የዛሬው የዘመን እንግዳችን መምህርና ተመራማሪ ናቸው ። አቶ ሱራፌል ጌታሁን ይባላሉ ። ትውልድና እድገታቸው ሻሸመኔ ከተማ ውስጥ ሲሆን የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው ከተማ በሚገኙት ቡርኪቱና ዶዶላ በተባሉ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው የተከታተሉት ። በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ዲፕሎማቸውን በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሰርተዋል ። በፖለቲካ ሳይንስና አለምአቀፍ ግንኙነት የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን እንዲሁም በፒስ ኤንድ ሴኩሪቲ ትምህርት መስክ ሁለተኛ ዲግሪያቸው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል ።
የተለያዩ ምርምሮችንና ጥናቶችን ያካሄዱት እኚሁ ሰው በተለይም በአባይ ወንዝ ተፋሰስ ሃገራት ውሃን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችና ትብብሮችን በሚመለከት ባካሄዱት ጥናት ይታወቃሉ ። እንዲሁም የለውጡ መንግስት መምጣቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ስርዓት ሂደትና ሽግግር ላይ ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ዙሪያ ያከናወኑት ጥናት ተጠቃሽ ነው ። ላለፉት አስር ዓመታት በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት እያገለገሉ ያሉት እኚሁ ሰው የዛሬው የዘመን እንግዳችን ናቸው ። ከፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ ከአቶ ሱራፌል ጌታሁን ጋር በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ በተለይም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን በቅርቡ በኢትዮጵያ ላይ ባወጣው ሪፖርት ዙሪያ ውይይት አድርገናል፤ እንደሚከተለው ይዘን ቀርበናል ።
አዲስ ዘመን፡- በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብት ባለሙያዎች በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ ተፈፅሟል ያሉትን የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንዲያጣሩ ያቋቋመው ኮሚቴ ሪፖርት አውጥቷል። በዚህ ሪፖርት ላይ ያለዎትን ምልከታ በማስረዳት ውይይታችንን ብንጀምር?
አቶ ሱራፌል፡- እንደምታስታውሽው ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር በጋራ ያወጡት ሪፖርት ነበር ። በተለይ የዘር ጭፍጨፋ እያሉ ለሚያነሱት ነገር ምንም ተጨባጭ ማስረጃ እንደሌለና ከዚህ ቀደም ‹‹ረሃብን እንደጦር መሳሪያ ተጠቅመዋል›› እየተባለ የሚነሳ ከፍተኛ ውንጀላ ነበር ። እነዚያ ውንጀላዎች ምንም አይነት ማስረጃና መረጃ በሌለበት ነገር ላይ በአሉባታና አሸባሪው ቡድን የፈጠረው ወሬና ፕሮፖጋዳ እንደሆነ አረጋግጧል ። በሌላ በኩል ግን ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ጉዳዮች ላይ ዘርዝሮ አስቀምጦ ነበር ። አማፂው ቡድን ደግሞ ያደረሰውን ከፍተኛ የሰው ፍጅት እንዲሁም የሰብአዊ መበት ጥሰት፤ ከዚህም ባሻገር የማህበራዊ ተቋማት ውድመትን በዝርዝር አስቀምጦም ነበር ። በጣም በሚገርም ሁኔታ በጥምረት የተሰራው ይህ ሪፖርት ተቀባይነት አግኝቶም ነበር ። በብዙ ሃገራትም ጭምር ይሁንታ ተሰጥቶትም ነበር ።
