ስብዕናቸው ማርኮን አልያም የተለየ ተፅዕኖ ፈጣሪነታቸውን ተመልክተን የምንከተላቸው ሰዎች በእኛነታችን ላይ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ቀላል አይደለም:: ይህ ተፅዕኖ በጎም መጥፎም ውጤት እኛ ላይ ሊያስከትል ይችላል:: ለዚህም ነው ለእኛ አርዓያ ይሆናል የምንለው ሰው ጠንቅቀን ማወቅ የሚኖርብን::
ዛሬ ላይ ማኅበራዊ ግንኙነታችን ረግቦ በአንፃሩ የማኅበራዊ ድረ ገፅ ትስስራችን ጠብቋል::በዚህም ምክንያት ለእኛ በጎነት ያጎናፅፉናል፣ የሕይወት ተሞክሯቸውን ያጋሩናል፣ በመልካም ያንፁናል፣ የማናውቀውን ያሳውቁናል፣ መረጃም ይሰጡናል የምንላቸው ግለሰቦች ወይም ቡድኖችን የምንከተለው ከዚሁ ዘመን አፈራሽ ማኅበራዊ ትስስር ገፅ ሆኗል::
እነዚህ የምንጠቀምባቸው ወይም ምንከተላቸው የማኅበራዊ ትስስር ገፆች ለእኛ እንደማኅበረሰብ በጎ ተፅዕኖ ማሳደር ካልቻሉ ነገሮች አስቸጋሪ ሊሆኑ ይችላሉ:: በሳይበሩ ዓለም እነማን ምን ዓይነት መልካም ነገር ላይ አዘወተሩ? እነማንስ ያገኙትን መልካም አጋጣሚ ለራሳቸው እኩይ ዓላማና ተግባር መጠቀሚያ አደረጉት? የሚለውን መመርመር ይገባል:: እዚሁ መድረክ ላይ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑና ማኅበረሰብ አንቂ ነን የሚሉ ግለሰቦች ራሳቸው መንቃታቸውን ማረጋገጥ ይገባል::
ለአገር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ በጎ አበርክቶ ይኖረን ዘንድ መንቃታችን በጎ ነው:: በብዙ ጉዳዮች ላይ መንቃት የሚፈልግ ማኅበረሰብ አለን:: ስለ በጎ ተግባርና አሳቤ ንቁ የሚያደርገን እንፈልጋለን:: ብዙዎቻችን በጉዳዮች ላይ ያለን ምልከታ ገና ብዙ መለወጥ የሚገባው ነውና መንቃት ይገባናል:: በብዙ ጉዳዮች እንድንነቃ የሚያደርገንና ንቃትን የሚያወርሰን እንሻለን:: ነገር ግን ላንቃችሁ የሚለን ራሱ ያልነቃ ከሆነ አሳሳቢ ነው::
ዘመኑ በፈጠራቸው ልዩ ልዩ የማኅበራዊ ትስስር ገፆችና መገናኛዎች አንቂ ነን የሚሉ ተበራክተዋል:: በእኛ ላይ “አንቂ ነኝ” ብሎ ራሱን የሚሾም በዝተል:: መብዛቱ በጎ ነበር፣ ማኅበረሰብ አንቂ ነን ብለው የሚያነሱት ሀሳብ እንኳን ሊያነቃ አደንዛዥ መሆኑ ነው የከፋው:: ያልነቁ አንቂዎች መበራከታቸው ነው የሚያሳስበው::
‹‹ስለማኅበረሰብ ሁለንተናዊ ለውጥ እሟገታለሁ፤ ማኅበራዊ ኃላፊነቴን እወጣለሁ›› የሚል ግለሰብና ቡድን የአንድን ማኅበረሰብ ስያሜ ተላብሶና “ማኅበራዊ አንቂ ነኝ” ብሎ ሲያበቃ ማኅበራዊ ቀውስ ፈጣሪ እየሆነ ተቸግረናል:: በእርግጥ ሁሉንም መኮነን ተገቢ አይደለም:: ከኃላፊነት የራቁና የራሳቸውን ጥቅም ለማሳደድ ብቻ የሚሠሩትን ግን እየተመለከቱ በዝምታ ማለፍ አይቻልም:: በኃላፊነት ስሜት በጎነትን የሚሠሩ መመስገን እንዳለባቸው ሁሉ ከመስመር የወጡት መሸንቆጥ አለባቸው እያልኩኝ መሆኑ ይሰመርበት::
