ብርቱ ፉክክር በነገሰባት የውድድር ዓለም ጠንካራው ደካማውን ጥሎ ሲያልፍ ማየት የተለመደ ነው። ዛሬ ደካማ የሆነው ነገ ጠንክሮ ወደ አሸናፊነት ለመምጣት የሚደረገው ትንቅንቅም በዚያው ልክ ሃያል ነው። አሸናፊነት የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ባህሪ ነው። ማንም ሰው ማሸነፍን እንጂ መሸነፍን አይፈልግም። አሸናፊነት ይዞት የሚመጣው ተድላና የተመቻቸ አለማዊ ኑሮ አለና የብዙዎች መሻት ቢሆን አይገርምም። ብዙዎች ‹‹ዓለም ለአሸናፊዎች እንጂ ለደካሞች ቦታ የላትም›› ብለው እንዲያምኑ የሚያደርጋቸውም ይህ የዓለም እውነታ ነው።
ስፖርት የውድድር አውድማ ነው። አሸናፊዎች ከተሸናፊዎች የሚለዩበት መድረክ። በስፖርታዊ ውድድሮች ወደ ፍልሚያው ሜዳ የሚገቡ ሁሉ አሸናፊነትን እንጂ ሽንፈትን አልመውና አቅደው ሊመጡ አይችሉም። ስፖርተኞች የትኛውንም ፉክክር በአሸናፊነት ለመወጣት ከዝግጅት ጀምሮ ብዙ ይለፋሉ። በማሸነፋቸው የሚያገኙትን ጥቅምና ሽልማት እያለሙም ሌት ተቀን ይዘጋጃሉ። የልፋትና ድካማቸውን ፍሬም የሚያፍሱት በውድድር በሚያስመዘግቡት ውጤት ነው። ስለዚህ አንዴ ወደ ውድድር ከገቡ ከተቻለ በአቅምና ብቃታቸው ካልሆነም የተፎካካሪያቸውን ደካማ ጎን ተጠቅመው ለማሸነፍ ይጥራሉ። ይህ የስፖርቱ ዓለም ሃቅ ቢሆንም አንዳንዴ የተገላቢጦሽ ታሪኮች ይከሰታሉ።
ልፋትና ጥረትን፣ ህልምና የረጅም ጊዜ እቅድን ሁሉ ወደ ጎን ትተው ማሸነፍ የሚችሉትን ውድድር የሚሸነፉ የስፖርቱ ዓለም በታሪክ የማይረሳቸው የብዙዎች ተምሳሌት ሆነው ይገኛሉ። እነዚህ ታሪክ የማይዘነጋቸው ስፖርተኞች ስማቸውና መልካም ተግባራቸው ከአሸናፊዎች ተለይቶም በወርቅ ቀለም ይጻፋል። ውድድር ማሸነፍ ባይችሉም የዓለምን ሕዝብ ልብ ማሸነፍ ከቻሉ ታሪካዊ ስፖርተኞች አንዷ ኬንያዊቷ አትሌት ጃኩሊን ኔይቲፔ ኪፕሊሞ በጉልህ ትጠቀሳለች።
እኤአ በ2010 ዤንካይ ዓለም አቀፍ የማራቶን ውድድር ላይ ይህች ኬንያዊት አትሌት የፈጸመችው መልካም ተግባር ለዓለም ሕዝብ ተሸንፎም ማሸነፍ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ ነበር። በዛሬው የስፖርት ማህደር አምዳችን ይህ አስተማሪ የስፖርቱ ዓለም ድንቅ ታሪክና ክስተት ተዳሷል።
ኪፕሊሞ በርካታ ዶላሮችን ለሚያሳቅፈው ውድድር እንደማንኛውም አትሌት ለማሸነፍ በቂ ዝግጅት አድርጋ ወደ ውድድር ገብታለች። የአርባ ሁለት ኪሎ ሜትሩን ፈታኝ ፉክክርም በትልቅ የራስ መተማመን መምራት የጀመረችው ገና በጊዜ ነው። አሸናፊነትን በውስጧ እያሰበች የመጨረሻውን ክር በድል ለመበጠስ የሚያስችላት ሙሉ አቅምም አላት። ገና ውድድሩ አስረኛ ኪሎ ሜትር ላይ እያለ ጀምሮ ግን አንድ ነገር ማስተዋል ጀመረች። ከማራቶን ውድድሩ ጎን ለጎን አካል ጉዳተኞችም የራሳቸውን ውድድር በተመሳሳይ ጎዳና ላይ እያካሄዱ ነው። በዚህ ውድድር ላይ እየተሳተፈ የሚገኝ አንድ ቻይናዊ አካል ጉዳተኛ ከአስረኛው ኪሎ ሜትር ጀምሮ በውድድሩ ላይ ከነበረው ከፍተኛ ሙቀት ጋር ሲታገል አስተዋለችው። አካል ጉዳተኛው አትሌት ውድድሩን አላቋረጠም፣ በጽናት ወደ ፊት መግፋቱን ተያይዞታል። የሮጡት ኪሎ ሜትር እየጨመረ ሲሄድ ከፍተኛው የሙቀት መጠን የሚፈጥረው የውሃ ጥም ስቃይም እየጨመረ ሄዷል። ይህ አካል ጉዳተኛ አትሌት የደረቀ ጉሮሮውን እንደ ሌሎቹ አትሌቶች በውሃ ለማርጠብና ጥሙን አስታግሶ በተሻለ ብርታት ወደ ፊት ለመግፋት አንድ የሚያግደው ችግር አለ። አትሌቶች በተወሰነ ርቀት ውሃ አንስተው ከሚጎነጩበት ስፍራ የተዘጋጀውን ውሃ ለማንሳት ሁለት እጅ ስለሌለው ተቸግሯል። ቆም ብሎ ውሃውን ለማንሳት ቢሞክር ወደ ኋላ መቅረቱ ነው። የወሰደው አማራጭ የውሃ ጥም ስቃዩን ችሎ በደረቀ ጉሮሮው ወደ ፊት መግፋት ነው።
ይህ አካል ጉዳተኛ አትሌት በዚህ ሁኔታ ውስጥ እየታገለ መሆኑን ኬንያዊቷ አትሌት ከመጀመሪያ ጀምሮ አስተውላለች። ውድድሩ ሰላሳ ስምንተኛ ኪሎ ሜትር ላይ ደርሷል። ኬንያዊቷ አትሌትም ውድድሩን ለማሸነፍ ከፊት እየመራች ከአራት ኪሎ ሜትር ያልበለጠ ርቀት ይቀራታል። እየሮጠች ባለችበት ፍጥነት ከቀጠለች ውድድሩን ለማሸነፍ የሚያስችላት እድል ሰፊ ነው። ትንሽ ከዘገየች ግን ከኋላ ለምትከተላት ተፎካካሪዋ አሸናፊነቱን አሳልፋ ትሰጣለች። በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያለች ግን አንድ ነገር ውስጧን ይታገለዋል። በውሃ ጥም የራደው አካል ጉዳተኛ አትሌት ህመሙ ተሰማት። ከአስር ኪሎ ሜትር ጀምሮ ሁኔታውን ያስተዋለች ቢሆንም ህሊናዋ በስተመጨረሻ በዝምታ እንድታልፈው አልፈቀደላትም። በዝምታዋ ቀጥላ የራሷ ውድድር ላይ ብቻ ትኩረት አድርጋ እንዳትቀጥል የሚያግዳት አንዳች አለማዊ ህግ የለም። ከአለማዊ ህግ በላይ ህሊና የሚባል ታላቅ የተፈጥሮ ህግ ግን ከዚህ በላይ በዝምታ እንድትጓዝ አላደረጋትም። የአሸናፊነት ግስጋሴዋን ገታ አድርጋ ለተጠማው አካል ጉዳተኛ አትሌት በሚመቸው መንገድ ውሃ አንስታ ጥማቱን እንዲያስታግስ ረዳችው። ይህም ቅጽበት አሸናፊ ሆና ማጠናቀቅ የምትችለውን ውድድር ሁለተኛ ሆና እንድትፈጽም አደረጋት።
ኪፕሊሞ ለህሊና ዳኝነት ተገዝታ ዋጋ ከፈለች። ቀዳሚ ሆና በማጠናቀቅ የምታገኘውን የገንዘብ ሽልማት አጣች። ከአሸናፊነት የሚገኝን ክብር አሳልፋ ሰጠች። በውድድር አውድማ ተሸነፈች። ነገር ግን በመልካም ተግባሯ የአለምን ሕዝብ ስሜት አሸነፈች። ከውድድሩ በኋላም ባሉት ቀናት የዓለም ሕዝብ ትኩረት ቀዳሚ ሆና ባጠናቀቀችው አትሌት ላይ አልነበረም። ማህበራዊ ድረ ገጾችና ታላላቅ ሰዎችም ‹‹ኬንያዊቷ አትሌት ተሸንፋ ሰብአዊነት አሸነፈ›› ሲሉ ሙገሳቸውን አዥጎደጎዱላት።
ስፖርታዊ ጨዋነት የስፖርት ሥነ ምግባራዊ ገጽታ ነው። እንደ ፍትሃዊ ጨዋታ፣ ታማኝነትና ለተቃዋሚዎች፣ ለቡድን አጋሮች፣ ለደጋፊዎችም ጭምር አክብሮት ባላቸው መልካም ባህሪያት ጥምረት ይታያል። ስፖርታዊ ጨዋነት በተሸናፊነት ጊዜም ቢሆን ጨዋነትን በማሳየትና ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ራስን በመግዛት ማሳየት ይቻላል። በስፖርት ውስጥ የሚደረጉ ማንኛውም የሞራል ተግባራት ስፖርታዊ ጨዋነትን የሚወክሉ ሲሆን፤ እንደ ደጋፊም ቢሆን የስፖርታዊ ጨዋነት መንፈስን መጠበቁ በእኛና በተቀናቃኞቻችን መካከል ሰላምን፣ ፍቅርንና መከባበርን ያቆያል። የኬንያዊቷ አትሌት ተግባር ግን ስፖርታዊ ጨዋነት ከዚህም እንደሚልቅ ማሳያ ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15 /2014