
የፊልሙ ዘርፍ ትሩፋት
ፊልም የአንድ አገር በጎ ገፅታን ከመገንባትና ባህልን ከማስተዋወቅ ባለፈ የአገር ኢኮኖሚን በማሳደግ በኩል ያለው ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም ነው ያደጉ አገራት ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የሚሰሩት፡፡ አገራቱ በፊልሞቻቸው ሁለንተናዊ ለውጣቸውን፣ ስልጣኔና ባህላቸውን፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የደረሱበትን ደረጃ ማሳያ መሳሪያቸው አድርገው ይጠቀሙበታል፡፡ በተጨማሪም ኢኮኖሚያቸው በዚሁ ዘርፍ በመደገፍ ትልቅ ጥቅም ተቀዳጅተዋል፡፡
ሆሊውድ የተሰኘው እውቁ የአሜሪካ የፊልም ኩባንያ ከሶስት ፊልም ሰሪ ድርጅቶች ማለትም ከዲስኒ፣ ኔትፍሌክስና ዋርነር ሚዲያ ከተሰኙ የፊልም ስራ ድርጅቶች ብቻ እኤአ በ2019 ከ41.1 ቢሊዮን ዶላር በላይ አመታዊ ገቢ መሰብሰብ ችሏል፡፡ ይህን በኢትዮጵያ ብር ዓይን ካየነው ደግሞ 2 ትሪሊዮን አካባቢ ማለት ነው፡፡ በሶስት የፊልም ኩባንያዎች ብቻ ይህን ያህል አመታዊ ገቢ ያገኘችው አሜሪካን፤ አጠቃላይ አመታዊ የፊልም ገቢዋ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ መገመት አይከብድም ፡፡
ይህ የፊልሙ ዘርፍ በትኩረት ከተሰራበት የሚያስ ገኘውን ከፍተኛ ኢኮኖያዊ ጠቀሜታ ማሳያ ተደርጎ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ከሁሉም የኪነጥበብ ዘርፎች ታላቅና በትርፋማነቱ የሚጠቀሰው የፊልም ኢንዱስሪ፤ አገራዊ ገጽታን ከመገንባትና የማህበረሰብን አመለካከት በበጎ መልኩ ከመቅረፅ ባሻገር የሚያበረክተው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ቀላል አይደለም፡፡ ይህን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ዘርፍ በአገራችን ያለበት አሁናዊ ሁኔታ በወፍ በረር ለመዳሰስ አስበን ብዕራችንን አነሳን፡፡
የፊልሞቻችን አሁናዊ ሁኔታ
የብዙ ጥበባት መፍለቂያና የጠቢባን አገር የሆነችው ኢትዮጵያ አገራዊ ገፅታዋ መገንባት፣ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታን ማሳደግና የማህበረሰቡን አስተሳሰብ ጥበባዊ በሆነ መልኩ መቅረፅ የሚያስችለውን የፊልም ጥበብን የመጠቀም ሰፊ ዕድል አላት፡፡ ነገር ግን ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት አነስተኛ በመሆኑ እድገት ማሳየትና የሚጠበቅበትን አስተዋፅዖ ማበርከት አልቻለም፤ በዚህም ምክንያት በተደገጋሚ ሲወቀስ ቆይቷል፡፡
ፊልም አገርን መገንባት የሚችል ታላቅ ጥበብ መሆኑን የሚናገረው የፊልም ባለሙያው ደራሲና አዘጋጅ ግዛቸው ገብሬ ነው፡፡ ይህን የተረዱ አገራት ልዩ ትኩረት ሰጥተው በፊልማቸው አለምን መድረስ እንደቻሉ ያስረዳል፡፡ ፊልም አገራዊ ኢኮኖሚን ከማሳደግ ባለፈ ኢትዮጵያ ያላትን ውብ ተፈጥሯዊ ገፅታ፣ ባህልና ልዩ ልዩ እሴቶቿን ለሌላው ዓለም ለማሳወቅ ልትጠቀምበት እንደምትችልም ያነሳል፡፡
