ወጣቶቹ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ናቸው። ሰላማዊ ሰልፉን ያስተባበሩት፤ መፈክር የጻፉት፤ በሰልፉ ላይ የመሪነትን ሚና የወሰዱት ሁሉም በተሰጣቸው ሃላፊነት ላይ ሆነው ስራቸውን ይሰራሉ። ስራቸውንም ሰርተው ሞቅ ደመቅ ያለውን ሰልፍ አድርገው ተመልሰዋል። የሰላማዊ ሰልፉን አፈጻጸም ለመገምገም ቀጠሮ ይዘው በቀጠሮው ቦታ ሁሉም አስተባባሪዎች ተገኝተዋል።
አንደኛው ወጣት “ዛሬ መቼስ ሚዲያዎች ይህን ሰልፍ እንዴት እያደረጉ እንደሚዘግቡት ለማየት ጓጉቼያለሁ አለ።” ወጣቱ በሞቅታ ነገሮችን በማስረዳት የሚታወቅ ነው። አንድ ስራ ጥሩ ተሰራ ብሎ የሚያስበው ነገሮች በሞቅታ ውስጥ ሲከናወኑ ነው። ስብሰባ ራሱ ሞቅ ካላለ ውሳኔ የተላለፈ አይመስለውም። ደጋፊዎች በሌሉበት ሜዳ ውስጥ ኳስ መጫወት በጠባብ ክፍል ውስጥ ፈረስ እንደመጋለብ እንደሆነም ሲያስረዳ ተደምጧል። ይህ ወጣት የሰልፉ ውጤት ምንም ይሁን ምን ሞቅ ያለ መሆኑና ሚዲያዎችም በደንብ የሚዘግቡት ሆኖ ማለፉ ትኩረቱን ይዞታል።
ሌላኛው ወጣት ሰልፉ በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደፈጠረ በማመን “መንግስት መቼስ ከእዚህ በኋላ ለጥያቄያችን የሚኖረው ምላሽ ዝምታ አይሆንም። በሰልፉ ላይ የተላለፈው መልእክት መንግሥት አካሄዱን እንዲፈትሽ የሚያስገድደው ነው።” አለ። ይህኛው ወጣት ሰልፉ የፈጠረው ተጽእኖ ውጤት ሊያመጣ እንደሚችል በማመኑ ከሚፈለገው ውጤት አንጻር የተቃኘ ነው።
ተከታዩ ወጣት ደግሞ ሲቀጥል “እኔ እኮ የሆነ ሰዓት ላይ ፖሊሶቹ ሊተኮሱብን ብዬ ፈርቼ ነበር፤ ግን በቃ ይህ ትግል ነው ብዬ ሞትንም ቢሆን ለመቀበል ዝግጁ ነበርኩ። አሁንም መክፈል የሚገባንን ዋጋ እየከፈልን ትግሉን ወደ ምን ማድረስ እንዳለብን ማሰብ አለብን። ትኩረታችን በትልቁ ምስል ላይ እንጂ በእያንዳንዱ ነጠላ ሁነት ላይ መሆን የለበትም። እያንዳንዱ ነጠላ ሁነት ተመጋግቦ ሊፈጥረው የሚገባውን ትልቁን ምስል ማግኘት ያስፈልጋል።” አለ። ሁሉም የየራሱን ሃሳብ እያወጣ እያወረደ ቆየና ሰልፉን ገምግሞ ለቀጣይ ሥራ ምክክር አድርገው፤ በቀጣይ ከሰልፉ ተከትሎ በተጨባጭ የሚሆነው ነገር ላይ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደየቤታቸው ተበታተኑ።
