ቂምና ጥላቻን ለመስበክና ለማስፋፋት አይሁን እንጂ ያለፈን ታሪክ ማስታወስና ማውሳቱ ክፋት አይኖረውም። ስለሆነም ካሌንደራችንን ወደ ኋላ አንድ ዓመት ያህል እንመልሰውና አገራችን የነበረችበትን ሁኔታ መለስ ብለን እናስታውስ። የመጣበትን የረሳ መዳረሻውን አያውቅም አይደል ብሂሉ?
በሁሉም ዓይነት መመዘኛ ከዛሬ አንድ ዓመት በፊት የነበረችው ኢትዮጵያ እጅግ አስፈሪ በሆነ ሁኔታ ላይ የምትገኝ አገር ነበረች። የህዝብ ቅሬታ የወለደው ህዝባዊ አመጽ ከጫፍ ጫፍ የወጠራት፣ ኢኮኖሚዋ እየደቀቀ ሄዶ መጨረሻው ምን ይሆን የተባለና የሚሰማው ዜና ሁሉ ሞት፣ ውድመትና ጥፋት የሆነባት አገር! እዚህ አካባቢ የተቃውሞ ሰልፍ ተደረገ፤ ትምህርት ተቋረጠ፤ አድማ ተመታ፤ መንገድ ተዘጋ፤ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋረጠ ወዘተ የሚሉ አሉታዊ ዜናዎች ለጆሯችን ሰልችተውን እንደነበር ከማንም አይሰወርም።
የህዝባዊ አመጹ መነሻም አፈና፣ ጭቆናና ኢ ፍትሃዊነት ነግሷል፤ አገሪቱ ያፈራችውን ወጣት የሚመጥን የሥራ ዕድል የለም፤ ነጻነት ጠፍቷል፤ በሀገራችን እንደሁለተኛ ዜጋ ሆነናል የሚል ነበር። ህዝባዊ አመጹ ሲበረታም አገሪቱን እየመራ ያለው ፓርቲ ኢህአዴግ በዚያ ሁኔታ መቀጠል እንደማይችልና እንደማይገባ ተገነዘበ።
የህዝቡ ጥያቄ እውነት ነው፤ እስር አፈናና ማዋከብ በዝቷል፤ ሁሉም ዜጋ በእኩልነት እየታየ አይደለም፤ በሥልጣን መባለጉ ጫፍ ደርሷል ስለሆነም ኢህአዴግ ራሱን ለውጦ እነዚህ የህዝብ ጥያቄዎች በአስተማማኝ ሁኔታ ካልተመለሱ አገር ፈርሶ የታሪክ ተጠያቂ እንሆናለን የሚለው የለውጥ ኃይል የተወለደውም በዚሁ ወቅት ነበር።
ይህንን መሰረት አድርጎ ለስብሰባ የተቀመጠው የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚም የተደቀነውን ታላቅ ስጋት በመመልከትና ለውጥ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በማመን መሰረታዊ የሚባሉ የለውጥ አቅጣጫዎችን ሊያስቀምጥ ችሏል። ሥልጣን ከሀገርና ከህዝብ በታች ነው የሚለውን የለውጥ ኃይሎች መርህ መሰረት በማድረግም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከሥልጣናቸው በመውረድ ለለውጡ ምቹ ሁኔታን ፈጥረዋል።
መጋቢት 18 /2010 ዓ.ም አገር በምጥ ላይ ውላ ያመሸችበት ቀን ነበር። ይሁንና በዚሁ ዕለት እኩለ ሌሊት አካባቢ የብዙዎችን ተስፋ ያለመለመና አገርን ከስጋት ያላቀቀ ዜና ከኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተሰማ።
ይህም ዜና የለውጥ ኃይሉ አካልና አገርን ወደመረጋጋት ህዝብን ደግሞ ወደ አንድነት ያመጣሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው የዶክተር ዐብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ መመረጥ ነበር።
