ዓመታት በፊት፣ በዚህ ሳምንት (ከመጋቢት 23 እስከ 29) በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከተከናወኑ /ከተከሰቱ/ ድርጊቶችና ክስተቶች መካከል ጥቂቶቹን እንደሚከተለው አቅርበናል፡- መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም – ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ አረፉ። ዘውዲቱ ምኒልክ የተወለዱት ከታላቁ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክና ከወ/ሮ አብችው በያን ነው። ገና የስድስት ዓመት ተኩል ልጅ ሳሉ ለንጉሰ ነገሥት አጤ ዮሐንስ ፬ኛ ልጅ ለራስ አርዓያሥላሴ ዮሐንስ ተዳሩ።
ከአምስት ዓመታት በኋላም ራስ አርዓያሥላሴ ዮሐንስ ስለሞቱ ዘውዲቱ ወደ ሸዋ ተመለሱ። በ1884 ዓ.ም ደግሞ ደጃዝማች ውቤ አጥናፍሰገድን አግብተው መኖር ጀመሩ። ይህ ጋብቻም ፈረሰና በ1893 ዓ.ም የእቴጌ ጣይቱ የወንድም ልጅና የጎንደር ገዢ የሆኑትን ራስ ጉግሳ ወሌን አገቡ። መስከረም 17 ቀን 1909 ዓ.ም ልጅ ኢያሱ ሚካኤል ከስልጣን ሲሻሩ ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥት፤ ተፈሪ መኮንን ደግሞ ታላቁን የሰለሞን ኒሻን ተሸልመው ‹‹ራስ›› ተባሉና አልጋ ወራሽ ሆነው ተሾሙ።
ልጅ ኢያሱ ከስልጣን ተሽረው ዘውዲቱና ተፈሪ ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ ዘውዲቱ ሞተው ተፈሪ መኮንን ንጉሰ ነገሥት እስከሆኑበት ጊዜ ድረስ እጅግ ከፍተኛ የስልጣን ሽኩቻ የታየበት ወቅት ነበር። ልዑል አልጋወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን ንጉስ ሚካኤል ዓሊን በሰገሌ ጦርነት፣ እነ ደጃዝማች አባውቃውንና ሌሎች የዘውዲቱ ደጋፊ መኳንንትን በጉልበትና በድርድር ካሸነፉ በኋላ አንድ ተቀናቃኝ ቀራቸው፤ ይህሰው የንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ የቀድሞ ባል ራስ ጉግሳ ወሌ ነበሩ።
ራስ ጉግሳ ከቤተ-መንግሥት እንዲርቁ በመደረጋቸውና የባለቤታቸው የዘውዲቱ ምኒልክ ስልጣን በራስ ተፈሪና ደጋፊዎቻቸው እየተገዘገዘ በመሄዱ በራስ ተፈሪ መኮንን ላይ ቂም ከቋጠሩ ውለው በማደራቸው የሁለቱ ወገኖች ልዩነትና ፀብም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ ሄደ። በመጨረሻም የሁለቱ ወገኖች ፀብ ወደ ጦርነት አምርቶ መጋቢት 22 ቀን 1922 ዓ.ም የአንቺም ጦርነት በጌምድር ውስጥ ተካሄደ።
በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የጦር አውሮፕላኖች ጥቅም ላይ ዋሉ። ራስ ጉግሳም የጨበጣ ውጊያ ላይ ሳሉ ጭንቅላታቸውን ተመትተው ሞቱ። በጦር አውሮፕላኖች የታገዘውና ከራስ ጉግሳ ጦር የተሻለ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀው የነራስ ተፈሪ ጦር ባለድል ሆነ፡፡ ራስ ተፈሪ ተቀናቃኞቻቸውን መንጥረው ጨረሱ። ዘውዲቱና ዘውዳቸው ብቻቸውን ቀሩ። ከጦርነቱ ሁለት ቀናት በኋላ (መጋቢት 24 ቀን 1922 ዓ.ም) ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ስርዓተ ቀብራቸውም ራሳቸው ባሰሩት በታዕካ ነገሥት ባዕታ ለማርያም ገዳም በደማቅ ሥነ-ስርዓት ተፈፀመ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 27/2011
አንተነህ ቸሬ