ይሁንና ይህንን በጋራ የተሰራን ጥናት ባፈረሰ መንገድ ድርጅቱ ሌላ ኮሚቴ አቋቁሞ የፖለቲካ ይሁንታ ያለው በአንፃሩ ደግሞ መሬት ላይ ያለውን እውነታ የማይዳስስ ሪፖርት አውጥቷል ። እንደእኔ እምነት ይህ ሪፖርት መሰረታዊ ስህተት ያለበትና አግላይ የሆነ ሪፖርት ነው ። ይህንን ጥናት ሲያካሂዱ ያናገሩት የትኛው ክልል የሚኖሩትን ሰዎች ነው? የትኛው አካባቢ ሄደው በተጨባጭ ስለደረሰው ውድመት ምንያህል በቂ መረጃ አግኝተዋል? የሚሉት ጉዳዮች ግልፅ አይደሉም ። ይልቁኑ ከማህበራዊ ሚዲያ በተለይም የአሸባሪ ቡድኑ አፈቀላጤዎች ቲዩተር የተወሰደ ሪፖርት የሚመመስል አምድታ ነው ያለው ።
ሲጀመር ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት የነበረውን ሪፖርት ወደጎን በመተው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲጮህና ሲደሰኩር የነበረውን ነገር ነው ይዞ መምጣቱ በራሱ የሪፖርቱን ታዓማኒነት ሙሉ ለሙሉ ጥርጣሬ ውስጥ የሚከተው ነው ። ከዚህ ቀደም እነሂዩማን ራይትዎች ኬኒያ ናይሮቢ ስደተኛ ካፕ ላይ ተቀምጠው በስልክ የሚደርሰውን የሃሰት ወሬ ሪፖርት አድርጎ ማውጣቱ በግሌ በጣም ነው የሚያሳፍረኝ ። አንደኛ በአፋርና በአማራ ክልል የደረሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰትና ጉዳት ለማጣራት ያለመፈለጉ ድርጅቱ የሚዛናዊነት ችግር እንዳለበት ማሳያ ነው ። እውነት ስለተደፈሩት ሴቶች ጉዳይ ስለማጣራታቸው ጥርጣሬ አለኝ፤ በተለይ ኮምቦልቻ፤ ቆቦ ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማጣርት ምን ያህል ሙከራ አድርገዋል? እነማን ናቸው በዚህ ቃለመጠይቅ ላይ የተካተቱት? የሚለው ነገር ግልፅ አይደለም ። ከዚያ ይልቅ የጁንታው አፈቀላጤ ጌታቸው ረዳ የሚነግራቸውን የሃሰት ፕሮፖጋንዳና መረጃ ይዘው እንደመጡ ግልፅ ነው ።
በአጠቃላይ ይህ ሪፖርት ሚዛናዊ አይደለም፤ ፈፅሞ ከእውነት የራቁ መረጃዎችን ያካተተ ሰነድ ነው ማለት ይቻላል ። አስቀድሜ እንዳልኩሽም በዚህ ሪፖርት ላይ ዋቢ ተደርጎ ሊጠቀስ የሚችል ታዓማኒ የሆነ ምንጭም የለውም ። በመሆኑም ከአሸባሪው ቡድን ፕሮፖጋንዲስቶች ያገኙትን ነገር ይዘው መጥተው እንዲህና እንደዚህ አይነት በደል ተፈፅሟል ቢልም ተቀባይነት አይኖራውም ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብትን ጨምሮ ይህንን ሪፖርት ራሺያ ቻይና ቬትናምና ሌሎችም ሃገራት በጥርጣሬ ሁኔታ ነው ያዩት ።
በተለይ ከዚህ ቀደም በሚዲያ የሚደረግ ቅስቀሳ ነበር፤ የሕወሓት ተወካዮች በከፍተኛ ደረጃ የሰራው ስራ ቢኖር በዲጂታል ዲፕሎማሲ ገለልተኛ የሆኑትን አካላት መውቀስ ነበር ።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ሪፖርት ሚዛናዊነት የጎደለው ስለመሆኑ ማሳያ የሚሆን ለአብነት ቢጠቅሱልን?
