ዘመን አይሽሬው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት፤
የዓለም ሀገራትን ለዘርፈ ብዙ የጋራ ጥቅምና ለማሕበራዊ መስተጋብር ከሚያገናኙ ዕድሜ ጠገብ መድረኮች መካከል አንዱ የሕዝብ ለሕዝብ ዲፕሎማሲ በቀዳሚነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ ሺህ ዘመናት የተቆጠረለት ይህን መሰሉ “የሰላም ማብሰሪያ ግንኙነት” የሩቅና የቅርብ ሕዝቦችን ከማቀራረብ አልፎ ተርፎ በብዙ በጎ ጉዳዮች ያቆራኘ “በረከት” ጭምር እንደሆነ በስፋት ይታመናል፡፡ የጂኦግራፊ ርቀትና ቅርበት፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት ልዩነት፣ የኢኮኖሚ ከፍታና ዝቅታ ለሕዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት ከቶውንም ቢሆን መሰናክልም ሆነ ገደብ የመጣል ብርታት የላቸውም፡፡ ምክንያቱም ተፈጥሯዊ ስለሆነ፡፡
በዚህ “ዘመናዊ ዓለምም” ቢሆን መደበኛውን የመንግሥት ዲፕሎማሲ ማገዝ ብቻም ሳይሆን ፍሬያማነቱ እጅግ ልቆ የሚነገርለት ይህን መሰሉ ሕዝባዊ ተልዕኮ (Publice Diplomacy) በተደራጀና ተገቢውን ተቋማዊ ቅርጽ ይዞ በሀገራችን መተግበር የጀመረው ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ነው፡፡ “ጥንት ጥንት” የሚባለው ዕድሜው የሚጠቀስለት በኢመደበኛ ባህርይው እንጂ ለመደበኛ “ተጽእኖ ፈጣሪነቱ” ሀገራችን ተቋም ፈጥራለት ተገቢው እውቅና መስጠት የተጀመረው በዋነኛነት የታላቁ ህዳሴ ግድባችን የግንባታ ዜና ከተበሰረ በኋላ ነበር፡፡
ዜናው ተበስሮ የግንባታው እንቅስቃሴ ወደ ሥራ ከተገባበት ጊዜ ጀምሮ በሕዝባችን ዘንድ የተፈጠረውን ደስታ፣ ሁሉን አቀፍ ያልተቆጠበ ተሳትፎና ድጋፍ በተመለከተ ምሳሌነቱን ለወደፊቱ የዓለም ታሪክ ተገቢውን አክብሮት በመስጠት “በወርቅ ቀለም” ከትቦና ሰንዶ እንደሚያስቀምጠው ለመገመት አይከብድም፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድባችን ለእኛ ለባለጉዳዮቹ “የእያንዳንዱ ዜጋ አሻራ የታተመበት” የደስታና የሃሴት ምንጭ፤ “ለተቀናቃኞቻችንና” ለበርካታ የዓለም መንግሥታት ደግሞ የጀርባ ሴራ መጎንጎኛና መነጋገሪያ ዋና አጀንዳ ስለምን ሆነ ብለን መጠየቁ አስፈላጊ የማይሆነው መልሱ ለማንኛውም ባለሀገርም ይሁን ባእድ እንግዳ ስለማይሆን ነው፡፡
የአባይ ወንዝ ፖለቲካ መጦዝ የጀመረው በዚህ በእኛ ዘመን ብቻም አይደለም፡፡ የውሃዎቻችን ጌቶች እንዳንሆን፤ በተለይም አባይ ወንዛችንን ጥቅም ላይ ማዋል እንዳንችል የብዙ ጦርነት ወዳድ ሀገራት “የእብሪት ክንድ” እየተደጋገመ ሲሰነዘርብን ኖሯል፡፡ በጥቋቁር ሰንዱቆች ውስጥ የቆለፍንባቸው አብዛኞቹ የውጭ ባእዳን የወረራ ታሪኮች መንስዔያቸው በዋነኛነት ቢመረመር ሰበቡ የአባይ ወንዛችንን እንዳናለማ እና በተፈጥሮ ሀብታችን እንዳንጠቀም ለማንበርከክ ታስቦ መሆኑ ለጥርጥር አይጋብዝም፡፡ “ውሃ” ብለው የመጡ ወራሪዎች “ውሃ ውሃ” እያሉ የተመለሱትና እንደ ፈሰሰ ውሃ ላይታፈሱ ከንቱ ሆነው የቀሩት በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ክንድ ደቀውና ተዋርደው ስለመሆኑ ደጋግሞ ስለተጻፈ ደግመን በዚህ ጽሑፍ በዝርዝር አናስታውሰውም፡፡
