በኢትዮጵያ አለባበስን የሚደነግግ ሕግ የለም። ሆኖም በአሰሪና ሰራተኛ አዋጅና በወንጀል ሕግ በሥራ ቦታቸው ላይ ጉንተላንም ሆነ ሌሎች ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃቶችን በሴቶች ላይ የሚፈፅሙ ክፍሎችን የሚቀጣ ሕግ አለ። ሕጉ ሴት አስተናጋጆች ከቀጣሪዎቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት የአሰሪና ሠራተኛ ግንኙነት መሆን እንዳለበት ይደነግጋል። በሕገ-መንግስቱም እንዲሁ ስለሴቶች መብትና ጥቃት ተቀምጧል። አሁን በመዲናችን አንዳንድ አካባቢዎች እንደሚስተዋለው ሴት አስተናጋጆች ከተቀጠሩበት ዓላማ ውጪ መጠጥና ምግብ ለማሻሻጫ እንዲውሉ እየተደረጉ ነው ከመባሉ ጋር ተያይዞ አንደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስፈላጊ ከሆነም በጥናት ላይ ተመስርቶ ሕግ ማውጣት ይችላል ሲሉ ምላሽ የሰጡን በመዲናችን አዲስ አበባ ብሎም በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በሚገኙ ሥጋ ቤቶችና ምግብ ቤቶች የሚያስተናግዱ ሴቶች በአሰሪዎቻቸውና በአስቀጣሪዎቻቸው አጭር ቀሚስ እንዲለብሱ የመገደዳቸው አጀንዳ መነጋገርያ መሆኑን አስመልክተን ስለ ሕግ መሰረቱና መፍትሄዎቹ ዙርያ ያነጋገርናቸው ወይዘሮ ሜሮን አራጋው ናቸው።
ወይዘሮ ሜሮን የአዲስ አበባ ሴቶችና ህፃናት ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የሴቶች ዘርፍ ኃላፊ ሲሆኑ፤ እንደወጣትነታቸው (ወጣቷን ኃላፊ) በአለባበስ ዙርያ የግል አስተያየታቸውንም ጠይቀናቸው አጋርተውናል። ጽሑፋችንን ከዚሁ እንጀምራለን።
ኃላፊዋ የግል አለባበሳቸውን በተመለከተ እንደማንኛዋም ወጣት ሴት የራሳቸው ምርጫ እንዳላቸው ነግረውናል። በአደኩበት፤ አስተዳደግ፤ በማምነው ዕምነትና በበባህሌ ስነ ምግባር የተሞላባቸው የምላቸው አለባበሶችን እከተላለሁ። ይሄ የኔ ትርጉም አሰጣጥ ለሌላኛው ትክክል ነው ማለት አይደለም ይላልም ወይዘሮ ሜሮን። እንደሳቸው ሁሉ ሌሎች ከወጣትነት በላይም ሆኑ ከወጣትነት በታች ያሉ ሴቶች የየራሳቸው ምርጫ አላቸው። በመሆኑም አለባበስ የምርጫ ጉዳይ ነው ማለት ይችላሉ።
ኢትዮጵያ የበርካታ ባህሎች፤ የበርካታ ሐይማኖቶችና እሴቶች ባለቤት ነች። እንደየ ክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ የአለባበስ ምርጫዎቻችን የተለያዩ ናቸውም ይላሉ ኃላፊዋ። የአለባበስ ምርጫ እንደየአስተዳደጋችን፤ እንደ ባህላችን፤ እንደ ምንኖርበት ሁኔታ ይወሰናልም ባይ ናቸው። ከዚህ ባሻገርም በአለባበሳችን ላይ ተፅዕኖ የሚያደርጉ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችም አሉ። ዓለም አቀፍ ፋሽኖችን መከተል፤ ዘመን አመጣሽ ልብሶችን መልበስ የየአንዳንዱ ግለሰብ ምርጫ እና መብት ነው።
ኃላፊዋ የአጭሩ ቀሚስ አጀንዳ በዋናነት ከሴቶች መብት መከበር፤ ከስርዓተ ጾታ ፍትሃዊነት፣ እንዲሁም እኩልነት ጋር ቀጥታ ግንኙነት አለው ይላሉ።
