ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታ የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር የተካሄደበትና ጠንካራ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ነው። በዚህ ግድብ ግንባታ የበርካታ አመታት ልምድ እና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የውጭ የግንባታ ድርጅት(ሳሊኒ) ከግማሽ በላይ ኮንትራቱን ወስዶ ከዚህ ቀደም ያልታዩ ዘመናዊ እና ኮምፒውተራይዝድ የሆኑ መሳሪዎችን ይዞ እየሰራ ይገኛል።
ከዚህ ኩባንያ ጋር የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የእውቀት፣ የክህሎት እና የቴክኖሎጂ ልምድ እያገኙ ነው። ቀሪውን ኮንትራት የያዘው ሃገር በቀሉ ብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንም ያለውን አቅም ይዞ ወደ ስራው በመግባት በተግባር ልምምድ ሰፊ ልምድ ማዳበር እንዲሁም በአለም የታወቁ አማካሪ ድርጅቶችን እያማከረ መስራቱ ሰፊ የክህሎት እና ቴክኖሎጂ ልምድ ለመቅሰም እና አቅሙን ይበልጥ ለማዳበር አስችሎታል።
ግድቡ በህዝብ ተሳትፎ በኩልም ከዳር ዳር በአንድ አይነት መንፈስ ዜጎችን ያነቃቃ ግንባታም ነው። ግንባታው በተፋጠነ መንገድ እንዲከናወን ዜጎች ከደመወዛቸው በማዋጣት፣ ቦንድ በመግዛትና ስጦታ በመስጠት የበኩላቸውን ተወጥተዋል። በቅርቡ የግድቡ ግንባታ መዘግየትና ለግድቡ የተበጀተው ገንዘብ ያለአግባብ ባክኗል በሚል የህዝቡ ተሳትፎ እየተቀዛቀዘ መምጣቱ ይጠቀሳል። የህዝቡን አመኔታም ለመመለስ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሀይሉ አብርሃም እንደሚናገሩት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግዙፍ ፕሮጀክት እንደመሆኑ በራስ ይቻላል መንፈስ እንገነባለን ተብሎ መነሳቱ እንዳለ ሆኖ በህብረተሰቡ አመለካከት ላይ ያመጣው ለውጥ ከፍተኛ ነው። ግንባታው ላይ የተለያዩ ተቋማት ተሳትፎ አድርገዋል። አገር በቀል ኩባንያ የሆነው የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን በተርባይን ስራው ላይ ባይሳካለትም ሌሎች ስራዎችን ሲሰራ ነበር።
በዚህም አቅም ተፈጥሯል ማለት ይቻላል። ነገር ግን ተርባይ ስራውን ሰርቶ ቢሆን ኖሮ ጥሩ ለውጥ ይመጣ ነበር። አጠቃላይ ግንባታውን የያዘው ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ሲሆን በሳሊኒ ኮንስትራክሽን ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ብዙ ኢትዮጵያውን ባለሙያዎች አሉ። እነዚህ በሲቪል ምህንድስና አቅማቸውና እውቀታቸው እየጨመረ መጥቷል።
ሳሊኒ የሚጠቀምባቸው ዘመናዊ መሳሪያዎች አሰራር ኢትዮጵያውን እየተማሩበት ይገኛሉ። የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ሲያሰራቸው የነበሩ ባለሙያዎች አቅም የፈጠሩ በመሆናቸው በተለያዩ ዘርፎች ላይ ገብተው እንዲሰሩ እየተደረገ ነው። እንደ አጠቃላይ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ የሚሰሩ ሰራተኞች እውቀታቸውን እያሳደጉ ይገኛሉ። በዚህ የተነሳም አገሪቱ ፕሮጀክቱን በራሷ መስራቷ ትልቅ ትምህርት የተወሰደበት ነው ማለት እንደሚቻል ይናገራሉ።
