ ግን እስከመጨረሻው አልገፋችበትም:: ከያዘችው በላይ የምታስቀድመው ሌላ ጉዳይ ከዓይኖቿ ገቡ :: የልጆችን ስቃይ እያዩ የራስን ምቾት ማደላደል ትክክል እንዳልሆነ ያሳሰባት ያዘ::
እሷ ዲፕሎማ እየተማረች በነበረ ጊዜ በርካቶች በትምህርት እድልም ይሁን በሌላ አጋጣሚ ውጭ አገር መውጣትን የሚመኙበት ጊዜ ነበር፣ አብዛኞቹም ከራሳቸው በላይ ሌሎችን ለማየት አይደፍሩም ::
ዮሀና ከሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታዋ የተለየ በመሆኑ ወዲያው የፈለገችውን አግኝታ ነበር:: በዛን ወቅት ከደቾች ወይም ከኔዘርላንድ ተወላጆች ጋር ትግባባለች :: ይህ አጋጣሚም ምን እናድርግልሽ ሲሉ ላቀረቡላት ጥያቄ ከቁሳዊ ፍላጎት ይልቅ ትምህርቷን እንደምታስቀድም ትገልጽላቸዋለች :: ዮሀና ውጭ አገር ሄዳ መማር እንደምትፈልግ ትናገራለች:: ፈቃዳቸውን በሰጧት ጊዜም ሂደቱን ጀመረች:: በዚህ መሐል ግን እነዚሁ ሰዎች ሌላውን ነገር አሳሰቧት::
ሰዎቹ ኢትዮጵያ በቆዩባቸው ጊዜያት በርከት ያሉ ሕጻናትን በችግር ሲማቅቁ አይተዋል:: በዚህም ልባቸው ሲያዝንና ውስጣቸው ሲጨነቅ ቆይቷል:: ይህን ስሜት ይዘው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ዮሀናን አማከሯት:: ይህ እውነት የበርካታ ልጆች ታሪክ ነው:: ችግሩ የእነሱ ሳይሆን የእሷና የሌሎች ወገኖች ግዴታ ሊሆን ይገባል::
ዮሀና ጉዳዩን ስታወጣ ስታወርድ አድራ ይበጃል ያለችውን ሀሳብ አቀረበችላቸው:: ይህም የእነሱ እገዛ ሳይለያት NGO አቋቁማ እነርሱን እየደገፈች መኖር እንደምትሻ የሚያበስር ነው:: ሰዎቹ እጅጉን ተደስተው በሀሳቧ ተስማሙ:: እንዳለችው ከጎኗ ቆመው ሥራውን ጀመሩ ኃላፊም፤ መሥራችም ሆና መሥራቱን ቀጠለች በዚህ መሀል ስትጓጓለት የቆየችው የትምህርት እድል ምላሹን አገኘ :: ዮሀና ውጭ ሀገር ተጉዛ የተሻለውን ትምህርት የምታገኝበት፣የልጅነት ሕልሟንና የአባቷን ፍላጎት የምትሞላበት ጊዜው ደረሰ:: አሁን በትናንቱ አለመሳካት አትቆጭም:: ባለፈው ታሪክም አታዝንም:: ይህ ዕድል ለእሷና ለመላው ቤተሰብ ዕንባን ከዓይኖች ያብሳል:: የሳቅ ዘመንን ያውጃል::
ዮሀና ዘንድ ያደረው ስሜት ግን ብዙዎች ከሚያሰቡት የተለየ ሆነ:: እሷ ይህን ዕድል እንደትናንቱ ልትቀበለው አልወደደችም:: ከራሷ ምቾት ይልቅ የሌሎችን አስቀደመች:: ከእኔ ዓለም የሌሎች ይቀድማል ስትል ዲፕሎማ መማሯን አቁማ ፤ ውጪ አገር መጓዙን ትታ ለዓመታት ድርጅቱን በኃላፊነት ለመምራት ወሰነች፤ አደረገችውም ::