የአባይ ወንዛችንን በተመለከተ በዘመናት ውስጥ ሀገራችን እምነቷን ስታስተጋባ የኖረችው “በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመሥርተን ውሃችንን ለልማት እናውለው” እንጂ “ከራሴ ማህጸን የሚፈልቀውን ፀጋ ለብቻዬ እጠቀምበታለሁ” በሚል ግትርነት እንዳልሆነ እንኳን ወዳጆቻችን ጠላቶቻችንም አይጠፋቸውም፡፡
እስከ ዛሬ ድረስ ሀገራችን ካከናወነቻቸው እጅግ አሰልቺና ውጤታማ የመደበኛ ዲፕሎማሲ ሥራዎች መካከል በአባይ ወንዝ አጠቃቀምና በህዳሴ ግድባችን ዙሪያ የደከመችበት አታካችና እልህ አስጨራሽ ጥረት በምንም መመዘኛ ቢለካ ወደርም ሆነ መጠን ያለው አይመስልም፡፡ አብዛኞቹ የዓለም ታላላቅ የሚዲያ ተቋማትም እንዲሁ የአባይን ወንዝና ይሄንንው “የብርሃን ተስፋችንን” ማዕከላዊ ጉዳይ በማድረግ የሰሩትን ዜናና ዘገባ ያህልም በሌሎች ጉዳዮች ላይ ስለማተኮራቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ እንደዚያም ቢሆን ግን ኢትዮጵያ የሰላማዊ የዲፕሎማሲ መርሆዋን ሳትለቅ በእውነቷና በእምነቷ እንደፀናች አለች፡፡ በዚህ ጽሐፍ ለመዳሰስ የሚሞከረውም ከመደበኛው ዲፕሎማሲ ጎን ለጎን የተካሄደውን አስመስጋኝ የሀገራችንን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጥረት ይሆናል፡፡
“ልበ ሰፊዋ ሀገሬ” የታሪካዊ ጠላቶቿንና ወደረኞቿን “ዛቻና የእጅ አዙር ዘመቻ” ለመመከት እየተጋች ያለችው በመደበኛ የዲፕሎማሲ አሰራሯ ብቻ አልነበርም፡፡ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ዜጎቿን ይወክላሉ በማለት ከተለያዩ የሙያ ዘርፎችና አደረጃጀቶች ባዋቀረችው ገለልተኛ የሕዝብ ተወካዮች የልዑካን ቡድን (ፐብሊክ ዲፕሎማሲ) አማካይነትም ጭምር እንጂ፡፡
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የተቋቋመው የህዳሴ ግድባችን መሠረት በተጣለበት ማግሥት ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስም በቀላሉ ሊታዩ የማይገባቸው ተልዕኮዎች በስፋት ተካሂደዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የመጀመሪያ ጉዞውን ያደረገው በ2007 ዓ.ም ወደ ግብጽ ካይሮ ነበር፡፡ ይዞት የሄደው የሀገር መልእክትም አጭርና ግልጽ ነበር፤ “በአባይ ወንዛችን ላይ እየተገነባ ያለው የታላቁ ህዳሴ ግድባችን የታችኛውን የናይል ተፋሰስ ሀገራት በምንም መልኩ የሚጎዳ አይደለም፡፡ መርሁ የጋራ ተጠቃሚነትን (win win strategy) የሚያከብር እንጂ በፍጹም የትኛውንም የተፋሰሱን ሀገር የሚጎዳ እንዳልሆነ በሕዝብ ስም እናረጋግጣለን” የሚል ነበር፡፡
ይህ መልእክት በቅድሚያ የደረሰው ለክቡር የግብጽ ፕሬዚዳንት አብድል ፈታህ ኤል ሲሲ ነበር፡፡ ክቡርነታቸውም በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም በቤተመንግሥታቸው ተገኝቶ ቡድኑ ያቀረበላቸው መልእክት “የአባይ ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ የማይናወጥና የህዳሴ ግድቡም ቢሆን በፍጹም በተፈጥሯዊ የውሃ ድርሻቸው ላይ ተጽእኖ እንደማይኖረው” በማረጋገጥ ሲሆን፤ ፕሬዚዳንቱም መልእክቱን በደስታና በአክብሮት መቀበል ብቻም ሳይሆን “መርሁ እንዳይሸረሸር ለላካችሁ መንግሥታችሁና ሕዝባችሁ አደራውን አስተላልፉን” በማለት ነበር፡፡
