
አዲስ አበባ:- መንግስት በጥልቀት ገምግሞ ባሳለፋቸው ውሳኔዎች መሰረት በተከታታይነት በተሰሩ ስራዎች ግድቡ አሁን ለደረሰበት የግንባታ ምዕራፍ እንዲደርስና ሩቅ የሚመስለውም የማመንጨት ሂደት እውን እንዲሆን እንዳስቻለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን ገለጹ፡፡
ኢንጂነር ኤፍሬም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሁለተኛው ተርባይን ኃይል ማመንጨት ማብሰሪያ መርሃ ግብርን መሰረት በማድረግ እንደገለጹት፤ የመንግስት ውሳኔ ግንባታው አሁን ለደረሰበት የግንባታ ምዕራፍ እንዲደረስና ሩቅ የሚመስለውም የማመንጨት ሂደት እውን እንዲሆን አስችሏል፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አሁን ላስመዘገበው ውጤት በርካታ ችግሮችን አልፏል፡፡ በተለይም ከ2010 ዓ.ም በፊት በነበረው ሂደት የኤሌክትሪካልና የሃይድሮሊክ እስቲል እስትራክቸር ስራዎች ብዙም ልምዱ ባልነበረው አገር በቀል ኩባንያ እንዲመራ መደረጉ ሥራዎቹን መጎተቱንና አገርንም ለኪሳራ መዳረጉንም አስታውሰዋል፡፡
ሙያው ላይ የበቃ አቅም ተፈጥሮ ባለመገባቱ የተቀመጠውን አላማ ማሳካት እንዳልተቻለ እና በግንባታ ሂደቱ መዘግየት መከሰቱንም ኢንጂነር ኤፍሬም ጠቁመዋል፡፡
የውሃ ሙሌቱን ተከትሎ ከግድቡ ሃይል ማመንጨት የሚያስችለው የኤሌክትሮ ሜካኒካል እና እስቲል እስትራክቸር ስራዎች ተከናውነው ባለፈው የካቲት ወር በአንድ ተርባይን አማካኝነት የመጀመሪያ ዙር ሃይል በይፋ ማመንጨት መጀመሩንም አስታውሰዋል፡፡
‹‹የዩኒት 10 የሃይል ማመንጨት ስራው በየካቲት ወር ጀምሮ እስካሁን እየሰራ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ እስካሁን ከ540 ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ማመንጨት ተችሏል›› ብለዋል፡፡
ከዩኒት 10 ተርባይን ማመንጨት ስኬት በኋላ ሁለተኛውን ማመንጫ ዩኒት 09 ወደ ስራ በማስገባት ኢትዮጵያውያን ከግድቡ የሚያገኙትን የኤሌክትሪክ ሃይል ለማሳደግ ያለረፍት ሲሰራ መቆየቱንና ተግባሩም በስኬት መጠናቀቁን ጠቁመዋል፡፡
ዩኒት 09 ለሃይል ማመንጨት አስፈላጊ መሳሪያዎች ተከላ ተከናውኖ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ቀሪ ስራዎችን የማጠናቀቅ ስራ ተሰርቷል፡፡ የግንባታ ስራው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ፍተሻና ሙከራ ስራዎች ተገብቶ ከሐምሌ 30 ቀን ጀምሮ በሙሉ አቅሙ ወደ ትግበራ መግባቱንም አመልክተዋል፡፡
እስካሁን እስከ 250 ሜጋ ዋት ጭኖ የሙከራ ሃይል ማመንጨት ስራ ላይ ይገኛል፡፡ የሃይል ማመንጨት መሰረታዊ ጉዳይን ውሃው የሚንደረደርበት የከፍታ መጠን እንዲሁም የውሃው ፍሰት መጠን ይወስነዋል፡፡ ሃይሉ ከእነዚህ ሁለት መለኪያዎች ጋር ቀጥተኛ ቁርኝት አለው ነው ያሉት፡፡
ሙሉ ለሙሉ የግድቡ ግንባታ ከተጠናቀቀ እና የመካከለኛ የግድቡ አካል የከፍታ መጠን እስከ 640 ሜትር ከፍታ በሚደርስበት ጊዜ በሙሉ አቅም 375 ሜጋ ዋት ማመንጨት የሚችሉበት አቅም ደረጃ እንደሚደርስም ጠቁመዋል፡፡
አሁን በተፈጠረለት የከፍታ መጠን እያንዳንዳቸው እስከ 270 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ይኖራቸዋል ያሉት ኢንጂነር ኤፍሬም፤ ዩኒት 09 እና 10 ብቻ በድምሩ እስከ 540 እና 550 ሜጋ ዋት ድረስ ማመንጨት ይችላሉ ብለዋል፡፡
ይህ ማለት ደግሞ በሁለቱ ተርባይኖች ብቻ፤ የግልገል ጊቤ አንድ፣ የተከዜ እና የአዋሽ መልካሳ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ተደምረው በሙሉ አቅማቸው ቢሰሩ የሚያመነጩት ሃይል ማለት ነው፡፡ የቀሪ ተርባይኖችን ስራ በማጠናቀቅ ሃይል እንዲያመነጩ ለማስቻልም ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውንም ተናግረዋል፡፡
መንግስት ከ2010 ዓ.ም በኋላ የፕሮጀክቱን ሁኔታ በጥልቀት በመገምገም በወቅቱ በአገር ውስጥ ተቋራጮች ተይዘው የነበሩ የስራ ውሎች ተቋርጠው በምትኩ ሙያው እና አቅሙ ባላቸው ኩባንያዎች እንዲሰራ በመደረጉ ለተገኘው ውጤት አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ነው የተናገሩት፡፡
ኢንጂነር ኤፍሬም እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ አሁን ደረጃ ላይ እንዲደርስ እያንዳንዱ ዜጋ፤ በአነስተኛ ስራ ላይ ከተሰማሩ ጀምሮ እስከባለሃብቱ ድረስ በሞራል፣ በሙያ፣ በገንዘብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገውበታል፡፡ በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ ርብርብ ያደረጉበት ነው፡፡ በዲፕሎማሲውም ከፍተኛ ስራ ተሰርቶበታል፣ የመንግስትም ከፍተኛ ውሳኔ ያረፈበት የኢትዮጵያውያን ፕሮጀክት ነው፡፡
ዘላለም ግዛው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 6 /2014