የክረምቱ ወቅት እንደ ቀጠለ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ወቅት ከሚጥለው ከባድ ዝናብ ጋር ተያይዞ የተለያዩ አደጋዎች በተለያዩ አካባቢዎች ሲከሰቱ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ሰሞኑንም በጣለው ከባድ ዝናብ የተነሳ በመዲናችን አዲስ አበባ ሳይቀር የተለያዩ በአንዳንድ አካባቢዎች መከሰታቸውን ከተለያዩ የዜና ምንጮች ተረድተናል፡፡ በክረምት ወቅት ይህ የተለመደ ነው፡፡ ከግምሽ ምዕተ ዓመት በፊት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በክረምት ወቅት የሚከሰቱ ችግሮችና አደጋዎች ምን ይመስሉ እንደነበረ በዛሬው የአዲስ ዘመን ድሮ አምዳችን መለስ ብለን ለመቃኘት ሞክረናል፡፡ በወቅቱ ይሠሩ የነበሩ የልማት ሥራዎች በክረምቱና በዝናብ ምክንያት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የደረሰባቸውን አደጋዎችን በሚመለከት የተሰሩ ዘገባዎችንም መርጠን አቅርበናል፡፡
ዝናብ በሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ
ደብረ ማርቆስ ደብረ ብርሃን አሰላ ደሴ (ኢ-ዜ-አ-)፤በጐጃም በሸዋ በአሩሲና በወሎ ጠቅላይ ግዛቶች በሚገኙት አንዳንድ ቀበሌዎች ሰሞኑን ዝናብ አስከትሎ የወረደው መብረቅና የተነሳው ኃይለኛ ነፋስ በሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት አደረሰ፡፡
በጐጃም ጠቅላይ ግዛት በቆላ ደጋ ዳሞት አውራጃ በደንበጫ ወረዳ ደብሪት ቀበሌ ከዘነበው ዝናብ ጋር የወረደው መብረቅ ፩ ሰው ገድሎ ሌሎች ፪ ሰዎች አቁሱሏል፡፡ በሸዋ ጠቅላይ ግዛት በመንዝና ግሼ አውራጃ ባለፈው ሳምንት ከዝናብ ጋር የነፈሰው ኃይለኛ ነፋስ የ፵፭ ሰዎች መኖሪያ የነበሩትን ፩፻፩ ክፍሎች የቆርቆሮ ክዳን ቤቶች አፈራርሶ ከአገልግሎት ውጪ አድርጓል፡፡
በአሩሲ ጠቅላይ ግዛት በገደብ ወረዳ በአሳሳ ከተማ ላይ በዚህ ሳምንት በተነሳው ኃይለኛ ነፋስ ፭ ክፍል ቤቶች መፈራረሳቸው ተረጋግጧል፡፡ በወሎ ጠቅላይ ግዛት በወረኢሉ አውራጃ በካቤ ከተማ ባለፈው ሳምንት የነፈሰው ኃይለኛ ነፋስ ስድስት የቆርቆሮ ክዳን ቤቶች አፈራረሰ፡፡ በዚሁ ኃይለኛ ነፋስ ምክንያት የፈራረሱት ክፍሎች ፬ የመኖሪያ ቤቶች ክፍሎች ናቸው፡፡ የአውራጃው ግዛት ዋና ጸሐፊ አቶ አሰፋ መክት እንደገለጡት፤በዚሁ የነፋስ አደጋ በሰውና በእንስሳት ላይ የደረሰ ጉዳት የለም፡፡
(ሰኔ 17 ቀን 1964 ዓ.ም የወጣው አዲስ ዘመን)
በአረጐ ተራራ ላይ 500ሺህ የዛፍ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው
ደሴ (ኢ-ዜ-አ-) ከደሴ ከተማ ፲፪ ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው የአረጐ ተራራ ላይ በመጪው ክረምት ፭፻ሺህ የዛፍ ችግኝ ለመትከል የሚያስችል ሥፍራ ለተከላው የሚያመች ሥፍራ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡
የአረጐ ተራራ የደን ጫካ ለማድረግ በተወሰደው ርምጃ መሠረት፤አፈሩ በጐርፍ ውሀ እንዳይወሰድ በሚከለክል መንገድ ለችግኞች ተከላ በሚያመች አኳኋን ሥራው የተጀመረው ባለፈው የካቲት ፷፬ ዓ/ም ሲሆን፤ይህም ሥራ በጥቂት ቀኖች ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል፡፡
በመደብ እየተከፈለ በዘመናዊ ዕቅድ በተዋረድ በመዘጋጀት ላይ የሚገኘው የዚህ ችግኝ መትከያ ሥፍራ ሥራ የሚካሄደው በአሜሪካ ምግብ ለሥራ ፕሮግራም ክፍልና የዓለም ምግብ ድርጅት ኅብረት መሆኑን የሥራው አላፊ አቶ ወልደኪዳን ንርኤ ፤ክቡር ደጃዝማች ሰሎሞን አብርሃም የወሎ ጠቅላይ ግዛት እንደራሴ ባለፈው ሳምንት የሥራውን ይዞታ በተመለከቱበት ወቅት ገልጠዋል፡፡
