መአዛው ማወድ ጀምሯል፤ የ2015 አዲስ አመት። አዲስ አበባም በገበያው ግርግር ውስጥ እየገባች ነው፤ ሁሌም ግብይት የሚካሄድባቸው ቦታዎች እየተጨናነቁ ናቸው፤ ነጫጭ ድንኳኖች በየአደባባዩ ተተክለው አዳዲስ የግብይት ስፍራዎችም ተፈጥረዋል፤ በየህንጻዎቹ የሚገኙ መደብሮች ቄጤማ ጭምር እየጎዘጎዙ ትላልቅ ድምጽ ማጉያ ስፒከሮችን በየበሮቻቸው አቁመው የአዲስ አመት ዜማዎችን እያሰሙ ጎብኙን፣ ግዙን እያሉ ናቸው።
አዲስ አመት ለኢትዮጵያውያን ብዙ ትርጉም አለው። የዘመን መለወጫቸው፣ ክረምቱ ሸኝተው በጋውን የሚቀበሉበት፣ ለሁለት ወራት የተዘጉ ትምህርት ቤቶች የሚከፈቱበትም ነው። ይህ ሁሉ የየራሱን ግብይት ይፈልጋል። እናም በእዚህ ወቅት ብዙ ግብይት ይፈጸማል። የገበያ ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው ህገወጥ ነጋዴዎችም ሸማቹን በዋጋ የሚጎዱበት ወቅት ነው።
መንግስት የኑሮ ውድነቱ በህብረተሰቡ ላይ እያስከተለ ያለውን ጫና ለመቀነስ ሁሌም ከሚያደርገው በበለጠ በዚህ አይነቱ የበዓል ወቅት በሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለህብረተሰቡ የተለየ አቅርቦት ያደርጋል። መጪውን የአዲስ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግም ለበዓል ፍጆታ የሚሆኑ በርካታ ምርት ወደ መዲናዋ አዲስ አበባ በብዛት እየገባ መሆኑንና በቀጣይም እንደሚገባ ከከተማ አስተዳደሩና ከህብረት ስራ ማህበራት የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሰሞኑን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው እንዳስታወቁት፣ መጪውን አዲስ አመት አስመልክቶ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተለያዩ የእሁድ ገበያዎችና የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች በኩል ለሸማቾች ቀርበዋል።
ምርቶቹም ከእሁድ ገበያዎች በተጨማሪ እስከ አዲስ አመት ድረስ ለህብረተሰቡ እንደሚቀርቡ ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ ያለ አግባብ ዋጋ ከሚጨምሩና የኢኮኖሚ አሻጥር ከሚፈጥሩ አካላት ራሱን እንዲጠብቅ አሳስበዋል። በየአካባቢው በሚገኙ የእሁድ ገበያዎችና የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች እንዲገበያይ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ምርቶቹን ከማቅረብ በተጓዳኝ ህገወጥ ግብይትን ለመቆጣጠር እንደሚሰራም ተጠቁሟል። የከተማ አስተዳደሩ የዋጋ ማረጋጋት ግብረ ሃይል ተደራጅቶ ወደ ስራ መግባቱን አስታወቋል። የዋጋ ማረጋጋት ግብረ ሃይል በቂ አቅርቦት ለከተማዋ እንዲኖር በማድረግ የዋጋ ንረት እንዳይፈጠር ክትትልና ህግ የማስከበር ስራዎችን ያከናውናል ተብሏል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ከአጎራባች አካባቢዎች በርካታ መጠን ያለው ምርት ወደ ከተማዋ መግባት ጀምሯል:: ከእሁድ ገበያ ባሻገርም ባሉት ቀናት በእሁድ የገበያ ቦታዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ጥሪ ቀርቧል።
