ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ታድላለች። አገሪቱ በአፍሪካ ግንባር ቀደሟ፣ በዓለምም ተጠቃሽ ከሚባሉት አገሮች ተርታ እንደምትመደብ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ ይህን ሀብቷን መጠቀም እንዳልቻለችና በተለይም ከምርትና ምርታማነት፣ ከግብይት፣ ከጥራት አንጻር የእንስሳት ዘርፉ ችግር እንዳለበት መረጃዎች ያመለክታሉ። አገሪቷ በተፈጥሮ ከታደለችው የእንስሳት ሀብቷ ተጠቃሚ መሆን ካልቻለችባቸው በርካታ ምክንያቶች መካከልም ሕገ ወጥ ንግድ፣ የጥራት ጉድለት፣ የእርድና የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር፣ የፋይናንስ አቅርቦት እና የእንስሳት ማቆያ ማዕከላት አለመኖር ይጠቀሳሉ።
ከግብይት ጋር ተያይዞ ከሚነሱ ችግሮች መካከል ሕገ ወጥ ንግድ በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። በተለይ በግብይት ሥርዓት ወደ ኋላ የቀረች በመሆኗ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እያገኘች አለመሆኗ ሁሌም ይገለጻል።
በኢትዮጵያ ኅብረት ሥራ ኮሚሽን የአርብቶ አደር አካባቢ የኅብረት ሥራ ማህበራት እንቅስቃሴና ተግዳሮቶች ላይ የተዘጋጀ መድረክ ሰሞኑን በተካሄደበት ወቅት በእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት የእንስሳት ምርቶችና መኖ ማቀነባበር ጥራት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ታሪኩ ተካ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ዘርፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
እንስሳት በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የማይሆኑት የለም የሚሉት አስተባባሪው፣ እንስሳት ምግብ፣ ገንዘብ፣ ጉልበት መሆናቸውን ያብራራሉ። ባህላዊ ምግቦች ጭምር የሚደምቁት ከእንስሳት በሚገኙ የተለያዩ ተዋጽኦዎች መሆኑን ያመለክታሉ። እንስሳት ለተለያዩ የገንዘብ ምንጮች ዋስትና በመሆን ለአርሶ አደሩ ባንክ ሆነው እያገለገሉ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት።
እሳቸው እንዳሉት፤ የእንስሳት ሀብት በኢትዮጵያ በሚገባው ልክ መልማት ባለመቻሉ አገሪቷ ከዘርፉ መጠቀም የሚገባትን ያህል መጠቀም ባትችልም ዘርፉ ትልቅ አበርክቶ ያለው ስለመሆኑ ግን የማይካድ ሃቅ ነው፤ በኢኮኖሚ ተደራሽነቱም ቢሆን ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ጋር ሲነጻጸር የእንስሳት ሀብት ከፍተኛ ድርሻ አለው።
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ18 ሚሊዮን በላይ መሬት ያላቸው አርሶና አርብቶ አደር የሆኑ አባወራዎች ስለመኖራቸው ጠቅሰው፣ ከእነዚህም መካከል 14 ሚሊዮን የሚደርሱት አባወራዎች በየቤታቸው ቢያንስ አንድና ከአንድ በላይ የዳልጋ ከብቶች እንዳሏቸው አቶ ታሪኩ አስረድተዋል። ኢትዮጵያ ከምሥራቅ አፍሪካ በግመል ቁጥር ቀዳሚ ስለመሆኗ ያነሱት አቶ ታሪኩ፤ ስምንት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ ግመሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ስለመኖራቸው ነው የጠቀሱት።
