ከምንም በላይ ትኩረት አድርገው ሲንቀሳቀሱ የነበረው ፍቅርን መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ፍቅር የሁሉ ነገራቸው መነሻ ሆኖ ዛሬም ድረስ አብሯቸው ዘልቋል፡፡ በደማቁ መርህ ያደረጉት ይህ ፍቅር የመደመርም ወላጅ አባት ነው፡፡ አንዱ ከሌላው ይደመር ዘንድ መንገዱን ማመላከት ብቻ ሳይሆን እርሳቸው ቀዳሚ በመሆን ነው፡፡ የተራረቀው ይደመር የማለታቸው ምስጢር አንዱን በአንዱ ለማስነሳት፣ አሊያም አንዱን አኮስሶ ሌላውን ለመካብ አለመሆኑንም ደጋግመው አስረድተዋ – የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ፡፡
ዛሬ መጋቢት 24 ቀን ድፍን አንድ ዓመት ሲሞላቸው ቀናቱና ወራቱ እንዲሁ እንደዋዛ እብስ ብለውባቸው ሳይሆን እያንዳንዷን ሰዓት በአግባቡ ተጠቅመውበት ነው፡፡ አንኳር አንኳር የሆኑና አንድ ሁለት ተብለው ሊቆጠሩ የሚችሉ ተግባራትን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከውነው ማሳየታቸው ደግሞ ለአብዛኞቹ ‹‹ይህ ነገር እውን ነውን›› ብለው እንዲጠይቁ ያስገደዳቸው ጉዳይ እንደነበርም የማይካድ ነው፡፡
ካከናወኗቸው አንጋፋ ተግባራት መካከል በወህኒ ቤት በጨለማ የተጣሉ እና እጃቸውን በሰንሰለት የተጠፈሩትን ሰንሰለቱ ከእጃቸው እንዲወድቅ ያደረጉበት ሲሆን፤ ይህ በአገር ቤትና በውጭም ላሉ እስረኛ ኢትዮጵያውያን ያልተጠበቀ የምስራች እንደሆነ እሙን ነው፡፡
በተለይ ደግሞ አንድ ሆነው ሳሉ የተለያዩትን፣ መዳረሻቸው ተመሳሳይ መሆኑ ቢታወቅም በመካከላቸው መግባባት የራቀውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሁለት ሲኖዶሶች መካከል ያለውንና በኢትዮጵያ እስልምና መካከል የተፈጠረውን አለመግባባትና መራራቅ በጥቅሉ ሆድና ጀርባ መሆን አሳስቧቸው ነበርና በሰሩት በጎ ተግባር አፍታም ሳይቆዩ እጅና ጓንት ማድረግ የቻሉ መሪ ሆነዋል፡፡ ይህ ፅሁፍ ሊዳስሰው የወደደውም ይህንኑ ጉዳይ ሲሆን፣ በጉዳዩ ዙሪያም የኢትዮጵያ የኃይማት ተቋማት ጉባኤ ዋና ፀሃፊ የሆኑትን መጋቤ ዘሪሁን ደጉን አነጋግረን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
በእምነት ተቋማቱ መካከል ስለተደረገው እርቀ ሰላም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ወደ ኃላፊነት ሲመጡ የመጀመሪያ አድርገው ከተንቀሳቀሱባቸው አጀንዳዎች መካከል በኃይማኖቶች መካከል ያለውን ችግር መፍታት ተጠቃሽ ነው። በኃይማኖቶች ውስጥ ተግዳሮት ሆነው የሚታዩት በተለይ በሁለቱ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ውስጥ የነበረውን ችግር ቅድሚያ ሰጥተው ነው እንዲፈታ ያደረጉት። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ያለ ችግር መፍታት ማለት የአገር ችግር እንደመፍታት ስለሚቆጠር ነው፡፡
ቤተ ክርስትያኒቱ ከታሪክም አንፃር ከምዕመ ኖቿም ብዛት የሚኖራት ተፅዕኖ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ስለዚህ ስራቸውን ከዚህ መጀመራቸው በእኔ እምነት ትልቅ ውሳኔ ነው። ደግሞም የተሳካና ውጤታማ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ሁላችንም እንደምናውቀው ሁለት ቦታ የነበረው ሲኖዶስ ወደ አንድ ለማምጣት የሰሩት ስራ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋሟት ጉባኤም በአድናቆት አይቶታል፡፡ በአሜሪካ የነበረው ሲኖዶስና እዚህ ያለው አንድ ሆነውና በአንድ ተቀምጠው የጋራ ውሳኔ እንዲወስኑና ቤተ ክርስትያኒቱ አንድነቷ የተረጋገጠበት እንዲሆን ያስቻሉ በመሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡
ይህ በእርግጥም ደግሞ ለአገሪቱ ያለው ጥቅም ትልቅ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንን ከአገሪቱ ታሪክ መለየት እንዲሁም ደግሞ የአገሪቱን ታሪክ ከኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን መለየት አይቻልም፡፡ስለዚህ ይህንን ችግር ከመፍታት መጀመራቸው ለእርሳቸውም ስራ ቀና መንገድን የሚፈጥር ነው። ምክንያቱም በኃይማኖቶቹ መካከል የሚፈጠረው ችግር ለመንግስት ራሱ ከባድ ችግር ነው የሚሆነው። የእነሱ አንድ መሆን የመንግስት ስራ ይቀል ዘንድ አድል የሚሰጥ ይሆናል፡፡
አንዳንዶች መንግስት በኃይማኖት መካከል ጣልቃ ገብቷል ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ይህን በማለታቸው
በጣም አዝናለሁ፡፡ እኛ መፍታት ያልቻልነው ችግር መንግስት ገብቶ ካገዘንና ከፈታልን መቀበልና አብሮ መሄድ ነው፡፡ ይህ ችግር እንዲፈታ ደግሞ መንግስት ብቻውንም አይደለም፤የኃይማኖቶች መሪዎቹ ፈቃደኝነትም አለ፡፡ በአሜሪካ የነበረው፣ እዚህም ያለው ሲኖዶስ ፈቃደኛ መሆን በፊትም የአብሮነት መፈላለግ እንዳላቸው የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ያንን እድል ተጠቅመው አንድ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡
እሱ ብቻ ሳይሆን ሁለቱም ፓትሪያሪኮች ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ምክንያም ከሁለት አንዳቸው አይሆንም ቢሉ ሊሳካ አይችልም፡፡ የሲኖዶሶቹ ወደ አንድነት መምጣት ለአገራችን ትልቅ ፋይዳ አለው፤ለሁላችን ደግሞ ለኃይማኖት ቅርብ ለሆንን ሰዎች ክብርም ነው። አገሪቱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለማስታረቅም ሆነ ተው ለማለት፣ መንግስት እርስ በእርሱ ሲለያይ፣ መንግስት ከህዝቡ ጋር ሲጋጭ፣ ቤተ ከርስትያኒቷ ታረቁ ብላ ድምጽዋን ከፍ አድርጋ ለመናገር አቅም ይሰጣታል፡፡
የእስልምና ጉዳዮች
ወደ እስልምና ጉዳዮች ስንመጣ የሚንጸባረቀው ይኸው ነው፡፡ የእስልምና ጉዳዮችም በአገራችን ታሪክ እንዲዚሁ የከበረ ታሪክ ያለው ነው፡፡ በተለይም ደግሞ ከሌላ ኃይማኖቶች ጋር አብሮ በመኖር፣ በሰላም ፈላጊነታቸውና ለኃይማታቸውና ለሌላ ኃይማኖት ያላቸው አክብሮት ትልቅ በመሆኑ እዛ አካባቢ የተፈጠረውን ችግር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለመፍታት ተንቀሳቅሰዋል፡፡
የኢትየጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤም ጉዳዩን በቅርበት ስለሚከታተል በቅርብ ጊዜያትም ውስጥ የእነሱም ይፋ የሚደረግበ ትልቅ ሁነት ይኖራል ብለን ከወዲሁ እየጠበቅን ነው፡፡ እስካሁን ረጅም ርቀት ሄደዋል፤ ከጠቅላይ ሚኒሰስትር ጋር ሁለቱም አካላት መፍትሄ አፈላላጊና የመጅሊሱ አመራሮች በጋራ ሆነው ኮሚቴ አዋቅረው እየሰሩ ናቸው፡፡ በዚህም ላይ ደግሞ የመጅሊሱ አመራሮች በእርግጥም ትልቅ ቅንነት የታየባቸው፣ ለአብሮነት ፍላጎት ያሳዩበትና ከጠቅላይ ሚኒስትሩም ጋር የነበራቸው ውይይት እንዲሁም ለእርቅና ለአብሮነት