ከሰልፉ በኋላ በተጨባጭ የመጀመሪያው ወጣት እንዳሰቡት ሚዲያዎችም ትኩረት አልሰጡትም፤ መንግሥትም ሰልፉን ተከትሎ አዲስ የወሰደው እርምጃም አልነበረም። ሁለቱ ወጣቶች ተስፋ ቆረጡ፤ ቀጣይ የሚደረገው ትግልም ወደ ውጤት ሊያደርስ ስለማይችል መተው ነው ብለውም አመኑ። ተስፋ በቆረጠ ድባብ ውስጥ ሆነው ተገኙ። ሦስተኛው ወጣት ግን በዚህ ጊዜ ወጣቶቹ ካሉበት ስሜት አውጥቶ ወደ ተሻለ ውጤት ሊያደርስ የሚችልን ሃሳብ ይዞ መጣ። ወጣቱ ይዞ የመጣው ሃሳብ ተስፋ መቁረጥ ሳይሆን ወደ እያንዳንዱ ሰው የበለጠ ቅርብ መሆን የሚል ነበር። በአደባባይ የሚቀርበው የራሱ የሆነ ውጤት ቢኖረውም፤ በሚዲያ የሚተላለፈውም እንዲሁ የራሱ ጥቅም ቢኖረውም በግለሰብ ደረጃ ሰዎች ጋር በሚኖር ግንኙነት የሚመጣው ውጤት ግን ከፍተኛ እንደሆነ አስረዳ። የበለጠ ወደ ሰው በቀረብን ቁጥር የበለጠ ተጽእኖ እንፈጥራለን ብሎ እንደሚያምን አስረዳ። የጋራ ስምምነት ላይም ደርሰው አዳዲስ ድምጻቸውን የሚያሰሙበትን መንገድ ቀየሱና ተሰማሩ።
የሰልፍና የሚዲያ አድናቂው እንዲህ አለ “በሜዳ ላይ ወጥተን ስለጮህን ብዙ ውጤት አላመጣንም፤ ነገር ግን የተወሰነ አካባቢን ለብቻ ነጥለን ሰውን በብዛት ሰብስበን ስናወያይ ውጤት አገኘን፤ ቀጥሎ ደግሞ በቡድን በቡድን እየሆንን የመንግሥት ሰዎች ለውጥ እንዲያመጡ ደብዳቤ ስንልክላቸው ለውጥ ማየት ጀመርን፤ እናም ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እንዲያመጡ ወደምንፈልጋቸው ሰዎች በተጠጋን ቁጥር ነው ለውጥ እያመጣን ያለነው።” በማለት ምስክርነቱን ሰጠ።
በምድር ላይ ለውጥ እንዲመጣ በብዙ የደከሙ አሉ። የደከሙት ለውጥ በምን ያህል ደረጃ ተጽእኖ አመጣ የሚለውን መርምረን በቅደም ተከተል አስቀምጠን የስኬታቸው ምክንያትን ለመመርመር ስንሞክር የምናገኘው መልስ አለ፤ እርሱም መመስረት፤ መገንባትን ያሳየናል።
ህዝብ እንደ ህዝብ ተንቀሳቅሶ አንድን አላማ ማሳካት እንዲችል ከጀርባው ህዝብን የሚያደራጁ፤ በህዝብ ውስጥ ሃሳብን የሚጨምሩ አለ። በማህበራዊ ለውጥም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ላይ ሰዎችን አንቀሳቅሶ ስለ ብዙሃን የሚሆን ለውጥን ለማምጣት ይህ አሰራር አዋጭ ሆኖ በታሪክ ውስጥ ተቀምጧል።
