የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት አምስተኛ ዙር አራተኛ ዓመት ስምንተኛ መደበኛ ጉባኤ ከጥቅምት 20 እስከ 24 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደበት ወቅት የክልሉ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የ2008 /9 በጀት ዓመት የፋይናንሺያልና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት በክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ቀርቧል፡፡ በጉባኤው የቀረበውን የኦዲት ሪፖርት መነሻ በማድረግ ከክልሉ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ዋና ኦዲተር አቶ ተስፋዬ ታፈሰ ጋር አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቆይታ አድርጓል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቅርቡ የ2008 /2009 ኦዲት ሪፖርትን ለክልሉ ምክር ቤት አቅርባችኋል፡፡ ከቅርበት አንፃር በ2011 ዓ.ም መቅረብ የነበረበት የ2010 በጀት ዓመት ሪፖርት መሆን አልነበረበትም?
አቶ ተስፋዬ፡- ለምክር ቤቱ የ2008 /2009 የፋይናንስና ሕጋዊነት እንዲሁም የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ነበር የቀረበው፡፡ የ2010 በጀት ዓመት የኦዲት ሪፖርት የሚጠቃለለው በ2011 ዓ.ም ከጥር ወር በኋላ ስለሆነ በቀጣይ ነው የሚቀርበው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሪፖርታችሁ መጀመሪያ ላይ የጥሬ ገንዘብ ጉድለትን የሚመለከቱ ጉዳዮች ተጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ረገድ የኦዲት ግኝታችሁ ምን ያሳያል?
አቶ ተስፋዬ፡- የፋይናንስና ሕጋዊነት ኦዲት ካካሄድንባቸው መሥሪያ ቤቶች የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት ሕጉን የተከተሉ መሆኑን ለማረጋገጥ ባደረግነው ኦዲት ስምንት መሥሪያ ቤቶች የጥሬ ገንዘብ አያያዛቸው ላይ ጉድለት መኖሩን አረጋግጠናል፡፡ በእነዚህ መሥሪያ ቤቶች 275 ሺ 49 ብር የጥሬ ገንዘብ ጉድለት ተገኝቷል፡፡ የክልሉ ዲዛይንና ግንባታ ቁጥጥር ድርጅት 155 ሺ 316 ብር፤ የክልሉ የውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት 67 ሺ 87 ብር በማጉደል ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኦዲት በተደረገበት ዓመት በሂሳብ መግለጫ ሪፖርትና በቆጠራ በተገኘው ጥሬ ገንዘብ መካከል ልዩነት መታየቱ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ቢያብራሩልኝ ?
አቶ ተስፋዬ፡- በክልሉ የፋይናንስ አስተዳደር ሕግ መሰረት በተቋማት ያለው የገንዘብ መጠን በየወቅቱ ይቆጠራል፡፡ በቆጠራ ሪፖርትና በሂሳብ መግለጫዎች ላይ የሚሰፍረው አሃዝ እኩል መሆን አለበት፡፡ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ በሂሳብ መግለጫ ሪፖርት የተደረገውና በቆጠራ በተገኘው ገንዘብ መካከል በ59 መሥሪያ ቤቶች 42 ሚሊዮን 284 ሺ 908 ብር በማነስ ታይቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህ ለምዝበራ አያጋልጥም?
አቶ ተስፋዬ፡- የቆጠራና የሂሳብ መግለጫ በመለያየቱ የተለያዩ ግምቶች ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡ አንደኛው አንተም እንዳነሳኸው ለምዝበራ ሊያጋልጥ ይችላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃም ትክክለኛ የገንዘብ አስተዳደር ሥርዓት መግለጫው እንዳይታወቅ ያደርጋል፡፡ ትክክለኛው የሂሳብ መግለጫው ነው ወይስ የቆጠራ ሪፖርቱ ? የሚለውን መረጃ የሚፈልግ ሰው በአግባቡ እንዳይገነዘብም ያደርጋል፡፡ ይህ ችግር የታየባቸው መሥሪያ ቤቶች በአስቸኳይ ችግሩን አርመው የተከሰተበትን ምክንያት እንዲያቀርቡ በኦዲት ሪፖርቱ አስተያየት ተሰጥቷቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኦዲት ግኝታችሁ የውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብን በተመለከተ የተጠቀሱ ችግሮች አሉ፤ ያጋጠመው ጉድለት ምንድን ነው?
