በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የካቲትን የሚያክል ብዙ ታሪኮች የተፈጸሙበት ወር የለም ቢባል ስህተት አይሆንም። ኀዘኑም ደስታውም የካቲት ላይ ጫን ይላል። የስርዓትም የመንግሥትም ለውጥ የተከሰተውና የተጠነሰሰው የካቲት ላይ ነው ቢባል አሁንም ከዕውነታው ፈቅ ማለት አይሆንም።
የንጉሡ ስርዓት በወታደራዊው ደርግ የተቀየረው በየካቲቱ አብዮት መሆኑን ስናስብ፤ ራሱ ደርግም በኢህአዴግ የተተካው በየካቲት ወር ላይ በተጀመረ ትግል መነሻ እንደሆነ ስናጤን የካቲት እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንዳች ቁርኝት ያላቸው ያስመስላቸዋል። በቅርቡም ቢሆን የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ መወሰናቸውን ይፋ ያደረጉት በዚሁ በየካቲት ወር መሆኑን ልብ ይሏል።
የየካቲት ፖለቲካ አገራችንን ወደፊትም ወደኋላም አስጉዟታል። ሰሞኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐብይ አህመድ እንዳሉት፤ የዚህ አገር የፖለቲካ ስብራቶችን በጥምረትና በፍጥነት ማከም ያስፈልጋል። የአገራችን የግራ እና የቀኝ ፖለቲካ ዘዋሪዎች ብዙዎቹ የድህረ የካቲት 1966 ዓ.ም ውጤቶች ናቸው። በእነዚህ ተዋንያን የተሰበረው የአገራችን ፖለቲካ መጠገን ካለበት በድህረ መጋቢት 2010 ዓ.ም የፖለቲካ ዑደትና ፖለቲከኞች ነው እንላለን።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ስብራት አለ ሲሉ ባላቸው የአደባባይም የደህንነትም መረጃ ተንተርሰው ነው ብለን እናምናለን። ይህንን ስብራት ማከም ደግሞ በዋናነት የእርሳቸው እና የመንግሥታቸው ሥራ ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም ታማሚ የየራሱን ህመም ማከም ከራሱ መጀመር እንዳለበት ማወቅ አለበት። እኔ ብቻ እና የእኔ ብቻ ይደመጥ፤ ይመረጥም የሚል ስግብግብነት፣ ዋልታ ረገጥነት፣ ልግመኝነት፣ የዛሬን እንጂ የትናንትን እና የነገን አለማሳብ ዞሮም አለማየት የፖለቲከኛ ነን ባዮች ስብራቶች ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግልጽ አድርገዋል።
ችግርን ማወቅ ለመፍትሔ ግማሽ መንገድ ስለሆነ ሁሉም ተዋንያን ከደሙ ንጹህ ነኝ ከሚል አባዜ ወጥቶ የቱ ጋር ነው የቆምኩት ብሎ ራሱን እና ፓርቲውን ሊፈትሽ ይገባል። ሁሉም ነገር አገር ሲኖር መሆኑን ተረድቶ የትናንቱን ስብራት ዛሬ ለመጠገን መነሳት አለበት። ይሄን ማድረግ ካልቻለ ነገን መጓዝ አይችልም። መጓዙ ቀርቶ ስለመቆሙም እርግጠኛ መሆን አይችልም። የሌላው አገር ቀርቶ የአገራችን የፖለቲካ ታሪክ የሚነግረን ቁጭ ብለው የሰቀሉት ቆመው ለማውረድ እንደሚቸግር ነው። ስለሆነም ለስብራቶቹ ህክምና ጊዜው ዛሬ ነው፤ ጊዜው አሁን ነው።
ስብራቶቻችን በመጋቢት ፖለቲካ ይታከሙ ማለታችንም በብዙ አሳማኝና በቂ ምክንያት ነው። 27 ዓመታት አገሪቷን ያስተዳደረው ኢህአዴግ በውስጡ ያደረገውን ትግል ቋጭቶ አዲስ ሊቀመንበር የመረጠው በመጋቢት 18 ቀን፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ በምክር ቤት ያሾመውም መጋቢት 24 ላይ ነው። የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትርና መንግሥታቸው የፖለቲካ ጉዞ የጀመረውም በመጋቢት ነውና፤ በየካቲት ሆነ በሌሎች ወቅቶች የተከሰቱ ስብራቶች በመጋቢቱ የመደመርና የይቅር ባይነት ብሎም ያለፈውን እንርሳ እንደማመጥ ፖለቲካ ይታከም።
የአደባባይ ጩኸቶች ወደ አዳራሽ ይግቡ። ስብራቶች መጠገን ካለባቸው በአዳራሽ ፖለቲካ በድህረ መጋቢት 2010 የፖለቲካ መንገድ እንጂ በቅድመ መጋቢት 2010 ዓ.ም የፖለቲካ አስተሳሰብ እና በአደባባይ ሁከት አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም፤ ጊዜውም አይደለም።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ መጋቢት 21/2011