አቶ ሱራፌል፡- እንደሚታወሰው ላለፉት ስምንት ወራት ለትግራይ ህዝብ ያለምንም ገደብ ሰብአዊ ድጋፍ ሲደረግ እንደነበር እየታወቀ ይህንን እንኳን በሪፖርቱ ላይ አለማካተታቸው ሪፖርቱ ከመሰረቱ ሚዛናዊነት የጎደለው ስለመሆኑ ያመላክታል ። ከሁሉ በላይ ደግሞ መጨረሻ ላይ የሚሰጠው ምክረ-ሃሳብም ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ በትግራይ ጉዳይ ሌላ ችግር ስለመጣ አንድ ውሳኔ ያሳልፋል የሚል በቀጥታ በውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት ያለመ ስለመሆኑ ግልፅ ሆኗል ። ይህም የራሱ ፖለቲካ አንድምታ ያለውና በእጅ አዙር ኢትዮጵያ ውስጥ ለመግባት መንደርደሪያ እንዲያበጅላቸው ያቀዱት ነው። በተለይ እነአሜሪካ ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ አካል መሆኑ ግልፅ ነው ።
በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰላም ድርድር ያስተጓጎለው ይኸው ፅንፈኛ ቡድን እንደሆነ ይታወቃል። ዋግህምራ 25 ሰዎችን ከስደተኛ ጣቢያ አውጥቶ ሲረሽን ዝም ነው ያሉት ። ለምን አላወገዙም?። ለዚህም ነው በእነዚህ ተቋማት ላይ በአንድም በሌላም ጥርጣሬ እንድናነሳ የሚያደርገን ። በጣም በሚያሳዝን መልኩ ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲቋጭ እንደማይፈልጉ ይህ ሪፖርት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ። ምክንያቱም በዚህች ሃገር ላይ ሰላም እንዲመጣ ከተፈለገ መጀመሪያ የአሸባሪውን ቡድን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደሚገባ አፅንኦት በሰጡት ነበር ። እነሱ ጦርነቱ በሰላም እንዲቋጭ ቢፈልጉ ኖሮ በቅርቡ የተመድን 70ሺ ሊትር ነዳጅ ዘርፎ በአማራና በአፋር ህዝብ ላይ ጥቃት ሲያደርስ አላወገዙም። ያኔ ለምን ድፍረትና አቅም አጡ? ከዚህ ይልቅም ምርጫቸው ያደረጉት የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና በማሳደር እንደፈለጉ ለማሽከርከር ነው ። በአጠቃላይ የተካተቱት መረጃዎች ፈፅሞ ከእውነት የራቁና ሚዛናዊ ያልሆኑ ከመሆናቸውም ባሻገር ከዚህ ሪፖርት ጀርባ ካለው እውነታ ጋርም የሚፃረር ሆኖ ነው ያገኘሁት ።
አዲስ ዘመን፡- ሌሎች ሃገራት ውስጥ በተከሰተ የእርስ በርስ ግጭት ዙሪያ መሰል ጥናት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ተካሂዶ ያውቃል? በተለይ መንግስትና የተጎዶ ማህበረሰቦችን ባላካተተ መልኩ የሚደረግ እንዲህ አይነት ጥናት ምንን ያሳያል?
አቶ ሱራፌል፡- አዎ ይህ ድርጅት ሁልጊዜም ቢሆን የሚያከናውናቸው ጥናቶች እንደአሜሪካ ያሉ ሃያላን ሃገራትን ጥቅም ለማስጠበቅ አላማ አድርገው የሚነሱ ናቸው ። ሲፈልጉ የእነሱን ጥቅም እስካልጎዳ ድረስ የቱንም ያህል ህዝብ ቢያልቅና የሰብአዊ መብት ቢጣስ ደንታ የላቸውም ። ጥቅማቸውን የሚነካ መስሎ ከታያቸው ደግሞ በሰበብ ባስባቡ ጫና ለመፍጠር የሚያስችላቸውን መሰል ጥናቶች በማካሄድ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማስተባበር ይጠቀሙበታል ። ይህ አቋማቸው ደግሞ በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ላይ በተደጋጋሚ የታየ ነው ።
