‹‹መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ ናት ››ይባላል፡፡አዎ! እንዲህ አይነቱን ቃል መስማት የብዙዎችን ልብ ያሞቃል።የአባባሉ ትርጉምና ውጤት ድንቅ ነውና ለሰውልጆች የህይወት ተምሳሌት ቢሆን እሠዬው ነው። በርካቶቻችን ሚስቶች ለባሎቻቸው ዘውድ የመሆናቸውን እውነት ደጋግመን ሰምተነዋል። ይህን ሀቅ ተከትለው ሀሳቡን ዕውን ያደረጉ ደግሞ በህይወታቸው ብዙ አትርፈዋል።
የየዕምነቱ ቅዱስ መጻፍትም ሀሳቡን አጠናክረው በተለያየ መልኩ ተንትነው ጽፈውታል።በእነዚህ ማሳያዎች ባልና ሚስት አንዳቸው የሌላቸው ግማሽ አካል በመሆናቸው እስከ ሕይወት ፍፃሜ ተሳስበው፣ መዝለቅ እንዳለባቸው ያስረዳሉ። በተለይ በአንዳቸው፣ የደረሰውን ችግር እንደራሳቸው ተቀብለው እስከ መጨረሻው ተደጋግፈው መኖር እንደሚገባቸው እነዚሁ ሐይማኖታዊ መጽሐፍት በጽኑ ይመክራሉ።
አንዳንድ የማህበራዊ ጉዳይ ጠበብቶችም ቢሆኑ የጥንዶቹ የትሰስር ጥግ አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን የፍቅር ጽናት የሚያሳይ እንጂ በቀለበትና በሰርግ ድግስ ጋጋታ ብቻ የሚለካ ግንኙነት እንዳልሆነ ሲናገሩ ይደመጣል።
ዛሬ ላይ በስፋት እንደሚስተዋለው ግን እንዲህ ያለው ጠንካራ የመተሳሳብ እውነታ እየተሸረሸረ መጥቷል ለማለት የሚያስደፍሩ ማሳያዎች ጎልተዋል ። የሚጠቀሱ ምክንያቶች እንደየሁኔታው ቢለያይም ጋብቻቸውን በመሰረቱ ሰሞን ፈጥነው ለፍቺ የሚበቁ፣ ጎጇቸውን የጭቅጭቅና የንትርክ ገበያ አድርገው ትዳርን የሚጀምሩ ጥንዶች ቁጥር ተበራክቷል።
የዛሬዋ እንግዳችን የወይዘሮ የኔነሽ ታዬ እና የባለቤታቸው ትዳር ከነዚህኞቹ በእጅጉ ይለያል። በተለይ ወይዘሮ የኔነሽ ለባለቤታቸው ሲሉ በሕይወታቸው ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። በዛሬው ጽሑፋችንም ይሄንኑ እውነታ የሚዳሰስና አርአያነቱ የጎላ የትዳር ታሪክ ልናካፍላችሁ ወደናል።
ወይዘሮ የኔነሽ ታዬ ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ልዩ ስሙ አዲስ ከተማ አካባቢ ነው። እስከ 12ኛ ክፍል ጎበዝ ተማሪ ነበሩ። ትምህርት ቤት ሳሉ ለጎበዝ ተማሪዎች ‹‹ስፔሻል›› ተብሎ በተለየው ክፍል የመማር ዕድል አግኝተዋል። ቤተሰቦቻቸው ለሀብትና ክብር ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ታዋቂ የሶዶ ጉራጌ ነጋዴዎች ነበሩ።
ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ የጉራጌ ክትፎን ጨምሮ የሴት የተባሉ ሙያዎችን ሁሉ ሲማሩ አድገዋል። አንድ ዕለት ለየኔነሸ የወላጆቻቸው ሰራተኛ አንድ ሚስጥር ሹክ አለቻቸው።ሰሞኑን ባልተለመደ ሁኔታ ሽር ጉዱ የበዛው እጅግ ሀብታም ለሆነና የአባት ያህል በዕድሜ ለሚበልጣቸው ሰው ሊዳሩ እንደሆነ አረዳቻቸው፡፡ይህን ሲያውቁ ወይዘሮዋ ጊዜ አላጠፉም። ሻንጣ መሸከፍ፣ጓዝ ማንሳት አላስፈላጋቸውም። በለበሱት ልብስ በአጥር ዘለው አመለጡ። ተወልደው ካደጉበት ቤት ጠፉ።
ራሳቸውን በመደበቅ በየሆቴሉ ማዕድ ቤት እየተሸሸጉ የምግብ ዝግጅት ሥራን ጀመሩ። ወላጆቻቸው በፍለጋ ደክመው እስኪያጡዋቸውና ተስፋ ቆርጠው እስኪቀመጡ ድረስ በየሆቴሉ ብዙ ሰሩ። የመጨረሻው የሆቴል ስራቸው ካዛንችስ ያለው አድዋ ሆቴል ነበር ።ይህ ጊዜ የስራቸው ፍጻሜ የትዳር አጋራቸው መገኛ ሆነ ፡፡
የኔነሽ ልባቸው የፈቀደው ሰው አካልጉዳተኛ ነው። የዛኔ ደግሞ ሕብረተሰቡ ለአካል ጉዳተኞች ያለው አመለካከት እጅግ ፈታኝና አሸማቃቂ ነበር። አካል ጉዳተኞች እንደ ሌላው የሚያገቡና የሚወልዱ አይመስለውም ። ቤተሰቦቻቸውም የተዛባ አመለካከት ቁራኛዎች ነበሩ። እሳቸውም ቢሆኑ ከእናቱ ማህፀን ጀምሮ ሁለቱም እጆቹና እግሮቹ የማይንቀሳቀሱ አካል ጉዳተኛ የትዳር አጋር እሆናለሁ የሚል ሀሳብ አልነበራቸውም። ያውም 10 ዓመታትን በመታዘል፣ በሰው ትከሻ ሲንቀሳቀስ የኖረ፤ የሚጎርሰው፤ የሚፀዳዳው፤ የሚለብሰው ሁሉ በሌሎች ድጋፍ የሆነ ሰው ፡፡እሱን አግብቼ ልጅ እወልዳለሁ የሚለው ዕውነት ፈጽሞ ውሳጣቸው አልነበረም።
ለትዳር የመረጡት ሰዉ በተፈጥሮ እጆች የሉትም። በመቀመጫው እየተፏቀቀ በየቤተክርስቲያኑ ቁራሽ የሚናፍቅ፣ በየቡና ቤቱ ደጃፍ እጁን የሚዘረጋ ምጽዋተኛ ነው፡፡የዚህ ሰው ፍቅር የወጣቷን ልብ ገዛ፡፡ጥንዶቹ ውሎ አዳራቸው በአንድ ሆነ።ሌሎች ተገርመው ቢያነውሯቸውም ፈጽሞ ጆሮ አልሰጡም ። ትዳር መሰረቱ፣ ልጅ ወልደው ሳሙ፡፡