ዮሀና ከዓመታት የሥራ ላይ ቆይታ በኋላ ነው ሁኔታዎች ከትምህርት ውጪ መሆን እንደሌለባቸው ቢገባት መማሯን ቀጠለች :: ዩኒቨርሲቲ ገብታም ከአንድም ሁለት ዲግሪዎችን ያዘች ::
ፈተናና ጣፋጩ ድል
ዮሀና 12ኛ ክፍልን እንዳጠናቀቀች ያለፈችባቸው አጋጣሚዎች ነገሮችን በተለየ ዓይን እንድታይ አድርጓታል:: እንዲህ መሆኑ ደግሞ የልጅነት ሕልሟን ለማሳካት ጭምር በር ከፍቶላታል:: በእርግጥ ይህም ቢሆን ቀላል ውሳኔን የሚጠይቅ አልነበረም:: አጋጣሚው የራስ እድልን ለሌላ እስከመስጠት በሚያደርስ ውሳኔ የተሞላ ነበር:: በወቅቱ ዮሀና ከተቀረጸችበት ማንነቷት ጋር ነበረች:: ሰውን መርዳት የኖረችለት ዓላማዋ ነውና አድርጋዋለች:: ‹‹ከትምህርቴ ሰውን መርዳት ይበልጣል›› ስትል ያገኘችውን ውጭ አገር ሄዶ የመማር እድል መልሳለች:: እንዳሰበችው ከሀገሯ ቀርታም ልጆችን የመታደግ ሥራዋን አሳክታለች ::
በራሷ ውሳኔ መርጣ መሐን የሆኑ ኔዘርላንዳዊ ባልና ሚስቶች እርሷን ጭምር እንደ ልጅ እያዩዋት የሀገሯን ልጆች እንድታግዝ አድርገዋታል:: ሕልሟ ስለተሳካላት የሚታገዙ ፤ ልጆችን ይዛ ከስምንት ዓመታት በላይ ሠራች:: ሕጻናትን የመርዳት ጉጉቷንም አሳካች:: በዚህ ውሳኔዋ ዛሬም ድረስ ደስተኛ ናት::
ዮሀና ለችግር የተጋለጡ ልጆችን ለማገዝ በእርሷ አነሳሽነት የተቋቋመውድርጅት ሴቭ ሄቨን የሚባል ነው:: የመጀመሪያዎቹን ዓመታት ሰዎችን በማገዝ ዙሪያ አተኩራ ሥትሠራበት ቆይታለች:: ድርጅቱን በምትመራበት ወቅት የቤተሰብ ፍቅር ብቻ ሳይሆን የሚፈልጉትን ዓመታዊ ድጋፍ የምታደርግላቸው 400 ልጆች ነበሯት :: ኤች.አይ.ቪ ፖዘቲቭ የሆኑ ሴቶችንም እንዲታገዙ አድርጋለች:: እነዚህን ሴቶች ከአልጋቸው ተነስተው ለልጆቻቸው እንዲደርሱ በብዙ ደግፋቸዋለች::
ድጋፉ የሚያተኩረው ለሴቶቹ የመጀመሪያ ስልጠና በመስጠት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ መንቀሳቀሻ ካፒታል እንዲያገኙ በማድረግ ነው:: በዚህ ደግሞ ብዙ ፍሬያማ ልጆችን ለአገር እንዲያበረከቱ አድርጋለች::
እነዚህ ሴቶች በመንግሥት በኩል የመጡ ሲሆኑ፤ በልደታ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 15 ወይም ትንባሆ ሞኖፖል አካባቢ የሚኖሩ ናቸው:: መንግሥት ቢሮ ሰጥቷትም ነው ሥራውን ስትሠራ የቆየችው:: ሁሉም የሚሹት ተሟልቶላቸው ጥሩና ሰኬታማ ተማሪዎች እንዲሆኑ አስችላቸዋለች::
