ኢትዮጵያውያን ጌዜን የማሞገስ፤ለጊዜ የመዝፈን ባህል አላቸው። ክረምትም ሆነ በጋ እንዲሁም ልምላሜም ሆነ ድርቅ በዘፈኖቻችን ውስጥ የተለየ ትርጓሜ ተሰጥቷቸው ይዘፈንላቸዋል። ከሁሉም በላይ መስከረም ደግሞ የተለየ ተደርጎ የሚዘመርበት እንደሆነ መናገር ለቀባሪው አረዱት ነው። ለመሆኑ ይህ ወር የወራት ሁሉ ቁንጮ ተደርጎ ለምን ተወሰደ፤ የተለየ ግጥምና ዘፈኖችስ ለምን ወጡለትና መሰል ነገሮችን ስናነሳ ብዙ ምክንያቶችን መጥቀስ እንችላለን። መጀመሪያ ግን ከተዘፈኑት ዘፈኖች ጥቂት እንበላችሁና ወደዋናው ጉዳይ እንገባለን።
ክረምት አልፎ መስከረም ሲጠባ
የእኔ ቆንጆ አጊጣ ተውባ
አምራ ደምቃ በአበቦች ታጅባ
ያቻትና መጣች ውብ አበባ ይላል።
ሌላም ልጋብዛችሁ። የአመልማል አባተን ዘፈን።
የክረምቱ ወር አልፎ ለበጋው ለቋል፣
ሜዳው ሸንተረሩ ጋራው በአበቦች ደምቋል፤
ሸሞንሟናዬ ውብ ሽቅርቅሩ
ድረስ በአውደ አመት በአገር በመንደሩ
በወራት መጀመሪያ በአዲስ ዓመት መግቢያ
በል ፈጥነህ ድረስልኝ በወዳጅ ዘመድ መሰባሰቢያ። ትላለች።
ስለመስከረም ያልዘፈነ፣ ያልዘመረ የለምና ሁሉንም ዘርዝረን ስለማንችል በአረጋኸኝ ወራሽ ዘፈኑን እናጠቃል።
እሰይ አበባው እሸቱ ደርሷል፤
ሰፈር መንደሩ አረንጓዴ ለብሷል፤
ገደል ሸለቆው ታጥሮ በአበባ፤
አደይ አበባ አመስከረም ጠባ፤
የሰላም የፍቅር የፍስሃ አዝመራ፤
ሸጋ ሸጋ ታብቅል እሰይ ምድር ታፍራ፤
የመከራ ዘመን ያዘን ስቃይ ያብቃ፤
ሀብት በመስከረም ይኸው ትታይ ደምቃ፤
መስከረም ሲጠባ አደይ ሲፈነዳ፤
ቤት ለእንቦሳ በሏት የልቤን እንቦሳ።
መስከረምን የዚህ ሁሉ ዘፈን ባለቤት ያደረጋትና የወራት ሁሉ ቀንዲል ያስባላት ምንድነው ከተባለ ምክንያቱ ብዙ ነው። ለአብነት ጥቂቶቹን እናንሳ። የመጀመሪያው ይህ ወር እንደ እኛ ኢትዮጵያዊን የዘመን አዋጅ የሚነገርበት ወር መሆኑ ነው። ዓመታችንን ስንቆጥር አንድ ብለን የምንጀምረው መስከረምን መነሻ አድርገን ነው። የ13 ወር ጸጋ የተባልነውም መስከረም አንድ ብለን ሰላሳ ቀናትን ደፍነን ትርፎቹን ጳጉሜን ብለን ስለሰየምን ነው።
ሌላው የመስከረም ወርን ታላቅ ወር የሚያደርገው ፍካትን፤ ደስታንና አብሮነትን የሚያበስር መሆኑ ነው። ለዚህም ብዙ ሊቃውንትና ጸሐፍት ምስክሮች ናቸው። ከእነዚህ መካከል መዝሙረኛው እና የዜማ ቀማሪው ቅዱስ ያሬድ አንዱ ሲሆን፤ በመፀሐፈ ድጓው ላይ የተለያዩ ሀሳቦችን አስፍሮ እናገኘዋለን። ለአብነት አንዱ ‹‹ኀለፈ ክረምቱ ጸገዩ ጽጌያት!›› ያለው ነው። ይህ ማለት በአማሪኛው ክረምቱ አለፈ አበቦችም ፈኩ የሚለውን ትርጓሜ ይይዛል።