አካል ጉዳተኛውን ዮሴፍ በቀለን አባወራቸው ሲያደርጉ ለእንጀራ የመረጡት የሆቴል ስራ ትዳር ጭምር እንደሰጣቸው አይዘነጉትም።በወቅቱ የምግብ ሥራ ባለሙያዋ ወጣት የኔነሽ ለእንግዶች ያዘጋጁትን ምግብ በወጥ ቤቱ መስኮት ለአስተናጋጆች ማቀበል አንዱ ግዴታቸው ነበር። እግረ መንገዳቸውንም በምግብ ቤቱ እልፍኝ የታደሙ ደንበኞችን ቃኘት ማድረግ ልምድ አድርገዋል።
አንድ ቀን ታዲያ እንደወትሮው ዓይናቸውን ጣል ሲደርጉ ከመመገቢያው ሳሎን በአንድ ጥግ ለየት ያለ ጉዳይ ያያሉ። ጠረጴዛው በርከት ባሉ ጎረምሶች ተከቧል። ሁሉም ጉርሻ የጠቀለለ እጃቸውን ወደ አንድ ሰው ሰንዝረዋል። በሳቅና በጫጫታቸው ውስጥ ‹ልታንቁኝ ነው እንዴ የስንታችሁን ልጉረስ ?› የሚል ድምፅ ሰሙ። ተንጠራርተው ተናጋሪውን ሊያዩ ቸኮሉ ፡፡ይህ ሰው የዛሬው ባለቤታቸው አቶ ዮሴፍ በቀለ ናቸው። ጓደኞቻቸው ተራ በተራ የሚያጎርሷቸው እጅ ስሌላቸው መሆኑ የገባቸው ጥቂት ቆይቶ ነበር ። ይህ ብቻ አይደለም ፡፡ሰውየው እግራቸው ጭምር የእንቅስቃሴ ችግር ስላለበት የሚቀመጡት በሌሎች እገዛና በመከራ መሆኑን አስተዋሉ። ሁኔታው ውሰጣቸውን ነካው፣ከልብ አዘኑ ።ዓይናቸው ማረፍ አልቻለም።ይሄንኑ ትዕይንት ሰርክ መከታተል ጀመሩ።ሰውዬው ሁሌም ምግብ ባዘዙ ቁጥር የሚያጎርሳቸው ።የሌላ ሰው እጅ ነው።
በአንድ ዕለት ምሳ ሰአት እንደተለመደው አንገታቸውን በመስኮቱ አስግገው ተመለከቱ።እነዚያ ወጣቶች ከሰውዬው ጎን አልነበሩም። አቶ ዮሴፍ ያዘዙት ምግብ ከፊታቸው ተቀምጧል። ባልንጀሮቻቸው ስለሌሉ የቀረበውን አልነኩትም፡፡የኔነሽ አንገታቸውን ብቅ እያደረጉ ሰዎቹን ጠበቁ፡፤ብቅ ያለ የለም።ምግቡ ሳይበላ ሰዓታት ተቆጠሩ።ዮሴፍ አቀርቅረው በትካዜ ተቀምጠዋል።የኔነሽ ውስጣቸው ተነክቶ ልባቸው ክፉኛ ቢያዝን ከኩሽናው ዞረው ወደ እሳቸው አቀኑ።
ምግቡን እያዩ በትካዜ ወደአቀረቀሩት ሰው ቀርበው ደረሱና ለምን እንደማይበሉ ጠየቋቸው። ውስጣቸው የሚያጎርሳቸው ሰው ያለመኖሩን አሳምሮ ያውቃል፡፡ያም ሆኖ ከሰውየው አንዳች ምላሽ ጠበቁ፡ዮሴፍ ያሰቡትን እውነት ዘርዝረው ነገሯቸው፡፡አጠገባቸው ቁጭ አሉና ፍቃዳቸውን ሳይጠይቁ ያጎርሷቸው ያዙ፡፡አብልተው ውሀ ካስጎጭዋቸው በኋላም ከአጠገባቸው አልራቁም፡፡
የዛን ቀን አቶ ዮሴፍ ቅዱስ ዑራኤል ቤተክስርስቲያን ሄደው የአራት ወር ህፃን ልጅ ጥላባቸው የሞተችውን የቀድሞ ባለቤታቸውን እያስታወሱ ለምን ሲሉ ለፈጣሪያቸው ያለቀሱበትና ከብቸኝነት ኑሮ የምታላቅቅ ውሃ አጣጪ እንዲሰጣቸው የለመኑበት ነበር ።