በቆላ አካባቢ የሚኖረው የማኅበረሰብ ክፍል በእርሻ ብዙ የሚጠቀም እንዳልሆነም ተናግረው፣ በእንስሳት ሀብት ተጠቃሚ መሆኑን ይገልጻሉ። በአካባቢው የሚገኘው የእንስሳት ሀብትም በተፈጥሮ የታደለው እንጂ ለእንስሳት ሀብቱ ትኩረት በመስጠት በእንክብካቤና በክትትል እንዲሁም እንስሳቱን በማልማት የተገኘ ውጤት እንዳልሆነም ይናገራሉ።
ተገቢውን ትኩረት በመስጠትና በእንክብካቤ እንስሳቱን ማልማት ቢቻል ዘርፉ የአገሪቱ በርካታ ችግሮች መፍቻ ቁልፍ መሣሪያ ሊሆን የሚችል አቅም እንዳለው ተናግረው፣ የእንስሳት ሀብቱ ቢለማ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ትርጉም ያለው ውጤት ማስመዝገብ እንደሚችል ነው ያስረዱት።
እንደ አስተባባሪው ገለጻ፤ በተለያየ ጊዜ በሚወጣው መረጃ መሠረት ከእንስሳት ሀብት ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ይቻላል፤ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ ነው። ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከ12 እስከ 19 በመቶ ድርሻ ይኖረዋል።
የግብርናው ብቻ ተነጥሎ ሲታይ ደግሞ የእንስሳት ሀብት 47 ከመቶ የሚሆን ድርሻ አለው። በአንስሳት ሀብት ከሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በላይ በአገሪቱ ውስጥ የተመጣጠነ ምግብ ሲታሰብ እንስሳት ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ። ከመቀንጨር ነፃ የሚያደርጉ የምግብ ዓይነቶች እንደ ወተት፣ እንቁላል፣ ስጋና ሌሎችም ሲታሰቡ የእንስሳት ጥቅም እጅግ ከፍተኛ ድርሻ ያለውና ከቤተሰብ ሕይወት ጋር ያለው ጥብቅ ቁርኝት ከፍተኛ ነው።
እንስሳት ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው በበለጠ ከሰው ልጆች ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላቸው በመሆኑ በተለይም ሜካናይዜሽን ባልተስፋፋበት አገር ለግብርናው ዘርፍ ጉልህ ድርሻ አላቸው። አብዛኛው እርሻ፣ ውቂያና መንገድ ባልተስፋፋበት አካባቢ ደግሞ ትራንስፖርትና ሌሎች ሥራዎችም በዚሁ የእንስሳት ዘርፍ የሚሸፈን ነው። በእነዚህና መሰል ምክንያቶች የተነሳ እንስሳት ለሰው ልጆች የሚሰጡት አገልግሎት በገንዘብ ከሚተመነው ዋጋ በላይ ይሆናል።
በአርብቶ አደር አካባቢዎች እንስሳት ማለት የኩራትም የክብርም ምንጮች ስለመሆናቸው የሚናገሩት አቶ ታሪኩ፤ ኤክስፖርቱን የሚደግፍ በኢንዱስትሪዎችም በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ሰፊ ዘርፍ ነው ሲሉ ያብራራሉ።
በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ተጠቃሚ ለመሆን ችግሮቹን የመለየት ሥራ በሚመለከታቸው አካላት እየተሠራ መሆኑንም አስተባባሪው ይጠቅሳሉ። ዘርፉን እጅግ ከሚፈታተነው ሕገ ወጥ ንግድና ኋላ ቀር የግብይት ሥርዓት በተጨማሪ የእንስሳት ዝርያዎች አለመሻሻል፣ የመኖ እጥረት እና በእንስሳት ጤና አጠባበቅ ላይ ብዙም አለመሠራቱ የዘርፉ ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውን ያብራራሉ።
ዘርፉ ዘመኑ የሚፈልገውን አገልግሎት መስጠት እንዲችል በዘመናዊ መንገድ መመራት እንዳለበት ያስገነዘቡት አቶ ታሪኩ፤ መንግሥት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ከእንስሳት ሀብቱ የሰው ልጆች ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ለማድረግ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል። በተለይም በዘርፉ ሰፊ ዕውቀት ያላቸው ባለድርሻ አካላት ያላቸውን ሰፊ ዕውቀት መሬት በማውረድ አገሪቷ ከተትረፈረፈው የእንስሳት ሀብቷ ይበልጥ ተጠቃሚ እንድትሆን ይሠራል ሲሉም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙመድ እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያ በቁም እንስሳት ምርት ከአፍሪካ አንደኛ ናት፤ ከዓለም ደግሞ ተጠቃሽ ከሚባሉት አገሮች መካከል ትገኛለች።
