ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ዋና ተጠቃሽ ጉዳይ ነው። የተጀመረውና እየሰፋ የመጣው የፖለቲካ ምህዳር ወደኋላ እንዳይመለስ የሚያሰጋቸው ነገር እንዳለ ምሁራኑ ይገልፃሉ።
በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑና የሦስተኛ ዓመት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በማጥናት ላይ የሚገኙት ዐብይ ወንድሜነህ፣ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ የፖለቲካ ምህዳሩን አስፍተዋል ከሚባሉት መካከል በርካታ ነገሮችን መጥቀስ እንደሚቻል ተናግረዋል። ለአብነትም የፍትህ ሥርዓቱን ለመሻሻል የተሠሩ ሥራዎች እንዲሁም የይቅርታና የእርቅ ሂደት መጀመሩ እንደ ትልቅ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ጠቅሰዋል። በተለይም የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸውና የሚዲያ ነፃነት ጉዳይም ከዚሁ ውስጥ የሚካተቱ እንደሆነ ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም በፀረ ሽብር ህጉ ተፈርጀው የነበሩ ድርጅቶች ሆኑ የሚዲያ ተቋማት በአሁኑ ወቅት በነፃነት በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኙም አመልክተው፤ እነዚህም ከነክፍተታቸው ማሳያዎች መሆናቸውን አስረድተዋል። ከዚህ ቀደም በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት በርካታ የታሰሩ ግለሰቦች እንዲሁም ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ የተከለከሉ አካላትም ነጻ ሆነው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ መቻላቸውም ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ማሳያ መሆን የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለፃ፤ አንዳንዶች የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ለአገራዊ ለውጥ ከማዋል ይልቅ የራስን ዝና ለመገንባት የመጠቀም አዝማሚያዎች ይታያሉ። ይህን የሚያደርጉ ሰዎች ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ የተማሩ፣ የፖለቲካ እውቀታቸው ትልቅ ነው የሚባሉ ናቸው። እናም ይህ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ትልቁንና አገራዊ የሆነውን ስዕል መመልከት አለመቻልም ይስተዋላል። የለውጥ ሂደቱን የሚደግፉትም ከመጡበት ማህበረሰብ እንጂ አገራዊ እይታን ከማስፋት አኳያ ችግር መኖሩን መረዳት ይቻላል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን በበኩላቸው፤ ኢህአዴግ ከዓመት በፊት በር ዘግቶ ከተገማገመ በኋላ በመጨረሻም ዶክተር ዐብይን ወደ ሥልጣን እንዲመጡ በማድረጉ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰው መሆን የቻለ መሪ ማየት መቻላቸውን ይናገራሉ። ብዙ ጊዜ መሪዎች ሰው መሆን አይችሉም ነበር። እርሳቸው ግን ህዝብ የሚናፍቀው አይነት መሪ ሆነው መገለፃቸውን ነው ያመለከቱት።
‹‹ቃላቸውን የሁላችንም ነው ብለን ሁላችንም ተንቀሳቀስን በርካታ ሥራም መሥራት ተቻለ።በሀገርም ውስጥ ሆኑ በውጭ የነበሩ