በጨዋታቸው መሀል የኔነሽ ለምን ሁልጊዜ ሆቴል እንደሚበሉ ጠየቋቸው። ሚስት እንደነበረቻቸው፣ ህፃን ልጅ ጥላባቸው እንደሞተች ነገሯቸው።አሁንም የኔነሽ ዕንባ እያነቃቸው በእጅጉ አዘኑ። ዕለቱን ሲሰነባተቱ ተመልሰው እንደሚመጡ ያውቁ ነበር። ከዛን ቀን ጀምሮ የኔነሽ የዮሴፍ ቀኝ እጅ ሆኑ።ሰርክ ያጎርሷቸው፣ያጠጡዋቸው ጀመር። መላመድና ይበልጥ መግባባት ሲጀምሩ ዘወትር እየመጡ እንዲጫወቱ ይጋብዟቸው ያዙ ።
ዮሴፍ የሚያጎርስ የሚያደምጣቸው አገኙ።በሁለት እግር ለመቆም ያስቻላቸው የቅዱስ ዑራኤል ጸበል፣ በሞት የተለየች የቀድሞ ባለቤታቸው እና ወላጅ እናታቸው መሆናቸውን አጫወቷቸው። የሚተዳደሩትና ቤተሰባቸውን የሚደጉሙት ቤተክርስቲያን ተቀምጠው በሚያገኛት ምፅዋት መሆኑን አልደበቋቸውም።
የኔነሽ ለዮሴፍ ጆሮ ሰጥተው አዳመጧቸው ።ሲወለዱ ሁለቱ እጆችና እግሮቻቸው እንደማይሰሩ፣ መቆም ባለመቻላቸው በሰው ትከሻ ይንቀሳቀሱ እንደነበር፣ እናታቸው፣ ታላቅ እህታቸውና በሕይወት የሌለው ወንድማቸው ለ10 ዓመት ያህል አዝለው ሲያንቀሳቅሷቸው እንደቆዩ ተረኩላቸው። ቅዱስ ዑራኤል ቤተክርስቲያን ግቢ በሚገኘው የቄስ ትምህርት ቤት ከፊደል እስከ ንባብ መማራቸውን ጭምር ነገሯቸው፡፡
ለወይዘሮ የኔነሽ ባለቤታቸው የአራት ወር ህፃን ልጅ ጥላባቸው መሞታቸውን ሲያወሱ ስቅስቅ ብለው እያለቀሱ ነበር። ሟች ሚስታቸው አብሮ አደጋቸውና የሰፈራቸው ልጅ ነበረች። ይህች ሴት ጓደኛቸው ከመሆኗ በፊት እዛው ወላጆቻቸው አጠገብ ያሉ ጎረቤት ለጅ በመሆኗ ሲለምኑ ቆይተው ከምሽቱ አምስትና ስድስት ሰዓት ሲመጡ በሩን የምትከፍትላቸው እሷ ነበረች ። መግባበቱ ሲጨምር ከህመማቸው እንዲፈወሱ በየሳምንቱ ፍልውሃ ይዛቸው ትገባና ታጥባቸው ነበር።ይህ ግንኙነት ቀስ በቀስ ወደ ፍቅር ተቀየረ። ይሄን ያወቁ በርካቶችና ወላጆቿ ለእነሱ የነበራቸው አመለካከት ጥሩ አልሆነም ። የገዛ ወንድሞቿና እህቶቿ ወንድ አጥተሽ ነው ወይ እሱን ያፈቀርሽው በሚል ትችት ይሰነዘሩባት ያዙ።
እሳቸውም ቢሆኑ ስድቡንና ግልምጫቸውን አልቻሉም። በነሱ ፍቅር መንደርተኛው ሁሉ ጉድ ማለቱ አሳቃቃቸው። ሁለቱ ፍቅረኛሞች ከቤተሰብ የሚደርስባቸውን ስድብና ግልምጫ ሲብስባቸው፣ ፈቃደኝነቷን ጠይቀው እሽ ስላለቻቸው ይለይላቸው ብለው ከምፅዋት የሚገኘውን ገቢ ተማምነው ቤት ተከራይተው በመጋባት መኖር ጀመሩ።አንዲት ሴት ልጅም ወለዱ።
