ገና ወደ ግዛታቸው ስትገባ «ሕግ ያለው ፍርድ ቤት ብቻ ነው» የሚል በትልቁ የተጻፈ የራሳቸው ሕገ መንግሥት አንቀጽ ፊት ለፊት ተጽፎ ታነባለህ። እናም የፈለገ ነገር ቢያደርጉህ እነኝህን ባለሥልጣናት መናገር አትችልም። መብቴ ተጣሰ ብለህ መብትህን ለማስከበር መከራከር ትርፉ ጆሮ የሚሰቀጥጥ ስድብ መስማት ነው። ያውም አንተን ብቻ ከሆነ የሚሰድቡህ። ዘጠኝ ወር አርግዛ፤ ጡቶቿን አጥብታ፣ በጉያዋ አቅፋ፣ በጀርባዋ አዝላ ከእርሷ በቀር ማንም ሊያደርገው የማይችለውን ተፈጥሯዊ ጣፋጭ ፍቅሯንም መግባ ያሳደገችህን በምንም በማንም የማትለውጣትን ውዷን እናትህንም ይጠሯታል፤ ጠርተው ይሰድቧታል።
ታዲያ «አሁንስ ይበቃል በእናቴ እንኳን አልችልም ብለህ» አጸፋ ብትመልስላቸው ባለሥልጣናቱ ጭፍሮቻቸውን ጠርተው ሊደበድቡህና ሊያስደበድቡህ ይችላሉ። ስለዚህ ግፋቸውን ቢያበዙብህ፣ ያሻቸውን ቢያደርጉብህ ምንም ማድረግ አትችልም። ያው እንደለመደብህ ቻል አድርገህ ዝም ከማለት በስተቀር። ምክንያቱም ባለሥልጣናቱ አይነኬ ናቸዋ! «በሕግ አምላክ» ብትል የሚሰማህ ያለ እንዳይመስልህ። የሕግ ነገርማ እነሱ ጋር በሕግ የተከለከለ እኮ ነው። መብትን መጠየቅስ? መብትን መጠየቅም ያው ነው፤ መጠየቅ አይቻልም ምክንያቱም ያሰድባል ባስ ሲልም በተለይ ደግሞ ምሽት ላይ ከሆነ ያስደበድባል። እነዚህ ፈላጭ ቆራጭ ፈርዖናውያን አይነኬ ባለሥልጣናት ደግሞ እነማን ናቸው ብላችሁ አትጠይቁኝም። በየቀኑ «የምንገለገልባቸው» የከተማችን ታክሲዎች አሽከርካሪዎችና አጋፋሪዎቻቸው ረዳቶች ናቸው።
እነዚህ ባለሥልጣናት የብር ከሃምሳ ሳንቲሙን መንገድ አምስት ብር ቢያስከፍሉህ፣ ሦስት እጥፍ አስከፍለውህም በወንበር ሦስት ወይም አራት እያደረጉ እንደጀሪካን አሰቃቅለው ቢጭኑህም፣ «በአቋራጭ» በሚለው አስገዳጅ የኮማንድ ፖስት ሕጋቸው መውረጃ ቦታህን አሳልፈው ተመልሰህ ወደነበርክበት ታክሲ እንድትይዝ ቢያስገድዱህም ምንም ማድረግ አትችልም። ምንም ማድረግ አይቻልም አለ ዲጄው። ምንም ልታደርጋቸው አትችልም። አይነኬ ናቸዋ። ግን እኮ አይደለምና ከታሪፍ በላይ ያለ አግባብ በምትከፍለው ክፍያ በሕግና በአግባቡ የመስተናገድ መብት አለህ። «በሕግና በአግባቡ» አልኩ እንዴ? ለካ ሕግ ያለው ፍርድ ቤት ነው ይቅርታ። ፌርማታህን ተገደህ ያለማለፍ፣ በአንድ ወንበር ሦስትና ከዚያ በላይ ሆኖ ያለመሳፈር፣ ለሦስት እንኳን የምትቀመጥበት ወንበር አጥተህ አግዳሚ ላይ ተደርድረህ ያለመሄድ መብት እኮ አለህ።
ወይ የኔ ጅልነት በሕጉ ተስፋ ብቆርጥ ደግሞ ስለ መብት ማውራት ጀመርኩ። ታክሲ ውስጥ መብት? እንደዚያ ብሶት እንዳጃጃለው የኔ ብጤ በጠራራ ፀሐይ ላምባዲና አብርተህ ብትፈልገውም ታክሲ ውስጥ መብተህን አታገኘውም። እናም እንደፈለጉ ቢጫወቱብህ መብትህን መጠየቅ አትችልም። አይነኬዎቹ የታክሲ ሹፌሮችና ረዳቶቻቸው እኮ ናቸው። ምንም ማድረግ አትችልም እንደለመደብህ ዝም ብለህ አቤት ወዴት ብለህ ታክሲህ ውስጥ ተሳፍረህ ከመነዳት በስተቀር! ውይ! ውይ! እንዲያውስ ከታክሲው ስወርድ ረስቼው ነው እንጂ ዝም ብዬ ይህን ሁሉ ስማቸውን የማጠፋው እነሱማ አይነኬዎቹ ቄሳራውን መች የዋዛ ናቸው። ስለ መብት የሚጠቅስ አንቀጽስ በሕገ መንግሥታቸው አስቀምጠው የለ። አዎ…አስታወስኩ…መብትን በተመለከተ በታክሲ ሹፌሮችና ረዳቶች ሕገ መንግሥት የተቀመጠው አንቀጽ እንዲህ ይላል፤ «መብትዎ ትዝ የሚልዎት ታክሲ ውስጥ አይሁን»
ሌላው ስለ ታክሲዎቻችንና ስለ አይነኬዎቹ ቄሳራውያን ሳስብ ግርም የሚያደርገኝ ነገር ቢያንስ እንኳን ለእንጀራቸው ሲሉ ተሳፋሪዎቻቸውን፤ ደንበኞቻቸውን አክብረው የማይሠሩት ለምንድነው የሚለው ነው። ደግሞ እውነቴን ነው። የታክሲ ሾፌሮችም ሆኑ ረዳቶቻቸው እኮ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበትና ኑሯቸውን የሚመሩበት የገቢ ምንጭ የሚያገኙት ለኅብረተሰቡ በሚሰጡት የትራንስፖርት አገልግሎት ነው። ስለዚህ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚፈልግ ኅብረተሰብ ከሌለ አገልግሎቱን የሚሰጠው አካልም አይኖርም ማለት ነው። የታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኛ ወይም ተሳፋሪ ከሌለ ታክሲውም ሾፌሩም አይኖሩም። እና ታዲያ ሾፌሮቹና ረዳቶች ተሳፋሪው ላይ ይህን ሁሉ ግፍ የሚፈፅሙት ተሳፋሪ ደንበኛቸውን ካጡ ሥራቸውንና ራሳቸውንም አብረው እንደሚያጡ ጠፍቷቸው ነው ወይስ የግል መኪና መግዛት ያልቻለው ብዙሃኑ ድሃ እስካለ ድረስ ታክሲ ተሳፋሪ አይታጣም ብለው ነው? መልሱን ለአንባቢ ልተወው።
ለነገሩ ብዙ ጊዜ የሚያደርሱብንን ስቃይ እያብሰለሰልን የሚፈፅምብን ስቃይ ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው መሆኑን እየረሳን ነው እንጂ ቄሳራውያኑ ደንበኛን ላለማክበርም ሕግ አላቸው። የዚህ አንቀጽም እንዲህ ይላል፤ «ደንበኛ ካልቀበጠ ንጉሥ ነው»። አይነኬዎቹ ቄሳራውያን የታክሲ ሹፌሮችና ረዳቶቻቸው እንግዲህ ይህን ያህል የተራቀቁ ናቸው። በማንኛውም የሥራ መስክ ደንበኛ ንጉሥ መሆኑን ያውቃሉ። ነገር ግን ሕጎች ሁሉ እንደየ መብቀያቸው ነባራዊ ሁኔታ ይለያሉና በእነሱ «ሕገ መንግሥት» ደንበኛ ንጉሥ የሚሆንበት አግባብ ይለያል።
የሕጋቸው ማብራሪያ እንዲህ ይላል፤ «ሌላ ትርጉሜ ካልተሰጠው በስተቀር በዚህ ሕግ ውስጥ «ንጉሥ ደንበኛ» ማለት «ያልቀበጠ ደንበኛ» ማለት ነው። መቅበጥ ሲሉ ገብቷችኋል አይደል? ያልቀበጠ ደንበኛ ማለት ከታሪፍ በላይ ሂሳብ ሲያስከፍሉት ዝም የሚል፣ በአንድ ወንበር ላይ ለሦስት እንዲቀመጥ ሲታዘዝ «ከፍዬ እኮ ነው የምሄደው እንዲህ ሆኜ አልሄድም» የማይል፣ በአቋራጭ ለመሄድ ያለ ሰፈሩ ጥለውት ሲሄዱ ለምን ብሎ የማይጨቃጨቅ፣ ሲሰድቡት፣ ሲደበድቡት፣ ሲዘርፉት «ቀብጦ መልስ የማይሰጥ» ደንበኛ ማለት ነው።
ታዲያ እነ አብየ የታክሲ ሾፌርና ረዳት ሕግ ባለበት አገር የራሳቸውን ሕግ አውጥተው መተዳደሪያ እንጀራቸው መሆኑን እያወቁት በተገልጋይ ደንበኛቸው ላይ ይህን ያህል ግፍና በደል ሲያደርሱ የማይጠየቁ አይነኬ ባሥልጣን እንዲሆኑ ያደረጋቸው ማን ነው? እውነት እውነት እልሃለሁ! እስከ መጨረሻው ድረስ ሄደህ መብትህን መጠየቅና ራስህን በማስከበር ሰው ሰውነቱን ሲያስከበር ሕግ የትም ሊኖር እንደሚችል እንዲያውቁት ማድረግ ሲገባህ «ሕግ ያለው ፍርድ ቤት ብቻ ነው» እያሉ ሲቀልዱብህ ዝም ያልከው፣ ታክሲ ውስጥ መብትን መጠየቅ አይቻልም እያሉ ሲዝቱብህ፣ መብትህን ስትጠይቅ ደግሞ «ቅብጢ» እያሉ ሲሰድቡህና ሲያዋርዱህ…ልክ እንደ ግዑዙ ታክሲያቸው ወደ ፈለጉት ሲነዱህ ዝም ያልከው አንተው ራስህ ተሳፋሪያቸው ነህ። እንደፈለጉ ሲያደርጉህ አሜን ብለህ የተቀበልከው በዝምታ መርቀህ፣ በስንፍና ቀብተህ በገዛእጅህ ያነገስካቸው ፈላጭ ቆራጭ አይነኬ ቄሳር ፈርኦን ያደረግካቸው አንተው ንግሥናህን ያላወቅከው «ንጉሡ» ደንበኛቸው ነህ። አንተም ግን አይፈረድብህም፣ አማራጭ ብታጣ ነው።
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን መስከረም 7/2015 ዓ.ም