የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን ለመልሶ ማቋቋሚያ የሚሆን የ300 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ስምምነቱን እንደገለፀ ግንቦት 8 ቀን 2014 ዓ.ም ተነግሯል። የድጋፍ ስምምነቱ በአማራ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በግጭት ለተጎዱ አካባቢዎች ለመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋሚያ የሚውል መሆኑም ተጠቁሟል። ባንኩ ሰኔ 8 አካባቢም በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ለተዘጋጀ ፕሮጀክት የሚውል የ300 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ አጽድቆ ነበር።
በድጋሚም ባንኩ ግንቦት 30 ቀን 2014 በኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ክትባትን ለዜጎች ለማዳረስና የጤና ዘርፉን ለማገዝ የ195 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማድረጉም ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በያዝነው ወር በሐምሌ 12 ቀን 2014 ዓ.ም ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለሰብዓዊ እርዳታ የሚውል 60 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በዓለም ምግብ ፕሮግራም በኩል ለኢትዮጵያ ማድረጉ ታውቋል።
እነዚህን የመሳሰሉ ድጋፎች ቀደም ሲል መቀዛቀዝ ከታየባቸው በኋላ አሁን ላይ ለኢትዮጵያ የተለያዩ ተቋማት ድጋፍ ለማድረግ መነሳሳት የጀመሩት ለምንድን ይሆን? በማለት ያነጋገርናቸው የፖለቲካ እና የዲፕሎማሲ ምሁሩ የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እምቢአለ በየነ ናቸው። ምሁሩ እንደሚናገሩት፤ አሁን ላይ እርዳታ እና ብድር የተገኘበትን ተጨባጭ ምክንያት በዝርዝር ለማስረዳት አስቸጋሪ ቢሆንም ነገር ግን በዋናነት ምክንያቱ ከሁለት አያልፍም ብለዋል።
አንደኛው የጦርነቱን የጉዳት ደረጃ በመገንዘባቸው ሊሆን ይችላል። ምናልባት አስከፊ የሆነ ሰብአዊ ቀውስ ከመከሰቱ በፊት ለመድረስ አስበው እርዳታውን እየሰጡ ነው ለማለት እንችላለን። ሁለተኛው ግን ከመንግስት ጋር ባደረጉት ስምምነት እርዳታ እና ብድር እየሰጡ ሊሆን ይችላል። ‹‹ይህ ስምምነታቸው ምንድን ነው?›› ከተባለ አይታወቅም። ለፖለቲካ ሲባል የማይገለፁ ስምምነቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ይህም ቢሆን ግን እርዳታ እና ብድር የሚሰጡት ለውሃው ዘርፍ ልማት ለሕዳሴው ግድብ ሳይሆን ለሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ለምሳሌ በጦርነት ለተጎዱት እና ለተፈናቀሉት ብለው እታች ድረስ ወርደው በሚከታተሉት አግባብ ሊደግፉ እንደሚችሉ መረሳት የለበትም ይላሉ።
በሌላ በኩል በአቶ እምቢአለ የተገለፀው፤ ዋነኛው ጉዳይ ሌሎች ግን የማናውቃቸው ነገሮች ሊኖሩ ቢችሉም ዓለም አቀፍ ተቋማት ከአባይ ተፋሰስ ጋር ተያይዞ እርዳታ እና ብድር የመስጠት ምንም አይነት ፍላጎት የሌላቸው መሆኑን ነው። በአባይ ተፋሰስ ላይ ለሚሠራ ማንኛውም ፕሮጀክት የዓለም የገንዘብ ድርጅት ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ልማት ባንክን ጨምሮ ማንም ቢሆን ድጋፍ ቀርቶ ምንም ዓይነት ብድር ለኢትዮጵያ አይሰጡም። ከውሃ ውጪ ባሉ ጉዳዮች ላይ ግን እርዳታ እና ብድር ይሰጣሉ። አሁን ግን አገር ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ማለትም የሰሜን ጦርነትን ምክንያት አድርገው እርዳታ እና ብድር ለመከልከል ቢሞክሩም መነሻቸው የአባይ ጉዳይ መሆኑ መዘንጋት እንደሌለበት ያስገነዝባሉ።