ለምሳሌ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አንዱ የሚወቀስበት ጉዳይ በምስራቃዊ ኮንጎ እ.ኤ.አ ከ1979 ዓ.ም ጀምሮ እስከ 2003 ዓ.ም ከአምስት ሚሊዬን ሰው በላይ ሲሞት በዝምታ ያለፉበት ሁኔታ ነው ። ምክንያቱም ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ሆነ ተቋሙን እንዳሻቸው የሚያሽከረክሩት ሃያላን ሃገራት በዚያ አካባቢ ላይ የምዕራብውያኑ ኩባንያዎችና የዘይት ማዕድን የሚያወጡና የሚዘርፉ ግለሰቦችን ለመታደግ ሲሉ ነው ። በዚያች ሃገር ላይ ከፍተኛ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ተካሂዶ ሳለ የእነሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ ምዕራባውያኑ ዝምታን ነው የመረጡት ። አንድም ቀን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ደፍሮ በዚያ ጉዳይ ላይ ሪፖርት ያወጣበት ነገር የለም ።
በሌላ በኩል ደግሞ እንደሚታወሰው በሱዳን ዳርፉር ላይ የተፈጠረውን የርስ በርስ ግጭት አስታኮ በመግባት ጉዳዩን ወደ ዘር ጭፍጨፋነትና ሰብአዊ መብት ጥሰት በማዞርና የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ያሳመኑበት ሁኔታ ነበር ። በጣም የሚያስገርመው ነገር በዳርፉር ጉዳይ ላይ የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት አልበሽር ለመክሰስ አንድ የአሜሪካ ፀሐፊ በየሳምንቱ ከ200 እስከ 400ሺ ሰው እየተጨፈጨፈ እንደሆነ እየፃፈ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብን ለማነሳሳት ጥረት ሲያደርጉ ነበር ። አልበሽርን ለመክሰስ ሲሉ ብቻ ግጭቱን የዘር ማጥፋት እንደሆነ በድፍረት ይፅፉ ነበር ። እነሱ አጋነው ባወጡት ሪፖርት ምክንያት ነው ዓለምአቀፉ ማህረሰብ አልበሽር ላይ እንዲነሳባቸው ያደረጉት ።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ ላይ ያወጡት የዚያ ሪፖርት ዋነኛ አላማው አስቀድሜ እንዳልኩሽ የፖለቲካ ፍላጎት ነበር ። ልክ አሁን እኛ ላይ እንደሚያደርጉት የሱዳን መንግስትን የማወከብና የመክስስ ሁኔታ ነበር ። በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ህዝብ በሚያልቅባቸው ሃገራት ዝምታን የመረጡበት ሁኔታ ነው ያለው ። ለምሳሌ የዛሬ ሶስት ዓመት ገደማ በርማ ላይ የፓርቲው ወታደር ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት ፈፅሟል፤ እስካሁንም ድረስ የምዕራብውያን ኩባንያዎች ናቸው በርማ ላይ ነዳጅ የሚቆፍሩት ። አሜሪካን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተካሄደውን ጭፍጨፋ ‹‹አፋቸውን ሞልተው የዘር ማጥፋት›› ብለው ለመጥራት አልደፈሩም ። እንዳውም ሰለጭፍጨፋው የሚናገሩትን አካላት ዝም ለማሰኘት ነበር ጥረት የሚደርጉት ።
አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ የሆነው ነገር ልክ እንደ ዳርፉር ነው ። አለምአቀፉ ማህበረሰብ በአንድም በሌላ የኢትዮጵያ ጦርነት ከራሳቸው ፍላጎትና ጥቅም መከበር ጋር ነው በቀጥታ የሚያያይዙት ። በፖለቲካ ፍላጎት የተቃኘው ይህ ሪፖርት የሚያሳየው ይህንን ነው ። አሜሪካኖች ኢራቅና ሶሪያ ላይ በሮኬት ከተማ ሲያወድሙና ህዝብ ሲጨፈጨፍ እንዲህ አይነት ሪፖርት ለምንድነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ያላወጣው?። እስራኤልስ በጋዛ ላይ ያንን ሁሉ በደል ስትፈፅም ለምን እንዲህ አይነት ሪፖርት አይወጣም? ብሎ መጠየቅ ይገባል ። ይሄ ድርጅት በአጠቃላይ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች ሚዛናዊነት የጎደለውና እውነታን ያላገናዘበ ነው ። በሌላ በኩል ደግሞ ኃላፊነት የጎደለውና የአንድ ወገን ፍላጎትን ብቻ ያማካለ ሪፖርት ለምን ጉዳይ ማስፈፀሚያ እንደሆነ ግልፅ ነው ።