የህብረት ስራ ማህበራትም በየመገናኛ ብዙሃኑ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ይዘው እንደሚቀርቡ ሲያስታውቁ ነው የሰነበቱት። የአዲስ አበባ እና የኦሮሚያ ህብረት ስራ ማህበራትን ለእዚህ በአብነት መጥቀስ ይቻላል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረት ስራ ኤጀንሲን ዋቢ አድርጎ የአዲስ አበባ ኮሙዩኒኬሽን ሰሞኑን እንደዘገበው፤ የዘመን መለወጫ በዓልን ተከትሎ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ የቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ውጤቶች ግብይት እጥረት እንዳይኖር እየተሠራ ይገኛል።
የአዲስ አበባ ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጥላሁን ጌታቸው እንደሚሉት፤ በመጪው 2015 ዘመን መለወጫ በዓል ለከተማዋ ነዋሪዎች በተመጣጣኝ ዋጋ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ የቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ውጤቶች በከተማዋ በሚገኙ የመሰረታዊ ሸማች ማህበራት በኩል እንዲቀርቡ በእቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው። ዳይሬክተሩ ከበዓሉ አስቀድሞ ባሉ ቀናት በ11 ክፍለ ከተሞች በሚገኙ 148 በሚሆኑ የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ምርቶቹ ይቀርባሉ።
ከ225 በላይ በሚሆኑ የሸማች ሕብረት ሥራ ማህበራት ልኳንዳ ቤቶች ለቅርጫ የሚሆኑ በሬዎች ለህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ዝግጅቶች ተደርገዋል። ለበዓሉ ቀይ ሽንኩርት፣ ዘይት፣ የስንዴ ዱቄት፤ የበቆሎ ዱቄት፣ ዶሮና እንቁላል፣ ከእንስሳት ተዋጽኦ ቅቤና አይብ እንዲሁም ሌሎች ለበዓሉ አስፈላጊ የሆኑ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ የቁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ውጤቶችን ለከተማዋ ነዋሪዎች በስፋት ለማቅረብ በቂ ዝግጅት ተደርጓል።
ለበዓል በሚያስፈልጉ ምርቶች ላይ እጥረት እንዳያጋጥም ሲባልም ከተለያዩ አምራች የህብረት ስራ ማህበራት ጋራ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረው፣ በዚህም በመዲናዋ የሸማች የህብረት ስራ ማህበራት እና በእሁድ ገበያ በተመረጡ በሁሉም አካባቢዎች የግብርና ምርቶች፤ የኢንዱስትሪ ውጤቶች እንዲሁም እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች ለህብረተሰቡ በብዛትና በጥራት እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በገበያው ምንም አይነት የምርት እጥረት አለመኖሩ እየታወቀ የገበያ መረጋጋት እንዳይኖር የሚሰሩ አካላት ሲያጋጥሙ በሚመለከተው አካል ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተናግረዋል።
የመቂ ባቱ ሁለገብ የገበሬዎች አምራች የህብረት ስራ ዩኒየን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ሮባ በበኩላቸው የግብርና ምርት በማህበራቸው በስፋት መኖሩን ገልጸው፣ ለበዓሉ የሚያስፈልጉ የግብርና ምርቶችን በተመጣጣኝ እና በስፋት ለማቅረብ በመጋዘኖቻቸው በቂ ምርት መኖሩን ነው የተናገሩት።
ሸማች ሕብረት ሥራ ማህበራት ለህብረተሰቡ የሚያቀርቧቸውን የመሰረታዊ ፍጆታ ምርቶች በተገቢው ተደራሽ እንዲሆኑ የድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር ስራ የሚከናወን መሆኑን የአዲስ አበባ ሕብረት ሥራ ኤጀንሲው ማስታወቁን የአዲስ አበባ ኮሙዩኒኬሽን መረጃ ያሳያል።