በግድቡ አካባቢ በምርምርና ጥናት ከዩኒቨርሲቲ የተወጣጡ ምሁራን ተሳትፎ አድርገዋል የሚሉት አቶ ሃይሉ በግንባታ ስራው ላይ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ተማሪዎች እንዲሰሩ በማድረግ ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች እውቀት እንዲያገኙ መደረጉንም ይናገራሉ። በተርባይን ስራው ላይ ክፍተት ቢኖርም ሌሎች ስራዎች ተሰርተዋል።
የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ላይ ክፍተቶች እንደነበሩ ያመለክታሉ። ከውጭ አገራት ለስራው ከመጡ ድርጅቶች ስር አገር በቀል ድርጅቶች እንዲሰሩ ማድረግ አለመቻሉ ስህተት መሆኑን በመጥቀስ፤ ለሙከራ ተብሎ ለአገር በቀል ኩባንያ መሰጠቱ ችግር መፍጠሩን ያስረዳሉ። በግንባታው ወቅት የቴክኖሎጂ ሽግግሩ የተዋጣለት ነበር ማለት
ባይቻልም መንግስት ሜጋ ፕጀክቶችን በራስ አቅም የመገንባትና የማስተዳደር አቅም እያጎለበተ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተግባር ልምምድ በማድረግና ጥናት እየሰሩበት እንደሚገኙም ይገልፃሉ።
እንደ አቶ ሀይሉ ገለፃ፤ በስድስት ወር 484 ሚሊዮን 72 ሺ ብር በቦንድና በስጦታ ተገኝቷል። ከዳያስፖራው ደግሞ 46 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ ተችሏል። የአሁኑ ዓመት ለህዳሴ ግድቡ የተደረገው ድጋፍ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ነው፡ አምና ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች ነበሩ በአጠቃላይ አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ነበር የተሰበሰበው።
በግንባው መዘግየትና ግንባታው ላይ ባለው የአስተዳደር ችግር ተብሎ በመገናኛ ብዙሀን በተለቀቁ ዜናዎች ምክንያት ህብረተሰቡ ተቀዛቅዞ ነበር። ባለፉት ወራት ስለ ህዳሴ ግድብ ብዙ እንቅስቃሴ አልነበረም። ህዝብን የመቀስቀስና ሲያደርገው የነበረውን ተሳትፎ እንዲቀጥል ማድረግ ላይ ስራዎች አልተሰሩም። በማህበራዊ ሚዲያዎች የግድቡ ግንባታ ቆሟል የሚሉ መረጃዎች በመውጣታቸው ህዝቡ ተቀዛቅዟል።
በአንዳንድ ክልሎች በተለይ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መምህራን ገንዘባችን ይመለስ የሚል ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሀይሉ፤ የጠራ መረጃዎች ባለመኖራቸው ህብረተሰቡን ማረጋጋት አልተቻም ነበር። መንግስት ጉዳዩን አይቶ በግድቡ ዙሪያ ያሉትን መረጃዎች ለህዝብ ይፋ አድርጓል። በዚህ መሰረት በህብረተሰቡ ዘንድ መነቃቃት በመምጣት ላይ እንዳለ ይጠቅሳሉ።
