አዳነች ወይብሎ ልብስ በማጠብና እንጀራ በመጋገር አንድ ልጇን ብቻዋን የምታሳድግ እናት ናት፡፡ በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ዘጠኝ ውስጥ የምትኖርበት መንድር በመልሶ ማልማት ከፈረሰ በኋላ እዛው አካባቢ በላስቲክ ቤት ውስጥ ስምንት ዓመታት ኖራለች፡፡ በሀገራችን የመጣው ለወጥ የኔንም ህይወት ይለውጣል ብላ ተስፋ በማድረግ ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድን ለመደገፍ በተጠራው ሰልፍ ላይ ተገኝታ በፈነዳው ቦንብ ጉዳት ደርሶባታል፡፡ አሁንም የተወሰነ ፍንጣሪ ሰውነቷ ላይ መኖሩን ሲንከባከቧት የነበሩት ጎረቤቶቿ ይናገራሉ፡፡ በመስከረም ወር አጋማሽ የአዳነች ተስፋ ማበብ ጀመረ፡፡
በልደታ ክፍለ ከተማ የወረዳ ዘጠኝ ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት አዲስ አመራር የላስቲክ ቤቶቹ በሚገኙባቸው መንዲዳ ፣ ሃምሳ ሁለት እና ሃምሳ ሦስት ተብለው በሚጠሩ አካባቢዎች ጥናት አድርጎ መጠለያ ይገባቸዋል ያላቸውን 105 ኗሪዎች ስም ዝርዝር ለክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት አቀረበ፡፡
የወረዳ ዘጠኝ ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደጀኔ ህጉ እንደሚናገሩት የአዲሱ አመራር የመጀመሪያ ሥራ የነበረው የላስቲክ ቤቶችን መለየት ነበር፡፡ ወረዳው የመልሶ ማልማት ሥራ የሚከናወንበት ስለሆነና በአካባቢው የላስቲክ ቤቶች በብዛት ስላሉ የወረዳው ካቢኔ ቤት ለቤት በመሄድ የነዋሪው ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን አጣርቶ 105ቱ የቀበሌው ነዋሪዎች መጠለያ ሊያገኙ ይገባቸዋል የሚል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለፃ ወረዳው ለከፋ ችግር የተጋለጡ ናቸው ያላቸውን 105 ኗሪዎች የለየው ከቀጠናዎች አደረጃጀት ጋር በመሆን ነው፡፡ ከዚያም 105ቱ ላይ ሕዝቡ አስተያየት እንዲሰጥባቸው ተደርጓል፡፡ በውይይት ወቅትም የማይገባው ተካትቷል የሚል አስተያየት አልተነሳም፡፡
በተጨማሪም በየአካባቢው ስም ዝርዝራቸውን በመለጠፍ ለአምስት ቀናት ያህል ጥቆማ የሚያቀርብ ካለ በሚል ክፍት ተድርጓል፡፡ ከዚህ በኋላ ነው በወረዳው በአመራሮች እንዲተች ተደርጎ በመስከረም ወር ለክፍለ ከተማ የቀረበው፡፡ ወረዳው ቀደም ሲል በማጥራቱ ሥራ እንዲያግዘው ጥያቄ ሲያቀርብ ዝምታን የመረጠው የክፍለ ከተማው ቤቶች አስተዳደር ጽህፈት ቤት የላካችሁትን መረጃ በራሴ መንገድ አጣራለሁ በሚል ጉዳዩን ለስድስት ወራት እንዳጓተተው የሚናገሩት አቶ ደጀኔ በመጨረሻ አስሩ አይገባቸውም በማለት 95ቱን መለየቱን እንዳሳወቃቸው ይገልፃሉ፡፡
የክፍለ ከተማው ውሳኔ አሰጣጥ ግልፅ አይደለም የሚሉት የወረዳው ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ፤ ክፍለ ከተማው 95 ነዋሪዎች ይገባቸዋል ብሎ ከለየ በኋላ እንደገና መልሶ ከ95ቱ ውስጥ 65ቱን ለዩ ብሎናል፡፡ የተቀሩት በቀጣይ እንደሚያገኙም ማረጋገጫ አልሰጠንም፡፡ እንዲያውም እነርሱ አይገባቸውም የሚል አይነት አዝማሚያ አለ፡፡