ለክቡር ፕሬዚዳንቱ ብቻም ሳይሆን ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎድሮስ ዳግማዊ በኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የእስክንድርያ ፖፕ እና ፓትርያርክ ዘመንበረ ማርቆስ በጽ/ቤታቸው በመገኘት ተመሳሳይ መልእክት አቅርቦላቸዋል፡፡ በተከታታይ ቀናትም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና ለውሃ ሚኒስትሩ፣ ለግብጽ ምሁራንና በእረፍት ላይ ለሚገኙ የሀገሪቱ ዲፕሎማቶች (retired diplomats) እና ለበርካታ የማሕበረሰብ ተወካዮች የማያወላውለው የኢትዮጵያ አቋም በሚገባ ተገልጾላቸዋል፡፡
የግብጽ ጉዞ ከተከናወነ ከጥቂት ወራት በኋላ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ክቡር አብድል ፈታህ ኤል ሲሲ ለአፍሪካ ሕብረት ስብሰባ አዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት የመጀመሪያ ሥራቸው ያደረጉት የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድንን በሸራተን ሆቴል አግኝተው የማይናወጠውን የኢትዮጵያን አቋምና መልእክት ቡድኑ በሀገራቸው ተገኝቶ ስላቀረበላቸው ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን በተመሳሳይ ዓመት በሱዳን ሪፐብሊክ፣ በ2012 ዓ.ም ደግሞ በዩጋንዳ ሪፐብሊክ በመገኘት ለርዕሳነ ብሔሮቹ፣ ለሚኒስትሮች፣ ለሕዝብ ተወካዮችና ለየሀገራቱ ምሁራንና በተጽእኖ ፈጣሪነታቸው ለሚታወቁ ዜጎች ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ አጠቃቀምና በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የምታራምደውን የጋራ ተጠቃሚነት የፀና አቋም በሚገባ ለማስረዳት ተሞክሯል፡፡
የልዑካን ቡድኑ ተልዕኮ ያተኮረው በአባይ ተፋሰስ ሀገራት ብቻ አልነበረም፡፡ በጂቡቲና በኤርትራ ሀገራት በመገኘትም ከሁለቱ ሀገራት ጋር ያለው ጠንካራ ጉርብትናና ወዳጅነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለመንግሥታቱ መሪዎችና ለሚመለከታቸው ተቋማት መሪዎች ሕዝባዊ መተማመኛውን በታላቅ አክብሮትን በግልጽ ቋንቋ አስረድቷል፡፡ በመደበኛው የዲፕሎማሲ አሰራርና በፐብሊክ ዲፕሎማሲ አማካይነት የተከናወነው ይህን መሰሉ ጥረት በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን ሀገራችን ለሰላማዊ ጉርብትናና ለጋራ ተጠቃሚነት መርህ ምን ያህል የማይናወጥ አቋም እንዳላት ጥሩ ማሳያ ሊሆን የሚችልና የሚያስመሰግን ተግባር ነው፡፡
በመሠረቱ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ ተቋማዊ ሆኖ በአንድ አቅጣጫ ብቻ የተቃኘ ሳይሆን በርካታ መንገዶች ስላሉት ሀገራችን በአግባቡ ብትጠቀምበት ብዙ ልታተርፍበት ትችላለች፡፡ ለምሳሌ፡- በስፖርት አደባባዮች ጀግኖቹ ባለ ድል አትሌቶቻችን የሀገራቸው ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብና ስሟ በክብር እንዲጠራ ማድረጋቸው ከሚያገኙት ሜዳሊያና ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞች በዘለለ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ትሩፋቱ ከፍ ያለ ነው፡፡ በእነዚህ መሰል መድረኮች የኢትዮጵያን የሰላም ፈላጊነት መርህ፣ የገለልተኛነት አቋምና ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ ተባብሮ ለማደግ ያላትን ጽኑ ፍላጎትና አቋም የስፖርቱን መርህ በማይጻረር መልኩ መግለጽና ማስተዋወቅ ቢቻል የሚገኘው ውጤት በቀላሉ የሚገመት አይሆንም፡፡
በኪነ ጥበባት ዘርፎች፣ በንግድ እንቅስቃሴና በሃይማኖታዊ ጉዞ ወዘተ. በመሳሰሉት ተሳትፎዎች ዜጎች በግልም ሆነ በቡድን ተደራጅተው ወደ ተለያዩ ሀገራት ሲጓዙ ሀገራቸውን ለማስተዋወቅ እንዲችሉ ልዩ ድጋፍና ግልጽ ተልዕኮ ቢሰጣቸው ውጤታማ ሥራ ሊሰሩ እንደሚችሉ ይታመናል፡፡
ይህ ጸሐፊ የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባል ሆኖ በተገኘባቸው በርካታ ሀገራት የተገነዘበው ዋነኛ ጉዳይ ቀደም ካለው ዘመን ጀምሮ ሀገራችን አገልግሎቱን አጠናክራ ባለመያዟ ብዙ እድሎች እንዳመለጧት ለመረዳት አላዳገተውም፡፡ በዋነኛነት ግብጽ ለዚህን መሰሉ ጉዳይ ትጉህ ስትሆን ሱዳንን የመሳሰሉ ጎረቤት ሀገራት ደግሞ ተጽእኖ ፈጣሪ ዜጎቻቸውን በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኖች በማደራጀት ጠንካራ ሥራዎችን ለመሥራት ሲሞክሩ እያስተዋልን ነው፡፡ የሁለቱ ሀገራት መሰል ብድኖች ኢትዮጵያ ውስጥ መምጣታቸውም አይዘነጋም፡፡
ወቅቱና ዘመኑ ከመደበኛው ዲፕሎማሲ ባልተናነሰ መልኩ የዜጋ ተኮር ሚሽን እጅግ ውጤታማ ፍሬ እየተስተዋለበት መሆኑን መንግሥታት በሚገባ ተረድተውታል፡፡ በተለይም እኛን መሰል “ለብዙ ጥቃቶች ጥርስ ለገባ ሀገር” የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አገልግሎት ተጠናክሮ መቀጠሉ ጊዜም ሆነ ቀጠሮ ሊሰጠው የሚገባ ሀገራዊ ጉዳይ አይደለም፡፡ በቅርቡ በጥቂት የሀገራችን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እየተጣለ ያለው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ መሠረት እጅግ ተጠናክሮና በኔት ዎርክ ተሳስሮ በጋራ መንቀሳቀስ ቢቻል ለሀገር የሚጠቅሙ በርካታ ውጤቶችን ማስመዝገብ ይቻላል፡፡
በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ላይ በግላቸው ሀገራቸውን ወክለው ከምሁራን ጋር ሙግትና ክርክር በማድረግ የዜግነት ድርሻቸውን እየተወጡ ያሉ ግለሰቦችም በአንድ ጥላ ሥር በቡድን ተሰባስበው በጋራ መመሥረት ቢችሉ ይበልጥ ፍሬያማ ውጤቶች ሊዘመርበት እንደሚችል ለማመን አይከብድም፡፡
በቅርቡ የተጠናቀቀው የሦስተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና የሁለተኛው ተርባይን ሥራ መጀመር በወደረኞቻችንና ከእነርሱ ጀርባ “አለንላችሁ” በሚሏቸው ታላላቅ ሚዲያዎች ሳይቀር ምን ያህል መንጫጫት እያስከተለ እንዳለ የምናየው ነው፡፡ በተለይም ከእውነት ባፈነገጠ እምነት “አባይ የሚመነጨው ከግብጽ ተራሮች ላይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እየሠራች ያለችው ይህንን