የሰለጠኑ አገራት የማደጋቸውና የሥልጣኔያቸው መነሻም ሆነ መድረሻ ታሪካቸውን ማወቅ፣ መማርና መጠበቅ ነው። በታሪክ አጋጣሚ የተከወኑ መጥፎ ስህተቶች እንኳን ቢኖሩ ዳግም እንዳይከሰት ለማድረግ ከሚያስተምሩበት መንገድ አንዱ ታሪክን ጽፎ ትውልድ እንዲያውቀውና እንዲማርበት ማድረግ ነው።
ታሪኩ የተከናወነበትን ቦታ በመከለል፣ አክብረውና ተንከባክበው በማቆየት ትውልድ ከዚያ ታሪክ መልካሙን እንዲያበለጽግ፣ ከስህተቱ ደግሞ እንዲማር ያደርጋሉ። ታሪኩን ለአዲሱ ትውልድ እየነገሩም ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፍ ይደረጋል። የተፈጠረው ታሪክም በጎ ይሁን አስከፊ በኩራት «ታሪካችን ነው» ሲሉ ይደመጣሉ።
የብዙ ሺ ዓመታት መልካም ባህሎችና ታሪኮች ያላት ኢትዮጵያ ግን ታሪክ ነጋሪ ቅርሶቿን እየተንከባከበች አይደለም። ለዚህ እንደማሳያ በዋናነት የምናነሳው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ወረዳ የሚገኘው የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ዲነግዴ ቤተመንግሥት ነው። ይህ ቤተ መንግሥት ስለ ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ መስዋዕትነት የሚተርክ ቋሚ ምስክር ነው። ሆኖም ማንም ቅርሱን የሚንከባከብ፣ ስለታሪኩም የሚናገር ስላልነበረ ዛሬ እንዳልነበር ሆኗል። ይህንን ታሪካዊ ቦታ ከአካባቢው ተወላጆችና በስፍራው ካሉ ነዋሪዎች በቀር የሚያውቀው የለም።
ላለመታወቁ የመጀመሪያው ምክንያት የመንገድ አለመኖር ነው። ያም ሆኖ ግን የመንገድ አለመኖር ችግር ሳይሆንባቸው ጥቂት የማይባሉ ከተለያዩ አገራት የመጡ የውጭ ዜጎች ጎብኝተውታል፤ ምክንያቱም ለታሪክ የሚሰጡት ቦታ ከፍ ያለ ነውና። ይህንን ቦታ ለተመለከተው ደግሞ ማንም ሊርቀው አይወድም። ይሁንና በሚገባ ባለመታወቁ የቱሪስት መዳረሻ ሊሆን አልቻለም። ፈልጎ ማየትስ ለምን አልተቻለም ከተባለ ቸልተኝነት ከሚለው ውጪ የሚገልጸው አይኖርም። ምክንያቱም ቦታው ከጊንጪ ከተማ ብዙም አይርቅም።
የጥርጊያ መንገዱን ይዞ ሽር ላለ ብዙም መንገድ ሳይጎዳው ይህንን ታላቅ የታሪክ ቦታ ይጎበኛል። ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ በዳግማዊ ምኒልክ መንግሥት ጦር ስር ከተራ ወታደርነት ተነስተው እስከ ጦር ሚኒስትርነት የደረሱ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ናቸው። በምክር አዋቂነታቸው እና በፍርድ ችሎታቸውም «አባ መላ» በሚል ቅጽል ስም እስከመጠራት የደረሱም ስለመሆናቸው ብዙ መላ ያበጁለትን ችግር በማንሳት የአካባቢው ታሪክ አዋቂዎች ይናገራሉ።
በአፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በተካሄዱት በአብዛኛዎቹ ትልልቅ የጦር ዘመቻዎች የተሳተፉ፤ በኋላም በአድዋ ጦርነት ሲዋጉ የቆዩና ፊታውራሪ ገበየውን ተክተው የጦር አበጋዝ ሆነው ያገለገሉ ለመሆናቸው ታሪክ ይናገራል። የእኝህን የሀገር ባለውለታ ታሪክ ሊናገር የሚችለው ቤተመንግሥት ግን ዛሬ አይሆኑ ሆኖ ፈርሷል። ፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ ከእህቶቻቸው ጋር አገርን ለማቅናት ነበር ወደ ምኒልክ ዘንድ የተወሰዱት።
እህቶቻቸው ወደ ቤተሰብ ሲመለሱ እርሳቸውን በዚያ ምኒልክ አስቀሯቸውና በዚያው ኖሩ። ልጅነት ጭምር ስላለ ከአካባቢያቸው ተሰውረው እንዳይቀሩ በወቅቱ እናታቸው ሲሸኟቸው አንድ ነገር ብለዋቸው በአንገታቸውም ላይ ክታብ አስረው እንደተሰናበቷቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ይናገራሉ። “ስታድግና ስትማር ይህንን አንብበህ የት እንደነበርክና የማን ልጅ እንደሆንክ ታውቃለህ።” ሲሉ ነግረዋቸዋልም ይባ ላል።