አቶ አብዲ አገሪቱ ከዚህ ሀብት ተጠቃሚ አለመሆኗን ጠቅሰው፣ ሀብቱን ከማልማትና ተጠቃሚ ከመሆን አንፃር አርብቶ አደሩ ከፍተኛ ውስንነት እንዳለበት ገልጸዋል። ለዚህም የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን በአርብቶ አደር አካባቢ የህብረት ሥራ ማህበራትን በማደራጀትና የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ከክልሎች ጋር ሰፊ ውይይት ማድረጉን አንስተዋል።
እንደ ምክትል ኮሚሽነሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሀብቷ ተጠቃሚ መሆን ካልቻለችባቸው ምክንያቶች መካከል በግብይት ሰንሰለቱ የሚስተዋለው ችግር በዋናነት የሚጠቀስ መሆኑን እሳቸው መረዳት ችለዋል። አብዛኛው የቁም እንስሳት ሕዝቡም ሆነ አገሪቷ ሳትጠቀምበት ወደ ውጭ እንዲወጣ እየተደረገ ሌሎች አገራት የውጭ ምንዛሬ እያገኙበት ናቸው።
ይህን ችግር ለመቅረፍም አርብቶ አደሩ በህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅቶ ተጠቃሚ የሚሆንበት እና አገሪቷም ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን ኮሚሽኑ በዋናነት እየሠራ ይገኛል። ለዚህም አምራችና ሸማቹን የሚያገናኝ ምቹ የገበያ መድረክ ለመፈጠር የታሰበ ሲሆን፣ በዚህ ላይም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ትልቅ ድርሻ ይኖራቸዋል።
የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ፍሬያለም ሽባባው በበኩላቸው፤ መንግሥት በአሁኑ ወቅት አርብቶ አደርና ቆላማ ተብለው የሚጠሩትን ክልሎች ትልቅ የኢኮኖሚ መሠረት ናቸው ብሎ የሚጠራቸው ክልሎች እንደሆኑ ገልጸዋል። እነዚህ አካባቢዎች ቀደም ሲል ድጋፍ የሚያሻቸውና ወደ ኋላ የቀሩ ተብለው ይታወቁ እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ትልቅ መሠረት ከሆኑት አካባቢዎች መካከል ተጠቃሽ እንደሆኑ አስታውቀዋል።
እንደ ኮሚሽነሯ ገለጻ፤ በእነዚህ አካባቢዎች በዋናነት ምን ይመረታል? በማምረቱ ሂደት ምን ዓይነት ችግሮች ይገጥማቸዋል? ተደራጅተዋል ወይ? በአካባቢያቸው የሚፈጥርባቸው ተጽዕኖዎች እንደምን ያሉ ናቸው? ለምሳሌ ድርቅ በየጊዜው በሚያጠቃቸው አካባቢዎች ምን ዓይነት ዝግጅት መደረግ አለበት? ከአርሶና አርብቶ አደሩ ምን ይጠበቃል? ተጋላጭነታቸውን ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት? የሚሉ በርካታ ሥራዎች በኮሚሽኑ በኩል እየተሠሩ ናቸው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ በሕገ ወጥ ንግድ በከፍተኛ ደረጃ ሰለባ የሚሆኑት በእንስሳት እርባታ የተሰማሩ አርብቶ አደሮች ስለመሆናቸው ወይዘሮ ፍሬያለም ጠቅሰው፤ እነዚህ አርብቶ አደሮችም ለሕገወጥ ንግድ፣ አስፈላጊ ላልሆነ የድንበር ላይ ንግድ ይጋለጣሉ ብለዋል።
በአገሪቱ በሚስተዋለው ኋላ ቀር የግብይት ሥርዓት በተለይም አርብቶ አደሩ ተጎጂ ነው ያሉት ኮሚሽነሯ፤ አርብቶ አደሩ በለፋበት ሌላው ምንም ዓይነት እሴት ያልጨመረው ሕገ ወጥ ነጋዴ ተጠቃሚ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል። አብዛኞቹ አርብቶ አደሮችም ለሕገወጥ ንግድ በመጋለጥ ለከፍተኛ ምዝበራ መደረጋቸውን ይጠቅሳሉ።