የማይገባቸው ከሆነ ውሳኔያችሁን በጽሑፍ ስጡን ብለን ብንጠይቅም መልስ ሊሰጡን አልቻሉም፡፡ እነዚህ ቀሪ ሰዎች እጣ ፈንታቸው ምን እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች እያለቀሱ ነው፤ ይሰጠናል በሚል ተስፋ አድርገው እየጠበቁ ናቸው ብለዋል፡፡ በለቅሶ የታጀበ ተስፋ ሰንቀው ቤት እናገኛለን ብለው ከሚጠብቁት በርካታ የላስቲክ ቤት ኗሪዎች መካከል ወይዘሮ ጥሩነሽ ጎበና አንዷ ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት አሁን ላስቲክ ወጥረው በሚኖሩበት ሰፈር ውስጥ ነው፡፡
የእንጀራ አባታቸው ቤት ውስጥ ይኖሩ እንደነበር የሚናገሩት ወይዘሮዋ፣ የእንጀራ አባታቸው ቤተሰቦች ቤት ተሰጥቷቸው ጥለዋቸው ከሄዱ በኋላ ሜዳ ላይ መቅረታቸውን ይናገራሉ፡፡ የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወይዘሮ ጥሩነሽ አሁን እድሜያቸው 40 ደርሷል፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸው የሃያ ዓመት ወጣትና የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ በላስቲክ ቤት ውስጥ መኖር ከጀመሩ ዘጠነኛ ዓመታቸውን የያዙት እናት አኗኗራቸው እንደ ስማቸው ጥሩ አልሆነላቸውም፡፡
የቀን ሥራ በመሥራት፣ ልብስ በማጠብና በተባራሪ ሥራ የሚተዳደሩት ወይዘሮዋ፣ የትውልድ ቦታ ያለው እኮ ወደዚያ ይሄዳል እኛ ግን እዚህ ተወልደን ያደግነው ወዴት እንሄደለን ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ አቶ ይድነቃቸው ፈጠነም ተወልደው ያደጉት አሁን ላስቲክ ወጥረው በሚኖሩበት ቦታ ነው፡፡ በላስቲክ ቤት ውስጥ መኖር ከጀመሩም ስምንት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
የሦስት ልጆች አባት ነኝ የሚሉት አቶ ይድነቃቸው ህይወት በላስቲክ ቤት ውስጥ ምን እንደሚመስል ሲገልፁ “የመጀመሪያ ልጄ ስምንት ዓመቷ ነው፡፡ ላስቲክ ቤት ውስጥ ተወልዳ፣ ላስቲክ ቤት ውስጥ ነው ያደገችው፡፡ በዚህ ምክንያት ማብሪያና ማጥፊያ እንኳን አታውቅም፡፡ እንደ ማማ ወተት ላስቲክ ቤት ውስጥ እየተንቦጫቦጭን ነው የምንኖረው፡፡” ብለዋል፡፡ አያይዘውም ከዚህ ቀደም ከአንድም ሁለት ጊዜ በላስቲክ ቤት ውስጥ ለሚኖሩ ኗሪዎች ቤት መሰጠቱን ጠቅሰው እኛ እንዳናገኝ አድርገው ለይተው እዚህ ያስቀሩን ስለምንታገላቸው ነው ብለዋል፡፡
ሦስት ልጆቼን ሻይ እየሸጥኩ ነው የማስተዳድራቸው፡፡ ባለቤቴ የካንሰር ታማሚ ሆኖ አልጋ ላይ ከቀረ አራት ዓመት ሆኖታል የሚሉት ወይዘሮ ሸምሲያ መሀመድ፣ አካባቢው ከመፍረሱ በፊት ስልሳ ብር እየከፈሉ 14 ዓመታት በጥገኝነት መኖራቸውን ይናገራሉ፡፡ በወቅቱ በተደጋጋሚ ቤት እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ ማመልከቻ ለወረዳው ሲያስገቡም ወረፋ እንዲጠብቁ እየተነገራቸው መቆየታቸውን ይገልፃሉ፡፡