በአረጐ ተራራ ላይ እስካሁን ድረስ ከ፬፻፶ ኪሎ ሜትር በላይ፤ርዝመት ያለው ሥፍራ ለዛፍ ተከላ ሥራ በሚያመች ሁኔታ ተዘጋጅቷል፡፡ ይህንንም ተግባር ለሚያከናውነው ሰው በቀን ፫ ኪሎ ስንዴ ይሰጠዋል፡፡በዚህም መሠረት ካለፈው የካቲት ወር እስከ ግንቦት ፲፪ ቀን ፷፬ ድረስ ፭ ሺህ ፬፻፺ ሰዎች የሥራው ተካፋዮች በመሆን ፤፩ሺህ ፭፻፷፮ ኪሎ ስንዴ ተቀብለዋል፡፡የዚህም አሠራር ዘዴ ዓላማ ፤ሥራን በመፍጠር ለሠራተኛው ሕዝብ ተመጣጣኝ የአገልግሎት ዋጋ እየከፈሉ አስፈላጊ በሆኑ ሥፍራዎች ላይ ዛፎች በብዛት እንዲተከሉ ለማድረግ መሆኑን አቶ ወልደኪዳን አስረድተዋል፡፡
በዚሁ የምግብ ለሥራ ፕሮግራም ወደፊት ለሚተከሉ ዛፎች ሥራ አመቺ እንዲሆን ተራራውን የሚያስወጣ ፪ ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ጊዚያዊ የመኪና መንገድም ተሠርቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
ክቡር ደጃዝማች ሰሎሞን አብርሃም በጉብኝቱ መጨረሻ ፤ፕሮግራሙ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ሥራውን ፈጥሮ ሕዝቡ እንዲጠቀም መደረጉም በሕዝቡም ዘንድ የዛፍ ተከላን ሥራና ጥቅም በይበልጥ ለማሳወቅ እንደሚረዳ ያላቸውን እምነት ገልጠዋል፡፡
ከደሴ ከተማ ኮምቦልሻ በሚወስደው መንገድ ፲፪ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አረጐ ተራራ ባለፉት ሁለት ዓመቶች ውስጥ ላይ ከ፫፻ ሺህ ባላይ የዛፍ ችግኞችን የወሎ ጠቅላይ ግዛት እርሻ ጽ/ቤት ማስተከሉ ተረጋግጧል፡፡
(ግንቦት 23 ቀን 1964 የወጣው አዲስ ዘመን)
በሮቢት የሚገኙ እሥረኞች 40 ጋሻ መሬት በማልማት ላይ ናቸው
በሮቢት ፳፫ ጋሻ መሬት በተጨማሪ ለሥራ እንዲውል ተፈቅዶ የወኅኒ ቤቶች ጽ/ቤት መረከቡን አቶ አሰፋ መርጊያ በሰጡት ወሬ ለማወቅ ተችሏል፡፡ይህም ማለት ከቀድሞው ፲፯ ጋሻ መሬት ጋር ተደምሮ በሕግ እሥረኞች የሚለማው መሬት ፵ ጋሻ መሆኑ ነው፡፡ከቀድሞው ፲፯ ጋሻ መሬት ውስጥ ፲፪ቱ ለሰብልና ለፍራፍሬ አገልግሎት ሲውል አምስቱ ጋሻ መሬት ግን ለመኖሪያ ቤቶች መደልደሉን ወሬው ያስረዳል፡፡
፳፫ ጋሻ መሬት ፤ለሦስት ዓይነት ጥቅም እንደሚውል ተገልጧል፡፡ ፩ኛ ለእሥረኞች ጥቅም የሚሰጥ ሰብል መዝሪያ
፪ኛ ለፍራፍሬ ፫ኛ ለሁለቱም ማለትም ለፍራፍሬና ለሰብልዎቹ ያልሆነውን ቃጫ በመትከል ጥቅም እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡በ፲፪ ጋሻ መሬት ላይ ይበቅል የነበረው ጤፍ ፤ማሽላ በቆሎ ፤ሰሊጥ፤አደንጓሬና ለውዝ ነው፡፡ቃጫም ለሙከራ ተተክሎ ጥሩ ውጤት መስጠቱ አቶ አሰፋ ገልጠዋል፡፡
ከዚሁ የተገኘው ሰብል በጨረታ እየተሸጠ ገቢ ይሆናል፡፡ ለዚሁ መሬት ማሚያ የወህኒ ቤቶች ጽህፈት ቤት 76.909.04 ተበድሮ ካፒታል በማድረግ ሥራው ፲፱፻፶፪ ዓ.ም ጀመረ፡፡ይህ የእርሻ ቦታ በሰው ጉልበት ብቻ ሳይከናወን ገቢ የሆነው ለውዝ (ኦቾሎኒ) 37, 101 ኪሎ፤ ጥጥ 40,992 ኪሎ፤በርበሬ 434 ኪሎ፤ሽምብራ 1,937 ኪሎ ጤፍ 21,157 ኪሎ፤ በቆሎ132,570 ኪሎ መሆኑ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በሮቢት የዶሮ ርቢ ለሙከራ ተቋቁሞ ጥሩ ውጤት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ከላይ እንደተጠቀሰው ዕዳ 180,000 ተከፍሏል፡፡በዚህ ዓይነት መሥሪያ ቤቱ በቅርቡ ያለበትን ዕዳ ሳይከፍል እንደማይቀር ይነገራል፡፡በልዩ ልዩ ሥራዎች ማለትም በጋራዥ ለመኖሪያ ቤት ሥራ ፤በግንብና በእርሻው የተሠማሩት የሕግ እሥረኞች ብዛት 500 መሆናቸውን የወህኒ ቤቶች ጽህፈት ቤት የሶሻልና ኢንዱስትሪ አማካሪ አስረድተዋል፡፡
(ጥቅምት 17 ቀን 1957 ዓ.ም ከወጣው አዲስ ዘመን)