በዚሁ ታሪካዊ ውሳኔ መንስዔነትም የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዶክተር ዐብይ አህመድን የዛሬ ዓመት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በማድረግ ሾሟል። በርካታ የቤት ሥራዎችን የተቀበለውና በብዙ ተግዳሮቶች የተሞላች አገርን የተረከበው የለውጥ አመራርም ኃላፊነቱን ተረክቦ መንቀሳቀስ ከጀመረ እነሆ ዛሬ ድፍን አንድ ዓመት ሞላው። 365 ቀናትን ባገባደደው የለውጥ ጉዞም በርካታ ስኬቶች፣ ተግዳሮቶች፣ ተስፋዎችና ስጋቶች ተስተናግደዋል።
የተለየ ፖለቲካዊ ርዕዮት ማራመዳቸው ለወህኒ ያበቃቸው በሺዎች የሚቆጠሩ አስረኞች ነጻ መሆናቸው፣ የሀገራቸውን መሬት መርገጥ ጉምን የመጨበጥ ያህል የማይሞከር የሆነባቸው በርካታ ዜጎች በነጻነት ወደአገራቸው መግባታቸው፣ ነፍጥን የትግል አማራጭ ያደረጉ ኃይሎች ጠብመንጃቸውን አስቀምጠው ሰላማዊውን የትግል ጎራ መቀላቀላቸው፣ በባዕድ አገር በወህኒ ሲማቅቁ የነበሩ ዜጎች በመንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ነጻ ወጥተው ለሀገራቸው መብቃታቸው፣ መገናኛ ብዙኃንና ብሎገሮች ያለምንም ገደብና አፈና በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት አውድ መፈጠሩ፣ ከ20 ዓመታት በላይ የዘለቀው የወንድማማቾቹ የኢትዮጵያና ኤርትራ ውጥረትና ግጭት የሰላም መፍትሄ ማግኘቱ፣ አይነኬ የነበሩና ብዙዎች አፍነውናል ሲሉ ይማረሩባቸው የነበሩ ህጎችን የማሻሻል እርምጃ መጀመሩ ወዘተ ባለፈው አንድ ዓመት የተመዘገቡ ወርቃማ ድሎች ናቸው።
እኒህና መሰል አንጸበራቂና በአጭር ጊዜ ውስጥ ይሳካሉ ተብለው የማይጠበቁ ድሎች ቢመዘገቡም የለውጥ ጉዞው አልጋ በአልጋ የሆነና ከተግዳሮቶች የጸዳ ግን አልነበረም። የተለያዩ ሰበቦችን ምክንያት በማድረግ ግጭት መፍጠርና ህዝቦችን ማፈናቀል፣ በሐሰተኛ ዜናዎች ህዝብንና አገርን ማሸበርና አለመረጋጋትን ማስፈን፣ ለውጡን እንደስጋት በመመልከት ለማደናቀፍ ሌት ተቀን መሥራት፣ በተለያዩ ሴራዎች በመንግሥትና በህዝብ መካከል ቅራኔን ለመፍጠር መሞከር ወዘተ የለውጥ ጉዞው ትልቅ ፈተናዎች ነበሩ፤ አሁንም ናቸው።
በአጠቃላይ የለውጥ ጉዞው ያስገኛቸው መልካም ፍሬዎች ተስፋን ሲያሰንቁን ተግዳሮቶቹ ደግሞ ትልቅ ስጋት ሆነው ከፊታችን ተደቅነዋል። የእኛ የኢትዮጵያውያን ምኞትና ፍላጎት የለውጥ ጉዞው ተሳክቶ ሁሉም ኢትዮጵያውያን እኩል የሚታዩባት፣ ዴሞክራሲ የዳበረባትና ነጻነት የሰፈነባት እንዲሁም ያለስጋት የምንኖርባት ኢትዮጵያ እውን ሆና ማየት እንደመሆኑ ስጋቱን በመግፈፍ ተስፋን ወደተጨባጭ ውጤት ለመለወጥ መትጋት ይኖርብናል።
ይህ ዕውን የሚሆነው ደግሞ የመልካም ዜጋ እሴቶችን በመላበስ፣ አገርንና ህዝብን በመውደድ፣ ከጥላቻና ከሐሰት ወሬ ራሳችንን በማራቅና በተሰለፍንበት አውድ ለሰላምና ለዕድገት በመታተር ይሆናል። መንግሥትም ሆደ ሰፊነቱና ታጋሽነቱ እንዳለ ሆኖ የሀገርንና የህዝብን ህልውና በሚፈታተኑ ጉዳዮች ላይ ግን ኮስተርና ኮምጨጭ ብሎ የህግ የበላይነት የማስከበሩን ሥራ መተግበር ይጠበቅበታል። ይህንን ካደረግንም የለውጡን ባቡር ጉዞ ማፋጠንና ለእኛና ለልጆቻችን የምትሆን የበለጸገችና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ዕውን ከማድረግ የሚያግደን ኃይል አይኖርም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2011