አዲስ አበባ፡- ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአዲስ የመነቃቃት መንፈስ ድጋፉን በማጠናከር ለውጤት ማብቃት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ። የከተማው አንዳንድ ነዋሪዎች በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት የኢትዮጵያውያን የአንድነት መገለጫ ለሆነው ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ግንባታው እስኪጠናቀቅ መቀጠል አለበት። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ አቶ መለሰ ጌታቸው እንዳሉት ታላቁ ህዳሴ ግድብ ከህዝቡ ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያለው ነው፤ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ሀብትም ፈሶበታል፤ በመሆኑም ህዝቡ ተጠናቆ ውጤቱን ማየት ይፈልጋል። እስከፍጻሜ እስኪደርስ ደግሞ ሁሉም ዜጋ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ድጋፉን በተነቃቃ መልኩ መቀጠል አለበት ብለዋል።
«እኔ በበኩሌ ከዚህ በፊት ሳደርግ የነበረውን ድጋፍ ለመቀጠል ዝግጁ ነኝ፤ ሌላውም ሰው ይሄንን ሃሳብ ይደግፋል ብዬ አስባለሁ። ሆኖም ግን ባለፈው አንድ ዓመት ለግድቡ የተሰጠው ትኩረት የተቀዛቀዘ ይመስላል። መቀዛቀዝ እንዳይኖር ህዝቡን የማነቃቃት ሥራ በመንግሥት በኩል ሊሠራ ይገባል» ብለዋል።
«የህዳሴው ግድብ ለኛ ብቻ ሳይሆን ለብዙ ሀገሮች ተስፋ ነው፤እኛም የአቅማችንን ቦንድ ስንገዛ ነው የኖርነው። ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ህዝቡን ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ሲወጡ ሰምተናል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ድጋፉ ላይ መቀዛቀዝ ታይቷል» በማለት የተናገሩት ደግሞ የአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ኤርሚያስ ተድላ ናቸው። የህዳሴው ግድብ የሚታይ፣ የሚዳሰስና የሚጨበጥ በመሆኑ መንግሥት ታአማኒነት ያለው መረጃን ለህዝቡ በማቅረብና ህዝብን በማስጎብኘት ወደ ሥራ መግባት አለበት ሲሉም አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኛ የሆኑት ወይዘሮ መሰረት መኮንን በበኩላቸው፤ ከግንባታው ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ስሜታችን ተነክቷል። አሁንም ህዝቡን በየእድሩ፣ በየማህበር፣ በእቁብ፣ በእምነት ተቋማት፣ በመስሪያ ቤትና በመሳሰሉ ቦታዎች የቅስቀሳ ሥራ በመሥራት በአዲስ መንፈስ እንዲነቃቃ ማድረግ ያስፈልጋል:: የህዳሴ ግድቡ ግንባታን አስመልክቶ ቀደም ሲል ችግሮች እንደነበሩ ቢታወቅም አሁን ግን በትክክለኛው መንገድ ሥራው እየተካሄደ መሆኑን ህዝቡን ማሳወቅና ለቀጣዩ ሥራም ድጋፍ እንዲያደርግ ማነቃቃት አስፈላጊ መሆኑን ወይዘሮ መሰረት ገልጸዋል።
«መንግሥት ትኩረት ከሰጠው እንደ እኔ በፅዳትና በጉሊት የተሰማሩ ሁሉ ሳይቀሩ ለአባይ ይቆጥባሉ» ያሉት ወይዘሮ መሰረት ይህን ስሜት በመመለስ በኩል ትልቅ ሥራ መሠራት አለበት ብለዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ እንደገለጹት፤ በፕሮጀክቱ ግንባታ በኩል ምንም ዓይነት መቀዛቀዝ እንደሌለ ገልጸው የህዳሴ ግድቡ መዘግየት ዋናው ምክንያት ብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽ በገባው ውል መሰረት ሥራውን ባለመሥራቱ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን መንግሥት በወሰደው ዕርምጃ ከብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በንዑስ ኮንትራክተርነት ሲሠሩ የነበሩ ሰባት ኮንትራክተሮች ሙሉ ኃላፊነት ተሰጥ ቷቸው ወደ ሥራውን መግባታቸውን ተናግረዋል።
የህዝብን አመኔታ ሙሉ ለሙሉ መመለስ የሚቻለው ሥራው መሠራቱን በዓይኑ ዓይቶ ሲረዳ ብቻ መሆኑን ጠቅሰው ይህንንም ለማድርግ የተሠራውን ሥራ መገናኛ ብዙሃን እንዲያዩትና እውነታውን ለህዝቡ እንዲያቀርቡ ይደረጋል ብለዋል። በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ግድቡ 66 ነጥብ 24 በመቶ የደረሰ ሲሆን በ2012 የመጀመሪያውን 750 ሜጋ ዋት ኃይል ያመጫል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2011
ሞገስ ፀጋዬ