አቶ ተስፋዬ፡- የመንግሥት ገንዘብ ለሥራ ሲወጣ አግባብነት ያላቸው መረጃዎች ቀርበው ሂሳቡ መወራረድ መቻል አለበት፡፡ በ133 መሥሪያ ቤቶች ላይ በወቅቱ መወራረድ ሲገባው ያልተወራረደ 629 ሚሊዮን 982 ሺ ብር አግኝተናል፡፡ ሥራ ያልተሠራበትም ካለ ተለይቶ ወደ መንግሥት ካዝና መመለስ አለበት፡፡ ሥራ ተሠርቶም ከሆነ መረጃዎች ቀርበው መወራረድ አለባቸው፡፡ ሥራ ተሠርቷል ተብሎ መረጃ ቀርቦለት በወጪ ማስረጃ አልተደገፈም፡፡ አንዳንዶቹ ተሰብሳቢዎች ረጅም ጊዜ ያስቆጠሩ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የመጥፋት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ፣ ከተማ ልማትና ቤቶች ቢሮና ፖሊስ ኮሚሽን ማወራረድ ሲገባቸው ካላወራርዱ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ መሥሪያ ቤቶች መረጃ አቅርበው ሂሳብ ማወራረድ አለባቸው፡፡ ማወራረድ የማይችሉ ከሆነ የመንግሥትን ገንዘብ ከግለሰቦችና ድርጅቶች መሰብሰብ እንዳለባቸው በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኦዲት ሪፖርት በየዓመቱ ለምክር ቤቱ ይቀርባል፤ ለረጅም ጊዜ ሂሳብ ሳያወራርዱ የቆዩ ተቋማት የሚሰጡት ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ ተስፋዬ፡- በእኛ እምነት እንዳይወራረድ የሚከለክል መሰረታዊ የሆነ ምክንያት የለም፡፡ ተቋማቱ በየጊዜው የሚያቀርቧቸው ምክንያቶች አሳማኝ ናቸው ብለን አንወስድም፡፡ ይልቅስ ለጉዳዩ የሰጡት ትኩረት በቂ አለመሆኑን ነው የሚያሳየው፡፡ እኛ ግን ምክር ቤቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እርምጃ የሚወሰድባቸውን አቅጣጫዎች ጭምር አቅርበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አዲስ የሚመጡ አመራሮች በሚመደቡበት ወቅት በፊት በነበሩት የተፈጠረ ችግር ነው የሚል ምክንያት እየቀረበ ሂሳብ ለማወራረድ እክል የሚፈጠርበት ሁኔታ አያጋጥምም ? የአመራሮች መለዋወጥ ጫና ይፈጥር ይሆን?