ዮሀና ‹‹ተሰጥዖ ማለት ለተጠሩበት ዓላማ መኖር መቻል ነው›› የሚል እምነት አላት:: በዚህ ውስጥ ደግሞ እርካታ ብቻ ሳይሆን ማንነትን ማወቅ ይቻላል ባይ ነች:: እርሷ ተሰጥዖዋን ማወቋ ለዛሬ መልካም ጉዞዋ መንገድ ጠርጋበታለች:: አምላክ ለሁሉም አንድ አይነት ነገር አይሰጥምና ለሰው መኖርን የተሰጣት በረከት እንደሆነ አረጋግጣለች:: በዚህም እናትና አባት የሌላቸውን 12 ልጆችን አሳድጋ ለወግ ማዕረግ አብቅታለች:: ልጆቹ ምንም አይነት ዘመድ የላቸውም:: እርሷ ግን ዘመድ ሆናቸዋለች::
ሁሉም ልጆች እንደሌሎች ሕጻናት የልደት ቀናቸው አይታወቅም :: እርሷ ግን ለእያንዳንዳቸው የውልደት ቀን አበጅታላቸዋለች:: ስማቸውን ሳይቀር ያወጣችላቸው ራሷ ናት:: እናትም ፣አባትም፣ ዘመድም ሆና ተንከባክባቸዋለች::
ለአገሯ ልጆች ያልከፈለችው መስዋዕትነት የለም:: ከልጆቿ በላይም ለእነርሱ ዋጋ ሰጥታለች:: ለልጆቹ የራሷን ዕድል አሳልፎ ከመስጠት ባሻገር የትምህርት ቁሳቁስና አጠቃላይ ምግባቸው ተችሏቸው እንዲማሩ አስችላለች:: የራሷን ልጆች ስታሳድግ በባለቤቷም ሆነ በቤተሰብ በኩል ድጋፍ ይኖራል:: በዚህም ደግሞ ሸክሟ ቀላል ይሆናል:: ወላጅ የሌላቸው ልጆችን ማሳደግ ግን ከዚህ እውነት ይለያል:: ለእነዚህ ልጆች ድጋፍና እንክብካቤ ማድረግ ግን ታላቅ አደራን እንደመሸከም ነው:: በዚህም ኃላፊነቴን በመወጣቴ ደስተኛ ነኝ ትላለች::
ዮሀና ወደዚህ ሥራ ስትገባ ገና በ18 ዓመቷ በመሆኑ ማንም ስኬታማ ትሆናለች ብሎ አልጠበቃትም :: ነገሮችን የመራችበትና ስትሠራበት የቆየችበትን ሁኔታ ሲመለከቱ ግን በርካቶች ያደንቋት እንደነበር አትረሳም:: ይህ እድሜ እንደሚታወቀው ከቤተሰብ እንኳን የማንላቀቅበት ነው:: ትምህርትንም ለማጠናቀቅ ብዙ የሚለፋበት ጊዜ እንደሆነ ግልጽ ነው::
ዮሀና በዚህ እድሜዋ ለሌሎች ተስፋ ሆናለች:: ለአገር መልካም የሆኑ ዜጎችን ፈጥራለች:: በዚህም ሁልጊዜ ደስ ይላታል :: ይሁንና የሚሠራ ሲኖር ነገሮች ፈተና የሚሆኑበት አጋጣሚ አይጠፋምና ይህንን መልካም ሥራዋን የሚያጨልምባት ክስተት ተፈጠረ:: ይህም በመንግሥት በኩል ለ NGO ድርጅቶች የወጣው የ70፤ 30 መመሪያ ነው::
ይህ መመሪያ ነገሮችን ድብልቅልቅ አደረገባት:: የምትወዳቸውንና የምትንሰፈሰፍላቸውን ልጆች እንድትበትን አስገደዳት:: ለዚህ ደግሞ መንስኤው የእርሷ የገቢ ምንጭ የውጪ አገር ዜጎች መሆናቸው ነበር :: እናም በራሷ አቅም ነገሮችን ማስቀጠል ስለከበዳት ያሏትን አነስተኛ ልጆች ለሌላ ድርጅት በመስጠት ለጊዜው ሥራውን አቆመች:: ከዓመታት በኋላ ግን የሕልሟን ጥሪ ዳግም ጀመረችው::