በዚህ ወቅት ሕብረተሰቡ የሚያደርስባቸው አሉታዊ ተፅዕኖ ይበልጥ ተባብሶ ቀጠለ ። ፍቅራቸው ሳይቀዘቅዝ፣ ኑሮን መቋቋም ያዙ።በድንገት ግን ባለቤታቸው የአራት ወር ህፃን ጥላባቸው አለፈች።ዮሴፍ ።ሌላው ቀርቶ፣ ጡጦ ለመስጠትና አቅፎ ለመንከባከብ የሚያስችል እጅ ስለሌላቸው በእጅጉ ተቸግረው ቆይተዋል። በዕጣ ፈንታቸውም ለመጀመርያ ጊዜ በእጅጉ ያዘኑበት ወቅት መሆኑን አልሸሸጉም፡፡ይህን ችግር ለማለፍ የወለዷትን ጨቅላ ይዘው፣ ወደ ቤተሰቦቻቸው ቤት ለመመላለስ መገደዳቸውን በዕንባ እየታጠቡ አወጓቸው።
ዮሴፍ የህፃንዋን ወተት ጨምሮ እናታቸውን ለማገዝ ምሽቱን በየቡናቤቱ እየዞሩ ምፅዋት ማሰባሰብ እንደሚጠበቅባቸው አልደበቋቸውም። የተሻለ ገቢ ለማግኘት ባላቸው ጥረትም እስከ ሌሊት የሚዘልቅ ቆይታ ሊገጥማቸው ይችላል ። በዚህ አጋጣሚ በአንድ የበዓል ዋዜማ እስከ ሌሊቱ አስር ሰዓት ቆይተው በር የሚከፍትላቸው እስከማጣት ደርሰዋል፡፡ላለፉት ሦስት ዓመታት ለመግለጽ በሚከብድ ችግር ተዘፍቀው ኑሮን እየገፉ ስለመሆኑ ለየኔነሽ ሲያወጓቸው በትካዜ ተውጠው ሆነ፡፡
የኔነሽ ይህን መሰሉን ታሪክ ሲያደምጡ ውሰጣቸው በተለየ ስሜት ተነካ።ዮሴፍ ወደሆቴሉ ብቅ በሚሉበት አጋጣሚ ሁሉ ከጎናቸው ተቀምጠው ማጉረሱን ስራዬ ብለው ቀጠሉ።ይህ ብቻ አይደለም።ዮሴፍ ባሻቸው ጊዜ እየመጡ እንዲጫወቱ ጭምር ፈቃዳቸውን ሰጡ፡፤መግባባት ፣መቀራረቡ ቀጠለ።መተሳሰቡ ጠነከረ፡፡
የሁለቱ ብርቱ ግንኙነት ለአብሮነት ጋበዛቸው።የኔነሽ ልክ እንቀድሞ ሚስታቸው አጋር ሊሆኑላቸው ቃል ገቡ። የመጀመሪያ ውጥናቸው ቤት ተከራይተው ከሆቴሉ መውጣት ነበር ።አብረው መኖር ሲጀምሩ ሆቴሉ ከችግር ወደቀ ።የባለሙያዋ እጅ ባለመኖሩ በቀድሞው ሁኔታ መቀጠል አልቻለም፡፡ቀስ በቀስ ደንበኞች እየራቁ እስከመዘጋት ደረሰ፡፤ይህኔ የሆቴሉ ባለቤት ተበሳጩ።ለየኔነሽ አለመኖርና ለሆቴሉ መዘጋት ሰበብ የሆኑትን ዮሴፍን ጠሏቸው።ሊገሏቸው ያሳድዷቸው ጀመር።ፈተናው በዛ ።ቤተሰብና ወዳጅ ዘመድ ጋብቻውን ኮነኑት።ሁሉም በትችትና በስድብ አላስቆም አላስቀምጥ አሏቸው፡፡
የዛኔ የኔነሽ የዮሴፍን ህጻን ልጅ ሊያሳድጉ ባመጡ ጊዜ የባለቤታቸው ዘመዶች የተናገሯቸውን ክፉ ቃል ዛሬ ድረስ አይረሱትም።ሰዎቹ የልጅቷንና የባለቤታቸውን ተመሳሳይ እንክብካቤ በእኩል መዝነው ‹‹ ሁለት ህጻናት ማስተዳደር ትችያለሽ ወይ ? ›› ብለዋቸው ነበር፡፡