ብዙዎቹ የማኅበረሰብ አንቂዎች‹‹ሕዝቤ ንቃ›› ብለው የሚያስተጋቡት መፈክር ከመንቃት የሚያርቅ፣ ‹‹ንቁ ዜጋ እንፍጠር›› ብለው የሚሞግቱበት ጉዳይ ፍካትን የሚያደበዝዝ ሲሆን ታዝበናል:: በርካቶቹም ይዘው የሚመጡት ሀሳብ ለማኅበረሰብ የሚበጅ ሳይሆን እርስ በርስ የሚያፋጅ፣ ከማስተሳሰር ይልቅ የሚነጣጥል ሆኗል::
ዛሬ ላይ ማንኛውም ግለሰብ ቤቱ ቁጭ ብሎ በማኅበራዊ ድረ ገፆች (ፌስቡክ፣ ዩቱዩብ፣ ኢንስትግራም፣ቴሌግራም) እና በመሳሰሉት ዓለምን መድረስ ይችላል:: ይህ መልካም እድል ሆኖ ሳለ ይህንን መልካም እድል በመልካም መንገድ ለመጠቀም የሚጥሩት ግን ጥቂቶች ናቸው::
አብዛኛው ማኅበረሰብ ለነዚህ በተለያየ አጋጣሚ እውቅና ቸሯቸዋል::አንድ ሰሞን በአጋጣሚ ከፍ አድርጎ ላሰባቸው ወደዝቅታ የሚያደርስ ሀሳቡን አጋጣሚ ተጠቅሞ ያራግፋል:: በማኅበረሰቡ ዘንድ እጅግ የሚታወቁ የሚሉትና የሚለጥፉት ሁሉ ሌሎች ትክክል ናቸው ብለው የሚያምኑባቸው ግለሰቦች ጭምር ከትክክለኝነት ብዙ የራቁ መረጃዎች እንካችሁ ሲሉ ይስተዋላሉ::
የማኅበራዊ ትስስር ገፆችን በወጉ መገልገል ቢቻል የማኅበረሰቡን ንቃተ ሕሊና ከፍ ለማድረግና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያለውን ግንዛቤ ለማስፋት ይጠቅማል:: ከስሜት የራቀና ምክንያታዊነት የተላበሰ ትውልድ ለመፍጠርም ምቹ ናቸው:: ችግሩ ግን በሌላ መልኩ እልፍ ምክንያት አልባዎች ማፍሪያ በርካታ የተሳሳተ መረጃዎች ማቅረቢያ መሆናቸው ነው የከፋው:: ማኅበራዊ ድረ ገፆች ከሁሉም መረጃ አውታሮች በፈጠነ መልኩ ሰዎች ጋር በተለያየ መልኩ መረጃዎችን ያደርሳሉ:: በቴክኖሎጂ ታግዘው በስርጭት እና አጠቃቀም ቀለው በብርሀን ፍጥነት ከአንዱ ወደአንዱ መረጃዎችን ያደርሳሉ::
ታዲያ በዚህ ሁሉ የሀሳብ ዝውውር ውስጥ በተለይ የማኅበረሰብ አንቂዎች መልካም ነገር ለሌሎች ማቅረብ ሲጠበቅባቸው የእነሱን በጎ ያልሆነ አመለካከት እና እሳቤ ሌላው ላይ ለመጫን ሲሞክሩ ማየት አንቂዎች እውን ሕዝብን ማንቃት ነው ተግባራቸው? ብሎ መጠየቅ ይኖርብናል::
በቀላሉ ከፍተን ወደላይና ወደታች እየተረተርን ማን ምን አለ? በምንልበት ገጽ ላይ የምናገኘው መረጃ ሁሉ እውነት ነው ብለን ከተቀበልን ችግር ነው:: መረጃውን ያቀረቡት ግለሰቦች ዓላማቸው ምንድነው? ብለን ካልመረመርን ስህተት ላይ እንወድቃለን::
“የማኅበረሰብ አንቂ ነኝ” ብሎ እራሱን የሰየመው አንቂ ግለሰቦችን አልያም ተቋማትን ማነውር፣ ያለ መረጃና ማስረጃ ማብጠልጠል፣ በሚዲያ ቀርቶ በድብቅ ሊነገሩ የማይገቡ የታፈሩ ቃላትን እየተጠቀሙ የማኅበረሰብን ባህል እና እምነት በሚፃረር መልኩ ለክፋት በማነሳሳት ተግባር ላይ ይገኛሉ::
