ዓለም አቀፍ የሚል ተቀጽላን አንግበው፤ የሰብዓዊ መብት የሚል ካባን ደርበው፤ ከስማቸው ይልቅ ለቡድን ፍላጎት፤ ከተልዕኳቸው የተሻገረ ፖለቲካዊ ግብን ተሸክመው የሚጓዙ “ዓለማአቀፍ የሰብዓዊ መብት… ተቋም” በሚል የዳቦ ስም የሚንቆለጷጰሱ ተቋሞች በርክተው ይታያሉ። ይሁን እንጂ ስምና ግብራቸው፤ ተልዕኮና ግባቸው ለየቅል ሆኖባቸው የጥቂቶች ጉዳይ ፈጻሚ፣ የፖለቲካ ፍላጎት ተሸካሚ ሆነው ከእውነት ይልቅ ለታይታና አዱኛ ሲባክኑ ውለው ማደራቸው የዓደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል።
በዚህ ረገድ እነ አምንስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂውማን ራይትስ ዎችን የመሳሰሉት ስማቸው ተደጋግሞ የሚነሳ ሲሆን፤ ትናንት በኢትዮጵያ ጉዳይ “የጥናት” ሪፖርት ያወጣው ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ተብዬውም የእነዚሁ መሰል ገጽታ ባለቤት ተቋማት መካከል አንዱ ነው። ምክንያቱም ይህ ኮሚሽን ትናንት ይፋ ባደረገው ሰነድ በግልጽ ማንነቱን አሳይቷል። እንዴት ቢሉ፣ ያቀረበው ሰነድ ለጥቂቶች የፖለቲካ ተልዕኮ የቀረበ የኮሚሽኑ ልብ የወለደው “ጥናት” ብሎ ከመግለጽ የዘለለ አንዳችም ጠብ የሚል እውነትን ያልያዘ፤ ይልቁንም ከጥናት ሳይንሶች የተፋታና በምናብ ዓለም ምኞች መስመር ተጉዞ የተዘጋጀ መሆኑን ጭብጡ በገሃድ ይናገራል።
ይህ ኮሚሽን ይሄን “ጥናት” ለማከናወን ከመዘጋጀቱ በፊት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጋራ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም በትግራይ ክልል ተከስቶ በነበረው ጦርነት ወቅት የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስለመኖር አለመኖራቸው ሰፊና በቦታው ተገኝተው ያከናወኑትን ጥናት ሪፖርት አድርገው ነበር። በዚህ ጥናት በጦርነት ውስጥ ሊፈጠር የሚችል የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖሩ የታመነ እንደመሆኑ ይሄንኑ የሚያሳይ፤ ነገር ግን በተባለው መጠን የከፋ እንዳልሆነ በማመላከት፤ ለተፈጠሩ ችግሮች በመንግሥት በኩል የእርምት እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።
በመንግሥት በኩልም የጥናት ሪፖርቱ መጠነኛ ክፍተት ያለበት መሆኑን (በተለይ በሽብር ቡድኑ ወረራ ስር የነበሩ የአማራ እና አፋር ክልል አካባቢዎች በሚፈለገው መጠን ደርሶ ችግሩን መለየት አለመቻሉን) በማስገንዘብ፤ የቀረበውን ሪፖርት ተቀብሎ ምክረ ሃሳቡን ለመተግበር ተግባራዊ እርምጃ ውስጥ መግባቱ የሚታወስ ነው። በዚህም በመከላከያ ሠራዊቱም ውስጥ ሆነ በየትኛውም ደረጃ ያሉ የችግሩ ፈጣሪ አካላት ተለይተው እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑ በግልጽ ተነግሯል። ሆኖም በጥምረት የተከናወነው የጥናት ሪፖርት ሰፊና በቦታው ተገኝቶ እውነትን ለመመልከት ጥረት ያደረገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለሽብር ቡድኑ ድጋፍ ሊሰጡ ለሚሹ አንዳንድ የምዕራቡ ዓለም አገራትና የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች መንገድ ሊሰጥ አልቻለም።
ለዚህም ነው የሚፈልጉትን የፖለቲካ ዓላማ ለማሳካት ሲሹ እንደራሳቸው ንብረት የከሚያዟቸው የሰብዓዊ መብት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነውን ይሄን ኮሚሽን በምናባቸው እንዲሆን የሚፈልጉትን ድምዳሜ አስጨብጠውና ኡጋንዳ/ኢንቴቤ አስቀምጠው “ጥናት” ስራ ያሉት። ከጅምሩ ፖለቲካዊ ዓላማን አንግቦ የተነሳው ይህ ኮሚሽንም የተባለውን አድርጎ፣ የተነገረውን ድምዳሜ አስቀምጦ፣ በል የተባለውንና የተጻፈለትን ድርሰት ተርኮ “የጥናት ውጤቴ እነሆ” ብሎ እርፍ ያለው። ይሄን መሰል የሃሰት የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሲደረግባት አዲሷ ያልሆነው ኢትዮጵያ ግን ቀድሞውም ለኮሚሽኑ “የጥናት” ጅማሮ እውቅናን ያልሰጠች ከመሆኑ ባሻገር፤ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በተከሰተው ግጭት አውድ ውስጥ፤ ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ከማጣራት፣ ተጎጂዎችን ከመጠበቅ እና ከመደገፍ አንጻር ስራዎችን ለማስተባበር የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑ ይታወቃል።
ይሄ የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይልም በትናንትናው ዕለት አራተኛ መደበኛ ጉባኤውን ያካሄደና የስራውን ደረጃ የገመገመ ሲሆን፤ በግምገማውም በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ ሲካሄድ የነበረው የምርመራ ሂደት በአብዛኛው መጠናቀቁን ነው ያረጋገጠው። ይሄም በልቦለድ መሰል “የጥናት” ሰነዶች ከሚነዙ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽንነት ስም ከተደራጁ ተቋማት የወጡ የሃሰት ስም የማጥፋትና አገርን የማጠልሸት ብሎም እጅ ለመጠምዘዝ የሚደረግን ሩጫ፤ የተጎዱ ብዙሃንን ሳይሆን የጥቂቶችን የፖለቲካ ተልዕኮ ተሸካሚነት ያጋለጠ ነበር።
ምክንያቱም የሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል ትናንት ባካሄደው ግምገማ ላይ እንዳመለከተው፤ በነበረው ግጭት ወቅት በአፋርና በአማራ ክልሎች በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ከጾታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ ሲካሄድ የነበረው የምርመራ ሂደት በአብዛኛው መጠናቀቁን እና ወደ ክስ ሂደት ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን ተመልክቷል። በተጨማሪም በምርመራና በክስ ኮሚቴ የሚመራው 158 አባላት ያሉት የምርመራ ቡድን በአፋርና በአማራ ክልሎች ሲያከናውናቸው የነበሩ ተግባራት ዝርዝር ሪፖርት፤ እንዲሁም ወንጀሎች በምን አይነት መልክ እንደተፈጸሙ እና የምርመራ ግኝቶቹንም ምን ምን እንደሆኑ በሪፖርቱ ተለይቶ ቀርቦለታል።
ለዚህ ደግሞ የምርመራ ቡድኑ በምርመራ ወቅት የተለያዩ ማስረጃዎችን በቪዲዮና በዶክመንት አደራጅቶ መያዙ፤ በጦርነት አውድ ውስጥ በርካታ ንጹሃን ላይ ያለፍርድ ስለተፈጸሙ የግድያ ወንጀሎች፣ ከባድ የአካል ጉዳት እና በሁሉም የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ ስለተፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች እንዲሁም በግዳጅ የመሰወር ወንጀሎች መፈጸማቸው፤ እንዲሁም በንብረት ላይ የደረሱ ጉዳቶች በምርመራ ግኝቱ መካተታቸው ታውቋል። በዚህ መልኩ ለሚኒስትሮች ግብረ-ኃይል የቀረበው ሪፖርት እንዳመላከተውም፤ አሸባሪው ትህነግ በአማራ እና በአፋር ክልሎች 3 ሺህ 598 ንፁሃኖችን መግደልን ጨምሮ በጦር ወንጀል የሚያስጠይቁ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መፈጸሙ በምርመራው አረጋግጧል።
ይሄን ሪፖርት ያቀረበው የምርመራ ኮሚቴ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን እና የተመድ የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የጋራ ምርመራ ውጤቶችን ተከትሎ በኢትዮጵያ መንግሥት የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል የምርመራ እና ክስ ኮሚቴ እውን መሆንን ተከትሎ ያደረገውን ምርመራ መነሻ በማድረግ ሲሆን፤ ይሄም በወልዲያ፣ ላሊበላ፣ ሰቆጣ፣ ጃማ፣ ወረኢሉ፣ ደሴ እና ኮምቦልቻ አካባቢዎች እንዲሁም፣ ሰሜን ሸዋ ዞን፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን እና በአፋር ክልል እ.አ.አ ከመስከረም 15 እስከ ጥር 31 ቀን 2021 ድረስ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ያጣራ መሆኑ ታውቋል።
የምርመራ እና ክስ ኮሚቴው ባደረገው ማጣራት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግ የጣሱ በጦር ወንጀል የሚያስጠይቁ በርካታ ጥፋቶችን አሸባሪዎቹ ትህነግ እና ሸኔ መፈጸማቸውን ያረጋገጠ ሲሆን፤ በዚህም ከሕግ ውጪ 3 ሺህ 598 ሰዎች መገደላቸውም፤ አንድ ሺህ 315 ሰዎች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን፤ ሁለት ሺህ 212 ሰዎች የአስገድዶ መድፈር እና ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው መሆኑን፤ እንዲሁም 452 ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸው መነካቱን አረጋግጧል። ይህ የማይካድ የብዙሃን ንጹሃን ዜጎች እውነት ነው። ነገር ግን “ጥናት” አደረኩ የሚለው ኮሚሽንና የፖለቲካ ተልዕኮ አሸካሚዎቹ ይሄን ከሃሰት ተረካቸው ባሻገር ያለውን የፈጠጠ ሃቅ ለማየትም፣ ለመስማትም አይፈልጉም!
በየኔነው ስሻው
አዲስ ዘመን መስከረም 11/2015 ዓ.ም