‹‹ አጀንዳቸው የሕዳሴ ግድብ ነው። በዚህ ላይ በቀዳማይ ኃይለስላሴ ጊዜም ሆነ በደርግ ጊዜ እንዲሁም በኢህአዴግ ጊዜ የውሃውን ዘርፍ ደግፈው አያውቁም። ምክንያቱም እነዚህ የገንዘብ ተቋማት የአውሮፓ ሕብረት እና የእነ አሜሪካ ጉዳይ አስፈፃሚዎች በመሆናቸው የአገራቱን ሃሳብ መደገፍ፤ ማዕቀባቸውን የማስፈፀም ሥራን ይሠራሉ። በዚህ ሳቢያ የአውሮፓ አገራት ለኢትዮጵያ ብድር እና ዕርዳታ ሊሰጣቸው አይገባም ካሉ እነርሱም ምክንያት ፈልገው ሊከለክሉ ይችላሉ። ስለዚህ አሁን ዕርዳታ እና ብድር መስጠት የጀመሩበት ሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ›› ብለዋል።
እነ አሜሪካ ከመንግስት ጋር በአባይ ፖለቲካ ዙሪያ አስገዳጅ ውል ተፈራረሙ አትፈራረሙ ከሚለው ወጥተው፤ በሌላ በኩል አንዱ በሆነው ማስገደጃቸው ዶላራቸውን እየተጠቀሙ ነው የሚል ግምት እንዳላቸው አመልክተዋል። በሌላ በኩል ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ቀውሱን ተረድተው ችግሩ የበለጠ የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ኃላፊነት እንዳለበት ተቋም ያንን ለማድረግ አስበው ሊሆን ይችላል የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልፀዋል።
በተጨማሪነት አቶ እምቢአለ እንደሚሉት፤ ድጋፍም ሆነ እርዳታ ሰጪዎቹ ያስቀመጧቸው መስፈርቶች ይኖራሉ። ይህ ሲባል መንግስት ይህን ማድረግ አለበት ብለው ይወስናሉ። ያስቀመጡት ነገር ከአገር ውስጥ ሽብር ጋር ተያይዞ፣ ሕወሓትን በሚመለከት ወይም በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ከሕወሓት ጋር ስለመወያየት ሲነሳ በቅድሚያ አሸባሪ ተብሎ ስለተፈረጀ ሕወሓት ወደ ውይይት መግባት የለበትም የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ። ከሕወሓት ጋር ተያይዞ አንዳንድ ነገሮች መንግስት ይፋ ከማውጣቱ በፊት በሚስጥር ተይዘው ነበር። ያንን ያደረገው የሕዝቡን ምላሽ በመፍራት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ደግሞ የእርዳታ እና ብድር ሰጪዎቹን አቅጣጫ በመቀበል የተፈፀመ ሊሆን ይችላል የሚል ሃሳብ አላቸው።
መንግስት ከእነርሱ ጋር የተስማማባቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ ሲባል ከሕወሓት ጋር መደራደርን በሚመለከት ብቻ ሳይሆን ሌላም ነገር ሊኖር ይችላል ይላሉ። እና እጅ መንሻውን እያቀረቡ ይሆናል። የእነርሱን እጅ መንሻ ተከትሎ መንግስት ለሰላም ስንል ከማንም ጋር እንደራደራለን ብሎ ሊሆን ይችላል ሲሉ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
‹‹አሜሪካንም ሆነች ሌሎች አገራት ሕወሓት ከአሸባሪነት መዝገብ መፋቅ አለባት የሚል እምነት አላቸው። በሌላ በኩል የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸውን በሙሉ እንዲመለሱ የማድረግ ፍላጎት አላቸው። አንዳንዴ የትግራይ መንግስት እና የኢትዮጵያ መንግስት እስከማለት ይደርሳሉ። ይህንን የሚሉት ለመነጣጠል ነው። ከዛ አንፃር እነርሱ ፈፅሙ የሚሉት ነገር እስከዚህ ሊዘልቅ ይችላል።›› የሚል ሀሳባቸውን ያስቀምጣሉ።