አቶ ተስፋዬ፡- ትክክል ነው ይፈጥራል፡፡ አልፎ አልፎ በዚህ ወቅት እኔ አልነበርኩኝም፤ ይህን መረጃ በቅርበት ማግኘት አልቻልኩም፤ ይህን የሠሩ ባለሙያዎች አሁን የሉም የሚሉ ነገሮች ይነሳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ተጠያቂነት እንዲላላ ከማድረጉም ባሻገር ገንዘቡንም ለብክነት ይዳርጋል፡፡ ዞሮ ዞሮ የመንግሥት ገንዘብ የሚከፈለው በማስረጃ ስለሆነ የሰነድ ማስረጃዎች በዚያ ተቋም ውስጥ አሉ፡፡
ኦዲቱም ‹‹ይህን ያህል አለ›› የሚለው የሰነድ ማስረጃዎችን መነሻ አድርጎ ነው፡፡ ስለዚህ ትናንት የነበሩ ባለሙያዎችና ኃላፊዎች አሁን ባይኖሩም አዲሱ አመራር የሰነድና የኦዲት መረጃዎችን መሰረት አድርጎ ማየት እንዳለበት ነው የምናምነው፤ አሠራሩም ይኸው ነው፡፡ በዚያ መንገድ ካልታየ ሰው የደረሰበትን ብቻ የሚያይ ከሆነና የትናንቱን ከተዘለለ ተቋማት ትልቅ ችግር ውስጥ ይገባሉ፡፡ የሰነድና የኦዲት መረጃ አለ፤ እነዚህን መሰረት አድርገው ተቋማትን መከታተልና መረጃዎቹ ከሚጠቅሷቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች ማስመለስ አለባቸው የሚል እምነት አለን፡፡
አዲስ ዘመን፡- በኦዲት ሪፖርቱ የገቢ አሰባሰብን በተመለከተ ከሥራ ግብርና ከሌሎች ግብሮች ጋር ተያይዞ የሚነሱ ችግሮች መኖራቸው ተመላክቷል፡፡ ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ግኝቶች ቢያብራሩልኝ?
አቶ ተስፋዬ፡- የገቢ አሰባሰብን በሚመለከት ኦዲት እናደርጋለን፡፡ ከዚህ አንፃር በግብር ሕጉ አሠራሮችና መመሪያዎች መሰረት የተፈፀመ መሆኑን ኦዲት በምናደርግበት ወቅት የተለያዩ ጉድለቶች ተገኝተዋል፡፡ ለመጥቀስ ያህል ከሠራተኞች ደመወዝ መቀነስ የሚገባው ግብር ያልተቀነሰባቸው ተቋማት መኖራቸውን አይተናል፡፡ ግብርን አሳንሶ የመወሰን፤ ለገቢ ሂሳቦች ደረሰኝ ያለመቁረጥ፤ ገቢን አሳንሶ መመዝገብ፤ ትክክለኛ ባልሆነ የሂሳብ ሥርዓቶች መመዝገብ፤ ቅድመ ግብር የምንለውንም ጭምር ያለመሰብሰብ የመሳሰሉትንም አግኝተናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከሥራ ግብር ገቢ ጋር ተያይዞ 18 ሚሊዮን 664 ሺ ብር ያልተሰበሰበ ገንዘብ መኖሩ ተረጋግጧል፡፡ የሥራ ግብር ገቢ ያልሰበሰቡት ተቋማት የትኞቹ ናቸው?
አቶ ተስፋዬ፡- ይህ ሁለት የገቢ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤቶችን የሚመለከት ነው፡፡ በተለይ ደመወዝ ሲከፈል የሥራ ግብር መቆረጥ አለበት፡፡ ይህ በግብር ሕጉ በግልፅ የተቀመጠ ነው፡፡ በጣም የተለመደ አሠራር ስለሆነ ማቀናነስም የሚያስቸግር አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር ኦዲት በምናደርግበት ወቅት በአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤትና በሶዶ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቅንጫፍ ጽሕፈት ቤት ብር 18 ሚሊዮን 664 ሺ ብር ከደመወዝ ያልተቀነሰ ግብር መኖሩን ለማረጋገጥ ችለናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ሁለት መሥሪያ ቤቶች ከራሳቸው ሠራተኛ ነው ወይስ መሰብሰብ ከሚገባቸው ተቋማት ነው የሥራ ግብር ገቢ ሳይቀንሱ ያለፉት?
አቶ ተስፋዬ፡- የግሉ ዘርፍ ሠራተኞች ቀጥሮ በሚያሠራበት ወቅት ለመንግሥት የሥራ ግብር ገቢ መሰብሰብ አለበት፡፡ ኦዲቱ የመንግሥት ግብር ሠራተኛ ቀጥረው ከሚያሰሩ ተቋማት አለመሰብሰባቸ ውን ነው የሚያሳየው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በሪፖርቱ ላይ የገቢ ግብር ማሳነስ የሚል ችግር መኖሩም ተመላክቷል፡፡ ግኝቱ ምንድን ነው የሚያሳየው? እንዴትስ ሊሆን ቻለ?
