አባይ የኢትዮጵያውያን የዘመናት የቁጭት ምንጭ ሆኖ ኖሯል። በአባይ ዙሪያ ስንሰማቸው የኖርናቸው ኪነቃሎቻችንም የቁጭት ድባብ ያጠላባቸው ነበሩ። “አባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል፤ የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው፤” ወዘተ። በቃልም ሆነ በፅሑፍ የምናገኛቸው ግጥሞች ጭብጥም ኀዘንና ቁጭት አዘል ነበሩ። ኢትዮጵያ በአባይ ጉዳት ከመቆጨት በዘለለ ጥቅሙን ሳታጣጥም ኖራለች። ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ምንም ዓይነት ልማት እንዳታካሄድ ዓለም አቀፍ ጫናዎችም ነበሩባት።
በዚህም የተነሳ አባይን ለማልማት ምንም ድጋፍ ማግኘት ሳንችል ለዘመናት ኖረናል። አባይም ለሌሎች አገራት ሲሳይ ለኛ ደግሞ የተረት ምንጭ ሆኖ ዘመናትን ተሻግሯል። የኢፌዴሪ መንግሥት የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በራስ አቅም ለመገንባት በህዝቡ ላይ እምነት በማሳደር ቆርጦ ተነሳ። የፕሮጀክቱ ግንባታም መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ጉባ ላይ ሲበሰር የኢትዮጵያውያን የቁዘማ ዘመንም አከተመ። ከዚህ በኋላ “እኔ ብቻ ልብላ” የሚለው ኋላ ቀር አስተሳስብ ቀርቶ “በጋራ እንጠቀም፤ በጋራ እንልማ፣ አባይ ለሁላችንም ይበቃል” የሚለው ቀናና ዘመናዊ አስተሳሰብ በኢትዮጵያዊን ዘንድ ናኘ።
እናም የታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን ሆነ። እነሆ የዘመናት የቁጭት ዜማዎችም በአዳዲስ ዜማዎች መተካት ከጀመሩ ስምንት ዓመታት ተቆጠሩ። “አባይ ተገድቦ ልማቱን ዓይቼ፣ እኔ ነገ ልሙት ልጆቼን ተክቼ” የሚሉ ግጥሞችም ተከተሉ። ለዘመናት በአባይ አለመጠቀም የታከታቸው ኢትዮጵያውያንም ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን በተለያየ መንገድ ድጋፋቸውን አጠናክረው ቀጠሉ። ሕፃን፣ አዛውንት፣ ሀብታም፣ ድሃ፣ የተማረ፣ያልተማረ ወዘተ ሳይል ለታላቁ ህዳሴ ግድብ እውን መሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድ ልብ ተነሳ። በያለበትም ድጋፉን አጠናክሮ ቀጠለ።
በአሁኑ ወቅት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታም 66 ነጥብ 26 ከመቶ ደርሷል። ለዚህ ግንባታ እውን መሆንም የዚህ ታሪካዊ ሥራ ተሳታፊ ለመሆን ዕድሉን ያገኙትን ከ15 ሺህ የማያንሱ ሠራተኞችን ጨምሮ ከጀርባ ሆኖ የማይታክት ድጋፉን እየለገሰ ያለው በሃገር ውስጥና በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ታሪካዊ አሻራውን እያኖረ ይገኛል። ህብረተሰቡም ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ በማዋጣት በመነሻው ወቅት የገባውን ቃል እውን እያደረገ ይገኛል። ያም ሆኖ ግን ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ ይህ የህዝብ ድጋፍ መቀዛቀዝ አሳይቷል።
ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት የቆየው ይህ ፕሮጀክት በአንድ በኩል በወቅቱ ኃይል ማመንጨት አለመጀመሩ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ህብረተሰቡ ሲያዋጣ የቆየው ገንዘብ አላግባብ ባክኗል በሚል ጥርጣሬ ውስጥ በመግባቱ ነው። ነገር ግን ዛሬም ቢሆን ህብረተሰቡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ተጠናቆ ማየትን ይናፍቃል። ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ በገንዘብም ሆነ በጉልበቱ የሚያደርገው ድጋፍ ለራሱ የሚያስቀምጠው ቅሪት እንደሆነ ያምናል። ያም ሆኖ ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ እውን መሆን ካለው ፍላጎትና ተነሳሽነት አንፃር ከዚህም በላይ የሚሳተፍባቸውን መድረኮች ማመቻቸት ከመንግሥት ይጠበቃል።
አባቶቻችን በገጠሟቸው ዓውደ ጦርነቶች ሽንፈትን አስተናግደው አያውቁም። በዋሉባቸው ዓውደ ግንባሮች ሁሉ ድልን ማጣጣም የወረስነው የጀግንነት ገድል ነው። ዛሬ ላይ ያለው ትውልድም ከድህነት ጋር ግብግብ ይዟል። ከእነዚህ ትግሎች ውስጥ አንዱ ደግሞ በታላቁ ህዳሴ ግድብ አማካይነት የሚያከናውነው የልማት ሥራ ተጠቃሽ ነው። በሆኑም እንዲህ ዓይነት በኛው ትውልድ የተጀመረ ትልቅ የልማት ዓውደ ግንባር በአሸናፊነት ማጠናቀቅ ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚጠበቅ ነውና ድጋፋችንን ዛሬም እንደትላንቱ አጠናክረን ልንቀጥል ይገባል።
በውጭ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያንም ለአገራችሁ ታሪክ ሠርታችሁ ከምታልፉባቸው ትላልቅ መድረኮች አንዱ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ነው። ዛሬ በውጭ አገር መኖር ቢቻልም ስለ ነገ እርግጠኛ መሆን ግን አይቻልም። ልጆቻችሁ ከስደት ወጥተው በአገራቸው በሰላም እንዲኖሩ ሰላሟ የተረጋገጠና የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የግድ ነው። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ደግሞ የዚህ አንድ አካል ነው። በመሆኑንም በዚህ ፕሮጀክት ላይ የማይደበዝዝ የድጋፍ አሻራችሁን በማኖር ኃላፊነታችሁን ልትወጡ ይገባል።
መንግሥትም በግንባታ ሂደቱ ህዝብን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከቱ ማናቸውንም ጉዳዮች በየጊዜው እየተከታተለ ማጥራት ላይ ተገቢውን ትኩረት መስጠት አለበት። ይህ ፕሮጀክት የህዝብ ባለቤትነት ጎልቶ የታየበት የጋራ ንብረት በመሆኑ ህዝቡ በእያንዳንዱ የግንባታ ሂደት መረጃ የማግኘት መብት እንዳለው መገንዘብ ተገቢ ነው። ችግሮችም ሲጋጥሙ መፍትሔውን ከህዝብ ጋር በመመካከር መፍታት ይጠይቃል። ይህ ሲሆን የህዝቡ ድጋፍ እንደትላንቱ ይቀጥላል። መቀጠልም አለበት። ህዝቡ ቃሉን ጠብቆ ለፍጻሜው መትጋት ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 23/2011