በመዲናችን የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፤ አፍላ በሚባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ። ቀን፣ ሰዓትና ቦታ ሳይመርጡ የቤት ውስጥ ተረፈ ምርቶችን (ቆሻሻ) ከያለበት ይሰበስባሉ። በተለይ የውሃ መያዣ ፕላስቲኮችን ከየቱቦ፣ ወንዞች፣ መንገዶች… ከወዳደቁበት ቦታ አጠረቃቅመው ጥቅም ላይ ለሚያውሉ ፋብሪካዎች በማቅረብ ሁልጊዜ በሥራ እንደተጠመዱ ናቸው። የመድከምና የመሰልቸት ስሜት አይታይባቸውም። ወጣቶቹ ለራሳቸው ከፈጠሩት የገቢ ማስገኛ ሥራ ጎን ለጎን የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫና ዕድሜ ጠገብ ለሆነችው መዲናችን ውብና ፅዱ አካባቢን ለመፍጠር ይተጋሉ።
በዚሁ ሥራ ከተሰማሩትና በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት በጥቃቅንና አነስተኛ ማህበራት ተደራጅተው ከሚንቀሳቀሱት መካከል ወጣት አስራት በላይ አንዱ ነው። በመጀመሪያ ለአካባቢ ፅዳት መንግሥት እንዳደራጃቸውና ቀስ በቀስ ደግሞ የውሃ መያዣ እና ሌሎች ፕላስቲኮች በመሰብሰብና ለተረካቢ ድርጅቶች በማቅረብ ተጨማሪ የገቢ ማስገኛ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ይናገራል።
የውሃ መያዣ ፕላስቲኮች ከተለያዩ ቦታዎች ሰብስበው ለድርጅቶች ማቅረብ ከጀመሩ አምስት ወራትን አስቆጥረዋል። ሥራውን ሲጀምሩም በ60 ሺ ብር ካፒታል እንደነበርም ይገልጻል። በአሁኑ ወቅት ልፋታቸው ፍሬ አፍርቶ ካፒታላቸው ከ400 ሺ ብር በላይ መድረሱንም ይናገራል። መንግሥትም የወጣቶችን የሥራ ፈጠራ ለማበረታታት አንድ ኪሎ ፕላስቲክ የውሃ መያዣዎችን በአራት ብር ሲያስረክቡ በኪሎ ሁለት ብር ድጎማ ያደር ግላቸዋል። በአጠቃላይ ከአንድ ኪሎ ስድስት ብር ያገኛሉ።
የሥራው ባህሪ ምንም እንኳን ከባድ ቢሆንም የአካባቢን ንፅሕናን ከመጠበቅና የሥራ ዕድልን ከመፍጠር አንፃር ጠቀሜታው ከፍተኛ በመሆኑ ጠንክረው እየሠሩ መሆናቸውን የሚያነሳው ወጣት አስራት፤ ገቢያችን ባደገ ቁጥር የአካባቢ ብክለትንም እንቀንሳለን የሚል ትልቅ ራዕይ እንዳላቸውና ይህንንም ለማሳካት ጠንክረው እንደሚሠሩ ያስረዳል። ለዚህ ውጤት ለመብቃት እንዲችሉ መንግሥት ያለባቸውን የቦታ ችግር እንዲፈታላቸው ይጠይቃል።
የኮባ ኢምፓክት የኅብረት ሥራ ማኅበራት የፕሮዳክሽን ሱፐርቫይዘር አቶ ዘመን ያሲን እንዳሉት ድርጅቱ በቀን ከ15 ሺ ኪሎ ግራም በላይ ፕላስቲክ የመረከብ አቅም አለው። ለሥራውም ከሰው ኃይል በተጨማሪ 11 ማሽን ገዝቶ ወደ ሥራ ተሰማርተናል፡፡ ነገር ግን «ባለን አቅም ልክ ግብአት አላገኘንም፤ በአሁኑ ወቅት ከ8 እስከ 10 ሺ ኪሎ ግራም ብቻ ነው እያገኘን ያለነው፡፡ ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፤ በዚህም ምክንያት ከሦስት ወር ጀምሮ ሥራውን በሚፈለገው ልክ እየሠራን አይደለም» ብለዋል። ለዚህም ምክንያቱ የውሃ መያዣ ፕላስቲኩን በሚሰበስቡና በሚያቀርቡት መካከል ደላሎችና ሌሎችም በመሰማራታቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ጉተማ ሞረዳ ፤የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ ከሚሠሩ ማህበራት ጋር በቅርበት እየሠሩ መሆኑን ይናገራሉ። በተጨማሪም ከተረካቢ ድርጅቶች ለአብነትም ኮባ ኢምፓክትና ኢኬት ህጋዊ የፕላስቲክ ማቅለጫ ድርጅቶች ጋር ተባብረው የሚሠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል። እነዚህ ድርጅቶች ከማህበራት የተሰበሰቡ ፕላስቲኮችን በመረከብ አጥበውና ፈጭተው ወደ ውጭ ሀገር የሚልኩ መሆናቸውን ነግረውናል።
ድርጅቶቹንም ሆነ ማህበራቱን ባለሙያ በመላክ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርጉ የሚገልጹት ኢንጅነር ጉተማ፤ ሌሎች ድርጅቶችም ይህንን ዓይነት ሥራ ለመሥራት ጥያቄ እያቀረቡ ናቸው። ለእነዚህም ድርጅቶች ወደ ፊት ፍቃድ ለመስጠት እንደተዘጋጁና መመሪያው በሚፈቅደው መሰረት እንደሚያስተናግዷቸውም ጠቅሰዋል።
የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ኮሚሽን የደረቅና አደገኛ ቆሻሻ ህግ ተከባሪነት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ኬኔ፤ ቆሻሻ ከምንጩ ጀምሮ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ መያዝና እንደየባህሪያቱ መወገድ እንዳለበት ይናገራሉ።
እንደ አቶ ግርማ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት በሀገር ደረጃ ከሚመረተው ጥቅል ቆሻሻ ከ9 እስከ 14 በመቶ የሚሆነው የሚሸፍነው ውዳቂ የፕላስቲክ ምርት ነው። ይህም ችግር ከፍተኛ በመሆኑ ተቋሙ ደረቅ ቆሻሻን ከመቀነስ አንፃር ብዙ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል።
ህብረተሰቡ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት የሚናገሩት አቶ ግርማ፤ የቆሻሻ አወጋገድ ሥር ዓቱ ላይ ትኩረት መስጠትና ጠጣር፣ ፈሳሽ፣ የሚ ቃጠል፣ የማይቃጠል፣ የሚበሰብስና የማይበሰብስ በማለት ለይቶ በማህበር ለተደራጁ አካላት ማስረ ከብ እንደሚገባው አሳስበዋል። ቆሻሻ በሥርዓት የማይወገድ ከሆነ በሰው፣ በአየር፣ በአፈርና በአጠቃላይ ህይወት ባለው ነገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል ብለዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 22/2011
ሞገስ ፀጋዬ