ማኅበራዊ አንቂዎች ሀገርና ሕዝብ የሚጠቅም መልካም ነገሮችን በማንሳት ሕዝብ እንዲወያይ በጉዳዮቹ ላይ ተነጋግሮ እንዲግባባ ማድረግ ዋንኛው ሥራቸው መሆን ይገባዋል:: ነገር ግን ከዚህ በተለየ መልኩ ለሕዝብ አለመግባባትና እርስ በርስ ግጭት መፈጠር ምክንያት የሚሆኑ ጽሑፎች በገፆቻቸው ላይ ያለ ሀፍረት ያሰራጫሉ::
እነዚህ ማኅበራዊ ሚዲያን ተጠቅመው አካባቢያዊና ዓለማዊ ሁናቴን በቁጥጥር ውስጥ በማዋል ሕዝብን በተሳሳተ መልኩ በማነሳሳት የተዛባና ተጨባጭ ያልሆነ መረጃ በመስጠት እነሱ በስውር የሚፈልጉትን ዓላማ ያስፈፅማሉ:: ማኅበረሰቡ በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ትክክለኛነትና እውነታ ላይ ያልተመሠረተ መረጃ በመታለል በግብታዊነት የተሳሳተ እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ ያደርጋሉ::
የሚገርመው ደግሞ ከበጎ ሀሳብና እይታ አጋሪዎች በላቀ መልኩ የእነዚህ ተከታይ መብዛቱ ነው:: ከልክ በላይ የተዛባና የተሳሳተ መረጃ የሚቀብሉትና የሚቀበሉት በዚህ ገጽ እጅጉን ንቁ ተሳታፊ ናቸው:: ያለ ትክክለኛ ምክንያት ሀሳባቸውን አቅርበው ወደተሳሳተ መንገድ የሚጠቁሙ የሚከተላቸውና የሚያጅባቸው እልፍ ነው::ለዚህም ነው የሚፈጥሩት አሉታዊ ተፅዕኖ የሚገዝፈው::
ሰሞኑ አገር ምድሩን ግራ የሚያጋባ መረጃን በመፈብረክ ለጊዜውም ቢሆን ብዙዎችን ያሳሳተ እውነታነት የሌለው መረጃቸውን ለብዙዎች አዳርሰው አገርና ሕዝብ በመንግስት ላይ እምነት እንዳይኖረው የሚደርጉ ግለሰቦች ለዚህ ዋንኛ ማሳያዎች ናቸው:: እነዚህ አንቂዎች ዛሬም ከተሳሳተ ተግባርና ከእኩይ አላማቸው ሊታቀቡ አለመቻላቸው ሲታይ ምን ያህል ለአገርና ለህዝብ ለውጥ እንቅፋት መሆናቸውን ማየት ይቻላል::
ማኅበረሰብ አገርን ይመስላልና እጅጉን ንቁ ለአገር መከታና ጥላ የሆነ ትውልድ ይበረክት ዘንድ በዘመኑ እንደ አሸን የፈሉት የማኅበራዊ ድረ ገፅ ተዋናዮች በጎ ሚናና በጎ ማንቃት ወሳኝ ነው:: ተጨባጭ በሆነ መረጃ ላይ ተመሥርተው ለሕዝብና ለአገር ጠቀሜታቸው ተረጋግጠው የሚዘዋወሩ መረጃዎች መበርከታቸው ግድ ይላል::
ከስሜት እና ጊዜያዊ ጥቅምን ችላ ብሎ የአገርና የሕዝብ ደህንነትን የሚያረጋግጥ መረጃ መስጠት ይገባል:: አገር በዜጎች መልካም አስተሳሰብ የምትቃና ናት:: በተሳሳተ እሳቤና በክፋት አስተሳሰብ ደግሞ የምትለዝብ:: ማህበራዊ ንቃት እንዲሰርፅና ለውጥ እንዲመጣ ማህበረሰብ አንቂ ማህበራዊ ሀላፊነትን ሊላበሱ ይገባል:: ቸር ይግጠመን::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/ 2014