አሁን ‹‹ኬር ፎር ጀነሬሽን ዴቨሎፕመንት ቻሪቲ›› የሚባል ድርጅት ከፍታ በመሥራት ላይ ትገኛለች:: ድርጅቱ እንደቀድሞው ሁሉ ሕጻናትና እናቶች ላይ ልዩ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራ ነው::
የመጀመሪያው NGO ሲዘጋ የሥራ ዘርፏን የቀየረችው ባለታሪካችን፤ የትምህርት ዘርፉን ለመቀላቀል ችላለች:: ይህም ዘርፍ ሌላ ፈተና ያለበት ቢሆንም እንደርሷ ግን ይህ ፈተና የሚሆንበት አጋጣሚ የለም ባይ ናት:: ስለዚህም ሥራውን ኮሌጅ ከፍታ በመሥራት ጀምረዋለች:: ኮሌጁ ‹‹ጎልደን ስታር›› ይባላል:: ዋና ትኩረቱም ማኅበረሰቡን ማገልገል ነው:: ኮሌጁ በተለያየ ችግር ላይ ያሉ ዜጎችን በማገዝ እየሠራ ይገኛል:: እንደሷ ዕምነት በተለይ አቅም ኖሯቸው መማር ያልቻሉ ሴቶችና አካል ጉዳተኞች ችግር እንዲገጥማቸው አትፈልግም:: ስለዚህም እነርሱን ማገዝ ባለባት ልክ እያገዘች በመሥራት ላይ ትገኛለች:: ፖሊሶችንና በማረሚያ ቤት የሚገኙ ወገኖችን በቅናሽ ዋጋ የመማር እድል እንዲያገኙ አመቻችታለች:: በተመሳሳይ የዓመት ሙሉ የክፍያ ወጪያቸውን በመሸፈን እስከ 20 ሰዎችን በነጻ ታስተምራለች::
ሌላው የሠራችውና ለውጥ እያመጣችበት ያለው ተግባር ደግሞ በማማከር ላይ የምትሠራበት ድርጅት ነው:: ድርጅቱ ጎልደን ብሪጅ ትሬኒግ ኤንድ ኮንሰልታንሲ ፒኤልሲ በመባል ይጠራል:: ስብሰባና ኮንፍረንሶችን በማዘጋጀት ጭምር የሚሠራ ድርጅት ነው:: የማማከር ሥራው በዋናነት ትኩረቱን የሚያደርገው ከለውጥ ሥራ ጋር በተያያዘ ነው:: ሥራ ፈጠራና ሴቶችን ማብቃት፣ እንዲሁም ወደአመራርነት ማምጣት ላይ ትኩረት ያደርጋል :: በዚህም እስካሁን በትምህርቱ ዘርፍ እንደሠራችው ባይሆንም በርካታ ተግባራትን ከውናለች:: በተለይም ከሴቶችን ጋር ተያይዞ ለውጥ ያመጣችባቸውም ቦታዎች እንዳሉ ታነሳለች::
ዮሀና በዚህ ዘርፍ በሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አካባቢ የተሠራውን ተግባር በምሳሌነት ታነሳለች :: ሴቶቹ ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ከነበሩበት ደረጃ ወደ አመራርነት ጭምር እንዲመጡና ከፍ እንዲሉ ማገዟ አንዱ መሆኑን ትጠቅሳለች::