ወጣቶቹ ወደ አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የጮሁት ጩኸት እንዳሰቡት ለምን ለውጥ እንዳላመጣ በገመገሙ ጊዜ የገባቸው እውነት እነርሱ ይዘውት የሚጮሁትን ጉዳይ ይዞ የሚያስተጋባ ከጀርባቸው የተፈጠረ ግንዛቤ አልነበረም። የተሻለ ግንዛቤን የያዙ፤ በእውቀት የተሞሉ ሰዎች ለማናቸውም ዓላማ አመቺ ናቸው። ውጤታማ የሆነን ስራ ለመስራትም የሚችሉ ሆነው ይገኛሉ። በዛሬው ጽሁፍ ስለ መሠረት እና ስለመገንባት እናያለን። ከሰፊው መድረክ ወደ እያንዳንዱ ሰው በመቅረብ ውስጥ ለውጥን ማምጣት ስለመቻል። ኢየሱሰ ክርስቶስ የተከተለው ሌሎችም ለውጥ ያመጡ ሰዎች ከአደባባይ በበለጠ በቅርርብ ውስጥ ተከታዮችን ያፈሩበት መንገድ።
መሠረት ለመመስረትም ሆነ ለመገንባት አስፈላጊ የሆነው መንገድ። መምህር ወደ ተማሪው ሲቀርብ፤ አሰሪው ወደ ሰራተኛው ሲቀርብ፤ አስተዳዳሪው ወደሚያስተዳድረው ህዝብ ሲቀርብ፤ ቄሱ፤ ሼኩ ሆነ መጋቢው ወደ መንጋው ሲቀርብ፤ የሚፈጠር ለውጥ። ግለሰብን በመቀየር፤ ቤተሰብን ሆነ ማህበረሰብን የመቀየር መንገድ። መሠረት በመመስረት መገንባት የሚያስችል መንገድ።
መሠረት
ወደ ላይ ምን ያህል ፎቅ እንደምትገነባ ስታስብ አስቀድመህ የምትሰራው መሰረቱን ነው። መሰረቱ አጥልቆ በተቆፈረ ልክ ወደ ላይ የሚወጣው ከፍታው ብዛት ይወሰናል። በመሰረት ላይ ጊዜውን ያጠፋ፤ የተሻለውን ግንባታ ማድረግ ይችላል። መሠረትን የመመስረት መርህ ለውጤታማ አመራር ቁልፍ እንደሆነ የተለያዩ ጸሃፍት ከትበውት ይገኛል። ሰዎችን አስተባብሮ ውጤት ማምጣት የሚያስብ አንድ መሪ ስለ መሠረት አብዝቶ ማሰብ አለበት። ከስራው በፊት የሚሰራው ቀዳሚ ስራ የመሰረት ስራ ነው። ተከታዩ ስራ እንዲሸከመው የሚታሰበው ስራ የመሰረት ስራ ነው። በወጀብም ሆነ በአውሎ ነፋስ ውስጥ አልፎ ወደ ውጤት መድረስ ታስቦ የሚሰራው ስራ የመሰረት ስራ ነው። በሰው ላይ የሚሰራ፤ በሰው በኩል የሚሰራ።
መሰረትን ለመመስረት ስናስብ የምናስባቸው የመሰረት ግብዓቶች ዋና እሴቶች/Core Values ይባላሉ። የተለያዩ ጸሐፊዎች ግለሰባዊ አቅምን ለመገንባት የሚያስፈልጉን ዐበይት እሴቶችን ይዘረዝራሉ። ዐበይት እሴቶቹ እኒህ ናቸው ብለውም ይዘረዝራሉ። ተቋማት ተልእኳቸውን ለማሳካት ግምት ውስጥ የሚከቷቸውን ዐበይት እሴቶች ዘርዝረው ይገልጻሉ። የተቋሙ በር ላይም ይለጥፋሉ። አንባቢው የሕይወቱ ዋና ወይንም ዐበይት እሴቶች የሚላቸው ምንድን ናቸው?። በተለያየ ጸሐፊያን ደጋግመው ከሚጠቀሱ ግለሰባዊ እሴቶች መካከል ታማኝነት፤ ፍመት (ነገሮችን በንቃት ማድረግ)፣ ጽናት፣ በራስ መተማመን እና ጠንካራ ሰራተኝነት ዋናዎቹ ናቸው። ራእይን፣ የዓላማ ሰው መሆንን፣ ጽናትን፣ ፍቅርን፣ ትእግስትን፣ ወዘተ የራሳችን እንዲሆኑ የምንሰራባቸው እሴቶች ናቸው። እሴቶቹን ለመላበስ በምናደርገው ጥረት ውስጥ ሆነን ማለፍ የፈለግነውን ሆነን ማለፍ እንድንችል የሚረዳ። ፍቅርን እሴቱ ያላደረገ ሰው ውጤታማ ግንኙነትን ከሰዎች ጋር አድርጎ ወደ ውጤት መድረስ አይችልም።