እስረኞች ተፈቱ። የፖለቲካ ድርጅቶችም በነፃነት ሐሳባቸውን መግለፅ ቻሉ። 13ኛዋ ወር ጳጉሜን ላይ በአምስቱም ቀናት መሪ ሐሳብን በማንገብ በልዩ ሁኔታ ማክበር ቻልን። በተስፋም መኖር ጀምርን›› ይላሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከርም ትልቁን ሚና መጫወታቸውን ዶክተር አባተ ይናገራሉ።
ዶክተር አባተ እንደሚሉት፤ ዶክተር ዐብይ በፍቅር ድልድይ ኢትዮጵያውያኑን ወደ አስመራ በማሻገር ከኤርትራውያን ጋር ማስተሳሰራቸውም በአንድ ዓመት ከታዩ ክስተቶች መካከል በዋናነት ተጠቃሽ ነው። አፍሪካዊ ስሜት እንዲኖርም ሚናቸው ላቅ ያለ ነበር።
አንዳንዶቹ በህይወታቸው ዘመን እንሾማለን ብለው ሳያስቡ ሴቶችን በኃላፊነት ቦታ በማስቀመጥ ቁጥራቸውን እስከ 50 በመቶ ማድረስ የቻሉም
መሪ ሆነዋል። በጥቅሉ ተስፋ ሰጪ ሥራዎች መካሄዳቸውን አመልክተዋል።
ረዳት ፕሮፌሰሩ ዐብይ እንደሚናገሩት፤ ለውጡን የሚመሩት በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ቢሆኑም አሁን ግን ግንባሩን በምናይበት ጊዜ ከተለመደው የዴሞክራሲያ ማዕከላዊነት ያፈነገጡ ጉዳዮች ይታያሉ። ለምሳሌ የአባል ድርጅቶቹ ዋና የሚባሉ አመራሮች የሚፃረሩ አስተያየቶች ሲሰጡ ይታያሉ።
ይህ እንግዲህ የውስጠ ድርጅት የፖለቲካ ችግር እንዳለው የሚያሳይ አንዱ ጉዳይ አሁን ያሉ ምልክቶች ሲስተዋሉ ቀድሞ እንዳለው አይነት መናበብ ያለ አይመስልም። ለለውጡ ዋና ናቸው የሚባሉ ኦዲፒና አዴፓ የአንድነት ኃይሉን የሚወክሉ ድርጅቶች ናቸው። በእነሱ መካከል የሚፈጠር ችግር አገሪቱንም እንደ አጠቃላይ ወደ አደጋ የሚያመራ ነው የሚሆነው። ስለዚህ ከፍተኛ መናበብ እንደሚጠይቃቸው ረዳት ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።
‹‹ለፖለቲካ ምህዳሩ ወደኋላ መመለስ በስጋትነት ሊነሳ ከሚያስችለው ጉዳይ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ነው። ይህም ለፖለቲካዊ ምህዳሩ መስፋት ከበጎ ነገሮች ይልቅ አሉታዊ ትርጉም ያላቸውን ሐሳብ በማቀንቀን ሂደት ላይ በመሆኑ ነው። ስለዚህ ይህን ጉዳይ መቆጣጠር የሚያስችል የህግ ረቂቅ በአፋጣኝ መውጣት ይኖርበታል›› ብለዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ ሰውም በአሁኑ ወቅት ለለውጡ መሪ ያለው ድጋፍ የመጀመሪያውን ያህል ነው ማለት አይቻልም፤ ምክንያቱም አንድ ሰው ለውጡን ሊመዝን የሚችለው ከኑሮ አንፃር ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ የኑሮ ውድነት በጣም እየጨመረ በመሆኑ ይህን ለማስተካከል በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል። የሥራ እድል ፈጠራ ላይም ከዚሁ ጋር የሚያያዝ ነው። ምክንያቱም የተለያዩ ጫፍ የረገጡ የፖለቲካ አቋምን የሚያራምዱ ግለሰቦች በቀጥታ የሚጠቀሙት ሥራ አጡን ወጣት ነው።ስለዚህ ይህን አካል ወደሥራ የማስገባት እንቅስቃሴ የሚከናወን ከሆነ የፖለቲካ ምህዳሩ ጠበበ ወደሚለው አቅጣጫ ላይወስድ ይችላል።
ዶክተር አባተ፣ ‹‹እስካለፈው ድረስ የፖለቲካ ምህዳሩ ይበል የሚያሳኝ ነው። ለቀጣይ ደግሞ ይህን መልካምነት የሚያደበዝዝ ስጋቶች ይታዩኛል። ለምሳሌ የመጀመሪያው ነገር በመንጋ መንቀሳቀስንና ኢትዮጵያዊ ያልሆነውን ባህል ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር አለመቻላችን›› ይላሉ።