ተፈጥሯዊ ፀጋችንን ልታጎድልብን ነው” እየተባሉ በሀሰት ትርክት የተሞሉትን የዋህ የግብጽ ዜጎች ከስህተታቸው ማረምና እውነቱን ማሳየት የሚቻለው ጠንካራ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራዎችን በመሥራት ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ ደራስያን ማሕበር ሃምሳኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር ከጋበዛቸው ዓለም አቀፍ እውቅና ካተረፉ ደራስያንና ደራሲያት መካከል አንዷ የግብፅ ደራስያንን ወክለው የተገኙት ዶ/ር ኢክባል ባራካ ነበሩ፡፡ እኚህ በሀገራቸውና በአረቡ ዓለም ዘርፈ ብዙ ዝናን የተጎናጸፉት ደራሲትና ጋዜጠኛ ኢትዮጵያ በተገኙበት ወቅት የተመለሱት አዲስ አበባን ረግጠው ብቻም ሳይሆን በርቀት የሚያውቁትን የአባይን ወንዝ “በኢትዮጵያዊ ጠረንነቱ በአካል ተገኝተው እንዲያሸቱት” ወደ ጎጃምና ጎንደር ጉዞ ተመቻችቶላቸው ነበር፡፡ ከእርሳቸው ጋርም ስድስት የሱዳን ደራስያንና አንድ የሊቢያ ደራሲ እንዲገኙ ተደርጓል፡፡
ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ ከተመለሰ በኋላ ስለ አባይ ወንዝና ስለ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በነበረ ውይይት ላይ በተለይም ዶ/ር ኢክባል በተሳሳተ መረጃ ሀገራቸው ግብጽ ሕዝቧንና ታዳጊ ልጆቿን “አባይ የሚመነጨው ከግብጽ ተራሮች ላይ ነው” የሚለውን የውሸት ትርክት በመጥቀስ የደራስያን ማሕበሩን አመራር ይቅርታ ጠይቀው ነበር፡፡
እኒሁ የተከበሩ ደራሲት የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ግብጽ በተገኘበት ወቅት በአንድ የምሁራን ጉባዔ ላይ ተገኝተው “የግብጽ ምሁራን፣ ዲፕሎማቶቻችንና ሚዲያው በውሸት ትርክት ‹የናይል ወንዝ የሚመነጨው ከግብጽ ተራሮች ላይ ነው› በማለት ለዘመናት ሲያደናግሩን መኖራቸው ውሸት ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿን ጥቅም ሳትነካ ከራሷ ምድር የሚመነጨውን የናይል ወንዝ ለሕዝቦቿ ጥቅም እንደፈለገች ማዋሏ መብቷ ነው፡፡” በማለት የመሰከሩት በአደባባይና በይፋ ነበር፡፡
እንዲያውም ተሰብሳቢውን ፈገግ ለማስደረግ የሞከሩት “እባካችሁ በግብጽ የኢትዮጵያ አምባሳደር አድርጋችሁ ሹሙኝ” በማለት ጭምር ነበር፡፡ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አገልግሎት በምርጫ የሚደረግ ሳይሆን ዘመኑ ግድ ስለሚል ነው፡፡ ይህ አሰራር የሕዝብ ለሕዝብ ማቀራረቢያ አንዱና ዋነኛ መንገድ ስለሆነ ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ የጀመረችውን ሥራ አጠናክራ ልትቀጥል ይገባል፡፡ ኃላፊነቱን ወስዶ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑን ላደራጀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ከፍተኛ አመራሮች ይህ ጸሐፊ የአደራ መልእክቱን የሚያስተላልፈው በቆይ ብቻ ዝንጋዬ ይህ ታላቅ አገልግሎት ቸል እንዳይባልና ተጠናክሮ እንዲቀጥል ነው፡፡ ሰላም ይሁን!
በ(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 14 /2014