አካባቢው መፍረስ ሲጀምር በወቅቱ የወረዳው አስተዳዳሪ ለነበሩት አቶ አትክልቲ ልጆቼን ይዤ የት ልግባ የሚል ጥያቄ አቅርበው “መጀመሪያ እንደ እናንተ አይነት ሰው ነው የሚስተናገደው” ተብለው በተስፋ ሲጠብቁ ቢቆዩም ዘጠኝ ዓመት ሙሉ ጠብ ያለላቸው ነገር አለመኖሩን ይናገራሉ፡፡
በክፍለ ከተማው እየተፈፀመባቸው ስለለው አድሎ ሲናገሩም፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ ስለነበርን ከአንዴም ሁለቴ በአካባቢው ኗሪ ላልሆኑ ሰዎች በኛ ስም ቤት ለመስጠት ሲጥሩ አስቁመናቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በቃ እኛን ማስተናገድ አይፈልጉም፡፡ መረጃ ይጠይቁኛል፤ የኗሪነት መታወቂያ አምጪ ይሉኛል ነገር ግን ያሉኝን ሁሉ ባቀርብም ቤት አይሰጡኝም፡፡
አሁን ደግሞ ከለውጡ በኋላ ወረዳው በብዙ ነገር የተበደላችሁ ፤ የተጎዳችሁ ናችሁ በሚል ማንኛውም አይነት ቤት ቢገኝ ቅድሚያ እናንተን ነው የምናስተናግደው ብሎን በተስፋ ስንጠብቅ ብንቆይም ክፍለ ከተማው አሁንም ለእናንተ አይደለም ለሌላ ሰው ነው የምንሰጠው እያለን ነው፡፡
ቤቶች ይሰጣቸው የተባሉት ሰዎች ቤታቸው ከፈረሰባቸው ገና ሁለትና ሦስት ዓመታት ያስቆጠሩ ናቸው ብለዋል፡፡ ከወላጆቼ ቤት አጠገብ በሠራሁት ቤት ውስጥ እኖር ነበር የሚሉት በዕድሜ በአርባዎች መጀመሪያ ላይ የሚገኙት አቶ ተስፋዬ በቀለ በበኩላቸው ዘጠኝ ዓመታት ውሃ፣ መብራትና መፀዳጃ ቤት በሌለበት ሜዳ ላይ መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ያህል እዚህ ለምንኖር ሰዎች ቤት የሰጡ ቢሆንም ታማሚ ለሆኑ ሰዎች ነው የሚሉት አቶ በቀለ፣ በተደጋጋሚ ለመንግሥት አካላት ያመለከትነው ችግረኞቹ እያለን ከዚህ በፊት የማናውቃቸው ሰዎች ሁሉ ቤት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሁለት ሥስት ጊዜ ደግሞ ቤት ሊሰጣቸው ሲል አስቁመን የማይገባቸው ሰዎች እንዲወጡ አድርገናል ብለዋል፡፡ አያይዘውም ወረዳው የራሱን ሥራ ሠርቶ ጨርሶ ለእኛ ነው እየተከራከረ ያለው፣ በር እየዘጋብን ያለው ቤት የመስጠት ሥልጣንን የያዘው ክፍለ ከተማው ነው፡፡
ከ15 ቀናት በፊት ክፍለ ከተማው በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ባዘጋጀው መርሃ ግብር እኛን ዘንግቶ ለ200 ሰዎች ቤት ሰጥቷል፡፡ በተለይ ክፍለ ከተማ ላይ ያለው የቤቶች ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊና ሥራ አስፈፃሚውን እንድትጠይቁልን እንፈልጋለን፡፡ ችግራችንን ተረድተው ባፋጣኝ ከዚህ ቦታ እንዲያነሱን ነው የምንጠይቀው፡፡ በጣም ችግር ላይ ነው ያለነው ብለዋል፡፡
ከወረዳ የመጣውን መረጃ ለማጣራት ክፍለ ከተማው ባዋቀረው ኮሚቴ ውስጥ ከተሳተፉት መካከል የልደታ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ሲሳይ ልመንህ አንዱ ናቸው፡፡ ቡድን መሪው ወረዳው የላከውን መረጃ መሰረት በማድረግ ቦታው ላይ በመገኘት አጣርተናል፡፡