ጠንካራ መሰረት ላይ የሚዘራው የእሴት ዘር አይነት፤ ዘሩ የሚኮተኮትበት መንገድ እና ዘሩ የሚጠበቅበት ጥበብ ወሳኝነት አላቸው። ከትውልድ ትውልድ ጠንካራ የሆነን መሰረት መመስረት እንደ አገር የሚኖርን ጥንካሬ ይወስናል። የእሴት መሰረትን ስናስብ ሦስቱን ነጥቦች ግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው። አይነቱን በማስቀደም እንጀምር።
በየአቅጣጫው የሚዘራው ዘር አይነተ ብዙ ነው። የሚዲያ ዘመን እና ሁሉም ነገር በተንቀሳቃሽ ስልክ ጋር የተገናኘ በሆነበት በዚህ ጊዜ ስንኖር የዘር ጉዳይ በደንብ ማሰብን ይጠይቃል። የሚዘራው የእሴት ዘር የሚኖረው ትርጉምን መረዳት የሚኖረንን መሰረት የሚኖረውን አቅም ያሳየናል። ልጆች፣ ታዳጊዎች እንዲሁም ወጣቶቻችን ዛሬ ያሉበት ሁኔታ ትላንት የተዘራባቸው ዘር ውጤት ናቸው። ትላንት የተዘራው የእሴት ዘር ዛሬ ላይ ይዘውት የሚገኙት እሴት ማሳያ ነው። ለነገ እንዲሆኑ የምናስበውን ነገር ደግሞ ዛሬ እንዘራለን። የዘሩ አይነት ግን ሁልጊዜ የሚታሰብበት ነው። በምናየው የቴሌቪዥን መርሃግብር፣ በምናነበው መጽሐፍ፣ አብረናቸው በሚውሉት ሰዎች እንዲሁ የእሴት ስንቃችን ይሰነቃል። የመረጥነውን እንመገባለን፤ በተመገብነው ልክም አቅምም ሆነ ጤንነት ይኖረናል። ከዘሩ ልየታ ቀጥሎ የሚመጣው ኩትኳቶው ነው።
የተዘራው ዘርን ውሃ ማጠጣትና መኮትኮት ለምንዘራው ዘር የሰጠነውን ትኩረት ያሳያል። መኮትኮት ዘሩን የበለጠ ወደ ፍሬ እንዲጠጋ ፍሬውም በጥንካሬ የሚገለጥ እንዲሆን የሚያደርገው ነው። መኮትኮት በሕይወታችን ላይ የተዘራውን ዘር እንደ አዋጅ አንዴ ታውጆ የምንተወው ሳይሆን መላለስን የምንሰራውን ስራ የሚገልጥ ነው። መኮትኮት ዘር የተዘራበትን ሰው ነባራዊ ሁኔታ ተረድቶ ነገሮችን በየጊዜው በመልኩ በመመልከት የሚገለጽ ነው። የተዘራው ዘር ወደ ፍሬ እንዲቀየር ከተፈለገ ሁልጊዜ ጥንቃቄን ይፈልጋል፤ ጥንቃቄውም በመኮትኮት ጊዜ በሚኖር ትኩረት ይገለጻል። መልካም ዘር ስለመዝራት የተጨነቅነውን ያህል ስለ መኮትኮት ትኩረት ካልሰጠን መገንባት ላይ መድረስ አንችልም። ትልቁ መገንባት ያለው መሰረት ላይ ነው፤ መሰረት ደግሞ የተዘራው በአግባቡ ሲኮተኮት የሚጸና ነው።