በተደጋጋሚ እንደታየው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰብአዊ ድጋፍ ስራው በትህነግ ቡድን ሲስተጓጎልበት ከመክሰስ ይልቅ ዝምታን ነው ምርጫው ያደረገው ። ይህ ተቋም በተጨባጭ እውተኛ ቢሆን ኖሮ የእርዳታ ስራው በአሸባሪ ቡድኑ ሲስተጓጎል ዝም ባላለ ነበር ። ማን ነው የህፃናትን አልሚ ምግብ ዘርፎ በምሽግ ውስጥ እያደረገ ያለው? የመንግስታቱ ድርጅት ሃቀኛ ቢሆን ኖሮ ይህንን ተግባር በይፋ መኮነን ነበረበት ። ለሰብአዊ እርዳታ የገባ ነዳጅ ሲዘረፍ ዝምታን መርጠው ይህንን የሽብር ስራ የደገፉበት ሁኔታ ተገቢ አልነበረም ።
እውነት ለመናገር አሁንም አለም አቀፉ ማህበረሰብ ወይም በተመድ ስር ያሉ ተቋማት ሊያደርጉ የሚገባው ትህነግ ተጨማሪ ችግር የትግራይ ህዝብ ላይ የሚያደርስ በመሆኑ ከዚህ ተግባሩ እንዲታቀብ ማድረግ ነበር ። የፌደራል መንግስቱ ላይ የሚያደርገውን ጩኸቱንም በአማፂ ቡድኑ ላይ ማድረግ ነበረበት ። በተመሳሳይ እንደሚታወሰው ይህ ጦርነት እንደተጀመረ እነዚህ ድርጅቶች በዝምታ ያለፉበት ሁኔታ ነበር ። ምክንያቱም በዚያ ጦርነት የራሳቸው ፍላጎትና ዓላማ ስለነበራቸው ነው። ጦርነቱ በተራዘመ ቁጥር ግን ለትግራይ ህዝብ ስቃይና መከራ ነው የሚተርፈው ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ሰላም እንዲሆን እንደማይፈልጉ ይታወቃል ። ጦርነቱን በማራዘም መንግስትን ማዳከምና የራስን ፖለቲካ አጀንዳ ማስፈፀም ነው አላማቸው ።
አሁን የያዙት ነገር ‹‹የትግራይ ህዝብ በፌደራል መንግስቱ አደጋ ውስጥ ገብቷል›› ብሎ ከበሮ በመደለቅ እነሱ በሚፈልጉት መንገድ በሃገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ነው ፍላጎታቸው ። በሌላ በኩል ደግሞ የሪፖርቱ ዓላማ በሰብአዊ መብት ሰበብ የኢትዮጵያ መንግስትን ወከባ ውስጥ እንዲገባ ማድረግ ነው ። በተለይ እነሱ መጀመሪያ ለመክሰስ የሄዱበት መንገድ አለ፤ ከዚያ ውጪ ሲኮን የፈለገ ጥሩ ነገር ቢሰራ እነሱ የማይቀበሉበት ነው የሚሆነው ። የተመድ የምግብም ሆነ የጤና ድርጅቶች እውነተኛ ተቋማት ቢሆኑ ኖሮ ትግራይ አማፂ ቡድን ላይ ጫና መፍጠርና ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ይጠበቅባቸው ነበር ።
በተጨማሪም እነዚህ የተመድ ተቋማት አሸባሪ ቡድኑ የሰረቀውን ንብረት እንዲመልስ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የእርዳታ ቁሳቁሶች በትክክል ለህዝቡ አለመድረሳቸውን ማሳወቅ ነበረባቸው ። ሌላው ይቅርና የሱዳን የስደተኞች ካምፕ ላይ የትህነግ አሸባሪ ቡድን አሸባሪዎች እየተመለመሉ እየሰለጠኑ ስለመሆናቸው የኢትዮጵይ መንግስት ደጋግሞ ሲናገር ሰሚ አላገኘም ነበር፤ ሆኖም ከአንድ ዓመት በኋላና ካምፑ ባዶ ከሆነ በኋላ የተባበበሩት መንግስታት የስደተኞች ኮሚሽን መረጃ አለኝ አለ፤ መረጃ ካለው ለምን ቀድሞ አላስቆመም? በጣም የሚሳዝን ነው።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ሪፖርት በኢትዮጵያ ላይ ምን ያስከትላል ብለው ይሰጋሉ?
