‹‹የሚዲያ ባለቤቶችና ሥልጣን ያላቸው አካላት በሙስና ዘገባ ላይ ምን ያህል ተጽዕኖ ያደርሳሉ›› በሚል ሃሳብ ዙሪያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀረበ ጥናት አዲስ ዘመንና ሪፖርተር ጋዜጦች በሙስና ዘገባ ላይ የሰጡት ሽፋን አናሳ መሆኑን አመለከተ፡፡ በአክሱም ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህርና ጋዜጠኛ ፍቃዱ ዓለሙ አማካ ኝነት የቀረበው ጥናት ከ2008 እስከ 2010 ዓ.ም ባሉት ወቅቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ተከስቶ
ለነበረው አለመረጋጋት የሙስና ጉዳይ አንዱ ምክንያት መሆኑን በማውሳት፤ መገናኛ ብዙኃን በተለይም አዲስ ዘመንና ሪፖርተር ጋዜጦች በወቅቱ ሙስናን በመዘገብ ረገድ የነበራቸው ሚና አነሳ መሆኑን አመላክቷል፡፡
የጥናቱ ባለቤት መመህርና ጋዜጠኛ ፍቃዱ፤ የሙስና ጉዳዮችን መመርመርና ለህዝብ ማሳወቅ፣ የሚጠየቀውን አካል ተጠያቂ ማድረግ፣ የሚመለከተውን አካል በዚህ ጉዳይ ላይ እንዲሳተፍ ከማድረግ አኳያ እንዲሁም የሙስናን ጉዳይ እንደ አጀንዳ ይዞ በመዘገብ ረገድ በተለይ የህትመት ሚዲያዎች አቅማቸው ውስን እንደነበር ጠቅሷል፡፡
በወቅቱ ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ በመንግሥት ተቋማት ይፈፀም ስለነበር የመንግሥት ባለሥል ጣናትና ኃላፊዎች የሙስና ጉዳይ እንዳይዘገብ ተጽዕኖ ያደርጉ እንደነበር፤ ለዚህም ጋዜጠኞች ላይ ማስፈራሪያና ዛቻ ብሎም ድብደባ እንደደረሰባቸው ገልጿል፡፡ ጋዜጠኞች አነፍንፈው የሙስናን መረጃ ማግኘት ሲፈልጉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት በቀጥታ ለሚዲያው ባለቤት በመደወል መረጃው እንዳይዘገብ ሲያስ ጠነቅቁ እንደነበርም በጥናቱ ታይቷል፡፡
እንደ ጥናቱ ዳሰሳ፤ በተጠቀሱት ጋዜጦች ላይ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የማስታወቂያ አስነጋሪ ድርጅቶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተጽዕኖ ያደርጉ ነበር፡፡ በተለይ ማስታወቂያ አስነጋሪ ድርጅቶች ሙስና ውስጥ ከገቡ አሊያም በእነርሱ ጉዳይ ላይ የሚያተኩር ዜና ከወጣ በጋዜጣው ላይ ያላቸውን ስምምነት የማቋረጥና ‹‹ስሜን አጥፍቷል›› በማለት የመክሰስ ሙከራዎችን ያደርጉ ነበር፡፡ ግ
ለሰቦች በመረጃ ጉዳዮች ላይ መረጃ ሲሰጡ ህይወታቸውን እስከ ማመሰቃቀል የሚደርስ ተጽዕኖ ይደረግ እንደነበረም ነው ጥናቱ ያመላከተው፡፡ ጋዜጣኞች በሙስና ጉዳይ ላይ ዘገባን ሲያቀርቡ ከመንግሥት አካላትም ሆነ ከሚዲያው ከለላ ማጣታቸው ዘገባው በሰፊው እንዳይዘገብ መደረጉን፤ የሙስና ተግባርን ይከላከላሉ የሚባሉ እንደ ፖሊስና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ያሉት በጉዳዩ ላይ መረጃ በመደበቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ የጥናቱ ትንተና ያሳያል፡፡
በእንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ መገናኛ ብዙኃን ከተጽዕኖ ተላቅቀው መረጃን ለህብረተሰቡ ማድረስ እንደሚገባቸውም ነው ጥናቱ በማጠቃለያ ምዕራፉ ያስቀመጠው፡፡
የጥናቱ መረጃ እንደሚያሳየው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ከ730 የሁለት ዓመት ህትመት ውስጥ ለሙስና ዘገባ ሽፋን የሰጠው 28 ጊዜ ሲሆን፤ ሪፖርተር ጋዜጣ ካሳተመው 192 ህትመት ውስጥ ለሙስና ጉዳይ ሽፋን የሰጠው 38 ጊዜ ነው፡፡ ይህም በአንፃራዊነት የግል ሚዲያ ከመንግሥት ሚዲያ በላይ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠቱን ያሳያል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2011
አዲሱ ገረመው