እንደ ዶክተሩ ገለፃ፤ በእርሳቸው እይታ የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ ሦስት ዘመንን ያሳለፈ ነው።የመጀመሪያው ለመኖር ሲል በተፈጥሮ ላይ ጡንቻ ያስፈልገው ነበርና የጡንቻ ዘመን ይባላል። ቀጥሎ እየሠለጠነ ሲመጣ በጡንቻ ብቻ ሳይሆን መሣሪያ መሥራት ጀመረ። ይህም የመሣሪያ ዘመን ይባላል።
በመሣሪያውም በጎጥ ተከፋሎም ይዋጋ ነበር። የመጨረሻው ማለትም አሁን ያለንበት ዘመን የተግባቦትና የመረጃ ዘመን ነው። ነገሮች ሁሉ በድርድር የሚያልቁበት ጊዜ ነው። ወይ መስማማት አሊያም ላለመስማማት መስማማት ነው። ወደ ዘመነ ጡንቻና ወደ ዘመነ መሣሪያ አይኬድም። ነገር ግን አፍሪካውያን ገና ከዚህ መላቀቅ አልቻሉምና እርሳቸውም ይህን ይጋራሉ። አሁን ላይ የጡንቻና የመሣሪያ ዘመን እያቆጠቆጠ ያለበት ጊዜ ሆኗል።
‹‹በአሁኑ ወቅት የፖለቲካ ድርጅቶችም ከ108 ሆነዋል። 84 ብሔረሰብ አለን፤ ከአንድ ብሔረሰብ ከአንድ ድርጅት በላይ ወጥቷል ማለት ያስደፍራል። እነዚህ ይህ አካሄድ ርዕዮተ ዓለማዊ ሳይሆን ጎሳ ወይም ጎጥ ተኮር የሆነ ፖለቲካ በመሆኑ ሁሉም በየጎጡ እንጂ በአመለካከቱ አይደለም። ይህ ስጋቴ ነው። ምክንያቱም ሁሉም ለጎጡ የሚሮጥ ከሆነ መስማማት አይመጣም። ኢትዮጵያዊነት አንዱ አንዱን የሚያጠፋ አይደለም። ሰው መለኪያው ተቀይሯል ይህን ቶሎ ማጥፋት አለብን›› ብለዋል።
ከአንድ ዓመት በፊት በርካቶች በእስር ቤት ተጥለውና ሰብዓዊ መብታቸው ተገፎ ለዓመታት ነፃነትን ሲናፍቁ መቆየታቸው ይታወሳል። ብዙዎችም የመፃፍም ሆነ የመናገር መብታቸው ተጥሶ ለስደት ብሎም ለእስራት መዳረጋቸውም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነበር። መደራጀትም እንደሸብርተኛ ተቆጥሮ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 34ኛ መደበኛ ስብሰባ በ2003 ዓ.ም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ)ን እና ግንቦት ሰባትን በአሸባሪነት መፈረጁ ይታወሳል።
ይሁንና በሽብር ክስ የተከሰሱትን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጨምሮ 740 ሰዎች ግንቦት 18ቀን2010 ዓ.ም በክስ ማቋረጥና በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑም ይታወቃል። በተለያዩ ወንጀሎችም ተከሰው በፍርድ ቤት ውሳኔ የተሰጣቸው ፍርደኞችም በይቅርታ ቦርድ ታይቶ 576 ያህል ሰዎች መፈታታቸውም ይታወሳል።
ዶክተር አባተ እንደተናገሩት፤ ሚዲያው አጎብዳጅ መሆን የለበትም። ሚዲያዎች ህዝባዊ ማድረግና ሚዲያው ራሱን ነፃ ማውጣት ያስፈ ልጋል።
እንደ ዶክተሩ ገለፃ፤ በቁጥር የበዙት የፖለቲካ ፓርቲዎች ለጥቅም እንጂ ህዝብን ለማገለገል የተፈጠሩ አይመስሉም። ስለዚህም ወደ አዕምሮአቸው ተመልሰው ህዝባዊ ሆነውና ሰብሰብ ብለው ርዕዮተ ዓለማዊ ፖለቲካ አድርገው ጠቅለል ያለ ስያሜ ኖሯቸው እንዲሄዱ ማድረግ ያስፈልጋል።ህዝቡም ለተጀመረው ለውጥ ከልቡ ቆርጦ መነሳት ይጠበቅበታል። ይህ ከሆነ ደግሞ የፖለቲካ ምህዳሩ እያደር እየሰፋ ስለሚመጣ አገሪቱ ይልቁንም ህዝቡ ተጠቃሚ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር አይኖርም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 24/2011
በአስቴር ኤልያስ