አቶ ሱራፌል፡- ሪፖርቱ ዓለም አቀፍ ማህበረሰቡን በከፍተኛ ደረጃ ሊያታልሉ ይችላሉ የሚል ስጋት አለኝ ። በተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ስር የሚወጣው ሪፖርት የተቋሙን ዓላማ የሚወክል ነው ተብሎ የሚነሳው ። ግን ሪፖርቱ አስቀድሜ እንዳነሳሁት ከዚህ በፊት የወጣውን ሪፖርት የጣሰ፣ ተዓማኒነት የጎደለውና ስህተት ያለበት ነው ። ከዚህ ባሻገር እነሱ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ መንግስት ለመጣል የሚፈልጉት ማዕቀብ እንዳለ ግልፅ ነው ። በተለይም እነአሜሪካ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አማካኝነት አንድ ማዕቀብ መጣል፣ ሲቪል ሶሳይቲዎች መንግስት ላይ ጫና እንዲፈጥሩ እና የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሃይል በአካባቢው እንዲሰማራ ማድረግ ዋነኛ ነው ፍላጎታቸው። ምክንያቱም የእጅ አዙር ቅኝ ግዛትን አሻፈረኝ ያሉ ሌሎች አገራት ላይም የተደረገው ይህ ነው። ሱዳን ላይ ያደረጉት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው ።
እርግጥ በኢትዮጵያ ካለው ነባራዊ ሁኔታ እዛ ካለው ሁኔታ ይለያል ። ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ አይነት ሪፖርቶች የፖለቲካ አንድምታው በከፍተኛ ሁኔታ የጎላ ስለሆነ መንግስትን በማዋከብ ጫና ውስጥ እንዲገባ ከማድረግና እነሱ በሚፈልጉት መልኩ ድርድሩን ማካሄድ ነው ። በአማራና በአፋር ክልል እየደረሰ ያለውን የሲቪል ተቋማት ውድመት፣ ሞትና ስደት ሪፖርቱ የሸፈነው ነገር የለም ። ሁሉም ወቀሳ የቀረበው በፌዴራል መንግስቱ ላይ ነው ። እናም የኤርትራን መንግስት በተወሰነ መልኩ የኮነነበት ሁኔታ አለ ። በአንፃሩ ደግሞ ስለሽብር ቡድኑ ተግባር የተባለ ነገር የለም ።
ይሁንና አሁንም ቢሆን የትግራይ ሕዝብ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ነው ያለው ። አሁንም ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ ካልተሰራና ስለትግራይ ዓለም አቀፍ ማሕበረሰብን ማስረዳት ካልተቻለ መንግስትን ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ይከትተዋል ። ይህ ከመሆኑ አስቀድሞ በዴሞክራሲው በኩል መሰራት ያለባቸው ትላልቅ የቤት ስራዎች አሉበት። የሀሰት ፕሮፖጋንዳዎችን መመከት መቻል ይገባዋል ። ይህንን ደግሞ ማድረግ የሚቻለው በእውነተኛ ማስረጃ አቅርቦ በመሞገት ነው ።
የአሜሪካ ልዩ መልእክተኛ መቀሌ ደርሰው ሲመለሱ ያወጡት ሪፖርት አስደንጋጭ ነበር ። የሰብአዊ ድጋፍ አስመልክቶ ምን ያህል በእነዚህ ሰዎች እንደተሸወዱ ያሳያል ። አሁን አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አኳያ ሌላ ማዕቀብ የመሸከም አቅም የላትም ። በመሆኑም ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ መሰራት አለበት ብዬ አስባለሁ ። የኢትዮጵያ ወዳጆች በሀገሪቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ጫና በመቃወም እንዲተባበሩ ማድረግ ያስፈልጋል ። በዚህም የውጭ ሃይሎች ዝምታ እንዲሰበር ማድረግ ይገባል ። በዋናነት በተለያዩ አገራት የሚገኙ አምባሳደሮች በተለያዩ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ስለኢትዮጵያ ሁኔታ በማስረዳት ኢትዮጵያ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጫና መቀነስ አለባቸው ።
በመሰረቱ መንግስትም ሪፖርቱን እንደማይቀበለው ወዲያውኑ ነው ያስታወቀው ። ሌሎችም ሃገራት ተቃውመውታል ። የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም ወንጀል ፈፅመዋል ያላቸውን ወታደሮች አስሯል። በራሱ መንገድ አጣርቶ የወሰዳቸው እርምጃዎች አሉ ። እነዚህ እርምጃዎች በመንግስት መወሰዳቸውን በሪፖርቱ አልተካተተም ። እነዚህን ነገሮች በማንሳትና በዲፕሎማሲ መንገድ በመጠቀም መንግስት የራሱን ስራ ይሰራል ብዬ አምናለሁ ። በተለይ ሪፖርቱን የተቃወሙ ሃገራትን በማስተባበር ዓለምአቀፍ ማህበረሰቡን የማሳመን ስራ መሰራት አለበት ብዬ አምናለሁ ። ይህንን ሪፖርት ኢትዮጵያ እንደማትቀበለውና የፖለቲካ አላማ እንዳለው፤ በአንፃሩ የሽብር ቡድኑን የመደገፍ አዝማሚያ እንዳለው ለማሳየት በከፍተኛ ደረጃ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ።