አቶ ተስፋዬ፡- የገቢ ግብር አወሳሰን የራሱ ሥርዓት አለው፡፡ ‹‹ሀ›› ‹‹ለ›› እና ‹‹ሐ›› የሚል የግብር ከፋዮች ደረጃ አለ፡፡ በዚህ ደረጃ ውስጥ እያንዳንዱ ግብር ከፋይ ምን ያክል መክፈል እንዳለበት ይታወቃል፡፡ በተወሰነው የገንዘብ መጠን መሰረት ነው ወይ ግብሩን የተሰበሰበው የሚለውን ነው ኦዲቱ ያየው፡፡ በዚህም በተወሰነው መሰረት ያልተሰበሰበ መሆኑን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ይህ ጉዳይ ግብር ከፋዩ ሕብረተሰብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይጥል ያደርጋል፡፡ ምክንያቱም አንዳንዱ መክፈል የሚገባውን እንዳይከፍል ሲያደርግ፤ ሌላው በተወሰነው መሰረት በሚከፍልበት ጊዜ የግብር አከፋፈል ፍትሐዊነትን ይጎዳል፡፡ በሌላ በኩል የመንግሥት ገቢ በአግባቡ ሳይሰበሰብ ይቀራል፡፡ ለምሣሌ የአርባምንጭ ከተማ ገቢዎች ባለሥልጣን 362 ሺ 780 ብር እንዲሁም የወላይታ ሶዶ ከተማ 202 ሺ196 ብር ግብር አሳንሰው ወስነዋል፡፡ ይህም መንግሥት ያጣው ገንዘብ መኖሩን ያሳያል፡፡ እኛ ያልተከፈለ ግብር ሊከፈል ይገባል የሚል አስተያየት ነው እንደ ኦዲተር የሰጠነው፡፡ እንዳይሰበሰብ ያደረጉ አካላት መጠየቅም አለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከገቢ አሰባሰብና አያያዝ እንዲሁም ከደረሰኝ አለመቁረጥም ጋር ተያይዞስ ክፍተቶች የሉም?
አቶ ተስፋዬ፡- ገቢ እንዲሰበስቡ በሕጉ ሥልጣን የተሰጣቸው አካላት ገቢ በሚሰበስቡበት ወቅት መንግሥት ያሳተመውን የገቢ ደረሰኝ መነሻ አድርገው ሊሆን ይገባል፡፡ መመሪያዎችንና የገቢ አሰባሰብ ሥርዓትና ደንቦችን ተከትለው መሆን አለበት፡፡ ከዚህ አንፃር ‹‹ተቋማቱ የገቢ ደረሰኝ ይሰበስባሉ ወይ?›› የሚለውን ኦዲት በምናደርግበት ወቅት 13 መሥሪያ ቤቶች ገቢ ደረሰኝ ያልተቆረጠለት 4 ሚሊዮን 412 ሺ ብር ገቢ መኖሩን አረጋግጠናል፡፡ ይህ ገንዘብ በመንግሥት የሂሳብ ሪፖርት ውስጥ በገቢነት ይታያል፡፡ ነገር ግን የገቢ ደረሰኝ የለውም፡፡ የገቢ ደረሰኝ ያልቆረጡና ገንዘቡን በገቢ ሪፖርት አካተው ከተገኙ ተቋማት መካከል የሐዋሳ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፤ አንገጫ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ቦንጋ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የገቢ ደረሰኝ የማይቆረጥ ከሆነ ምን ይፈጠራል?