ህይወት ከባድና ፈታኝ ቢሆንም የኔነሽ ተንገዳግደው አልወደቁም።ህጻንዋ አራት አመት ሳይሞላት ትምህርት ቤት እንድትገባ አደረጉ ።ይህኔ ባለቤታቸው የእጃቸውን ገቢ መዝነው ቄስ ትምህርት ቤት ትግባ ሲሉ ሞገቷቸው ።እሳቸው ግን እኩዮቿ የሚማሩበት የግል ትምህርትቤት ትዝለቅ በሚል አቋማቸው ጸኑ።በወቅቱ ‹‹ልጅቱን አስመዝግበው ሲመለሱ መንገድ ላይ ከባለቤታቸው ተጨቃጭቀዋል። ‹‹ብሩ ከየት ይመጣል ሲሉ ተጣልተዋቸዋል።በእርግጥ በጊዜው ምንም ገቢ ለሌላቸው ባልና ሚስት ለግል ትምህርት ቤት በየወሩ 80 ብር መክፈል ይከብዳል። ወይዘሮ የኔ ነሽ ልጅቱን ትምህርት ቤት ያስገቧት ግን ባለቤታቸውን ከመንከባከብ ባሻገር በወር አንዴም ቢሆን የድግስና የሆቴል ምግብ አዘጋጅተው በሚያገኙት ገቢ ክፍያውን እሸፍናለሁ በሚል ነበር።
እሳቸው ይህን ቢያስቡም ሁኔታዎች አልተቃኑም። ባለቤታቸውን ከማፀዳዳት ጀምሮ አስከማልበስ፣ የቤት ስራውን ሸፍኖ ከጎን ሆኖ እስከመደገፍ፣ ሲወጡና ሲገቡ በር ከፍቶ አስከመዝጋት ያለውን ግዴታ የሚሸከመው የእሳቸው ጫንቃ ብቻ ነበር። ጊዜ ተረፏቸው እንዳሰቡት በሥራ አልዋሉም ።
የወይዘሮ የኔነሽ ቅንነት ግን ብቻውን አልቀረም።ውሎ አድሮ የአንድ ወንድና የአንዲት ሴት ልጅ እናት ለመሆን በቁ።አካል ጉዳተኛ በመሆናቸው የተነወሩባቸው ባለቤታቸውም የሦስት ልጆች አባት ሆነው ሙሉነታቸውን አስመሰከሩ፡፡
ያለፈው ትናንት በዛሬ …
እነሆ! ዛሬ የትናንቱ ታሪክ በዛሬው እውነት ተሽሯል።በአራት ወሯ እናቷን በሞት ያጣችው የዛኔዋን ህጻን ጨምሮ አንደኛው ልጃቸው በወጉ ተምረው በዲግሪ ተመርቀዋል። ይህ ብቻ አይደለም፡፡ባለቤታቸው አቶ ዮሴፍ በውስጣቸው የኖረውን የስዕል ችሎታ የሚያሳዩበት ጊዜው ደርሷል፡፡እ ጅ ባይኖራቸውም በአፋቸው የሚስሏቸው ድንቅ ስዕሎች ባክነው አልቀሩም፡፡
ባለቤታቸው የኔነሽ ለሙያቸው ትኩረት ሰጥተው ባደረጉት ጥረት ሙያቸውን የሚያስመሰክሩበትን ዕድል አመቻችተዋል።ዛሬ ዮሴፍ በስነ-ስዕል የዲፕሎማ ተመራቂ ሆነዋል ።ትናንት ከልመናና ከምጽዋተኝነት ታሪክ ተሻግሮ ዛሬ ላይ ለደረሰው ህይወት መሰረቱ የብርቱዋ ሴት የማይላላ ጥንካሬ ነው።አሁንም ይህች መልካም ሴት ለባሏ ዘውድ የመሆኗ እውነት አልተሻረም።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2014