ባለፉት ጥቂት ዓመታት አንስቶ የለውጡ አማካይ ዕድሜ ድረስ ቁጥራቸው 80 ይደርሳል ሲባሉ የነበሩት ፓርቲዎች በአንድ ጊዜ 107 ደርሰው መስማታችን አስገርሞን ሳያበቃ 108ኛው ፓርቲ ተመሰረተ መባሉን መስማታችን ሩጫው በፓርቲዎች ብዛት ቀዳሚ ለመሆን ነውን? ለማለት ተገደድን።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት 107 የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚመሩበትንና በመካከላቸው የሚኖረውን ግንኙነት እንዲሁም በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሠራር ሥርዓት ቃል ኪዳን ሰነድ መፈረማቸው ይታወሳል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕጋዊ ዕውቅና ኖሯቸው በዴሞክራሲያዊ መንገድ መንቀሳቀስ እንዲችሉ የተለያዩ መስፈርቶችን አሟልተው መገኘት ይኖርባቸዋል። የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በርካታ መስፈርቶችን አውጥቶ መስፈርቱን ያሟሉና ያላሟሉትን የለየበት የጥናት ሰነድ በመኖሩ ቦርዱ ባደረገው የመለየት ተግባር በአሁኑ ወቅት «ንቁ» ሊባሉ የሚችሉትና የተመዘገቡት ፓርቲዎች 66 ብቻ ሲሆኑ፤ አገር አቀፍና ክልላዊ ተብለው የተቀመጡ ናቸው። በዚህ ሁኔታ በተሟላ ቁመና የሚገኙት 16ቱ ብቻ ናቸው።
ለመሆኑ108 የሆኑት ፓርቲዎች ከየት ተፈጥረው ነው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ እንኳ በአገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካ ለውጥ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ በማሳደሩ የፖለቲካ ድርጅቶች መብዛታቸው አያስደንቅም። ከስደት የተመለሱ፣ አዲስ የተፈጠሩ፣ ምዝገባ ሳያካሂዱ የቆዩ ወዘተ… እኩል የፓርቲ ማዕረግ ሲያገኙ ቁጥራቸው ሊበዛ እንደቻለ ይገመታል።
የፓርቲዎች ቁጥር መብዛትን እንደ ችግር የሚያዩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። የፖለቲካ ድርጅቶች መብዛት ችግር ያለመሆኑን ባደጉት አገራት ከተከሰተው ነባራዊ ሁኔታ መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ በእንግሊዝ ከ76 በላይ፣ በጀርመን 47ና በአሜሪካ 40 ያክል የፖለቲካ ድርጅቶች አሉ። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ባልዳበረ ዴሞክራሲ ውስጥ ለሚገኝ አገር በፓርቲዎቹ ቁጥር ልክ ገንቢ የሃሳብ ብዝሃነት ቢፈልቅ ጠቃሚ እንጂ ጎጂ ባለመሆኑ የሚደገፍ ሊሆን ይችላል።
ዋናው አጠያያቂ ጉዳይ ፓርቲዎቹ ሕጋዊ መስፈርቶችን ሳያሟሉ፣ በቤተሰብ የካቢኔ አባላት የተዋቀሩ ከሆኑ፤ የሕዝብን ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ የፖለቲካ አፈና በበዛበት ወቅት የይስሙላ መድብለ ፓርቲ ሥርዓት አለን የሚል ሽፋን ከመስጠት የዘለለ ትርጉም አይኖራቸውም።
በአገሪቱ ላሉት በርካታ ፓርቲዎች የሚሆን የመከራከሪያ አጀንዳ ሲኖር ሁሉም ፓርቲዎች አጀንዳ የሆነውን ጉዳይ በማንሳት ገዢ የሆነውን አካል ለመሞገት አቅም እንዲኖራቸው ዕድል ይፈጥራል። ይህ በቀደሙት ዓመታት በተግባር ታይቷል። የዛሬ አንድ ዓመት የተቀጣጠለውን ለውጥ ተከትሎ በለውጡ ኃይል የተወሰደው ዕርምጃ በየእስር ቤቱ የነበሩ እስረኞች ነፃ መውጣት፣ የፍትህ ተቋማት እንደ አዲስ መደራጀት፣ የመገናኛ ብዙሃን በነፃነት የሁሉንም ሃሳብ ያለ አድልዎ ማስተናገድ ዴሞክራሲያዊ አካሄዶችን መከተል የመሳሰሉት አዎንታዊ ተግባራት መከናወናቸው ፓርቲዎቹ ሲታገሏቸው የነበሩ በመሆናቸው በውጤታማነት የሚደመደም ነው።
በአገሪቱ ችግሮች አሉ ተብሎ በታመነበት ወቅት ቁጥራቸው እጅግ የተጋነነ ያልነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉም ዜጋ የተሻለ ጊዜ ላይ ደርሰናል ብሎ ባመነበት ወቅት 108 መድረሳቸው ይሄ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ለየት ያለ ጠቀሜታ ይኖረው ይሆን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል እንጂ፤ ችግሮቻችን ከሞላ ጎደል በተፈቱበት ወቅት ቁጥራቸው መብዛቱን አጠያያቂ ያደርገዋል።
አንድ ዓመት ብቻ እንደቀረው በሚነገርለት የአገሪቱ ምርጫ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው እና መስፈርቶችን አሟልተው ያቀረቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዕቅድና አማራጮቻቸውን ለደጋፊዎቻቸው አቅርበው ተመራጭነትን እንዲያገኙ ቅስቀሳ የሚያደርጉበት ሰዓት ሊኖራቸው ሲገባ፤ በዚህን ያህል ቁጥር ሰፍተው መገኘታቸው አካሄዱን አዳጋች ሊያደርገው እንደሚችል ያሳስባል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ባገኙት መድረክና አጋጣሚ ሁሉ በፖለቲካ ፕሮግራማቸው ተቀራራቢነት ያላቸው ፓርቲዎች በመሰባሰብ ለውድድር መዘጋጀት እንዳለባቸው ቢያሳስቡም በርካቶቹ ዝምታን መርጠው ባሉበት ሁኔታ መጓዛቸው የሁሉም ፓርቲ አመራሮች ለሕዝብ አገልጋይ ከመሆን ይልቅ ሥልጣን ላይ ለመቆናጠጥ ምኞት ብቻ ያላቸው ያስመስላቸዋል።
በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ዜጎች የሚፈልጉት የሥልጣን ስፍራዎችን ተቀራምቶ ገዢ የሚሆንባቸው ሳይሆን፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸው እንዲፈቱ በአገልጋይነት መንፈስ ወደላቀ ደረጃ የሚያሸጋግሩ መሪዎች ወደ ኃላፊነት የሚመጡበት መሆን አለበት። ስለዚህም ከመቶ የላቁት ፓርቲዎች በርግጥም የሕዝብ አገልጋይነት ስሜት ካላቸው በጋራ ተሰባስበውና በጋራ መክረው ሰላማዊ የምርጫ ሂደት እንዲከናወን ቀና አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይገባል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም መደበኛ የቅድመ ምርጫ ዝግጅቱን ይፋ በማድረግ በአግባቡ ለተመዘገቡትና መስፈርቱን ላሟሉትና ላልተበታተኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች ብቻ ተገቢውን ዕገዛ ማድረግ ይጠበቅበታል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2011