አቶ ተስፋዬ፡- የገቢ ደረሰኝ የማይቆረጥ ከሆነ አጠቃላይ የቁጥጥር ሥርዓቱን ያላላና ለምዝበራ በር ይከፍታል፡፡ የመንግሥት ሂሳብ መግለጫዎችን ተአማኒነት ያሳጣል በሚል ነው ኦዲቱ ያየው፡፡ ያለደረሰኝ የተሰበሰበው ገቢ ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚለውም ሌላ ጥያቄ የሚፈጥር ነው፡፡ ለምዝበራ በር የሚከፍት ሁኔታ እንዳለ አይተናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ዕቃዎች ሲገዙ ለመንግሥት የሚቆረጥ ገቢ አለ፡፡ ለመንግሥት መቆረጥ ያለበትን ገቢ የማይቆርጡ ተቋማት መኖራቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፤ ይህ ምን ማለት እንደሆነና ጉዳቱን ቢያስረዱን?
አቶ ተስፋዬ፡- ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ግዥ በሚፈጽምበት ወቅት ከአስር ሺህ ብር በላይ ዕቃ የሚገዛ ከሆነና ከ500 ብር በላይ የአገልግሎት ግዥ ካከናወነ ግብር ከፋዮቹ ከፈፀሙት ክፍያ 2 በመቶ አስቀድሞ መቀነስ አለበት፡፡ 2 በመቶ የተቀነሰበት ደረሰኝ ለግብር ከፋዩ ይሰጣል፡፡ ግብር ከፋዩ ለመንግሥት ግብር በሚከፍልበት ወቅት በዚያ መንገድ ወስዶ ያካክሳል ማለት ነው፡፡ 88 መሥሪያ ቤቶች ለዕቃና አገልግሎት ግዥ ከፈፀሙት ክፍያ የግብር ሕጉ በሚያዘው መሰረት ያልሰበሰቡት 1 ሚሊዮን 32 ሺ ብር የቅድመ ገቢ ግብር ተገኝቷል፡፡ ይህ የሕግ ጥሰት ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሪፖርቱ በሂሳብ እንቅስቃሴ መዝገብ የተመዘገቡ የገቢ ሂሳብ መረጃዎች በትክክል በቀረበው ማስረጃ ልክ መከናወና ቸውን ለማረጋገጥ በተደረገው ኦዲት ክፍተት መገኘቱንም ይገልፃል፤ ይህ ምን ማለት ነው?
አቶ ተስፋዬ፡- ማንኛውም የገቢ ሂሳብ እንቅስቃሴ መዝገብ ውስጥ የሚገቡ ማስረጃዎችና መረጃዎች በትክክለኛ የገንዘብ መጠን መሆን ሲገባቸው በኦዲቱ ወቅት ያየነው ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ የገቢ ሂሳቦች በትክክል በቀረበው ማስረጃ ልክ የተመዘገቡ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ኦዲት በተደረገበት ወቅት በ17 መሥሪያ ቤቶች 12 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ከቀረበው ማስረጃ በታችና በላይ እንዲሁም በድጋሚ የተመዘገቡ መሆናቸው ተረጋግጧል፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን ስናይ፤ ለምሣሌ ከቀረበው ማስረጃ በታች መመዝገብን በተመለከተ ማስረጃው የሚለው 100 ሚሊዮን ብር ቢሆን 80 ሚሊዮን ብር ብሎ መመዝገብ እንደማለት ነው፡፡
አሳንሶ የገቢ ሂሳብን ከመዘገቡት መካከል ንግድ ኢንዱስትሪና ልማት ቢሮ እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ ገቢዎች ባለስልጣን ጽሕፈት ቤትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ የገቢን ሂሳብ አስበልጠው ከመዘገቡት መካከል ደግሞ ጨንቻ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤትና ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት ናቸው፡፡ ድጋሚ ከመዘገቡት መካከል ሳውላ ሆስፒታልና ሶሮ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት ይገኙበታል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ከፍተኛ ችግር የታየባቸው ናቸው፤ ሌሎችም ችግር ያለባቸው አሉ፡፡ ይህ የሂሳብ መረጃ ሥርዓቱን ተአማኒነት ያሳጣል፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሳንሶ፣ አስበልጦ ወይም ደጋግሞ መመዝገብ ተአማኒነት ከማሳጣት ውጭ የመንግሥት ገንዘብ ብክነት መኖሩን ያመላክት ይሆን?