የኦሮሚያ ህብረት ስራ ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፊሮምሳ አበራ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳሉት፤ ህብረት ስራ ማህበሩ 2015 አዲስ አመት በዓልን አስመልክቶ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለማቅረብ ሰፊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል፤ ካለፈው ዓርብ ጀምሮም 80 የሚሆኑ ማህበራት የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርቶችን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ለነዋሪው ማቅረብ ጀምረዋል። በኤጀንሲው ለከተማው ገበያ እየቀረቡ ካሉ ምርቶች መካከል እህል፣ የቁም እንስሳት እና ኢንዱስትሪ ምርቶች ይጠቀሳሉ።
ከግብርና ምርቶች መካከል ጤፍ እና የቁም እንስሳት እንደሚገኙበት የጠቆሙት አቶ ፊሮምሳ፤ የግብርና ምርቶችም ሆነ የኢንዱስትሪ ምርቶች በገበያ ከሚቀርብበት ዋጋ አንጻር ሲታይ ሰፊ ልዩነት መኖሩንም ነው የጠቀሱት። በአዲስ አበባ በሚገኙ በመደበኛ ገበያዎች የአንድ በሬ መሸጫ ዋጋ ከ80ሺህ እስከ 120 ሺህ ብር መድረሱን ጠቁመው፤ ኤጀንሲው ግን ከ45ሺህ ብር ጀምሮ በሬዎችን እያቀረበ መሆኑን ነው የጠቆሙት። አቶ ፊሮምሳ በገበያ ከሚቀርብበት ዋጋ ጋር ሲነጻጸር በአንድ በሬ ላይ እስከ 20ሺ ብር ልዩነት ይታያል ነው የሚሉት።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ የጤፍ ዋጋ በገበያ ከስድስት ሺህ ብር በላይ ደርሷል፤ ህብረት ስራ ኤጀንሲው ግን ጥራት ያለው ጤፍ በአምስት ሺህ ብር እያቀረበ ይገኛል። ከግብርና ምርቶች በተጨማሪ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶችም እየቀረቡ ሲሆን፣ ከነዚህ ምርቶች መካከል ዱቄት እና መሰል የኢንዱስትሪ ምርቶች ይገኙበታል።
ምርቶቹ በአዲስ አበባ ውስጥ በአራት ቦታዎች እየቀረቡ መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ ፊሮምሳ፤ ኦሮሞ ባህል ማዕከል፣ ቦሌ፣ ጀሞ እና ሳርቤት ፑሽኪን አደባባይ አካባቢዎች ምርቶቹ መቅረባቸውን አስታውቀዋል። የግብርና ምርቶቹ በብዛት መቅረባቸውንም ገልጸው፣ ጥራታቸውም የጠበቀ ነው ብለዋል። ህብረት ስራ ኤጀንሲው ከበዓል ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ምክንያት እንዳይጎዱ ምርቶቹን እያቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል፤፤
ኤጀንሲው አምና ሙሉ ዓመት እሁድ እና ቅዳሜ ለከተማው ነዋሪዎች ምርቶችን ሲያቀርብ እንደነበር አስታውሰው፣ ለበዓላትም እንዲሁ ሲያቀርብ እንደነበር ጠቅሰዋል። ዘንድሮ አምና ይቀርብ ከነበረው በተጨማሪ በሬ፣ በግ፣ ፍየል፣ ዶሮ እና እንቁላል ጭምር ማቅረቡ ልዩ እንደሚያደርገው ይጠቁማሉ። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ጥራት ያለው ምርት በቅናሽ ዋጋ በመግዛት ተጠቃሚ እንዲሆኑም ጥሪ አቅርበዋል።
የበዓል ገበያው እስከ ፊታችን ዓርብ ይቀጥላል ያሉት አቶ ፊሮምሳ፣ አዲስ አመት ካለፈ በኋላ ለመስቀል በዓል በተመሳሳይ የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርቶችን ለከተማው ነዋሪዎች ለማቅረብ እቅድ መያዙንም ይጠቁማሉ። በቀጣይ ለመስቀል በዓል ከአራቱ ቦታዎች በተጨማሪ በሌሎች የከተማዋ አካባቢዎችም ለማቅረብ መታቀዱን ገልጸዋል።