አለባበስ የግለሰብ የምርጫ ጉዳይና መብት ነው የሚሉት ወጣቷ የስራ ኃላፊ አስተናጋጅ ሴቶች በሥራ ቦታቸው ላይ አጭር ቀሚስ እንዲለብሱ በአሰሪዎቻቸው የመገደዳቸውን ቅሬታ በተለያየ መንገድ ማንሳታቸውንም ያወሳሉ። በዋናነት የአብዛኞቹ አስተናጋጅ ሴቶች ቅሬታ አጭር ቀሚስ በመልበሳችን ውርጩና ብርዱ እጅግ በከበደበት የዘንድሮ ክረምት ለተለያየ የጤና እክል እየተጋለጥን ነው የሚል እንደሆነም ይጠቅሳሉ። የጤንነታቸው ጉዳይ በሕክምና ከተረጋገጠና አሰሪያቸው አጭሩን ቀሚስ እንዲለብሱ የሚያስገድዳቸው ከሆነ በሕግ የሚያስጠይቀው እንደሆነም ይናገራሉ። አንዳንዶቹ አስተናጋጆች ”አጭሩን ቀሚስ አለብስም” በማለታቸው ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ይባረራሉ። እስከ መደብደብም የሚደርሱ አሉ። ይህን የምናገረው ዝም ብዬ አይደለም፤ ሴት አስተናጋጆቹ በተለያየ ጊዜ የገለፁትን እንዲሁም ከሴቶች ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ተቋማት የሰሩትን ዳሰሳ መሰረት አድርጌም ነው ይላሉ። እንደሳቸው ይሄ ተግባር ሕገወጥ ድርጊት ነው። አሰሪና ሰራተኛ ተስማምቶ የሚኖርበት ስምምነት አለ። ከዛ ስምምነት ውጪ ሰብዓዊ መብትንና ሰብአዊ ክብርን የሚነካ ጉዳይ ወንድም ሆነ ሴት ላይ ከተፈፀመ የሚቀጣ ሕግ አለን ይላሉ። ለአብነትም ስለዚህ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 1156/11ን ይገልፃሉ። በዚህ አዋጅ አንቀጽ 11 ላይ በግልጽ መስፈሩንም ያነሳሉ። እንደሳቸው ማብራሪያ ሴት አስተናጋጆች ከቀጣሪዎቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት የአሰሪና ሰራተኛ ግንኙነት ነው። በመሆኑም በሥራ ግንኙነታቸው ላይ በሚያጋጥማቸው እክል አሰሪዎቻቸውን መጠየቅ ይችላሉ። ከወንዶች ባልደረቦቻቸው ጋር እኩል ሥራ እየሰሩ እኩል ክፍያ የማይከፈላቸው ከሆነ እንዲሁም በሥራ ቦታቸው ላይ ጉንተላ፤ ወሲባዊ ትንኮሳና ሌሎች ጥቃቶች የሚደርስባቸው ከሆነ ሕጎች አሉ። አለባበሳቸውን ተከትሎ ለሚደርስባቸው አስገድዶ መድፈርም ሆነ ሌላ ጾታዊ ጥቃት የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ አንቀጽ 4 ላይ በግልጽ መቀመጡንም ይጠቅሳሉ።
አጠቃላይ ጾታዊ ጥቃት ሥራ ከተቀጠሩ በኋላ ጤናችን ላይ ችግር ስለሚያጋጥመን ይሄን ቀሚስ አንለብስም ስለዚህ ቀሚሱን በሱሪ እንቀይረው ወይም በሚመቸንና የጤና ሁኔታችን በሚፈቅደው እናድርገው ሲሉ አይ ጤናሽ እየተበደለም ቢሆን ቀሚሱን ለብሰሽ ስራሽን መሥራት አለብሽ የሚል አሰሪ ካለ በሕግ ተጠያቂ ይሆናል። ይሄ የወንጀል ሕጉና ሕገ መንግስቱም ላይ ሰፍሯል። ሕገ መንግስቱ ላይ ሴቶች ከወንዶች እኩል መብቶቻቸውን ኤክሰርሳይ (ተግባራዊ) ማድረግ አለባቸው ይላል። ከዚሁ ጋር ለእኩል ሥራ እኩል ክፍያ ማግኘት፤ ቅጥር ላይ፤ ዕድገት ላይ በተፈጥሮ ካላቸው ልዩነት ውጪ ከወንዶች እኩል ክብካቤ የማግኘትና የመጠቀም መብት እንዳላቸው ተደንግጓል።