አቶ ተስፋዬ፡- የሰነድ መረጃው የያዘው እውነታ ብቻ ነበር በሂሳብ ሥርዓቱ ውስጥ መግባት የነበረበት፡፡ ይህ በቀጥታ የሚገናኘው የሪፖርት እውነታውን ከማዛባት ጋር ነው፡፡ በዚህ ሂደት ገንዘብ ባክኗል ብለን እንደ ኦዲተር ለመውሰድ ይከብደናል፡፡ ምክንያቱም የሰነድ መረጃዎች ትክክለኛ ከሆነ ሰነዱ አለ፡፡ ሰነዱ ላይ የተጭበረበረ ነገር ከሌለ የሰነዱን ሁኔታ በትክክል የሂሳብ ሥርዓቱ ውስጥ የማስገባት ችግር ነው፡፡ ያለው ተጽዕኖ ምንድነው የሚለውን በምናይበት ጊዜ የገቢ አሰባሰብ የሪፖርት ሁኔታ ለምክር ቤትም ለሕዝብም ይቀርባል፡፡ ስለዚህ ትክክለኛ የአፈፃፀም መረጃ እንዳይገኝ ይከለክላል፡፡ ከማጭበርበር ጋር ሊገናኝ የሚችለው የገቢ ሰነዱን በሚጽፉበት ጊዜ የገንዘቡን መጠን አሳንሰው፣ አስበልጠው ወይም ደጋግመው ከፃፉ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- እነዚህ ችግሮች መንግሥት ግብር በመሰብሰብ ለሚያከናውነው የልማት እቅድ እንቅፋት አይሆኑም?
አቶ ተስፋዬ፡- መሰብሰብ የሚገባውን ገቢ በአግባቡ ያለመሰብሰብ፣ አሳንሶ መሰብሰብና ሳይሰበስቡ ማለፍ አጠቃላይ የመንግሥትን ዕቅድ ያዛባል፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት ዕቅድ የሚፈፀመው በዋናነት ከዜጎች በሚሰበሰበው የግብር ገቢ ነው፡፡ ስለዚህ ገቢ በአግባቡ የማይሰበሰብና የገቢ አስተዳደሩ በሕግና በሥርዓት የማይመራ ከሆነ ብዙ የልማት ሥራዎች ይደናቀፋሉ፡፡ ሳይከናወኑ የሚቀሩ የልማት ሥራዎችም እንዲኖሩ ያደርጋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኦዲት ግኝታችሁ ከወጪ ጋር በተያያዘ በ137 መሥሪያ ቤቶች ላይ እክል መገኘቱን ያሳያል፤ ጉዳዩን ቢያብራ ሩልኝ?