በእርግጥ ይህ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ደረጃ እድገቱ ጅማሮው ላይ እንደመሆኑ፤ በአገር ደረጃ ከፊልሙ ዘርፍ የሚገኘው አጠቃላይ አገራዊ ገቢ አመርቂ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ይህንን ለማወቅ ብዙ ጥናቶች ማድርግ ቢጠይቅም፤ በዚህ ዘርፍ የተሰማሩ አያሌ የፊልም ስራ ድርጅቶችና ባለሙያዎች በመኖራቸው የተፈጠረው የስራ ዕድል ከኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታው ባለፈ በግልፅ መመልከት ያስችላል፡፡
ደራሲ፣ ዳይሬክተርና ፕሮዲዩሰር ግዛቸው ገብሬ በድርሰት ከ40 በላይ ፊልሞች በዝግጅትና በፕሮዲዩሰርነት ደግሞ 10 ፊልሞች በማዘጋጀት ለህዝብ አቅርቧል፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ጥሩ መነቃቃት መፍጠር ችሎ የነበረው የፊልሙ ኢንዱስትሪ፤ ዛሬ ላይ በብዙ ችግሮች ወደኋላ መጎተቱን ባለሙያው ይናገራል፡፡
አሁን ላይ የፊልም ተመልካች ከሲኒማ የጠፋበትና የፊልም ስራው እጅግ የተቀዛቀዘ መሆኑን የሚያስረዳው ግዛቸው፤ በዚህ ከቀጠለ ዘርፉ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ አያጠያይቅም ብሏል፡፡ በተለያዩ ምክያቶች በፊት ሲኒማ ይመለከት የነበረው ተመልካች አሁን ላይ በኢንተርኔት ፊልሞችን ማየት የጀመረበት ወቅት መሆኑንም ያስረዳል፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ጥሩ ፊልሞች ተሰርተው ለተመልካች እንዳይቀርቡ አድርጓል፡፡
ለኢንተርኔት ተብለው የሚሰሩ ስራዎች የጥራት ደረጃቸው አነስተኛ መሆናቸውን የሚናገረው ግዛቸው፤ ይህ ሙያውን በእጅጉ የሚጎዳው መሆኑን ያነሳል፡፡ ለፊልም ገባያው መቀዛቀዝ ዋነኛ ምክንያት ተደርገው የሚነሱ ሶስት ዋና ዋና የፊልሙ ዘርፍ አገራዊ ችግሮች አሉ፡፡
እንደ ዋነኛ ችግር አድርገው ባለሙያዎች የሚጠቅሷቸው ጉዳዮች ቢኖሩም በዋናነት የሚነሱት ግን የፊልም ስራ ከጥራት አንፃር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መሄድ፣ ተመልካቹ ከሲኒማ ቤት ይልቅ ወደ ኢንተርኔት ፊልም ማምራቱና በፊልም ስራው ላይ ያሉ የአሰራር ግድፈቶች ይጠቅሳሉ፡፡
ባለሙያው ግዛቸው ቀደም ባሉት ዓመታት ይሰሩ የነበሩት ጥሩ ፊልሞች መሰራት እና ወደ ሲኒማው መቅረብ የቀነሱበት ምክንያትም የተመልካቾች ከሲኒማው መራቅ መሆኑን ያነሳል፡፡ በዚህም ምክንያት ከጥቂት አመታት በፊት እጅግ አመርቂ የነበረው የፊልም ስራ ዛሬ ላይ እጅግ መዳከሙን በማስረጃዎች ይጠቅሳል፡፡
አሁን ላይ አዳዲስ ፊልሞች ተሰርተው ለሲኒማ ቤቶች ለእይታ ቢቀርቡም ተመልካች እስካሁን እንዳልተመለሰ የሚገልፀው የፊልም ፕሮዲዩሰር አማን ደረጄ፤ ዘርፉ ትኩረት እንደሚያሻው ያስረዳል፡፡ ለፊልም ዘርፍ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ከሁለት አመት በፊት የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ትልቅ ተፅዕኖ ፈጥሮባቸው ማለፉን የሚያስታውሰው አማን፤ ይህ ተፅዕኖ ዛሬም እንዳልተቀረፈ ያስረዳል፡፡
በየሲኒማ ቤቶች ወይም ፊልም ማሳያዎች በር ላይ ተሰልፎና በርከት ብሎ ይታይ የነበረው ተመልካች ዛሬ ላይ ከሲኒማ ቤት ደጃፍ ጠፍቷል ፡፡ ፊልም ማሳያ ቤቶቹ ለሌላ አገልግሎት መዋላቸውም የዘርፉን መቀዛቀዝ ማሳያ ነው፡፡ ከኮሮና ወረርሽኝ በኋላ መልሰው ወደ ስራ የገቡት ሲኒማ ቤቶች ቀድሞ የነበረውን ያህል ተመልካች አላገኙም፡፡