ሌላው በጦርነቱ የደረሰውን ጉዳት ለመዘገብ የተለያዩ ጋዜጠኞች ከአውሮፓ መጥተዋል። አማራ ክልልም ሆነ አፋር ክልል ላይ የደረሰውን ጉዳት በአካል ሔደው አይተው ፅፈዋል። ባህርዳር ላይ መነሻ ፅሁፍ ሁሉ አቅርበዋል። ሚዲያው የተወሰነ ሽፋን ማድረግ ስለጀመረ ምናልባት ጉዳቱ ተሰምቷቸውም እርዳታ እየሰጡ ሊሆን ይችላል ይላሉ።
የሕዝብ ተወካዮች የ2014 ዓ.ም 6ተኛው ምክር ቤት የአንደኛ ዓመት የሥራ ዘመን 16ኛው መደበኛ ጉባኤ ከሕወሓት ጋር ስለሚኖረው የሠላም ድርድር ጥያቄ ቀርቦላቸው ጠቅላይ ሚነስትር ዐቢይ አሕመድ፤ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሁልጊዜም ለሰላም ቅድሚያ ይሰጣል ማለታቸው ይታወሳል። “ ነገር ግን ለሰላምም ይሁን ለጦርነት የምንወስነው በብሔራዊ ጥቅማችን ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያን አንድነትና ጥቅሟን በሰላማዊ መንገድ ማስጠበቅ ካልተቻለ የህይወት ዋጋ ከፍለን በመስዋዕትነት ለማስጠበቅ ዝግጁ ነን። ነገር ግን በምንም መልኩ መንግስት በሰላማዊ አማራጭ ተወያይቶ መፍትሔ ለማምጣት ፈቃደኛ ከመሆን በተጨማሪ በዋናነት ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ መዘንጋት የለበትም” ብለዋል።
እንደ አቶ እምቢአለ ገለፃ፤ ከእርዳታ እና ብድር ለመላቀቅ መፍትሔው ውስጣዊ ሁኔታ ማስተካከል ነው። ይሔ በሃይማኖት እና በብሔር ውስጥ ያለው ሽኩቻ ቀርቶ በአንድነት መቆም ከተቻለ የእነርሱን አቋም የሚወስነው የውስጥ ወቅታዊ ሁኔታ በመሆኑ የሚያሳስብ አይደለም። እነርሱ ጫና ለማሳደር የሚሞክሩት ውስጣዊ ሁኔታ እያዩ ነው።
‹‹የአባይም ሆነ ሌላው ፖለቲካ የሕዳሴውም ጭምር ለምን አሁን ተወሳሰበ ከተባለ እርስ በእርሳችን በመተረማመሳችን ነው። መንግስትም የተዳከመ ስለመሰላቸው ጉዳያችንን የምናስፈፅመው ዛሬ ነው። አጀንዳችንንም የምናስፈፅመው ዛሬ ነው። ብለው ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር አካባቢ የማራቅ የአባይን ውሃ እንዳትጠቀም የማድረግ ሥራን ይሰራሉ።›› ካሉ በኋላ፤ ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካ ሞተር መሆኗን የሚጠሉም ብዙ አሜሪካንን ጨምሮ ምዕራባውያን በመኖራቸው የግብፅ እና ሱዳን አቋም እንዳለ ሆኖ የእነርሱም አቋም ከኢትዮጵያ እድገት ተፃራሪ መሆኑ ሁሉም ማወቅ አለበት ይላሉ።
ኢትዮጵያ ማደግ እንደሌለባት ብዙ ሰዎችም ፅፈዋል። ያንን በራሳቸው መፈፀም አይችሉም። ስለዚህ በኢትዮጵያ አስቻይ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለው እየሰሩ እንደሚመስላቸው ተናግረው፤ ይህንን ተረድቶ ሁኔታዎችን መቀየረ ከተቻለ ወደ ፊት የሚስተካከል ይሆናል ብለዋል።
ነገር ግን የእጅ አዙር ጦርነት ከቀጠለ እርዳታም ቢሰጡ የሆነች የጎደለችውን ነገር ለማሟላት እንጂ በትክክል ለውጥ በሚያመጣ መልኩ ስለማይሆን መፍትሔ ለማግኘት ኢትዮጵያ በራሷ መጣር እንዳለባት አስረድተዋል።
ዋነኛው መፍትሔ ‹‹ የሕዳሴ ግድቡን ጨርሰን፤ ግድቡ በሙሉ ሃይሉ ማመንጨት እና መጠቀም ከጀመርን ምናልባት አንድነታችን የሚጠናከርበት ሁኔታ ስለሚፈጠር እነ ግብፅም ሆኑ እነ አሜሪካ ይህንን አስገዳጅ ስምምነት ካልፈረመች እያሉ የሚጮሁትን በተወሰነ ደረጃ የሚያስታግስላቸው ይሆናል። ›› ያሉት አቶ እምቢአለ ከዛም በኋላ እርዳታ እና ብድር ማጣት ብዙ አሳሳቢ ላይሆን እንደሚችል ያመላክታሉ።
