በአገሪቱ እየተባባሰ ለመጣው የኑሮ ውድነት ከሚጠቀሱ በርካታ ምክንያቶች መካከል የምርት አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም አንዱ መሆኑ ይገለጻል፡፡ የግብይት ሰንሰለት መብዛትና አገራዊና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች ለዋጋ ንረትና ለኑሮ ውድነት መከሰት ዓይነተኛ ድርሻ እንዳላቸውም ይታወቃል፡፡
በአገሪቱ እየታየ ያለውን የሸቀጦችና የግብርና ምርቶች የዋጋ ውድነትና ከዜጎች የመግዛት አቅም በላይ መሆንን የተረዳው መንግስት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መፍትሔ ያላቸውን የተለያዩ አማራጮችን እየወሰደ ይገኛል፡፡
መንግሥት ገበያውን ለማረጋጋት ከወሰዳቸው አማራጮች መካከል የህብረት ሥራ ማህበራትን በመጠቀም የግብርና እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን ለሸማቾች ማቅረብ የሚለው ይገኝበታል፡፡ ምርቶቹን ደላላ ባልገባበት ሁኔታ የግብይት ሰንሰለቶችን በማሳጠር በህብረት ስራ ማህበራት መደብሮች በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ ለሸማቹ ተደራሽ ለማድረግ እየሰራም ነው፡፡ በዚህም በኩል እንደ ስኳር፣ ዘይት፣ እህልና የመሳሰሉትን ለሸማቾች ቅርብ በሆኑ መደብሮች በኩል እያቀረበ ይገኛል፡፡
መንግስት ህብረተሰቡን ከኑሮ ውድነት የመታደጉን ስራ በማስፋት በአዲስ አበባ ከተማ የእሁድ ገበያዎችን ወደ ስራ በማስገባት ሸማቾች ምርቶችን በየአቅራቢያቸው በተቋቋሙ የእሁድ ገበያዎች አማካይነት ከአምራቾች ሊያገኙ የሚችሉበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ በእነዚህ ገበያዎችም አትክልትና ፍራፍሬ፣ እህልና ሌሎች ምርቶች እየቀረቡ ይገኛሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አማካኝነት የተጀመረው የእሁድ ገበያ የዋጋ ንረትን ለማርገብ ብሎም ገበያን ለማረጋጋት ጉልህ ድርሻ እየተጫወተ ይገኛል፡፡ የእሁድ ገበያ ሲጀመር ከፍተኛ ቁጥር ያለው የማህበረሰብ ክፍል በሚኖርበት አካባቢ ከአስር በማይበልጡ ቦታዎች ነበር፤ በአሁኑ ወቅት ግን የክልል ከተሞችን ሳይጨምር በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 96 በሚደርሱ አካባቢዎች ቅዳሜን ጨምሮ በቋሚነት ግብይቱ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በእነዚህ የገበያ ቦታዎችም ሰፊ ቁጥር ያለው ሸማች በየሳምንቱ እየተገበያየ ነው፡፡ በተለይም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ በሚንቀሳቀስባቸው እንደ መገናኛ፣ ሜክሲኮ፣ ጀሞና፣ ፒያሳ ጊዮርጊስና የመሳሰሉት አካባቢዎች ገበያው ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ሜክሲኮ ከሚገኘው የእሁድ ገበያ አትክልትና ፍራፍሬ ሲሸምቱ ያገኘናቸው አቶ አበራ ማሞ በእሁድ ገበያው ደስተኛ ናቸው፡፡ አሁን ደግም ቅዳሜ ገበያ መጨመሩ የተሻለ እንደሆነና በየአካባቢው መገኘቱም ጠቃሚ ነው ይላሉ፡፡
ገበያው በየአካባቢው መኖሩ ሰዎች ከአካባቢያቸው ውጭ ሲንቀሳቀሱ እግረ መንገዳቸውን እንደየአቅማቸው መሸመት እንዲችሉ ያደርጋል የሚሉት አቶ አበራ፤ እርሳቸውም የእሁድ ገበያ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በየጊዜው የተለያዩ ምርቶችን ከገበያው ይሸምታሉ፡፡ በተለይ አትክልትና ፍራፍሬ በተመጣጣኝ ዋጋ እንደ ልብ የሚገኝ መሆኑን ነው ያስታወቁት፡፡ በሜክሲኮ፣ መገናኛና በሌሎች ዋና ዋና አደባባዮች አካባቢ ተወስኖ የነበረው የእሁድ ገበያ በአሁኑ ወቅት በየሰፈሩ እየታየ መሆኑንም የገበያ ተደራሽነት እየሰፋ እንዲመጣ እንዳደረገ ይናገራሉ፡፡
ከእሁድ በተጨማሪ ገበያው ቅዳሜም መኖሩ ደግሞ እሁድ የማያመቸው ቅዳሜ እንዲሸምት ማስቻሉንና ሌላው ጥሩ አማራጭ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ በዚሁ ገበያ የተለያዩ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ አበራ፤ በዋጋ በኩልም ከሱቅ ከሚገዙበት ዋጋ መጠነኛ ቅናሽ እንዳለው ነው ያስታወቁት፡፡ የገበያው ቦታ ሜዳ ላይ መሆኑ ግን ለሸማቹም ሆነ ለአቅራቢዎቹ ምቹ አይደለም ሲሉ እንደ ችግር ያነሳሉ፡፡
እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በሚል የተጀመረው የእሁድ ገበያ አሁን ላይ ቅዳሜን ጨምሮ በየአካባቢው እየሰፋ መጥቷል፡፡ በዚህም በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ዘንድ ተደራሽ መሆን የቻለው የእሁድ ገበያ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ያለው ሂደት ምን ይመስላል? የታለመለት ዓላማንስ አሳክቷል ወይ? ያጋጠሙ ችግሮችስ እንደምን ያሉ ናቸው? ስንል ላነሳነው ጥያቄ በአዲስ አበባ ከተማ ህብረት ሥራ ኤጀንሲ የግብይትና የገበያ መሰረተ ልማት ክትትል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ደብሪቱ ለዓለም ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
የእሁድ ገበያ ከተጀመረ ከ42 ሳምንታት በላይ እንደሆነው ወይዘሮ ደብሪቱ ያስታውሳሉ፡፡ ገበያው አስር በማይሞሉ አካባቢዎች የተጀመረ መሆኑን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ምንም ሳይቆራረጥ በ96 ቦታዎች እየተካሄደ ነው ይላሉ፡፡ በዚህም ህብረተሰቡ ከገበያው ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን ይገልጻሉ፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ በአሁኑ ወቅት ቅዳሜን ጨምሮ በ96 የተለያዩ አካባቢዎች በየሳምንቱ እየተካሄደ ያለው የእሁድ ገበያ ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ በርካታ ሰዎች ይገኙበታል፤ ማዕከል ናቸው ተብለው በሚገመትባቸው አካባቢዎች ብቻ ይደረግ ነበር፤ በዚሁ ገበያ የአካባቢው ማህበረሰብ ሳይሆን የሚጠቀመው መንገደኛው ብቻ ነው የሚል አስተያየት ኤጄንሲው የደረሰውን መሆኑን ተከትሎ ገበያውን ማስፋት ውስጥ ተገብቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በየሳምንቱ እሁድ እንዲሁም ቅዳሜ በየአካባቢው በሚገኙ የሸማች ህብረት ሱቆች አካባቢ ድንኳን ተዘርግቶ ምርቶቹ ለማህበረሰቡ መቅረብ እንዲችሉ ተደርጓል፡፡
በዚሁ ገበያ የሚቀርበው ምርት ተመጣጣኝ ዋጋ፤ ትኩስና ጥራት ያለው እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ በተለይም አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ የተለያዩ የግብርና ምርቶች መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በተመጣጣኝ ዋጋ እየቀረቡ ስለመሆናቸው ያብራራሉ፡፡ ለአብነትም ሶስት አይነት ጤፍ በጥሬውና ተፈጭቶ እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰዋል፤ ሸማቾች ጤፍ እንደየአቅማቸው መሸመት እንዲችሉ ከአምስት ኪሎ ጀምሮ ታሽጎ እየቀረበ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ለገበያ የሚቀርቡት ምርቶችም በተለያዩ ሸማች የህብረት ሥራ ማህበራት እየቀረቡ ሲሆን፣ በዚህ ስራ የተሰማሩት የሸማቾች የህብረት ሥራ ማህበራትም በአሁኑ ወቅት 150 መድረሳቸውን ያብራራሉ፡፡
በየሳምንቱ ቅዳሜና እሁድ አትክልትና ፍራፍሬ ይዘው የሚቀርቡት በተለይ አምራቾች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ አምራቾቹ የተለያዩ ምርቶቻቸውን በቀጥታ ለሸማቾች የሚያቀርቡበት ሁኔታ መፈጠሩን ይናገራሉ፡፡ ምርቶቹም ትኩስና ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡ ከምርቶቹም መካከል ሽንኩርት፣ ድንች፣ ካሮት፣ ቲማቲም፣ ፎሶሊያ፣ ጎመንና ሌሎችም ይገኙበታል። ፍራፍሬዎችም እንዲሁ አቦካዶ፣ አናናስ፣ ሙዝ፣ አፕልና ሌሎችም ፍራፍሬዎች እንደየወቅቱ ሁኔታ በየሳምንቱ በገበያው ይቀርባሉ ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ዳይሬክተሯ እንደሚሉት፤ በየአካባቢው የሚገኘው የማህበረሰብ ክፍልም ምርቶቹን በአቅራቢያው ማግኘት በመቻሉ በደስታ በሰልፍ ጭምር ወረፋ ይዞ እየሸመተ ይገኛል፡፡ በተለይም በስፋት በገበያው የሚቀርቡትን አትክልትና ፍራፍሬዎች በየሳምንቱ እየሸመተ ስለመሆኑ ራሳቸውም ማረጋገጥ ችለዋል፡፡