ዮሐና ‹‹ የእኔ ስኬት በእኔ ሰበብ ሌሎች መኖር ሲችሉ ነው›› የሚል እምነት አላት:: ይህንን ደግሞ በእውቀት አዳብራ መሥራት ትፈልጋለችና አድርገዋለች:: ከራሷ ፍላጎትና ከራሷ ምቾት ይልቅ ሌሎችን አስቀድማም አሳይታለች:: እንደእርሷ እምነት ሰው ለሰው ኖርኩ ሲል ከአለው ምቾቱ ላይ ቀንሶ ለሌሎች ማካፈል ሲችል ነው:: የዚያን ጊዜ ለእነርሱ ብቻ ሳይሆን ለራሱም የሚደርስ ስኬትን፣ደስታን ያገኛል:: ይህንንም በራሴ አይቸዋለሁ ትላለች:: ስኬት ላይ ግን አልደረስኩም እንደውም ገና ዳዴ እያልኩ ነው ባይ ነች:: ብዙ የምሠራቸውና ለሀገሬ የማበረክታቸው ነገሮች አሉኝ፤ ሀገሬና ፤ አባቴ የከፈሉልኝን ዋጋ ገና አልጀመርኩትም ትላለች ::
አሁናዊ ሁኔታ
ወይዘሮ ዮሀና ጎልደን ስታር ኮሌጅን በኃላፊነት ትመራለች:: ሌላው ጎልደን ብሪጅ ትሬኒንግ ኤንድ ኮንሰልታንሲ ፒኤልሲ እንዲሁም ‹‹ኬር ፎር ጀነሬሽን ዲቨሎፕመንት ቻሪቲ ›› በመክፈት ድርጅቱን በዳይሬክተርነት እየመራች ትገኛለች:: በሦስቱም የሥራ ዘርፎች ላይ ለ70 ሠራተኞች የሥራ እድል ፈጥራለች::
ጎልደን ስታር ኮሌጅ በሀዋሳ ፣ በሆሳዕና እና በአዲስ አበባ ከተሞች በመሥራት ላይ ይገኛል:: በቅርቡ ደግሞ በሐዋሳ ሁለተኛውን መደበኛ ቅርንጫፉን ይከፍታል::
ቀጣይ ህልም
ዮሀና በትምህርት ዘርፉ የተሻለ መሥራት የመጀመሪያው እቅዷ ነው:: እንደ ሀገር የለንም የሚባለው ያልተማረ ሰው ሳይሆን የተማረው ሰው ሀገሩን፣ ኅብረተሰቡን የሚያይበት ዓይን ነው:: የተማረው ዜጋ ሀገሩንና ሕዝቡን መውደድ አለበት:: ስለዚህም ስብዕና ግንባታ ላይ ፍሬያማ ሥራ ማከናወን ትፈልጋለች:: በተጨማሪም አቅም ያላቸው ሴቶችን ማፍራት :: ለዚህም የተለያዩ ስልጠናዎችን በግልም ሆነ በተቋም መስጠት፣ የሚማሩበትን እድል ማመቻቸት ዓላማዋ ነው::
ወጣቶች ከሱስና ከመጥፎ ተግባራቸው ወጥተው የራሳቸው ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ማስቻል ላይም የመሥራት ፍላጎት አላት :: እናቶችን የማመስገኛ ቀን በቋሚነት የማዘጋጀትና እንዲታገዙ ማድረግ ላይም እቅድ አላት:: በተመሳሳይ ወጣቶች በተለይም ተመራቂ ተማሪዎች ደም እንዲለግሱ በማበረታታት አገር ወዳድነታቸውን እንዲያሳዩ የማስቻል ዓላማን ሰንቃለች:: ይህም ከዘንድሮ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ለመሆን ዝግጁ ነው ::
መልዕክት