አቶ ተስፋዬ፡- ማንኛውም የመንግሥት ገንዘብ ለዜጎች አገልግሎት ነው የሚውለው፡፡ አገልግሎት ለማቅረብ የሚወጣ ገንዘቡ የት እንደዋለ? ምን እንደተሠራበት? የሚያሳይ ትክክለኛ መረጃ ሊኖረው ይገባል፡፡ ገንዘቡ ሥራ ላይ ውሏል ብሎ የሚያረጋግጠው ማስረጃ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የወጪ ሂሳቦቹ ትክክለኛ ናቸው ወይ ? የሚለውን ለማየት ኦዲት በምናደርግበት ጊዜ በ137 መሥሪያ ቤቶች 128 ሚሊዮን ብር ማስረጃ ሳይቀርብ፣ የተሟላ ማስረጃ ሳይኖርና ህጋዊ ባልሆነ ማስረጃ ተወራርዶ እንዲሁም ተመዝግቦ ተገኝቷል፡፡ ይህ በመንግሥት ፋይናንስ አስተዳደር አዋጆች፣ ደንቦችና መመሪያዎች መሰረት ያልተፈፀመ በመሆኑ ሕጋዊ ያልሆነ ሥራ ነው፡፡
የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ወደ 13 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር፣ ፖሊስ ኮሚሽን 9 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር፣ የቦንጋ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የሲዳማ ዞን ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ 7 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ማስረጃ ሳይቀርብ፣ የተሟላ ማስረጃ ሳይኖርና ህጋዊ ባልሆነ ማስረጃ የወጪ ሂሳብ አወራርደው ከተገኙት መሥሪያ ቤቶች መካከል ተጠቃሽ ናችው፡፡ በሕጉ መሰረት ያልተሟላ ማስረጃ ሳይኖር ሂሳብ አወራርዶ መገኘት ያስጠይቃል፡፡ እኛም በላክነው ሪፖርት ይህን የፈፀሙ አካላት በሕግ መጠየቅ እንዳለባቸው አሳውቀናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ገንዘብ ወጪ ሲደረግ ማስረጃዎች መሟላታቸውን ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ በፋይናንስ አስተዳደር አዋጁ ተቀምጧል፡፡ መመሪያና ደንብ ያልተከተለ ግዥ የሚፈፅሙ አካላት እንደምክንያት የሚያቀርቡት ምንድን ነው?
አቶ ተስፋዬ፡- መንግሥት አገልግሎት ሰጪ እንደመሆኑ መጠን በሕጉ መሠረት መሥራት እንዳለበት የሚታወቅ ነው፡፡ ይህን የሚፈፅሙ አካላት ሕግ የማያከብሩበት የታወቁ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንደኛው የመንግሥትን ገንዘብ ያለአግባብ መጠቀም ሲፈለግ በዚህ አግባብ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡ በሌላ መንገድ ከባለሙያ ክህሎትና እውቀት ማነስ ጋር ሊገናኝ ይችላል፡፡ ተቋማቱ የተለያዩ ምክንያቶችን ቢያነሱም ለእኛ አሳማኝ አይደሉም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ደንብና መመሪያ ሳይከተሉ በብዙ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ውሎ አበል የከፈሉ ተቋማት መኖራቸው በኦዲት ተጠቅሷል፡፡ ተቋማቱ ይህን እንዴት ሊፈፅሙ ቻሉ? መንግሥት ላይ የደረሰው ጉዳትስ ምንድን ነው?
አቶ ተስፋዬ፡- የውሎ አበል የሚከፈልበት በአገር ደረጃ እንዲሁም እንደየተቋማቱም የተቀመጠ የአሠራር ሥርዓት አለ፡፡ የውሎ አበል ክፍያ በመመሪያ መሰረት የተከፈለ ነው ወይ? የሚለውን በምናጣራበት ጊዜ በ144 መሥሪያ ቤቶች 14 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር ያለአግባብ የአበል ክፍያ መፈፀሙን ለማረጋገጥ ችለናል፡፡ ከሥራ ቦታቸው ሳይርቁ እንዲሁም የአምስት ቀን ሊከፈላቸው ሲገባ የ10 ቀን የተከፈላቸው ሠራተኞች አሉ፡፡ ዳሌ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር፣ ይርጋለም ከተማ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት 1 ሚሊዮን 58 ሺ ብር በመክፈል ከፍተኛውን ድርሻ ሲይዙ፤ ሌሎችም ተቋማት ያለ አግባብ አበል ከፍለዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በብልጫ የተከፈለ ሂሳብ መኖሩ በሪፖርቱ ሰፍሮ ይገኛል፤ በብልጫ የተከፈለ ሂሳብ ማለት ምን ማለት ነው? የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖስ?