ማህበረሰቡ ምርቶቹን የሚገበይበት ቦታ ራቅ ያለ እንደነበር አስታውሰው፣ በሁለት ሳምንትና በወር አንድ ጊዜ ብቻ ይሸምት እንደነበርም ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ገበያው ለየአካባቢው እንዲቀርብ መደረጉን ተከትሎ የትራንስፖርት ወጪ ሳያወጣና ጊዜውን በሚቆጥብና አቅሙን ባገናዘበ መልኩ በየሳምንቱ እየሸመተ እንደሆነ መረዳት ችለናል ይላሉ፡፡
‹‹በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሁም ጥራት ያለውና ትኩስ ምርት በየሳምንቱ ስለማግኘቱ ማህበረሰቡ ግብረ መልስ እየሰጠ ነው›› ያሉት ዳይሬክተሯ፤ የሚቀርቡ የግብርና ምርት አይነቶች እንደየጊዜው እንደሚለያዩም ነው የተናገሩት፡፡ ለአብነትም የእሁድ ገበያ በተጀመረበት አካባቢ የሚቀርቡ ምርቶች ጥራት ያላቸውና ተመጣጣኝ ዋጋ እንደነበራቸው ያስታውሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የሽንኩርት ዋጋ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን፣ ያለውም በጥራትና በመጠን ያነሰ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ይህም ወቅቱ ክረምት በመሆኑና መኪኖች እርሻ ውስጥ ገብተው ለመጫን ካለመቻላቸው ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ችግር መሆኑን አብራርተዋል፡፡
‹‹ሽንኩርት የመበላሸትና የመበስበስ ባህሪ አለው፤ ለገበያ የሚቀርበው ሽንኩርት መጠንና ዋጋውም የሚጨምርበትና የሚቀንስበትም ወቅት አለው፡፡›› ያሉት ዳይሬክተሯ፣ ህብረተሰቡ ጊዜውን በመረዳት መታገስ ይገባዋል›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ያለው የሽንኩርት እጥረትና በዋጋም መወደድ ምክንያታዊ መሆኑን ነው ያስረዱት፡፡ ሽንኩርት ላይም ሆነ ሌሎች ምርቶች ላይ ለአብነትም ሙዝ ላይ እየታየ ያለው የዋጋ ግሽበት ከወቅትና ከምርት እጥረት ጋር ተያይዞ የመጣ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ዳይሬክተሯ እንዳስታወቁት፤ ወቅታዊ ከሆኑ ችግሮች ውጭ ያሉትን ችግሮች በመፍታት ገበያው ለማህበረሰቡ ተደራሽ እንዲሆን በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡ ከወረዳ እስከ ማእከል ባሉ የንግድ ቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች፤ የህብረት ሥራ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም በከንቲባ ደረጃ የተቋቋመ ግብረ ኃይል ጭምር ገበያውን በመከታተልና በመቆጣጠር እየሰሩ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም የምርት እጥረት ባለበት አካባቢ ምርት እንዲቀርብ በማድረግ ማህበረሰቡ ከሚሰጠው አስተያየት በመነሳት ተደራሽ ለማድረግ ሰፊ ጥረት ይደረጋል፡፡
ከኢንዱስትሪ ምርቶች ጋር ተያይዞ የስንዴ ዱቄት አቅርቦት አለመኖሩን አስመልክቶ የጠየቅናቸው ዳይሬክተሯ በሰጡት ምላሽ፤ አቅርቦቱ የተስተጓጎለው የምርት እጥረት ከመኖሩ ጋር በተያያዘ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በጥሬ ዕቃ እጥረት ምክንያት የፓስታና የመኮረኒ ምርት እጥረት ስለመኖሩም ነው የጠቆሙት፡፡
የስንዴ እጥረት በእነዚህ ምርቶች ላይ እያሳደረ ካለው ተጽዕኖ ውጭ በሌሎች ምርቶች በተለይም የግብርና ምርቶች የሆኑ አትክልትና ፍራፍሬ የመሳሰሉት ግን በተመጣጣኝ ዋጋ በጥራት ለማህበረሰቡ እየቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ህዝብ ብዛት እየጨመረ የመጣ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ አቅርቦቱን ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ማድረግ የማይቻል እንደሆነ ያነሱት ዳይሬክተሯ፤ በተቻለ አቅም አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ 11 ክፍለ ከተሞችና በ19 ወረዳዎች በሚገኙ 150 ሸማች የህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት የተለያዩ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ሳምንቱን በሙሉ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት ለህብረተሰቡ ደራሽ መሆናቸው ታምኖበት መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድጎማ ማድረጉን ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፤ በተለይም ከ2013 ዓ.