ዘሩን የመጠበቅ ጥበብ ደግሞ ሦስተኛው ለመሰረት የሚሆነውን ዘር ወደ ፍሬ የምናደርስበት መንገድ ነው። የተዘራውን ዘር ሊነጥቅ የሚመጣ ከተዘራው ዘር በተቃራኒው ያለ የመልካም ዘር ጠላት አለ። በተቃራኒው በኩል ያለውን የክፋት መንገድን በዘመናዊነት እንዲሁም በስልጣኔ ወዘተ አሳቦ የሚመጣን ዘርን መከላከል ያስፈልጋል። ትጋትን ስንዘራ የትጋት ተቃራኒ የሆነ በአቋራጭ መክበር የሚባል ጠላት አለ። ለእያንዳኑ ዐብይ እሴት ተቃራኒ የሆነ ልብን ሰርቆ የሚወስድ ስላለ ራስን መጠበቅ ያስፈልጋል።
ልጆቻችን በቤተሰብ፣ በመደበኛ ትምህርት እና በሃይማኖት መድረኮች ላይ ዛሬ ላይ የሚዘራባቸው ዘር አይነቱ፣ መኮትኮቱ እና ከተቃራኒ ዘር መጠበቁ መሰረታቸው ለረጅም ጉዞ የሚሆን ያደርገዋል። አገራችን በአመታት ውስጥ የምታልፍበት አስቸጋሪ መንገድ ውስጥ ማለፍ መቻሏ በልጆቿ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው። የኢትዮጵያ መዳከም የተዳከመ መሰረት ባላቸው ልጆቿ ውጤት መሆኑ ጥርጥር የለውም። በዘመናት መካከል አገራዊ ጥቅምን ወደ ጎን አድርገው ግለሰባዊ ጥቅምን ባሳቀደሙ ልጆቿ የዓለም ውራ ለመሆን በቅታለች። ዛሬም እንደ ትውልድ የተጋረጠብንን ሙሉ ሰው ሆኖ የመገኘት ፈተናን መወጣት የምንችለው አጥልቀን መቆፈር በቻልንበት የመሰረት ግንባታ ነው። መሰረቱ የጠራና ለፍሬ የሚሆን ትውልድ እንዲመጣ ስለምንዘራው ዘር እናስብ። ዘሩ ወደ ሚታጨድ ምርትነት እንዲቀየር መኮትኮቱና የቅርብ ክትትል ማድረጉ የግድ ነው። ጦሩን ሰብቆ የሚመጣ አፍራሽ የሆነ አስተሳሰብ እየተዋጉ መጠበቅ ደግሞ ሌላው ቁልፍ ነጥብ።
መገንባት
ግንባታው ተጠናቆ የሚታየው ነው። ግንባታን ሊያደርግ ዝግጅት የሚያደርግ ግለሰብ ከዝግጅቱ ጀምሮ እስከ ግንባታው ማጠናቀቅ ድረስ የሚያልፍባቸው ምዕራፎች ለሕይወት አስተማሪ በርካታ ቁምነገሮችን ይዟል። በውበቱ ሆነ በጥንካሬው የምንደመምበት ግንባታ እንዲሁ በዋዛ የተገኘ አይደለም። ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው የተግባር ስራ ውጤት እንጂ። በተጨባጭ የተሰራ ስራ። ግንባታው ከመሰረቱ ጀምሮ በአግባቡ ሲገነባ ቆይቶ የፊንሽኒግ ስራ ቢቀረው ህንጻው የሚሰጠው አገልግሎት በከፍተኛ ሁኔታ ከሚጠበቀው በታች መሆኑ አይቀሬ ነው። ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ከገባ በኋላ በየወቅቱ የሚደረገው አስተዳደራዊ የሆነ ስራዎች ካልተሰሩም እንዲሁ በተመሳሳይ ሁኔታ። የተወሰኑትን የግንባታ ምዕራፎች መነሻ በማድረግ መሰረት፤ መገንባትን እንቀጥል።