ሰዎች ስኬታማ ለመሆን ሦስት ነገሮችን አጥብቀው መሻትና ወደተግባር መቀየር አለባቸው:: የመጀመሪያው የሚሠሩትን ነገር መምረጥና ለዚያ ነገር ራሳቸውን ማዘጋጀትና ማሳመን ሲሆን፤ ሁለተኛው የሚመጡ እድሎችን ወደ ዓላማው መቀየር የሚለው ነው:: ከሌሎች ሳይሆን ከራስህ ለራስህ እድልን ተጠቅሞ ወደ ዓላማ ማምጣትን ማሳየት ያስፈልጋል:: በተለይም የራስን እድል በራስ ለመወሰን መትጋት ይገባል::
ዛሬ እያጨድን ያለነው የዘራነውን ነው:: ትውልድ ላይ ያለመሥራት ውጤት መልካም ነገሮቻችንን ጭምር ያወድምብናል:: ማንነታችንንም ያስረሳብናል:: ደፋር፣ አገር ወዳድ፣ ባለታሪክ፣ ጀግና፣ እንግዳ ተቀባይ የምትባለው ኢትዮጵያ በግጭት መነሳት የጀመረችውም ለራሳችን ብቻ በመጨነቅ ውስጥ ተዘፍቀን ሌሎችን ማየት ባለመቻላችን ነው::
እናም ዛሬን ዛሬ ላይ ችግራችን እንዲያከትም ከፈለግን፤ ግጭቶች እንዳይቀጥሉ ካሰብን ትምህርቱ ዘርፍ ላይ ከጥራቱ ባልተናነሰ መልኩ ሥነምግባር ላይ መሥራት አለብን:: የዚያን ጊዜ ሀገርን የሚወደውን ዜጋ እናገኘዋለን፤ ከአገሩ አልፎ ለዓለም ተስፋ የሚሆነውን ትውልድ እናየዋለን ስትል መልዕክቷን ታስተላልፋለች::
የትምህርት ተቋም ትውልድ የሚቀረጽበት ቦታ ነው:: ትውልድን ስናነሳም ሀገርን ማንሳታችን አይቀርም:: ስለዚህም ሀገርን መገንባት ተደርጎ መወሰድ አለበት:: በተለያዩ አገራት የመዞር አጋጣሚው ነበረኝና ማንም ዜጋውን ሳይሠራ ሀገሩን እንደማይገነባ ተረድቻለሁ:: ስለዚህም የትምህርት ተቋማት የሚያስተምሯቸውን ተማሪዎች ሀገራቸውን እያሰቡ መሥራት አለባቸው የሚል እምነት አለኝ:: እኔም በዚያ ልክ እየሠራሁ እገኛለሁ:: አባቴ የሚወዳትና የሞተላትን አገር እኔም መታደግ አለብኝና በትምህርት ጥራቱ የተሻለች እንድትሆን እተጋለሁ ::
የከፈትኩት ኮሌጅ ስያሜ ‹‹ወርቃማ ኮከብ›› ነው:: ወርቅ ለማግኘት ደግሞ ከባድ ልፋትን ይጠይቃል:: እናም የእኔ ኮሌጅ ዓላማ ተማሪዎች ወርቃማ ኮከብ ሆነው ለአገራቸው ብሎም ለዓለም እንዲያበሩ ማድረግ ነው::
እውቀት የሚገዛም የሚሸጥም አይደለም:: ትምህርት የንግድ ቦታ አይደለም:: ማንኛውም መሥሪያ ቤት ሄደን ለአገልግሎት እንደምንከፍለው ሁሉ በዚህም ለመምህራንና ለሌሎች ወጪዎች የሚሆን ገንዘብ ከፍለው እንዲማሩ ይደረግበታል እንጂ :: ስለዚህም ትምህርት ንግድ ሳይሆን ትውልድን የማውጣት አደራ ነውና ያንን አስበን እንሥራ መልዕክቷ ነው::
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 22 ቀን 2015 ዓ.ም