አቶ ተስፋዬ፡- በብልጫ የተከፈለ ሂሳብ ማለት ለአንድ ጉዳይ ሊከፈል የሚገባው የገንዘብ መጠን አለ፡፡ የሚከፈለው የአገልግሎት ግዥ 500 ብር ከሆነ መከፈል ያለበት ጨረታ ወጥቶ ጨረታውን ላሸነፈውና ውል ለገባው አካል 500 ብር ብቻ ነው፡፡ ሆኖም ጨምረው የሚከፍሉ ተቋማት አሉ፡፡ 500 ብር መክፈል ሲገባ 700 ብር መክፈል እንደማለት ነው፡፡ በ70 መሥሪያ ቤቶች ወደ 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በብልጫ ተከፍሎ ተገኝቷል፡፡ ከነዚህ ተቋማት መካከል ቴፒ ከተማ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤትና ይርጋለም ከተማ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አነስተኛ የጨረታ ዋጋ ያቀረቡ እያሉ ከፍተኛ ዋጋ ካቀረቡ የግዥ ዘዴ ሳይጠበቅ ግዥ የመፈፀም ሁኔታ መኖሩ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፤ ተቋማት ለምን ይህን ያደርጋሉ?
አቶ ተስፋዬ፡- ግዥ በግልፅ ጨረታ ተወዳዳሪዎች ተወዳድረው ተጫርተው የቴክኒክ ገመና ገላጩ ግምገማውን ካለፉ በኋላ ፋይናንስ ግምገማ ተደርጎ በፋይናንስ ግምገማ ከሚቀርቡት አራት ወይም አምስት ተጫራቾች ዝቅ ያለ ገንዘብ ያቀረበ አሸናፊ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት መንግሥት በዋጋ ውድድር የሚያገኘው ጥቅም አለ ማለት ነው፡፡ በ 43 መሥሪያ ቤቶች ሕጉን በመጣስ ከፍተኛ ዋጋ ካቀረቡት መሥሪያ ቤቶች የ15 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግዥ ተፈጽሟል፡፡ ይህ ማለት የዜጎችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚጎዳ ተግባር ተፈጽሟል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል መንግሥት ሊያገኝ የነበረውን ጥቅም ያጣል፡፡ በዚህ ውስጥ ከተሳተፉ ተቋማት መካከል ላንፉሮ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤትና ቦንኬ ወረዳ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ያለዋጋ ጥናት የተፈፀሙ ግዥዎች መኖራቸው በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ ይህስ ምን ማለት ነው?
አቶ ተስፋዬ፡- ማንኛውም መሥሪያ ቤት ግዥ ከመፈፀሙ በፊት የገበያ ጥናት ማካሄድ አለበት፡፡ ገበያው ላይ እነዚያ የሚፈልጋቸው ዕቃዎች ወቅታዊ ዋጋቸው ምንድነው የሚመስለው የሚለውን አስቀድሞ ከተለያዩ አቅራቢዎች የዋጋ ጥናት አድርጎ መረጃ በሰነድ መያዝ አለበት፡፡ ሰነድ ላይ ከያዘ በኋላ ወደ ጨረታ ሂደት በሚገባበት ወቅት የሚቀርበው ዋጋ በጣም የተጋነነ ከሆነ ጨረታውን ለመሰረዝ ዕድል ይኖረዋል፡፡
አስቀድሞ የገበያ ጥናት ማካሄድ መንግሥትን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ነው የዋጋ ጥናት ከግዥ ሂደት በፊት መካሄድ እንዳለበት በአሠራር የተቀመጠው፡፡ ነገር ግን በዚህ መሰረት ያደረገ ግዥ የማይፈጽሙ መሥሪያ ቤቶች አሉ፡፡ 31 መሥሪያ ቤቶች ያለ ዋጋ ጥናት 4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ግዥ ፈጽመዋል፡፡ አቅራቢዎቹ ባቀረቡት ዋጋ ነው ግዥውን የፈፀሙት፡፡ ይህ የሕግ ጥሰት ከመሆኑም ባሻገር መንግሥት ተወዳዳሪ ዋጋ እንዳያገኝ ያደርጋል፡፡ ከዚያ ባሻገር ለጥራት መጓደልና ለግብር ስወራ ጭምር የሚያጋልጥ ነው፡፡