መገንቢያውን ቦታ ከማግኘት እንጀምር። መገንባት ሲታሰብ የመገንባት አቅም ስላለ ብቻ እንዲሁ ብድግ ተብሎ ወደ ግንባታ ሊገባ አይችልም። ምክንያቱም ግንባታውን ማከናወኛ ቦታን ማግኘት ስለሚገባ። የግንባታ ቦታውን ለማግኘት በመንግስት መመራት ወይንም በሊዝ መወዳደር ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ህገወጥ ግንባታ ሆኖ አንድ ቀን ሊፈርስ ይችላል። ግንባታው ተገቢውን ውጤት ስለማፍራቱ እርግጠኛ የምንሆንበት እክል ቢገጥመን ጉዳያችንን ይዘን ለፍርድ ቤት አቤት የምንልበት ላይሆንም ይችላል። በሰው ላይ የምናደርገው ግንባታም እንዲሁ ፈቃድ ይጠይቃል፤ የግለሰቡን ፈቃድ።
ግለሰቡ ፈቀዶ ለግንባታው ዝግጁ መሆን አለበት። ህጻናት በተፈጥሮ ህግ ሆኖ ፈቃዳቸውን ሳይገልጹ ግንባታ ይከናወንባቸዋል። ጨቅላ ህጻናት በተፈጥሮ ህግ ገፊነት የእናታቸውን ጡት ፈልገው ይጠባሉ። ህጻናቱ እንዲያድጉ ይጠቅማቸዋል ተብሎ የታሰበውን ምግብ ቤተሰብ አቅም እንደፈቀደ ይመገባል። ውጤቱ አካልን መገንባት ነው። በትምህርት እንዲሁም በማህበራዊ እሴቶች እንዲሁ እንደ ግለሰብ ግንባታው ይሆናል። ነገር ግን ይህ በተፈጥሮ ህግ ተከትሎ የሚደረገው ግንባታ እስከመጨረሻው አይሄድም። ጨቅላው አድርጎ ግራ ቀኙን ማገናዘብ ሲፈልግ ምርጫውን ማሳለፍ ይችላል። በህጻንነት ጊዜ አለመፈለግን በማልቀስና በሌላም መንገድ የሚገለጽ ቢሆንም በእድገት ጊዜ ግን በምክንያት ፍላጎትን ይገልጻል። ከህጻንነት ወቅት በተሻለ ሁኔታ ምክንያታዊነት ቦታውን ይይዛል፤ ምርጫ የሚባለው ሃሳብ በተግባር ይተገበራል።
አንባቢው እድገት ጨርሼያለሁ ከእዚህ በኋላ ማደግ አያስፈልገኝም እስካላለ ድረስ ዛሬም ፈቃዱን ከሰጠ ለማደግ እድል አለው። አካላዊ እድገታችን እንደ ልጅነት ወቅታችን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚቀያየር ባይሆን እንኳን አስተሳሰብ እንዲሁም እሴትን መገንባት ግን ይቻላል። ትላንት የተዘራው በቀላሉ መልቀቅ አዳጋች ቢመስልም ለውጥ ግን ማድረግ ይቻላል። ዛሬ ታዳጊዎች ራሳቸው ላይ መርጠው እንዲዘሩ ማስገንዘብ አስፈላጊ የሚሆነው በብዙ ምክንያት ነው።
መሰረቱ በዋና እሴቶች እንዲሁም ግንባታው በመልካም ፈቃድ ላይ አድርጎ ለቀናቱ ትርጉም የሚሰጥ ሰው መጠሪያው ለመገንባት የተሰራ፤ ለመመስረት የተመሰረተ ማለት ነው።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 5 ቀን 2014 ዓም