ታዋቂው ደራሲ በዓሉ ግርማም ‹‹ደራሲው›› በተሰኘው ልቦለዱ ላይ የመስከረምን መጥባትና ገጸ በረከቱን በተመለከተ እንዲህ ሲል አብራርቶታል። ‹‹መስከረም ጠባ። የመስከረም ጮራ ዕንቁጣጣሽ ብላ ተግ አለች። ልጃገረዶች ሳዱላቸው አሳመሩ፤ አደስ ተቀቡ፤ እንሶስላ ሞቁ፤ወንዝ ወረዱ፤ ቄጤማ ለቀሙ፤ ፀዳል ልብሳቸውን ለብሰው፤ አሸንክታባቸውን አጥልቀው ‹ አበባየ ሆይ ለምለም› በማለት ተሰብስበው ብቅ አሉ እንደጮራይቱ።የወርሀ መስከረም ብሩህ ተስፋና ስሜት በምድሪቱ አስተጋባ። ጠፍ እያለ መጣ ምድሩ። ወንዙም እየጠራ። ኩል መሰለ ሰማዩ። ሜዳው፣ ጋራው፣ ሸንተረሩ ወርቃማ የአደይ አበባ ካባ ለበሰ። ደመራ ተደመረ። ተቀጣጠለ ችቦ። ‹ኢዮሃ አበባዬ -መስከረም ጠባዬ› ተባለ።›› በማለት።
ሌላው ሀብተማርያም አሰፋ (ዶ/ር) ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄዎችና ባሕሎች›› በተሰኘው መጽሐፍ ላይ መስከረም እንዲህ ትገልጸለች። ‹‹ምስከረም›› ከከረመ በኋላ ወይም ክረምት ካለፈ በኋላ ማለት ነው። የመስከረም ወር ዝናብ የሚቆምበት ፀሐይ የምትወጣበት ወንዞች ንጹሕ ውሃ ጽሩይ ማይ የሚጎርፍበት፣ አፍላጋት የሚመነጩበት፣ አዝርዕት አድገው ማሸት የሚጀምሩበት፣ ሜዳዎችና ተራራዎች ሸለቆዎችም በአበባ የሚያሸበርቁበትና የሚያንቆጠቆጡበት ነው።የጨለማ፣ የችግርና የአመጻ ጊዜ የሚያበቃበት ፤ የብርሃን፣ የደስታ የእሸት፣ የፍሬና የጥጋብ ጊዜ የሚጀመርበትና የሚተካበት ነው።
መስከረም ፍቅረኛሞች የሚገናኙበት፤ የተነፋፈቀ ቤተዘመድን የሚቀራረቡበትና የሚደጋገፉበት ፤ ደስታና ፍስሃ የሚበዛበትም ወር እንደሆነ አባባሎቻችን በደንብ ያስረዱናል። ለአብነትም ጥቂቶችን እናንሳ። ‹‹ጉድ ሳይሰሙ መስከረም አይጠባም፤ መስከረም በአበባው ሰርግ በጭብጨባው፤ በመስከረም ስፍራው ሁሉ ለምለም፤ በመስከረም የሚቀድምህ የለም፤ የመስከረም ወፍ ሆንሽ›› የሚሉት ወሩ ምን እንደሚመስል ከሚያሳዩት መካከል የሚነሱ ናቸው።
አሁንም ስንቀጥል ይህ ወር ሌላ ቁንጮ የሚያደርገው ምን መለያ አለው ካልን በስነፈለግና በዘመን አቆጣጠር ብዙ ጥናት ያደረጉት መጋቢ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰና መምህር ሄኖክ ያሬድ ፋንታን አዲስ ዓመትን በተመለከተ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ባነጋገርናቸው ወቅት ያሉንን ሀሳቦች አብነት በማድረግ እናንሳ።
