• በታኀሳስ ወር መግቢያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስ ትር ዶክተር አብይ አህመድ ከእንግሊዝ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር፣ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንና ከኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ለማ መገርሳ ጋር በመሆን በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን ጊኒር ወረዳ ተገኝተው የዱረም ስንዴ አምራች አርሶ አደሮችን ጎብኝተዋል።
• ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከመከላከያ ጋር ባደረጉት ውይይት መከላከያ በሪፎርሙ ሥር ነቀል ሊባል የሚችል ለውጥ እንዳደረገ መናገራቸው አይዘነጋም። በዚህም መሰረት በታኀሳስ የመጀመሪያው ሳምንት በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምክንያት በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ተከማችቶ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያና ኤርትራ የሰላም ስምምነት ላይ በመድረሳቸው ወደ ሌሎች የሀገራችን ክፍሎች እንደሚንቀሳቀስ አሳውቆ ነበር። ይህም በሪፎ ርሙ ከታዩ ታላላቅ ውሳኔዎች አንዱ ነበር።
• የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በታኀሳስ ሁለተኛ ሳምንት በአራተኛ ዓመት የሥራ ዘመኑ ባካሄደው 13ኛ መደበኛ ስብሰባ የማንነትና የአስተዳደር ወሰን ጉዳዮች ኮሚሽንን አቋቁሟል። የኮሚሽኑ መቋቋም አሁን በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ለሚታ ዩት የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ያለመ ነው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዚሁ ወር የእርቀ ሰላም ኮሚሽንን ለማቋቋም የወጣው ረቂቅ አዋጅም ጸድቋል። አዋጁ ያስፈለገው የሰላም ፣የእርቅ የመቻቻልና የአብሮነት ስሜት እንዲዳብር ለማድረግ መሆኑ ተገልጧል።
• በታኀሳስ ወር አጋማሽ ዶክተር አብይ በአፍሪካ ህብረት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተገናኝተው የግብር ንቅናቄ ዓላማን አስረድተዋል። በዚህም መንግሥት እጅና እግር የሚኖረው ግብር መሰብሰብ ሲችል እንደሆነ በመግለጽ ዜጎች የሚጠበቅባቸውን ግብር በመክፈል ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
• ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተገኙ ከህብረተሰቡ ጋር ሀሳብ መለዋወጣቸው ይታወሳል። በአንቦ ከተማ ተገኝተው የአንቦ ከተማና አካባቢ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት የትግል ማዕከል ሆኖ እንዳገለገለ በመጥቀስ ከዚህ በኋላ ለነጻነት መስዋዕትነትን መክፈል የለበትም በማለት ከእንግዲህ ለትምህርት ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግና ለውጡንም ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸው ነበር።
• በዚህ ወር ከፈጸሟቸው ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶች አንዱ የኢትዮ-ቻይና ግንኙነት በተጠናከረ መልኩ በሚዘልቅበት መንገድ መምከራቸው ነው። ባለፈው ታኀሳስ ወር የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ተገኝተው ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ቻይና ለውጡን አስመልክቶ ኢትዮ ጵያን የማገዝ ፍላጎት እንዳላት መግለጻቸው ይታወሳል።
• ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ ሶስት ሺ ስድስት መቶ ዘጠና ስድስት መምህራንን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረው ነበር። በመሆኑም በትምህርት ዘርፍ በተሰጠ ትኩረት ፣በትምህርት ጥራት፣ በመምህራን ጥቅም ፣ በሀገር ሰላምና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 26/2011