እንደ አቶ እምቢአለ፤ ወደ ፊት የሚሆነውን የሚወስነው የኢትዮጵያ ሁኔታ ነው። ግድቡ አልቆ የፖለቲካ ሽኩቻው መላ ካገኘ እና ከተረጋጋ የሚፈለገውን አይነት እርዳታ እና ድጋፍ ማግኘት ብቻ ሳይሆን በትብብር ለመስራትም ግብዣ የሚቀርብበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
የውስጥ ፖለቲካውን ለማረጋጋት የኑሮ ውድነት ችግርን መፍታት፣ መልካም አስተዳደርን እና ሙስናውን መቆጣጠር፤ መንግስት በትክክል የህዝብ አገልጋይ እንዲሆን በማድረግ ዘላቂ መፍትሔ ማበጀት ከተቻለ ኢትዮጵያን ከእርዳታ እና ብድር ማላቀቅ አዳጋች አይሆንም።
የህዳሴው ግድብ ሲያልቅ እነዚህ ካልፈረማችሁ እያሉ የሚጣደፉ አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ጫና የሚያሳድሩ አካሎች ዜሮ ይሆናሉ። የህዳሴው ግድብም ኢትዮጵያን ከብዙ ብድር ከማዳን በተጨማሪ ኃይል በመሸጥም እንደተባለው እስከ አንድ ቢሊየን ዶላር በዓመት በማግኘት የሃብት ምንጭ ማድረግ ስለሚቻል የወደፊቱን ተስፋቸውን ያመላክታሉ።
በተቃራኒው የህዳሴው ግድብ ግንባታ በተራዘመ ቁጥር ወጪው ስለሚበዛ እና የውጪ ምንዛሬ ችግር ስለሚቀጥል በሌላ አገራት ብድር እና እርዳታ ላይ በመንጠላጠል የሌሎች ተፅዕኖ ተጋላጭ የመሆን ዕድል ሊያጋጥም እንደሚችል ያስረዳሉ።
ስለዚህ ትልቁ መፍትሔ የሕዳሴ ግድብን መጨረስ በኢኮኖሚ ላይ የሚፈጥረውን ጫና ቀንሶ ራሱ ገቢ የሚያስገኝ ይሆናል። የሥራ ዕድል እና ሌሎች የቱሪዝም መስኮች ተጨማሪ የገቢ ማግኛ ዕድሎችንም ያመጣል።
በተጨማሪ አሁን ላይ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ችግሮችን መቆጣጠር ከተቻለ በትክክልም ሉአላዊ አገር መሆን አያዳግትም። አሁን ግን በጀቱ ከሌላ ሆኖ ሉዑአላዊ አገር ነን ማለት እንደሚያዳግት በመጠቆም፤ እውነተኛ የሆነ ሉዑላዊ አገር ለመሆን የምግብ እና የኢነርጂ ዋስትናችንን ማረጋገጥ እና ለህዝብ የሚቆረቆር ስርዓትን መዘርጋት ዋነኛው መፍትሔ መሆኑን ይናገራሉ።
ከአቶ እምቢአለ በተጨማሪ ሌሎችም ምሁራን እንደሚገልጹት፤ አሁን ላይ እርዳታ እና ብድር መስጠት የተጀመረው በተለያዩ ምክንያቶች ቢሆኑም ምናልባትም መንግስት ለሰላም የሰጠውን ዋጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አላቸው። በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተሰራው ስራና የተገኘው ውጤትም ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ።
ነገር ግን ከውጪ ምንም አይነት ብድርና እርዳታ ላለመፈለግ መፍትሄውና ቀዳሚው ስራ የአገር ውስጥ ገቢን ማሳደግ ነው። የመሠረተ ልማት እና የሰብዓዊ ልማት ፍላጎትን በዕርዳታ እና ብድር ላይ ከመመስረት ይልቅ በራሳችን ክፍያ መፈጸም እና የበጀት ጉድለታችንን ለማስተካከል የግብር ገቢን ማሳደግ ያስፈልጋል የሚል እምነት አላቸው ።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርበው ሸቀጥ ቀንሶ የምትሸምተው በመብዛቱ ምክንያት በ2017 ዓ.ም. የበጀት ጉድለቷ ጭማሪ አሳይቷል። በገቢ ማሽቆልቆል ሳቢያ ይኸው የበጀት ጉድለት እየሰፋ ቆይቷል። ይህም ኢትዮጵያ የገባችበትን ጦርነት ተከትሎ የተፈጠረባት የተወሳሰበ ችግር እንዲሁም ቀድሞም ቢሆን የተጠራቀመባት የዕዳ ጫና አሁንም ድረስ ላለችባት የበጀት ጉድለት መንስኤ ሆኖ የቀጠለ መሆኑን የሚናገሩት ምሁራኑ፤ የኢትዮጵያ ችግር ሌላኛው መፍትሔ የምጣኔ ሐብት ፖሊሲዋ ላይ የምትወስዳቸው እርምጃዎች ሊኖር እንደሚገባ ገልፀዋል። ኢኮኖሚዋ ከተሻሻለ የወደፊት እርዳታም ሆነ ብድር የማያሳስባት መሆኑንም ነው ምሁራኑ የሚስማሙት።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 18/2014