እርግጥ ነው፣ አንዳንዴ እንደቢሮ ስናየው እንዲህ ዓይነት ህጎችን በማስፈፀም ሂደት ላይ ክፍተቶች ይገጥማሉ። ለአብነት አንዲት አስገድዶ መድፈር የደረሰባትን ሴት አስመልክቶ ያለውን ክፍተት ማሳያ ያደርጋሉ። እንደ ተቋም ባይሆንም በተቋም ውስጥ እንዳሉ ባለሙያዎች ሕብረተሰቡ ውስጥ ለሴቷ የሚሰጠው ቦታም በባለሙያዎች የሚንፀባረቅበትና ቢሯቸው ከሥር ከሥር እያረመ የሚሄድበት ጊዜ ብዙ ነው። ለአብነት እንዳነሱት አንዲት ሴት አስገድዶ መደፈር ደርሶባት ወደ ፍትህ አካላት በምትሄድበት ጊዜ ቀድሞ የሚነሳው ምን ለብሳ ነበር የሚለው ጥያቄ ነው። ለምን አመሸሽና ለምንስ ብቻሽን ሄድሽም የሚል ተበዳይዋን የሚያሸማቅቅ ጥያቄም አለ። አጭር ቀሚስ ለብሳ የነበረ በመሆኑ አነሳስታው ነው የደፈራት ያለም ባለሙያ ገጥሟቸው ያውቃል።
አስተናጋጆቹ አጭር ቀሚስ በመልበሳቸው ሙሉ በሚባል ደረጃ አካላቸው ግልጽ ነው የሚሉት ኃላፊዋ ኢትዮጵያ የተለያዩ ዕምነቶችና ባህሎች ያሉባት አገር መሆኗንም ያወሳሉ። ከዚህ አንፃር ሕብረተሰቡ አጭር መልበሳቸውን ላይፈልገው ይችላል። በዚህ የተነሳም ሊያገላቸው፤ ለባሾቹ ራሳቸውም ሞራላቸው የማይፈልገው ሁኔታ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ። አለባበሳቸውን ተከትሎ የሚደርስባቸው ወሲባዊ ትንኮሳ፤ ወሲባዊ ጥያቄ ሊቀርብላቸው፤ በአጠቃላይም ከተቀጠሩበት ዓላማ ውጪ የሆኑ ጉዳዮችን እንዲያስተናግዱና እንዲሸማቀቁ ይዳረጋሉ። ተገልጋዮቹ አገልግሎት የሚሰጥበት መዝናኛ ወይም ምግብና መጠጥ ቤት የሚመጡት አገልግሎቱን አግኝተው ለመሄድ ብቻ ላይሆን ይችላል። ከዚህ አንፃር አሰሪዎቻቸውም የያዙት ሴቶቹን እንደ ማሻሻጫ ማቅረብም ጭምር ነው። ሆኖም ሴት አስተናጋጆች ለምግብና መጠጥ ማሻሻጫ መልበስ (መዋል) የለባቸውም። ሴቶቹ በሚያስተናግዱበት ወቅት ሥራ ላይ የሚደርስባቸው ማንኛውም ተፅዕኖና የመብት ጥሰት አልፎ ተርፎም ሥራ ላይ በሚደርባቸው ጾታዊ ጥቃት የሕግ ከለላ አላቸውም ባይ ናቸው። በሥራ ገበታቸው ላይ ይሄንኑ መብታቸውን ከግንዛቤ እንዲያስገቡም ይመክራሉ።
ሆኖም አስተናጋጅ የሆኑ ሴቶች በሥራ ቦታዎቻቸው ላይ እንዲለብሱ የሚገደዱት አጫጭር ቀሚሶችን በተመለከተ ምን ህግ አለ፤ ወደ የሚለው ሲመጣ በኢትዮጵያ አለባበስን የሚደነግግ ሕግ የለም ይላሉ ኃላፊዋ። በመሆኑም እከሌ ይሄን ልብስ በመልበሷ ትክክል ነች፤ ወይም ትክክል አይደለችም ብሎ መፈረጅ አስቸጋሪ አንደሆነም ያወሳሉ።
ነገር ግን አሁን በተጨባጭ በምግብና መጠጥ ቤቶች፤ መዝናኛ ቦታዎች በሴት አስተናጋጆች ላይ የሚደርሰውን አጭር ቀሚስ ካለበሽ አታስተናግጂም፤ ከሥራ ትባረሪያለሽ የሚል በደልና ጥቃት አስመልክቶ በጥናት ላይ ተደግፎ ሕግ ማውጣት አስፈላጊም እንደሆነ ይጠቅሳሉ ኃላፊዋ። አስተናጋጆችን አጭር ቀሚስ ልበሱ ብሎ ማስገደዱ ሴቶች ላይ፣ እኩል ተሳትፏቸው ላይ፣ ጤና ጉዳያቸው ላይ እና መብቶቻቸውን ከማስከበር አንፃር ችግር ይፈጥራል ከተባለ እንደ ከተማ አስተዳደር ጥናት ተሰርቶ በጥናቱ መሰረት ሴቶች በአሰሪዎቻቸው ተገድደው በሥራ ቦታቸው ላይ አጭር ቀሚሱን ለብሰው መሥራት የለባቸውም የሚል ሕግ ማውጣት እንደሚቻልም ያስረዳሉ።