ኮሚሽነሯ እንደሚሉት፤ አካባቢዎቹም ጠረፍ አካባቢ መገኘታቸውም ለዚሁ ሕገ ወጥ ንግድ ተጋላጭ ሆነው ይገኛሉ። ሌሎችም እንዲሁ በእንስሳትና በማዕድን ንግድ ላይ የተሰማሩ ማህበራት ዘመናዊ የንግድ አሠራር ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ለችግሮች ተጋፍጠዋል።
አርብቶ አደሮች አስፈላጊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ባለመቻላቸው፣ የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አቅርቦት ባለመኖሩ፣ የማስቀመጫ እና ሌሎችም ችግሮች ያሉባቸው መሆኑን ኮሚሽኑ መረዳቱን ጠቅሰው፣ ችግሮቹን ለመፍታት የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነም ተናግረዋል።
‹‹ኮሚሽኑ ከክልሎች ጋር በተናጠል ባደረገው ውይይት በርካታ መረጃዎችን አግኝቷል›› ያሉት ኮሚሽነሯ፤ ምርቶችን እንደገና በአዲስ አይታ ለማየት ሰፋ ያለ ውይይት መደረጉንም አስታውቀዋል። በተገኘው መረጃ መሠረትም የአርብቶ አደር አካባቢዎች በከፍተኛ ደረጃ ምርት የሚገኝባቸው ክልሎች ስለመሆናቸው መለየቱን ጠቅሰዋል። የአርብቶ አደሮቹ የማምረት አቅም ከአገር ውስጥ አልፎ በውጭ ገበያ ተደራሽ በመሆን ትልቅ ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉ የምርት ባለቤቶች እንደሆኑም ተናግረዋል።
ነገር ግን የቁም እንስሳትን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ሂደት ያለው የግብይት ችግር ፈታኝ እንደሆነ በማንሳት አርብቶ አደሮቹ፤ ከማስቀመጫ ቦታዎች ጀምሮ የተለያዩ ችግሮችን እየተጋፈጡ እንደሆነ ኮሚሽኑ መረዳት እንደቻለ ጠቅሰው፣ እነዚህን የተለያዩ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የአርብቶ አደሩ ድርሻ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
እንደ አሳቸው ገለጻ፤ መንግሥት አርብቶ አደርና ቆላማ ቦታዎችን በከፍተኛ ደረጃ ለማልማት እየሠራ ነው። ማልማት ሲባልም አንዱና ቀዳሚው መሠረተ ልማት ማሟላት ነው፤ ለአብነትም በሶማሌ ክልል በነበረ ውይይት የካርጎና የማቆያ ችግር መኖሩን መረዳት ተችሏል፤ እነዚህን ችግሮች በመቅረፍም ትላልቅ የትራንስፖርት ወጪዎችን መቀነስ ይቻላል።
ሌሎችም በማህበራት ተደራጅተው የአቅም ውስንነት ያጋጠማቸው እንዲሁም የአርብቶ አደር ፋይናንስ ያጋጠማቸው ለአብነትም የብድር አገልግሎት ያጡ ስለመኖራቸውም ጠቅሰው፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የአርብቶ አደር ልማት ተብሎ ሲታሰብ ቀዳሚ የሚሆነው ሀብቱን እንዴት እናስተዳድር የሚለው ነው። ስለዚህ ያለንን ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ለክልሎች አቅም በመጨመርና በማገዝ መሥራት ያስፈልጋል። ያሉት ኮሚሽነሯ፤ በተለይም የግብይት ሥርዓቱን ዘመናዊ በማድረግ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ገበያ አላስፈላጊ የሆኑ ሕገ ወጥ ንግዶችን ለመከላከል የሚሠራ መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይ ችግሮችን በመቅረፍ ምቾት ያለውና ጤናማ የሆነ የግብይት ሥርዓት ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25 /2014