ለሰላምም የነበራቸው ፍላጎት በጣም ትልቅ ነው፡፡ እናም በቅርቡ ሁላችንም የምንደሰትበት በኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤም ሆነ አገር ደስ የሚሰኝበት ትልቅና ወደ አንድነት የሚያመጣቸው ነገር ይኖራል ብለን እንጠብቃለን፡፡
የእምነት ተቋማት ጉባኤ ድርሻ
በእርቀ ሰላሙ ላይ ድርሻው ምን ነበር ቢባል እውነት ለመናገር የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አንዱ መመሪያው በኃይማኖቶቹ የውሰጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አለመግባት ነው፡፡እናም በእነሱ መካከል ችግር ሲፈጠር ለምሳሌ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ችግር ሲፈጠር እኛ ጣልቃ ገብተን ለመነጋገር መመሪያው ይከለክለናል፡፡
ሌላው ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የሲኖዶሱን ችግር ብንመለከት በእኛ ተቋም ደረጃ የሚፈታ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስትያኒቱ በራሷ ትልቅ ተቋም ናት፡፡ አገር እንደማለት ነች፡፡ ስለዚህ ይህ ተቋም ደግሞ ይህን ነገር ገብቼ ልፍታ ቢል ከአቅሙ በላይ ነው የሚሆንበት፡፡ በመሆኑም እነዚህ ሰባቱ ተቋማት የተስማሙበትና አብረን እንስራ ብለው የለዩአቸውን ተግባራት ብቻ ነው የምናከናውነው።
ስለዚህ የኢትዮጵያ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን እንዲሁም በኢትዮጵያ እስልምና፣ ጠቅላይ ምክር ቤት ጉዳይ፣ በአብያተ ክርስትያናት ጉዳይ በቀሩትም ተቋማት ጉዳይ በውስጥ አስራር ጣልቃ አይገባም፡፡
ስለዚህ ምን ስተትደርጉ ነበር የተባለ እንደሁ እውነት ለመናገር ፀሎት ነው፡፡ ከዚህ ያለፈ ድርሻ አልነበረንም፡፡ እርቁ የኢትዮጵያ ኃይማኖቶች በሙሉ ደስታ ነው ብለን ነው የወሰድነው፡፡ በእስልምናውም በቅርቡ እንዲሁ እንደሚሆን እናስባለን፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች እንደምናውቀው በብዙ ሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሙስሊሞችን የሚወክል ተቋም ነው፤ ይህ ተቋም በራሱ በመንግስት ደጋፊነት ችግሩን ወደመፍታት እየሄደ ስለሆነ ራሳቸው ናቸው የሚቆሙት፡፡ የእኛ ድርሻ እንዳልኩት መፀለይ ነው። እና በተለያየ ጊዜ የእርቅንና የአብሮነትን አስፈላጊነት
ለምዕመናኑ በማስተማር ከፍተኛ ድጋፍ አድርገናል። አንድ መሆን እንዳለባቸው፤ የውስጥ መከፋፈል እንዳይኖር በተለያየ መንገድ የራሳቸው ሰዎች ማለትም ከኦርቶዶክስ እንዲሁም ከእስልምና የመጡ ምሁራን ሲያስተምሩ ነበር፡፡ በክልል፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች ስልጠናዎች ስንሰጥ ነበር፡፡ እንግዲህ ይህ ጠቅሞ ከሆነ አናውቅም፡፡ እና ተቋማቱ የነበራቸው ዝግጁነት ትልቅ ነውና ትልቅም አክብሮት ይገባቸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትራችንም ትልቅ አክብሮት ይገባቸዋል፡፡ ሁለቱም ፓትሪያሪኮች ትልቅ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትም እንዲሁም ለመፍትሄ አፈላላጊ ለነበሩት ኮሚቴዎችም ለሁሉም ምስጋና ይገባቸዋል።
በመታረቃቸው የመጣ ለውጥ
በመታረቃቸው ለውጥ መጥቷል፤ የመጀመሪያው በውስጥ በኩል የመጣውን ለውጥ ቤተክርስትያኒቱና የመጀሊሱ ሰዎች ናቸው ሊገልፁት የሚችሉት፡፡ እኛ ግን ስንመለከት አንድ ናቸው መባሉ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በአሁኑ ውቅት ስለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሲታሰብ ስለሁለት ሲኖዶስ አይታሰብም፡፡ ብፁዓን አባቶች በአንድነት መጥተው ጉባኤ አድርገው አገረ ስብከት ላይ እንደሚሳተፉ ሰምተናል፡፡ ስለዚህ የቤተ ክርስትያኒቱን የውስጥ ሰላሟንና አንድነቷን አጠናክሮላታል፡፡
የቤተ ክርስትያኒቱ ሰላም ማለት ደግሞ የአገር ሰለም ማለት ነው፡፡ምክንያቱም በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ነው ያለው፡፡ የህዝብ ብዛቱ አንደኛ ነገር ሲሆን፣ የቤተ ክርስትያቱ ታሪክ ሁለተኛው ነገር ነው፡፡ እና ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ሁልጊዜ ስናወራ ስለትንሽ ተቋም እያወራን አይደለም፡፡ ስለ አገር እየተወራ እንደሆነ ነው ማሰብ ያለብን። ስለ እስልምና ጉዳዮች ስናወራ ስለትንሽ ተቋም አሊያም አጀንዳ አይደለም እያወራን ያለነው። ስለ አገር ነው የምናወራው። የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትንሽ ቁጥር አይደለም። የቁጥር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ሰላም መሆን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሶች ሰላም መሆን ነው። ለፕሮቴስታንቱም ሰላም መሆን ነው፡፡ ለሌሎች
ኃይማኖቶች ሁሉ ሰላም መሆን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስም ሰላም መሆን ማለት ለሙስሊሙ፣ ለአገር ሰላም መሆን ማለት ነው።፡ ለሌሎቹም የእምነት ተቋማት ሰላም ተደርጎ ነው የሚወሰደው፡ምክንያቱም እነዚህ ትልልቅ ተቋማት የአገርንም ታሪክ ጠብቀው የመጡ ናቸው፡፡ይህንንም ጉዳይ የታሪካችን አንድ አካል በመሆኑ ሁላችንም ልንደግፍና ልናግዝ ይገባል። የአንዱ ሰላም የሌላው ሰላም ነው። ሙስሊሙ ሲበጠበጥ ክርስትያኑ እጁን አጣጥፎ ከተቀመጠ አደጋው የሁሉም ነው የሚሆነው።
ወደፊት መሆን የሚኖርበት
በኃይማኖቶቹ መካከል የተፈጠረው አንድነትና አብሮነት ለአገር ሰላምና ልማት እንዴት አድርገን እንለውጠው የሚለው ሲታይ በተለይ አገራችን የገጠማትን ተግዳሮት ማለትም ከተግዳሮቱ እንድትወጣ የኃይማኖት አባቶች በጋራ ቆመው ወጣቶችን እየመከሩ፣ ልዩነቶች የሚስተናገዱበት ሰላማዊና የውይይት ባህላችን እንዲዳብር፣ ይህን የማስተማር፣ አብሮ የመቆምና በተለይም ደግሞ በሰው ልጆች ላይ መፈናቀል፣ ግድያ፣ ዛቻ ሲፈጠር እጃቸውን አጣጥፈው ማየት የለባቸውም፡፡
ሰው በብሄሩ፣ በቋንቋው ጉዳት ሲደርስበት የኃይማኖት አባቶች ቀድመው ይህንን የመከላከል ኃላፊነት የእነሱ ነው መሆን ያለበት፡፡የጋራ ተቋም ያላቸው እንደመሆናቸው በጋራ ሆነው የማስተማር፣ የመምከር እንደ አገር ደግሞ መልካም ስራ ሲሰራ እንደ አገር ማመስገን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ችግሮችን በመለየት ደግሞ እነሱን የማረም ስራ አብረን ከመንግስት ጋራ መስራት አለብን፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰየመው ብሄራዊ የእርቀ ሰላም ኮሚሽኑ ከኃይማኖት ጋር የሚገናኝ ስለሆነ የኃይማኖት አባቶች ከእነሱ ጋር ሆነው ባለፈው ጉዳይ ያለፈውን መልካም ነገር አድንቀን ችግር ያለበትን ደግሞ አርመን ያለፈውን ምዕራፍ በይቅርታ ዘግተን በአዲስ መንፈስ እንድንነሳ የመስበክ፣ የማስተማርና የማሳወቅ ኃላፊነት የአባቶች ነው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2011
በአስቴር ኤልያስ