እርሳቸውም የተባሉትን ተግባራዊ ያደረጉት አድገውና ተምረው እንዲሁም በብዙ ሹመቶች ላይ ካለፉ በኋላ ነው። የአንገታቸው ክታብ ትውልድ ስፍራቸውን መርታቸው ሄዱ። ቦታው ላይ ሲደርሱ ግን ያሰቡትን ሁሉ አላገኙትም፤ እናታቸው በሕይወት አልነበሩም፤ አባታቸውን በማግኘታቸው ብዙም ሳይከፉ እርሳቸው የሚያስደስታቸውን ለማድረግ ቃል ገብተው መትጋት ጀመሩ። ቤተመንግሥቱ በትውልድ ቀያቸው ላይ የተሰራውም ለዚህ ነው። በራሳቸው በፊታውራሪው እንደተሰራም ይወሳል።
የፊታውራሪ ሀብተጊዮርጊስ አራተኛ ትውልድና ቀደም ሲልም የአካባቢውን ቀበሌ በሊቀመንበርነት ያስተዳደሩት አቶ ታደለ ደበበ ታሪኩን መለስ ብለው በማስታወስ ሲናገሩ፤ አቶ ዲነግዴ ልጃቸው ሦስት ነገሮችን እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋቸው ነበር። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ እዚህ ቦታ ቤተመንግሥት እንዲያቆሙ ነበር። እርሳቸው የአባታቸውን ቃልአክብረው ቤተመንግሥቱን ቢያቆሙም ትውልዱ ግን የአባቶቹን ታሪክ ሊጠብቅ አልቻለም። ቃላቸውን አክባሪነታቸው፤ ለእያንዳንዱ ነገር መላ ሰጪነታቸውን አልተከተለም። አሁን ታሪክ ተረካቢ በመጥፋቱ፣ ባለቤት ነኝ የሚል ተቋም ባለመኖሩ ቅርሱ የቱሪስት መስህብ መሆን አልቻለም፤ ቤተመንግሥቱም እየፈራረሰ ይገኛል።
አባ መላ የመላ ባለቤት ቢሆኑም መላቸውን ተከትሎ ማንነታቸውን ሊነግርላ ቸው የሚችል ሰው መጥፋቱ እጅግ አሳዛኝ እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ታደለ፤ የሰዎች ማንነት የሚታወቀው በሰሯቸው ሥራዎች ቢሆንም በቅርስ መልኩ የተቀመጠና ለትውልድ የሚተላለፍ መሆን አለበት። ይህ ደግሞ ስለ እርሳቸው አገሬው ብቻ ሳይሆን ዓለምም ጭምር ታሪኩን እንዲያውቅ ዕድል ይሰጠዋል። ነገር ግን የእርሳቸውን መርህ መከተል ያልቻለው ትውልድ ቤተመን ግሥቱ እስኪፈርስ ጠብቆታል ይላሉ። «ቤተመንግሥቱ የተለያዩ የአገር ባለውለታዎችን የሸሸገ ነው። እነ ራስ ሚካኤል ዓመታትን ያሳለፉበት እንደነበረም ይነገርለታል። በተለይ በግዞት የነበሩ ትልልቅ የዘመኑ ሹማምንት ብዙ ቆይተውበታል» ያሉት ደግሞ የአካባቢው ተወላጅ አዛውንት አቶ ዳመነ ኃይሉ ናቸው።
በቤተመንግሥቱ ውስጥ ሙሉ የጥንት ቅርሶቸ እንደነበሩ እርሳቸው የዓይን እማኝ እንደሆኑ ይናገራሉ። ይሁንና ይህም ዛሬ የለም። ማን እጅ ውስጥ እንዳለ አይታወቅም። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ የተለያየ እንደሆነ ያነሳሉ። የአካባቢው ሰው ስለ ታሪካዊ ቅርሶች የሚያውቀው ነገር ያለመኖሩ፤ ስለቤተመንግሥቱ ታላቅነትም ማንም አለመናገሩና ስለቅርስ ምንነት የሚያስተምር በአካባቢው ዘንድ ስለሌለ የነበሩ ቅርሶች ሁሉ ሲጠፉ ሀይ ያለ አልነበረም ሲሉ ይቆጫሉ።
የአካባቢው ማህበረሰብ ቤተመንግሥቱ ያለበትን ስፍራ መንከባከብ ትቶ ቦታውን እያሰፋ ለራሱ የእርሻ መሬት እያደረገው ይገኛል። ለዚህም በዋናነት ተወቃሹ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ መሆኑን ይናገራሉ። አሁንም ለዚህ ቤተመንግሥት መኖር የሚያስፈልገው ወሬ ሳይሆን ተግባር ነውና የድረሱልኝ ጥሪውን ሁሉም ይስማና መፍትሄ ይስጠው ሲሉ ያሳስባሉ። «አካባቢው ለአዲስ አበባም ሆነ ለኦሮሚያ ክልል ከተሞች በጣም ቅርብ ነው።