ቀድሞ ከፊልም ያገኙት የነበረ ገቢ ቀርቶባቸዋል፡፡ ሰራተኞቻቸውንም ለመቀነስና ከስራ ለማሰናበት ተገደዋል፡፡ ማቲያስ አለነህ አዲስ አበባ ቦሌ አካባቢ በሚገኝ አንድ ሲኒማ ቤት በፊልም ገምጋሚነትና በሲኒማ ቤቱ አስተባባሪነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ በተከሰተ ጊዜ ሲኒማ ቤቱ መዘጋቱንና ከዓመት በኋላ ቢከፈትም በፊት የነበሩት የፊልም ተመልካቾች ወደ ሲኒማው መመለስ እዳልተቻለ ያስረዳል፡፡
በዚህም የሲኒማ ቤቱ ገቢ መቀነሱንና ሰራተኞችም እንደተቀነሱ ያነሳል፡፡ እንደ ማትያስ የመቀዛቀዙ መነሻ የኮሮና ወረርሽኝ ይሁን እንጂ፤ ከወረርሽኙ በፊትም የፊልም ተመልካች ቁጥር እየቀነሰ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ፊልሞች ከይዘትና ከታሪክ አንፃር ተመሳሳይ ሆነው በተደጋጋሚ መቅረባቸው ለተመልካቹ መራቅ ምክንያት ሊሆን ይችላል የሚል ሀሳብም አለው፡፡
ለሲኒማ ቤቶች ተመልካች ማጣትና ለፊልሙ ገበያ መቀዛቀዝ ምክንያት ተደርጎ በማቲያስ በቀረበው ሀሳብ ሌላኛው የዘርፉ ባለሙያው ግዛቸው ሙሉ በሙሉ ባያምንበትም እንደ አንድ ምክንያት ግን ሊወሰድ እንደሚችል ይናገራል፡፡ ይህንንም ውድቅ የሚያደርግ ማሳያም አለው። ፊልሞች በጥሩ ታሪክና ጥሩ በሆነ ሙያዊ ክህሎት ተሰርተው ለተመልካች ቀርበው የማይታዩበትን አጋጣሚም አያይዞ ያነሳል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥሩ ስራ መሆኑ በተደጋጋሚ የተነገረለትና በአገራችን ከተሰሩ ጥሩ ፊልሞች ተርታ የሚመደበው “ጤዛ” የተሰኘው ፊልም በአገር ውስጥ የነበረው እይታ የፊልሙን ታላቅነት የማይመጥን እንደነበር ያስረዳል፡፡
ፕሮዲዩሰሩ አማን፣ በፊልም ገበያው ላይ መቀዛቀዝ መፈጠሩ በራሱ ጥሩ ፊልም ተሰርቶ ወደእይታ እንዳይቀርብ አድርጓል የሚል ራሱን መከራከሪያ ነጥብ ያስቀምጣል። ይህም ፊልም ሰሪው በቂ በጀት መድቦና ጥሩ ባለሙያዎችን አሳትፎ ከሰራ በኋላ ለፊልሙ ያወጣውን ወጪ የመመለስ ስጋት እንዲጋረጥበት በማድረጉ ደረጃቸውን የጠበቁ ፊልሞች እንዳይሰሩ መሰናክል መሆኑን ያስረዳል፡፡
በኢትዮጵያ በመዝናኛው ዘርፍ እንደ አጠቃላይ ሰፊ ክፍተት ይስተዋላል። እንደ አገር ለፊልም ስራ መነሻ የሚሆን ቱባ ባህልና እሴት ሞልቷል። ኢትዮጵያ ምቹ የሆነ ውብ ተፈጥሯዊ ገፅታና የፊልም ኢንደስትሪው ሰፊ ገበያ እያለው ከአገር አልፈው በአለማቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ፊልሞች በብዛት መሰራት አለመቻላቸው ሁሉንም ያስቆጫል፡፡
በእርግጥ ከዘርፉ ካለው ትልቅ ተጽእኖ የመፍጠር አቅም አንፃር እስካሁን የተሰሩ ፊልሞች የፈጠሩትን በጎ ተፅዖኖ ማየት አለመቻል ፊልም በኢትዮጵያ ገና ያልተጀመረ ያህል እንዲቆጠር ቢያደርግ አይገርምም፡፡ ለፊልም ባለሙያውና ለዘርፉ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ልዩ ትኩረት መስጠት ቢቻል ግን በእርግጥም የዘርፉ ብዙ ጠቀሜታ ማረጋገጥ በተቻለ ነበር።
የዘርፉ አዲስ ክስተቶች
