አዲስ አበባ፡- በቀጣይ ጊዜያት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የነበረውን ህዝባዊ ድጋፍና አመኔታ ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት እንደሚከናወኑ የፕሮጀክቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሎ ሆሮ ተናገሩ።
ኢንጂነር ክፍሌ፣ የፕሮጀክቱን ስምንተኛ ዓመት አስመልክቶ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባዳረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ የህዳሴው ግድብ የህዝቡ የዘመናት ህልም እውን የሆነበት እንደመሆኑ በታላቅ ደስታና ሞራል ሲደግፈውና መጠናቀቁንም በተስፋ ሲጠባበቅ ቆይቷል። ይሁን እንጂ በመካከል የተፈጠሩ ችግሮች የህዝቡን አመኔታ በመሸርሸር ቅሬታንም ፈጥረውበታል። በመሆኑም በቀጣይ ጊዜያት ይሄን የህዝብ ድጋፍና አመኔታ ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን ተዘጋጅተዋል።
እንደ ኢንጂነር ክፍሌ ገለጻ፤ የህዝቡ አመኔታ የታጣበት አንዱ ምክንያት ፕሮጀክቱ ይደርሳል በተባለበት ጊዜ አለመድረሱ ሲሆን፤ ይሄን በተመለከተም ሆነ በግድቡ ዙሪያ የነበሩ ችግሮችን አስመልክቶ ለህብረተሰቡ ትክክለኛ መረጃ አለመድረሱ ለህዝቡ አመኔታ መሸርሸር እንደምክንያት ይጠቀሳል። ምክንያቱም ግድቡ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ የቆየ ቢሆንም ይሄ መረጃ ተደብቆ፤ ያልተሠራውን እንደተሠራ፤ ሊደርስ ያልቻለውን እንደደረሰ፤ ተደርጎ ለህዝብ ሲገለጽ ነበር።
በመጨረሻ ላይ እውነቱ በሚታወቅበት ጊዜ ህዝቡንም መንግሥትንም አስቆጥቷል። በመሆኑም በቀጣይ የህዝቡን አመኔታ ለመመለስ ለህዝቡ ትክክለኛ መረጃ ከማድረስ ጀምሮ የሚሠራ ሲሆን፤ ሥራውም ተሠርቶ በዓይኑ እንዲያይ በማድረግ አመኔታውን ለመመለስ በትኩረት የሚሠራ ይሆናል።
እንደ ኢንጂነር ክፍሌ ማብራሪያ፤ አሁን ያለው መቀዛቀዝ በግድቡ ዙሪያ የተስተዋሉ የአሠራርና ተያያዥ ችግሮችን ለማረምና ግድቡ ያለምንም የጥራት ችግር ለትውልድ የሚተላለፍ ሆኖ በሚጠናቀቅበት አግባብ ለማከናወን የሚያስችሉ የእርምት ዕርምጃዎችን ለመውሰድ
እንጂ ግድቡን ለማጓተት ወይም እንዲቆም ለማድረግ አይደለም። ባለው ሁኔታም ችግሮቹን ከመለየት አልፎ የእርምት ዕርምጃዎች ተወስደው ወደ ሥራ እየተገባ ሲሆን፤ በቅርቡም በሙሉ አቅም ግንባታው መካሄድ ይጀምራል። ሂደቱም ህዝቡ ውስጥ የነበረውን ጥርጣሬ በሚያስወግድና አመኔታውን ለመመለስ በሚያስችል መልኩ ይከናወናል።
ችግሮች እንዳሉ በተገለጸበት ሁኔታ እንኳን የህዝቡ ድጋፍ አለመቋረጡን የገለጹት ኢንጂነር ክፍሌ፤ ይሁን እንጂ በቦንድ ግዢ የሚገለጹ ድጋፎችን በተመለከተም ሆነ ተስፋ ከማድረግ ጋር በተያያዘ የተወሰኑ መቀዛቀዞች መኖራቸውን መረጃዎች እንደሚያሳዩ ጠቁመዋል። በመሆኑም እነዚህን መቀዛቀዞች ለመሻርና ህዝቡ እንደ ቀድሞው ግድቡን በሙሉ ልብና ፍላጎት እንዲደግፍ ለማስቻል ከቃል ጀምሮ እስከ ተግባር የሚገለጹ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አብራርተዋል። በእነዚህ ሂደቶችም የመገናኛ ብዙሃን በቦታው እየተገኙ እንዲዘግቡና ህብረተሰቡ ተገቢውን መረጃ እንዲያገኝ እንደሚደረግ፤ ህዝቡም ግድቡ ድረስ በመሄድ የሚያረጋግጡበት ዕድል እንደሚመቻች ገልጸዋል።
አዲሰ ዘመን መጋቢት 23/2011
ወንድወሰን ሽመልስ