በሌላ በኩል ደግሞ አሁንም ቢሆን የዓለምአቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ሕወሓት ጉዳይ ላይ ዝምታን መምረጡ የትግራይን ህዝብ መከራና ስቃይ ነው ያረዘመበት ። ይህ የሚያሳየው ቡድኑ አንድም የእነዚህ ተቋማት መሸሸጊያ መሆኑን ነው ። ይህንን በማጋለጥ በኩል መንግስት ከፍተኛ ስራ መስራት አለበት ብዬ አምናለሁ። በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚህ ረገድ ሰፊና ተከታታይ ስራ መስራት ይጠበቅበታል ። በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ውስጥ ያሉ ተቋማት ራሳቸው በየጊዜው የሚያወጡት ሪፖርት እርስበርሱ የተጣረሱ መሆኑን መተቸትና ለኃያላን አገራቱ መጠቀሚያ እንደሆነ ማጋለጥ ያስፈልጋል ። ደግሞም እንደኛ በዚህ መልኩ የተጎዱ ሃገራት በመኖራቸው እነሱንም ማስተባበርና ከጎናችን እንዲሰለፉ ማድረግ ይገባል ።
በአጠቃላይ በሃገር ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባቱንም ነገር በዚያው አለም አቀፍ ህግ መሰረት በማድረግ መቃወምና ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ መስራት ይኖርብናል ። በተለይ በኤምባሲዎቻችን በኩል የአለም ህዝብ እውነታውን እንዲረዳና ተመድም ሆነ የሚመሩት ሃገራት ሴራን ማጋለጥ ይገባል ። በአሸባሪው ብድን ላይ ድርጅቱ ዝምታን መምረጡ የሃገራቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ምን ያህል እየጎዳ መሆኑን ማሳየት ይጠበቅበታል ።
እንዲሁም መንግስት በራሱ መንገድ ሰብአዊ መብት እንዲከበር የጀመራቸው ሥራዎች መቀጠል አለባቸው ብዬ አምናለሁ ። በቋንቋና በዲፕሎማሲ ክህሎት የዳበረ እውቀት ያላቸው ዲፕሎማትና ባለሙያዎችን መመደብና በዋናት ይህንን ጉዳይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ማድረግ ይገባል ። በተጨማሪም በዲጂታል ዲፕሎማሲው በኩል ብዙ ስራ መስራት መቻል አለበት ብዬ አስባለሁ ። እንዲሁም በአለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ የተሻለ እውቀትና ተናግሮ የማሳመን ብቃት ያላቸው ሰዎች እየቀረቡ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ማስረዳት ይገባቸዋል ። ይሄ እንደሃገር የመጣብን ችግርና በእጅ አዙር የሚደረግ ቅኝ ግዛት በመሆኑ አሻፈረን ልንል ይገባል ።
እኔ አሁንም ቢሆን በኢትዮጵያ መንግስት በኩል ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ መሰራት አለበት ብዬ አምናለሁ ። በተለይ የተመድ ተቋማትን ግልፅ አድሏዊ ሪፖርት የተቋማት ከተቋቋመበት ዓላማ ውጪ አካሄድን በመንግስት በኩል ከፍተኛ የሆነ የዲፕሎማሲ ስራ ሰርቶ ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ና ፖለቲካዊ ችግር፤ እንዲሁም የእነዚህን ተቋማት ዝምታ በደንብ አድርጎ ለአለም አቀፍ ተቋማት ማሳወቅ አለበት ። በተለይ እነዚህ ተቋማት ላይ ጫና ማሳደር አለበት ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አለም አቀፉን ማህበረሰብ ጠርቶ ማወያየትና ሪፖርቱን እንዲነቅፉ ማድረግ ይገባል ።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ሥም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ሱራፌል፡- እኔም አመሰግናለሁ ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን መስከረም 21/2015 ዓ.ም