የሲኒማው ዘርፍ መቀዛቀዝ በስፋት በሚወራበት በዚህ ወቅት ለየት ባለ የአቀራረብ ስልትና አዲስ በሆነ መንገድ ብቅ ማለት የጀመሩ የቴሌቪዥን ድራማዎች ለፊልሙ ዓለም ተስፋ የፈነጠቁ ይመስላሉ፡፡ ለዚህም በተመልካቹና በባለሙያዎች የተወደዱና አሁን ላይ ለእይታ እየቀረቡ የሚገኙ ድራማዎችን ለአብነት ማንሳት ይቻላል፡፡ በባለሙያዎች ጥምረት እየተሰሩ የሚገኙት እንደ እረኛዬ፣ የእግር እሳት፣ አደይ እና መሰል ድራማዎች በማሳያነት ይጠቀሳሉ። ከእነዚህ የቴሌቬዥን ድራማዎች መረዳት የሚቻለው፤ ባለሙያው ሙያውን አክብሮና ተመልካች በሚመጥን መልኩ ሃላፊነቱን ከተወጣ የፊልሙ ተመልካች አሁንም ፊቱን እንዳላዞረ ነው።
ባለሙያው ግዛቸውም እነዚህ ድራማዎች ለዘርፉ ጥሩ መነቃቃት እንደፈጠሩ ያምናል። በጥንቃቄ የተሰራ ስራ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት እንደሚችልም ማሳያ መሆናቸውን ያነሳል፡፡ የቴሌቪዥን ድራማዎቹ ከይዘትና ከአሰራር አንፃር አዲስ ነገር ይዘው በመቅረባቸው ተወዳጅ ሆነው በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኙም ይናገራል።
ከተወደዱት የቴሌቪዥን ድራማዎች ውስጥ ዘንድሮ በተካሄዱ የፊልም ሽልማቶች በርካታ ክብሮችኝ በመውሰድ የአመቱ ምርጥ የቴሌቪዥን ድራማ የተሰኘው ‹‹እረኛዬ›› ድራማ በማሳያነት ይጠቅሳል፡፡ ባለሙያዎቹም በህብረት ተቀናጅተው መስራታቸው፣ በፊት ከተለመደው የከተማ ታሪክ ወጣ ብለው ብዙ ሰው ወደሚመለከተው የገጠሩን ህይወት መዳሰሳቸውና በአቀራረብም አዲስ መሆኑ ለመወደድ እንዳበቃው ግዛቸው ይናገራል፡፡
ከዚህም ጋር ተያይዞ የፊልም ስራ ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎች በጥምረት መስራታቸው የተሻለ ስራ ይዞ ለመቅረብ ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከቱን ያስረዳል፡፡ የፊልም ስራ በባህሪው የህብረት ስራ በመሆኑ በሙያው የሚሳተፉ ባለሙያዎች በመግባባትና የተሻለ የፈጠራ ሀሳብ በማቅረብ ውጤታማ መሆን የሚቻልበት መስክ መሆኑን የሚናገረው ግዛቸው፤ ድራማዎቹ የተሻሉ የሆኑበትም አንዱ ምክንያት ከዚህ የተለየ እንደማይሆን ያስቀምጣል።
የፊልም ፕሮዲዩሰሩ አማን በበኩሉ፣ የፊልም ስራ ዘርፍ ተስፋ ወደማስቆረጡ ሲቃረብ ብቅ ብለው ትልቅ ተስፋ የጫሩት እነዚህ የቴሌቬዥን ድራማዎች መሆናቸውን ይናገራል። ስራው በቂ ትኩረት ተሰጥቶበት ከተሰራም ተወዳጅ መሆን እንደሚችል የቴሌቪዥን ድራማዎቹ ማሳያ መሆናቸውን ይጠቅሳል፡፡
“የፊልም ስራ በራሱ ነፃነት ይፈልጋል፤ ነፃነቱም በሀሳብ በገንዘብና በሙያ ሊገለፅ ይችላል” የሚለው ግዛቸው፣ ለፊልም ስራ የሚሆን በቂ በጀት፣ ደራሲው በሀሳብ በኩል ሳይገደብ በነፃነት ታሪክ የሚነግርበት ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረ ይህም ብቁ በሆነ ሙያዊ ስራ ፊልም ላይ መተግባር ከቻለ ጥራቱን የጠበቀ ፊልም መስራትና ተመልካቹን ወደ ሲኒማ መመለስ ይቻላል የሚል እምነትም አለው።
በአጠቃላይ ይህ ትልቅ ዘርፍ በሚመለከተው ሁሉ ትኩረት ከተሰጠው ለአገር ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ሊያበረክት የሚችልበት አቅም አለው። የፊልሙ ኢንደስትሪ ያሉበትን ችግሮች በመቅረፍም ከዘርፉ የሚጠበቀውን በጎ አስተዋፅዖ መመልከት እንደሚቻል ባለሙያዎቹ የሃሳብ ልዩነት የላቸውም።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓ.ም