ከጊንጪ ትንሽ ጉዞ ተደርጎ የጠጠር መንገዱ 12 ኪሎ ሜትር ብቻ ነው የሚኬደው። ይሁንና ማንም ዝር ብሎበት አያውቅም። ስለዚህም ታሪክን በታሪክ መክፈል ይገባልና ዛሬ ላለን ቅርስ እንድረስ። ትውልድ ወቃሽና አስወቃሽ እንዳንሆንም እንስራ» ሲሉም አባ ገዳዎች በእንባ ጭምር መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። በተለይ በቱሪዝም ዘርፍ የሚሰሩ ባለሙያዎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ቢሮዎች ሀብቱን በማሳወቅ ዙሪያ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት።
የደንዲ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕ ፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባንቲ ለሚ ዘርፉን ከተቀላቀሉ አጭር ጊዜያቸው መሆኑን ይናገራሉ። በመሆኑም በወረዳው ያሉትን ሀብቶች በሙሉ ለማየትና የድጋፍ ሥራ ለመስራት አልቻልኩም ይላሉ። አሁንም ቤተመንግሥቱ በዚህ ደረጃ ወድቆ መመልከታቸው እጅጉን አሳስቧቸዋል።
ከጉብኚዎች እኩል ሰሞ ኑን ቤተ መንግሥቱን ማየታቸውም ትክ ክል እንዳልሆነ ይጠቅሳሉ። በቀጣይ ለመ ማርና ከስህተት ለመታረም ጥሩ ዕድል ይሰጣል፤ ችግሮቹ የሚፈቱበትን ሁኔታ ለማመቻቸትም ተነሳሽነት እንደሚፈጥር ገልጸዋል። በዚህ ቦታ በርካታ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም ሀብቶች መኖራቸውን ዛሬ በስፋት እንዳዩ ገልጸውም፤ ቦታው ባለመታወቁና ባለመታየቱ ምክንያት ቤተመንግሥቱ የመፍረስ አደጋ ደርሶበታል። ስለዚህ ብዙ ተግባር ማከናወን እንዳለብን ተረድተናልም ብለዋል። በዚህ ዕድል መነሻነትም በቀጣይ በጥልቀት አይቶ ለመስራት ይሞከራል። ከዚህ በኋላ በአጭር ጊዜ ጥገና እንዲደረግና ሀብቱን ወደ ገንዘብ የመለወጥ ተግባር እንደሚከናወንም ቃል ገብተዋል።
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ልማት ቡድን መሪ አቶ አበራ ታደሰ እንደተናገሩት፤ በ2010 ዓ.ም በቦታው ላይ የቱሪዝም ቀን ተከብሯል። ቀደም ሲል ቦታው አይታወቅም ነበር። ይህም ቤተመንግሥቱ ዛሬ ላለበት ሁኔታ እንዲበቃ አድርጎታል። ሁኔታው በጣም ያሳዝናል። እኛም አለማየታችንና አላማሳወቃችን ለውድቀት አጋልጦታል። በመሆኑም የመጀመሪያ እርምጃ መሆን ያለበት የመንገድ ግንባታው ነውና እርሱ ላይ ይሰራል። በዚህ ዓመት በጀት አልተያዘም። ያለዕቅድ መስራት ደግሞ አዳጋች ነው። ስለሆነም እየተመካከርን የሚቻለውን ሁሉ እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል።
ለቤተመንግሥቱ አለመታወቅና መፈራረስ ሁሉም ምክንያት ያሉትን ቢደረድሩም ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ታሪክን እየፈለገ ለትውልድ እንዲታወቅ አለማድረጉ ሰፊ ችግር ሆኖ ይታያል። ዛሬ እርቃኑን የቆመው ቤተመንግሥትም ለታሪክ መጥፋት አንዱ ምስክር ነው። በወቅቱ አምስት ትልልቅ ግቢዎችና እርከኖችን አልፎ ዋናው ቤተመንግሥት ውስጥ እንደሚገባ የተነገረለት ቤተመንግ ሥት ዛሬ ያለከልካይ ዘው ብሎ ይገባበታል። ቤተመንግሥቱ ምንም ዓይነት በርና መስኮት የለውም። ይባስ ብሎ ቤቱን በምሰሶነት የያዘው እንጨት ሳይቀር ተነቅሎ ይታያል። በአጠቃላይ አጽመ ታሪኩ ቀርቷል። እኛም ትውልድ ይፍረደኝ አቤቱታውን አይተንና ሰምተን «እንታደገው» አለን።
ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው