አዲስ አበባ፡- አዲሱ የለውጥ አመራር በአንድ ዓመት ጉዞው በኢኮኖሚው ዙሪያ በርካታ መፍትሔ ሰጪ ሥራዎችን መሥራቱ እና ከዚሁ ጥንካሬው ጋር ተያይዞም ችግሮችን ያስተናገደ እንደነበር የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ገለጹ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ባለሙያው ዶክተር ኢዮብ ተስፋዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት አዲሱ የለውጥ አመራር በአንድ ዓመት ጉዞው በኢኮኖሚው ዙሪያ በርካታ መፍትሔ ሰጪ ሥራዎችን ሠርቷል። በተለይም የውጭ ምንዛሬ ችግርን ለመፍታት የተሠራው ሥራ በምንዛሬ እጥረት ሊያርፍ የሚችለውን ጫና በብዙ መልኩ ያቃለለና እፎይታን ያስገኘ እንደነበር አስታውሰዋል ።
የአገሪቱ የውጭ ብድር ጫናን ለመቀነስ የአዲስአበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር ብድር በ10 ዓመት መከፈል እንዳለበት ስምምነት ቢኖርም ይሄንን የዕዳ ክፍያ ወደ 30 ዓመት እንዲራዘም መደረጉም አንዱ የጥንካሬ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል። የፋይናንስ ተቋማትን አሁን ባሉበት ቁመና ይዞ መቀጠል ማክሮ ኢኮኖሚውን በእጅጉ እንደሚጎዳው የሚናገሩት ዶክተር ኢዮብ፤ ፖሊሲን በሚመለከት ብቻ የሚሠራ የፋይናንስ ተቋማት ያስፈልጋሉ። ይሁንና በአገር ውስጥ ከሰው ሀብት ጀምሮ ምንም የተሟላ ነገር የላቸውም። ስለሆነም መንግሥት ይህንን ሊያስተካክል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኤክስፖርት ሴክተሩንና በቱሪዝም ላይ መሥራቱን ማጠናከር እንዲሁም የተረጋጋ ኢኮኖሚ መፍጠር ላይ ማተኮር እንደሚገባም መክረዋል። እንደ ዶክተር ኢዮብ ገለጻ፣ለውጡ ላይ የመጣው የኢኮኖሚ ችግር ቀድሞ የተጠራቀመ ነው። በዓመት ውስጥ ደግሞ ወደነበሩበት መመለስ እጅግ ያዳግታል። ለአብነት የውጭ ምንዛሬ ችግር፤ የሥራ አጥ ቁጥር መጨመር፤ የንግድ ሚዛን ጉድለት በስፋት እየጨመሩ የመጡ መሆናቸውን አንስተው ይህም በአንድ ዓመት የተፈጠረ ችግር ብቻ አይደለም። ሆኖም አሁንም የለውጡ ችግሮች ከመሆን የሚያስቀራቸው አይኖርም ብለዋል።
«የግል ዘርፉን በማጠናከር ዙሪያ የፖሊሲ ሮድ ማፕ አለመኖሩ እንደ ችግር የሚነሳ ነው» የሚሉት ዶክተር ኢዮብ፤ ማክሮ ኢኮኖሚውን ለማስተካከል በፍጥነት አለመኬዱ፤ ቁልፍ የሆኑ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ከተለመደ ሥራቸው አለመላቀቃቸውና መሰል ጉዳዮችም ለኢኮኖሚው ችግር መሆናቸውን ጠቅሰዋል። ጥቅማቸውን የጨረሱ ፖሊሲዎች መስተካከልና መውጣት ሲኖርባቸው ባሉበት መቀጠላቸው፤ መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ የሚበደረውን ገንዘብ በአዋጅ መገደብ አለመቻሉ፤ የፋይናንስ ተቋማትን ማሻሻል ላይ ማስተካከያ አለመውሰዱ በችግርነት ይነሳል።
የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው እንዳሉት ፤የግብይት ስርዓቱ በሰላምና መረጋጋቱ ችግር ምክንያት መቋረጡ፤ ሥራዎች እንደተፈለገው መሠራት አለመቻላቸውም በአንድ ዓመት ውስጥ ከነበሩ ችግሮች የሚጠቀስ ነው። የውጭ ምንዛሬ አቅርቦቱ በአገሪቱ መቋቋም በማይቻልበት ሁኔታ ዝቅ ብሎ መቆየቱ በአገር ውስጥ የዋጋ ግሽበት እንዲፈጠርና የኤክስፖርት መጠኑ እንዲቀንስ አድርጓል። ሆኖም መንግሥት በአጭርና በረጅም ጊዜ የሚከናወኑ ፖሊሲዎችን በማውጣት መፍትሔ መስጠቱ የሚያስመሰግን መሆኑን ተናግረዋል።
የግል ዘርፉ ላይ ለመሥራት የታቀደው የመንግሥት ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በከፊል ወደ ግል ለማዘዋወር መሞከሩ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ የግል ዘርፉ ሊበረታታበት የታሰበው ሥራ አዳዲስ አሠራሮችን በማምጣት የውጭ ምንዛሬን ያስገኛል። መንግሥትንም ካልተገባ ወጪ ይታ ደጋል። ስለሆነም የተጀመረውን ተግባር ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
የህዝብ ብዛቱ ከሥራ ዕድል ፈጠራ ጋር አለመመጣጠኑ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጫና መፍጠሩን ገልጸው ሰላምና መረጋጋት ያለመኖሩም ኢኮኖሚውን በሚፈለገው ደረጃ እንዳያድግ ገድቦታል። ብዙው ህዝብ ፖለቲካ እንጂ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ትኩረት እንዳይሰጥ ሆኗል። የሚፈናቀለውና ሜዳ ላይ የሚውለው ወጣት መብዛትም ሌላው በኢኮኖሚው ላይ የታየ ችግር ነው የሚሉት አቶ ሙሼ፤ መንግሥት ተፈናቃዮችን ሲደግፍ ገንዘቡን ወደ ልማት ማዋል እንዳይችል አድርጎታል።
የኢኮኖሚው ትልቁ ሞተር መንግሥት በመሆኑና ታክስን ሰብስቦ ዕዳ መክፈል ላይ ብቻ ማዋሉም ሌላው ችግር እንደሆነ ያነሳሉ። መንግሥት ብዙዎቹን የኮንስትራክሽን ዘርፎች በመያዙም እንዲሁ የሥራ አጥ ቁጥር እንዲበራከት አድርጓል። የግል ሴክተሩ በስፋት እንዳይሠራም ገድቦታል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ በተወካዮች ምክር ቤት የስምንት ወር ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፤ ባንኩ እንደገና መሠራት ያስፈልገዋል። በዚህም ከልማት ባንክ ጋር በመሆን የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች ተጀምረዋል። ይህ ሥራ ደግሞ ባንኩን ከማዳን በተጨማሪ እግረመንገዱን ተልዕኮውን እንዲያሳካ የሚያስችለውም ይሆናል።
አገሪቱ ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ እንዳትገባ እዳ መክፈል ግድ ነው ያሉት ዶክተር ይናገር፤ ለብድር ክፍያው ቅድሚያ በመስጠት ተቋሙ ራሱን ችሎ እንዲቆም ማድረግ ላይ ይሠራል ብለዋል።
የንግድ ሚዛን ጉድለት እንዲሁ በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱንና በስምንት ወር ብቻ 8 ነጥብ ስድስት ቢሊየን ዶላር መድረሱንም አንስተዋል።
የአገሪቱ የወጪ ንግድ ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 9ነጥብ 4 በመቶ ያነሰ ነው ተብሏል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2011
ጽጌረዳ ጫንያለው