እንደ አቶ ፊሮምሳ ገለጻ፤ መጪውን በዓል ምክንያት በማድረግ ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች ከማቅረብ ጎን ለጎን ኤጀንሲው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። አምራቹ ምርታማነቱን ማሳደግ እንዲችል ኤጀንሲው የበኩሉን እየተወጣ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የኦሮሚያ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዋና ዓላማውም የኑሮ ውድነትን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እና የአርሶ አደሩን እና የአምራቹን ሕይወት መቀየር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ፊሮምሳ፤ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ፊሮምሳ ማብራሪያ፤ አርሶ አደሩ ምርቱን በጥራትና በብዛት ማምረት እንዲችል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ነው። በክልሉ በሚገኙ 20ሺ የሚሆኑ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት ለአርሶ አደሮች የግብርና ግብዓቶችን እያቀረበ ነው።
ኤጀንሲው ወደ 10 ሚሊየን አባላት ያሉት ሲሆን፣ ለነዚህ አርሶ አደሮች ማዳበሪያ እያቀረበ ነው። ለግብርና ምርታማነት ወሳኝ የሆነ ጥራት ያለው በቂ ማዳበሪያም እያቀረበ ነው። ከማዳበሪያ ባሻገር ለምርት እድገት ወሳኝ የሆኑ ግብዓቶችንም ያቀርባል።
ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ ለክልሉ አርሶ አደሮች ትራክተሮችን በማቅረብ ረገድ ኤጀንሲው ከክልሉ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ የትራክተር ተጠቃሚ አርሶ አደሮችን ቁጥር ማሳደግ መቻሉን ያነሱት አቶ ፊሮምሳ፤ በርካቶች ትራክተር የመጠቀም ልምዳቸው እያደገ መምጣቱን ጠቁመዋል።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ ትራክተር መሰል ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም እንዲያስችል አርሶ አደሩ ምርቶችን በክላስተር እንዲያመርቱ እየተደረገ ሲሆን፤ በርካታ አርሶ አደሮች ወደ ኩታ ገጠም አስተራረስ መግባታቸው የግብርና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ እድል እየፈጠረ ነው።
በየዓመቱ በርካታ ትራክተሮች እና ኮምባይኖሮች ለአርሶ አደሮች ማድረስ ተችሏል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ ወደ 92 ትራክተሮች በዩኒየኑ በኩል ለአርሶ አደሮች ቀርበዋል። እንዲሁም 72 ኮምባይነሮችም ለአርሶ አደሩ ቀርቧል። አርሶ አደሮች ተደራጅተው ኮምባይነሮችን እና ትራክተሮችን እየተጠቀሙ መሆኑንም አንስተዋል።
ትራክተሮቹ እና ኮምባይነሮቹ ህብረት ስራ እና ዩኒየኖች ባቀረቡት ገንዘብ የተገዙ ሲሆን፣ የክልሉ መንግስት እና የፌዴራል መንግስት ደግሞ የግዥውን ሂደት በማሳለጥ ረገድ የበኩላቸውን ሲወጡ ቆይተዋል። መሰል ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሮች የማቅረብ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው አቶ ፊሮምሳ የጠቆሙት።
ከዚህ ቀደም በነበሩት ጊዜያት ምርትን ከፍ ከማድረግ እኩል አሳሳቢ የነበረው የገበያ እጦት ችግር እንደነበር ያነሱት አቶ ፊሮምሳ፤ ህብረት ስራ ኤጀንሲው የአርሶ አደሮች ምርቶች ለገበያ የሚቀርብበትን መንገድ እያመቻቸ መሆኑንም ይገልጻሉ። በዚህም በገበያ እጦት ምክንያት አርሶ አደሮች ላይ የሚደርሰውን እንግልት ማስቀረት ተችሏል ብለዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 2/2014