ም እስከ 2014 በጀት ዓመት ማጠናቀቂያ ድረስ የጤፍ ዋጋን ማረጋጋት መቻሉንና ይህም በመንግስት በኩል የተደረገው ትልቅ ድጋፍ ውጤት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ምርቱ ከአምራች ህብረት ሥራ ማህበራት በአስር ዩኒየኖች አማካኝነት እየመጣ በመሰረታዊ ሸማች ማህበራት በኩል ለማህበረሰቡ እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ መሰረታዊ ሸማቾችም ማህበረሰቡ እንደየአቅሙ መሸመት እንዲችል ጥሬ ጤፍ፣ የተፈጨ ጤፍና እንጀራ በመጋገር ጭምር ለማህበረሰቡ እንደየፍላጎቱ እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያትም መንግሥት እያገዘ በመሆኑ ነው፡፡
ማህበረሰቡም ከሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት የሚያገኘውን ጥቅም በመረዳት በስፋት እየተጠቀመ እንደሚገኝ ተናግረው፣ ከፊቱ በተሻለ ጥራት ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የእሁድ ገበያ የተነሳበትን ዓላማ ማሳካት ችሏል ያሉት ዳይሬክተሯ፤ በተለይም የጤፍ ዋጋ እንዲረጋጋ ማድረግ መቻሉን ነው ያስታወቁት፡፡ ለአብነትም ነጭ ጤፍ በአሁኑ ወቅት በግለሰብ ነጋዴዎች ደረጃ በኪሎ 56 ብር መሆኑን ጠቅሰው፣ ዋጋ በሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት 48 ብር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሰርገኛ ጤፍም በኪሎ 44 ብር ሲሸጥ በሌሎች የገበያ ቦታዎች ግን በኪሎ 52 ብር ድረስ እየተሸጠ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡ ይህ ሰፊ የዋጋ ልዩነት የታየበት ምክንያት መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠቱ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ይሁንና አብዛኛውን የማህበረሰብ ክፍል በሳምንት ሁለት ጊዜ የተለያዩ ምርቶችን ማግኘት ባስቻለው የእሁድ ገበያ የኢንዱስትሪና የግብርና ምርቶች እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦን ጨምሮ በኪሎ ከአምስት ብር እስከ አስር ብር ቅናሽ እያገኘ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
መንግሥት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ባደረገው ከፍተኛ ጥረት አሁን ድረስ በሸማች የህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ጤፍን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማህበረሰቡ እየቀረበ መሆኑን ጠቅሰው፣ ማህበረሰቡ ጤፉን እዛው ገዝቶ አስፈጭቶ መውሰድ እንደሚፈልግም ይገልጻሉ። አብዛኞቹ ወፍጮ ቤት የሌላቸው መሆኑን ማህበረሰቡ የሚያነሳው ቅሬታ እንደሆነም ያነሱት ዳይሬክተሯ፤ ይህን ችግር ለመፍታትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ ዩኒየኖች የመጋዘን እጥረት ያለባቸው በመሆኑ ሌላኛው ችግር ነው፡፡ የመጋዘን ችግሩንም ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ የገበያ ቦታም ምቹ አለመሆንም ሌላው የሚነሳ ተግዳሮት ነው፡፡ በተለይም ሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት ቅዳሜና እሁድ ሠራተኛ ይዘው ድንኳን ተከራይተው የሚወጡ በመሆኑ አትራፊ አይደሉም፡፡ በትንሹ ለአንድ ድንኳን ከ500 እስከ 700 ብር ድረስ ያወጣሉ፡፡ ይህ አንድ ችግር ነው፡፡
በቀጣይም በእሁድ ገበያው ያጋጠሙ ችግሮችን በመፍታት ገበያውን በቋሚነት ለማስቀጠል ጥናት እየተካሄደ እንደሆነ ያመላከቱት ዳይሬክተሯ፤ እስካሁን ባለው የእሁድ ገበያም ከአራት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ መገበያየት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የእሁድ ገበያዎች እንደ አትክልትና ፍራፍሬ ያሉ የግብርና ምርቶች በስፋት እየቀረቡባቸው የኑሮ ውድነትን ለመከላከል እያስቻሉ ናቸው::
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18 /2014