እንደ አቶ ሀይሉ ማብራሪያ፤ በዘንድሮ በጀት ዓመት ገቢ ማሰባሰቢያ ላይ የሚሰራ ስራ የለም። የቦንድ ሳምንትና የታላቁ የህዳሴ ግብ ሩጫ አልተካሄዱም። በዋናነት ብሄራዊ መግባባት ላይ እና የህዝቡን አመኔታ መመለስ ላይ ነው እየተሰራ የሚገኘው። የህዳሴ ግድቡ ገቢ ማሰባሰቢያ የእግር ኳስ የተካሄደው ከስታዲየም ገቢ የተወሰነ ለማግኘት ነው። በዚህም የስፖርት ቤተሰቡ ለግድቡ ድጋፍ እንዲያደርግ ታስቦ ነው። የህዝብ አመኔታ ለማግኘት ብዙ ስራዎች ይጠበቃሉ።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረስላሴ እንደሚሉት፤ የሕዝቡ ተሳትፎ ለማሳደግ መጀመሪያ መግባባቱ ወደነበረበት መመለስና ማጠናከር ይገባል። በዚህ ረገድ መልካም ጅማሮዎች እየታዩ ነው። ሌላው የተለያዩ ሁነቶች ከዚህ ቀደም ሲሠራ የነበረውን ተሞክሮ አክለን እንሠራለን። ለአብነት የሙዚቃ ምሽቶች ይኖራሉ፤ የስዕል አውደ ርዕይ ይኖራል፤ ሕፃናት ሴቶችንና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚያንቀሳቅሱ ሕብረተሰቡን በማያሰለችና በሚያዝናና መንገድ ለመሥራት እቅዶች ተይዘዋል።
ለህዳሴ ግድቡ ግንባታ መዋጮ የተገቡ ቃሎች ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት ወይዘሮ ሮማን፤ በዚህ ዓመት የገቢ ማሰባሰቢያ ስራዎች እንደማይኖሩን ውሳኔ ላይ ደርሰናል። ይህን ስንል ሁሉም ነገር ይቆማል ማለት አይደለም። ለአብነት ‹‹አሻራዬን አኑሬያለሁ›› የሚል የግድቡ ምስል ያረፈበት የደረት ፒን በ50 ብር የመሸጥ እንቅስቃሴዎች እንደሚኖሩ ገልፀዋል።
በአሁን ወቅት ሰዎች በፍላጎት የሚያደርጉት ተሳትፎ አስፈላጊ ነው። ከዚህ ባለፈ ግን ይህንን ቃል ገብታችሁ ነበር ይህንን ማድረግ አለባችሁ በሚል ወይንም ደግሞ የቦንድ ግዢ ራሱ ፈልጎ ካልሆነ በቀር በዘንድሮ ዓመት ቅስቀሳዎች እንደማይኖሩ ወይዘሮ ሮማን አመልክተዋል። በአሁኑ ወቅት በስድስት ወራት የተሰበሰበው ገንዘብ በህብረተሰቡ በፍላጎት እንጂ በተደረገ ቅስቀሳ አለመሆኑን መታየቱን አስረድተዋል።
እንደ ወይዘሮ ሮማን ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት እቅዶች ተከልሰዋል። ከሁኔታው ጋር እንዲጣጣሙ ተደርገዋል። ዋናው ሥራችን የሕዝብ አመኔታውን መመለስ በመሆኑ ወደ ቅስቀሳና ገቢ ማሰባሰቢያ የሚገባበት ሁኔታ የለም። ሕዝቡ ግን በራሱ ተነሳሽነት አዋጣለሁ የሚል ከሆነ ይሄን በፀጋ ነው የምንቀበለው። ለምሳሌ አንድ ቤተሰብ በእናት፣ በአባትና በልጆች እንዲሁም በየልጅ ልጆች ስም ባለ 50 ሺህ ብር ቦንድ በግለሰብ ደረጃ ግዢ ፈፅመዋል። ይህንን የተገዛው አምስት ዓመት ደርሶ ሊመለስላቸው ሲል ግድቡ ሳያልቅ እንደማይወስዱ ገልፀው መዋጮውን ያስቀጠሉ ቤተሰቦች አሉ።
ሕብረተሰቡ በየቦታው በራሱ ተነሳሽነት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እኛም እናበረታታለን። አዲስ ቦንድ መግዛት እንዲሁም የተለያዩ ነገሮችን ራሱ ካደረገ እንጂ ጽህፈት ቤቱ እንደ ዕቅድ ይዞ አይሠራበትም። መቀዛቀዙ በሁሉም ቦታ የነበረ ሲሆን የመቀዛቀዙ ምክንያት በወቅቱ ጽህፈት ቤቱ ግልጽ የሆነ መረጃ ሊኖረው ይገባ እንደነበር ይጠቅሳሉ።
ግድቡ እንዲህ ሆነ ሲባል ችግሮቹ ሳይለዩና የመፍትሔ አቅጣጫዎቹ ሳይቀመጡ ለሕብረተሰቡ የተጨበጠ ነገር ሳይያዝ መንገር ከባድ መሆኑን ይገልፃሉ። የዳሰሳ ጥናት ከተደረገ በኋላ ለህብረተሰቡ መረጃ ተሰጥቷል። ስሜቱንም ለመረዳት ተችሏል። ሕብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ ያለውን አቋም ግድቡ ሙሉ ለሙሉ አይሰራ የሚል አቋም እንደሌለው ተረጋግጧል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2011
በመርድ ክፍሉ