‹‹በጥናት ላይ ተመስርቶ ሕግ ማውጣት አስፈላጊ ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ሜሮን በጥናት ላይ የተደገፈ ሕግ በሌለበት ሁኔታ አሰሪዎቻቸውን ወይም ራሳቸውን አስተናጋጆቹን ጭምር ይሄን ልብስ ለምን ለበሳችሁና ልበሱ አላችሁ ብሎ መጠየቅ እንደማይቻልም ያስገነዝባሉ። ነገር ግን አንዲት አስተናጋጅ አሰሪዋን በዕወቀቷ፣ በጉልበቷ የማስተናገድ፤ ቀጣሪው ድርጅት ደግሞ በአግባቡ እስካገለገለች ድረስ በውሉ መሰረት ክፍያዋን የመፈፀም ግዴታዎች አሉባቸው። ሴት አስተናጋጆች ከዚህ አልፈው መብተን የሚነኩ ጉንተላዎችን፤ ጾታዊና ወሲባዊ ጥቃቶችንና ትንኮሳዎች ሲደርሱባቸው በአገራችን ወንጀል ህግ ስነስርዓት መጠየቅና መብቶቻቸውን ማስከበር ይችላሉም ብለዋል ወይዘሮ ሜሮን።
በተጨማሪም፣ አስተናጋጆችም ሆኑ ሌሎች ሴቶች ተገድደው ለጤና እና ለመብት ጥሰትም በሚዳረጉበት ጊዜ ቢሮው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር ተባብሮ ይፋ ባደረገው በ991 ነፃ የስልክ መስመር ባሉበት ሪፖርት ማድረግ እንደሚችሉም ያስገነዝባሉ። ቢሮአቸውም በዚሁ ዙርያ ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
‹‹ፍትህ ቢሮ ከእኛ ጋር የሚሰራ መንግስታዊ ተቋም ነው›› የሚሉት ወይዘሮ ሜሮን አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ላይ በተለይ ጥብቅና የሚያስፈልጋቸው፤ የሕግ ክርክር የገጠማቸው፤ መብቶቻቸው የተጣሱ ሴቶች፤ ህፃናትና አካል ጉዳተኞች በመጡ ጊዜ ከአዲስ አበባ ፍትህ ቢሮ ጋር በመሆን መብቶቻቸው እንዲከበር፤ ፍርድ ቤት ላይ ነፃ ውክልና እንዲኖራቸው አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ያወሳሉ።
አስተናጋጅ ሴቶች አጭር ቀሚስ እንዲለብሱ የሚገደዱት በሕገወጥ ደላሎች ጭምር በመሆኑ ከዚህ ጋር ተያይዞ ቢሯቸው ምን እየሰራ እንደሚገኝ ለጠየቅናቸው ጥያቄም ምላሽ የሰጡን ወይዘሮ ሜሮን ”ሕገወጥ ደላሎችን መከታተልና መቆጣጠር የቢሮው ኃላፊነት አይደለም። ሆኖም በዚህ ሂደት ውስጥ ወደ አረብ አገር የሚሄዱ ሴቶች ገንዘባቸውን ያጣሉ። ይታለላሉ። ከዚህም አልፎ ለወሲብ ጥቃት የሚጋለጡበት ሁኔታ አለ። እናም ለእነዚህም ሆነ በየትኛውም ደረጃ ለሚገኙ ሌሎች ሴቶችም መብቶቻቸው እንዳይጣሱ ለማድረግ የሕግ ከለላ ይሰጣል። ከሌሎች ቢሮዎች ጋር በመቀናጀት ችግሩ እንዲፈታ የማድረግ ሥራም እየሰራ ይገኛል። የተዛባ የሕብረተሰብ አመለካከትን ማስተካከል፤ ሴቷን በትምህርት፤ በኢኮኖሚ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ማብቃትና ማሳተፍ እየሰራቸው ካሉት መካከል ይጠቀሳሉ። ሆኖም የሴቶች ጥያቄ፤ የሴቶች የስርዓተ ጾታ ፍትሃዊነትና እኩልነት ጉዳይ ሴቶች ላይ በሚሰራ መዋቅር ብቻ ይፈታና ጥያቄው ይመለሳል ማለት የዋህነት ነው። የሴቶች ጉዳይ ትልቅ አገራዊ አጀንዳ እንደመሆኑ መጠን፤ የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑም ሊተኮርበት የሚገባ መሆኑን በመግለጽ ሀሳባቸውን አጠናቀዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3/2014 ዓ.ም