መስከረም 2011
ከመስከረም 1 እስከ መስከረም 30 ምን ምን ክስተቶችን አሳለፍን።
* በዚህ ወር ውስጥ የኦነግ አመራሮች ወደ አገር ውስጥ መግባታቸው አንዱ ነው። በአገር ውስጥ ገብተው ሠላማዊ ትግል እንዲያደርጉና ለአገራቸው የዲሞክራሲ መጎልበት እንዲሰሩ ተደርጓል።
* ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከውጭ የመገናኛ ብዙኃን ጋዜጠኞች ጋር የተወያዩትም በዚሁ የመስከረም ወር ነው።
* የኢህአዴግ 11ኛ ጉባኤ የተከናወነውም በመስከረም ሲሆን፤ በዚህ ጉባኤ መክፈቻ ላይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በንግግራቸው የተለያዩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። «አሁን ተግተን በመሥራትና ነቅተን በመገስገስ አዲስ ታሪክ መሥራት የምንጀምርበት ታሪካዊ የዘመን አካፋይ አንጓ ላይ እንገኛለን። መልካም ምኞት ሳይሆን ንቁ ተሳትፎ፣ ጥረት ብቻ ሳይሆን ፍጥነት፣ ፍጥነት ብቻም ሳይሆን ብልሃት፣ ብልሃት ብቻም ሳይሆን አብሮ መሥራትና መደመር ያስፈልገናል» ብለው ነበር። « የተረከብናትን ኢትዮጵያ ያለመውደድ መብታችን ነው። የምናስረክባትን ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ አስውበን መቅረጽ ግን ግዴታችን መሆኑን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም»
* ይህ ወር የኦህዴድ ጉባኤ በአዲሱ ሊቀመንበር የተመራበትና ትልልቅ ውሳኔዎችን ያሳለፈበት ነበር፤ በተመሳሳይ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ብአዴን፤ ደኢህዴንም ጉባኤያቸውን አካሂደዋል። ትልልቅ የፓርቲ ውሳኔዎችን አሳልፈውም የስም ቅየራ አድርገዋል። የግንባሩ ማጠቃለያ መርሀ ግብሩን አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ንግግሮችን ያደረጉ ሲሆን፤ ለአብነት
– «ኢትዮጵያን እና ድንቅ ሕዝቦቿን ደግሜ ማገልገል እንድችል እድል ስለተሰጠኝ አመሰግናለሁ»
– በመንግሥት በኩል የሠላም ተቋም እንደ አዲስ ማደራጀት እና በጠንካራ አመራሮች ትኩረት ሰጥተን እንሥራለን፤ የአገር ሽማግሌዎች፣ የጎሳ መሪዎች፣ ወጣቶች፣ ምሁራን እና የሃይማኖት አባቶች በነፃ የተሰጠንን ሠላም ለመጠበቅ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2011