መጋቢ ሀዲስ ዶክተር ሮዳስ ስናስቀድም መስከረም በኢትዮጵያዊያን በቅብጥ በእስራኤል በቤዛንታይን ባሉ ሀገራት ባሉ ሊቃውንት ትውፊት ሁሉ ዓለም የተፈጠረበት ወር ተብሎ ይወሰዳል ይላሉ። ይህ ወር በጽርዕ “አታኒን”፤ በዕብራይስጥ “ኤታኒም”፤ በእኛ “አታሚን” ይባላል። ፤ ኤታን ማለትም ጥንት፣ መሠረት፣ ጥንተ ወርኅ (የወር መነሻ)፤ ጥንተ ዓመት (የዓመት መነሻ)፤ ጥንተ ዓለም (የዓለም መነሻ)፤ ጥንተ ፍጥረት (የፍጥረት መነሻ) ማለት ነው። የግእዝ ቋንቋ ሊቅ የሆኑት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላታቸው ላይ ኤታኒም በጨረቃ ለሚቆጥሩ ጥቅምት ሲሆን፤ በፀሓይ ቁጥር ለምንጠቀም ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ግን የመስከረም ጫፍ እንደሆነ አስቀምጠዋል።
በመሠረታዊ ነገሩ ቀደምት ግብጻውያን ቱት ብለው የሚጠሩትን የመስከረምን ወር ከክርስቶስ ልደት 3000 ዘመን አስቀድሞ የአዲስ ዓመት መግቢያ የነበረ ሲሆን የዐባይ ወንዝ ጐርፍ ግብጽ የሚያጥለቀልጥበት ጭምር ነበርና የመጥለቅለጥ ወቅት (Season of Akhet (Inundation)) ይሉት ነበር። ይህም ወቅት ከመስከረም እስከ ጥር ድረስ ይቆይ ነበር። በዚህ ወቅት ደማቋ ኮከብን ሳይረስን በልዕልና የሚያዩበትና የኮከቧ በመስከረም 1 መውጣት ለአዲስ ዓመታቸው ምልክት ነበረ።የእነዚህ ሁሉ ጥንታውያን ሀገራት ትውፊት የሚያስረዳን መስከረም ወር የሥነ ፍጥረት መነሻ እንደሆነ ነው።
ሌላው መስከረም ወርን የገለጹበት ደግሞ የመተካከል ወር በማለት ነው። ለዚህ መነሻቸውን የሚያደርጉት ጥንታዊው መጽሐፍ ስንክሳርን ሲሆን፤ “ወርኃ መስከረም ቡሩክ ርእሰ አውራኅ ዓመታት ዘግብጽ ወኢትዮጵያ ሰዓተ መዓልቱ ፲ወ፪ቱ ዕሩይ ምስለ ሌሊቱ ወእምዝ የሐጽጽ” (የተባረከ የመስከረም ወር የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመታት ወሮች ራስ ነው፤ የቀኑ ሰዓትም ከሌሊቱ ሰዓት የተስተካከለ ዐሥራ ሁለት ነው፤ ከዚህ በኋላ እያነሰ ይሄዳል) በማለት የመፀው እኩሌታነትን ያነሳበትን ሀሳብ ይጠቅሳሉ። ሀሳቡ በዓመት ውስጥ ቀን እና ሌሊት እኩል የሚሆኑባቸው ጊዜያቶች የሚያሳይ ነውም ይላሉ።
ሌላው መስከረም ለኢትዮጵያውያን ልዩ የተስፋ ምልክት ነው ያሉት ሲሆን፤ ይህንንም በማስረጃ ያብራሩታል። አበው በብኂላቸው “በሰኔ ዝናቡን ወደ እኔ፤ በሐምሌ ልኑር እንዳመሌ” እንደሚሉ በሰኔ ወር የገባው የክረምት ወቅት እየበረታ ሰማዩ በመብረቅ ብልጭታና በነጐድጓድ ድምፅ የሚታጀብበት፤ ከላይ የዝናብ ዶፍ ከሥር ጐርፍ የሚጨምርበት፤ ዐልፎ ተርፎም በረድ የሚዘንብበት የጨለማ፣ የጭጋግ፣ የደመና፣ የጉም ጊዜ ነው።
“በመስከረም ስፍራው ሁሉ ለምለም” እንዲሉ ይህ አስፈሪው የሰኔ፣ የሐምሌ፣ የነሐሴ ወራት ዐልፎ የዐዲስ ዓመት መጀመሪያችን የመስከረም ወር ላይ ግን የበረደውን የምታሞቀው፣ የጨለመውን የምታስለቅቀው፣ የተሰወረውን የምትገልጠው፣ የረጠበውን የምታደርቀው ፀሓይ ከሰወራት ደመና ወጥታ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ብርሃኗን መፈንጠቅ ትጀምራለች። ስለዚህም መስከረም ወር በክረምቱ ዝናብ ረግፈው የነበሩት አበባዎችን በየጋራው በየሸንተረሩ ፈክተው መዐዛን ሲመግቡን፤ ንቦችም አበባዎችን ቀሥመው ጣፋጭ ማራቸውን ለመሥራት ከአበባ ወደ አበባ ሲዘዋወሩ፤ ቢራቢሮዎችም በየመስኩ ሲሽከረከሩ፤ የመስቀል ወፍና የተለያዩ ወፎችም ከተደበቁበት ጐጆዎቻቸው ወጥተው ደስ በሚያሰኝ ዝማሬያቸው ሀገራችንን የሚያደምቁበት ነው ይላሉ።
መምህር ሄኖክ ያሬድ ፋንታ በበኩላቸው፤ ስለ መስከረም ወር ታላቅነት ወይም አውራነት በአማርኛ ግጥም በመጀመር ያስረዳሉ።
‹‹ጨለማው ሲጠፋ ዝናቡ ሲያቆም
ያ የለውጥ ወራት መጣ መስከረም
ሰዎች ይነሣሉ ሊሠሩ ታጥቀው
መስከረም ነውና ብርሃን ሰጪው›› እያለ ዓመቱን ይዘልቃል። ይህ የሆነበት ምክንያትም መስከረም ከባዱ ክረምት ቀዝቀዝ የሚልበት ደመራ ከተለኮሰ በኋላ መሰስ ብሎ የሚወጣበት፣ ምድሪቱ በአደይ አበባ የምታሸበርቅበት ነው። መስከረም ‹‹መስከረም መስከረም የወራቱ ጌታ አበቦች ተመኙ ካንቺ ጋር ጨዋታ›› የተባለለት ወርም ነው።
መስከረም ‹‹መስከረም›› ይባላልም። መዘክረ ዓም (የዓመት መስታወሻ) ተብሎ ዘመን ይሰላበታል፤ በዓላትና አጽዋማት ይታወጅበታል። ይህ ቀን ከዘመነ አክሱም ጀምሮ ክረምቱ ማለፉን አበቦች መፍካታቸውን ለማመልከት ‹‹ተቀፀል ጽጌ›› (አበባን ተቀዳጅ) እየተባለ በየዓመቱ እስከ 15ኛው ምዕት ዓመት ሲከበር ቆይቷል። ከዚያ ወዲህ ግማደ መስቀሉ ከመጣበት ጊዜ አንሥቶ ግን በመስከረም 10 ቀን እየተከበረ ይገኛል። እንደእርሳቸው አገላለጽ፤ መስከረም በተሞሸረ ዓመት በተቀመረ ቁጥር ሰው መልካም ምኞት የሚለዋወጥበት ወር ነው።
ሰኔ ግም ብሎ፣ የሐምሌን ጨለማ አልፎ፣ የጎርፍ ሙላትን በእኝኝ ተሻግሮና ተንተርሶ በጠንካራው ዝናብ (ውሃ) ምክንያት ብቅ የምትለዋ የአደይ አበባን ይዞ ብቅ የሚል ወርም ነው። ስለዚህም መስከረም ውሃ ያደረገውን ታምር፣ ያስበቀለውን አበባ የምናይበት ወርም ራስ፣ ቁንጮ አውራ እየተባለ እንዲጠራ ሆኗል። ሁሉም አምኖበት እንዲያከብረውና እየተደሰተ እያሳለፈው ይገኛል። አዎ ይህ ሁሉ ምስጢር ያለውን መስከረም ሁላችንም በሐገርኛ ባህላችን እያደመቅነው እንቀጥል በማለት ለዛሬ አበቃን። ሰላም
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን መስከረም 6/2015 ዓ.ም