105 ተባለ እንጂ በቦታው ያሉት የላስቲክ ቤቶች ከተጠቀሰው ቁጥር በላይ ናቸው፡፡ በኛ በኩል አጣርተን ይገባቸዋል ብልን የለየናቸው የላስቲክ ቤቶች 95 ብቻ ናቸው፡፡ ከለየናቸው በኋላ ምላሽ ለመስጠት የዘገየነው የቤት እጥረት ስለነበረብን ነው። አሁን ግን ለእነዚህ ዜጎች 65 ቤቶች አዘጋጅተናል ብለዋል፡፡ የልደታ ክፍለ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አህመድ እንድሪስ፣ ክፍለ ከተማው ከዚህ በፊት ሁለት ጊዜ ለላስቲክ ቤት ኗሪዎች ቤቶች ሰጥቷል፡፡
አሁን መንዲዳ፣ 52 እና 53 በሚገኙት ላስቲክ ቤቶች ውስጥ ያሉት ኗሪዎች የተወሰኑት በጊዜው የነበሩና አይመለከታቸውም ተብለው የተቀነሱ፤ ቀሪዎቹ ደግሞ በጊዜው አቅም ስላልነበረ በቤት እጦት ያልተስተናገዱ ናቸው ብለዋል፡፡ ወረዳው ላይ ብዙ ቤት የለም፤ ለእነዚህ ኗሪዎች ቤት የምንሰጠው በሌሎች ወረዳዎች ውስጥ ነው የሚሉት የጽሕፈት ቤት ኃላፊው፤ የክፍለ ከተማው ካቢኔ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ጥያቄ ስላስተናገደ ከቦታዎቹ በሚቀርቡ የቤት ጥያቄዎች ላይ እምነት አጥቷል፡፡
ባሉን አስር ወረዳዎች ለሃያና ለሰላሳ ዓመት የቤት ጥያቄ እያቀረቡ ያልተስተናገዱ ኗሪዎች አሉን ብለዋል፡፡ ክፍለ ከተማው ከ15 ቀናት በፊት 200 ቤቶችን ሲሰጥ እነዚህ የላስቲክ ቤት ኗሪዎች ለምን እንዳልተካተቱ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ እውነት ነው አልተካተቱም ነገር ግን ከ200ዎቹ ቤቶች ውጭ 35 ቤቶች ለላስቲክ ቤት ኗሪዎች አዘጋጅተን ነበር፤ አብረው ያልተላለፉት የላስቲክ ቤት ኗሪዎቹ መረጃ ስላልተጣራ ነው ብለዋል፡ ፡
አያይዘውም ክፍለ ከተማው በቅርቡ በአነስተኛ ዋጋ ተከራይተው መኖር ለሚችሉ 90 የሚደርሱ የ10/90 ቤቶች ሲሰጠው 30ዎቹን ቤቶች በላስቲክ ቤት ላሉት ነዋሪዎች መመደቡን ጠቅሰው በድምሩ 65 ቤቶችን ለመስጠት ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ክፍለ ከተማው ያዋቀረው ኮሚቴ ይገባቸዋል ብሎ የለያቸው 95 ኗሪዎች ናቸው፤ ቤት የተዘጋጀው ግን ለ65ቱ ነው የተቀሩት 30 ነዋሪዎችስ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ሁሉም የተለዩት የላስቲክ ቤቶች ጉዳያቸው ለካቢኒ ቀርቦ እስካሁን ያልተስተናገደ ቅድሚያ ይሰጠው የሚል ውሳኔ ተላልፏል፡፡
ስለዚህ ከሁለትና ከሦስት ዓመት በፊት ቤታቸው ለፈረሰባቸው የመንዲዳ ኗሪዎች ነው ቅድሚያ የምንሰጠው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ 52 ያሉት ላስቲክ ቤቶች እንዲስተናገዱ እናደርጋለን ቀሪዎቹ ሰላሳ ነዋሪዎች ቤት ማግኘት አለባቸው ብለን አልወሰንንም በቀጣይም ስለማግኘታቸው የምሰጠው ማረጋገጫ የለም ብለዋል፡፡
ከሦስቱ የላስቲክ ቤት መንደሮች 45 ነዋሪዎችን በመያዝ ትልቁ የሆነውንና ዝግጅት ክፍላችን ሲያናግራቸው አድሎ ይፈፀምብናል ያሉት አብዛኞቹ ነዋሪዎች የሚገኙበትን 53ን አስመልክተው ሲናገሩም፣ 53 በጣም ብዙ ኗሪ እንዳለ እናውቃለን፡፡
እኛ ለጽሕፈት ቤቱ አዲስ ነን፤ በቅርብ ነው የመጣነው፡፡ ነባር ካቢኔዎች ግን እዚያ አካባቢ እጃችንን አናስገባም እስከማለት ደርሰዋል፡፡ አሁንም እዚያ ቦታ ላይ የከፋ ችግር አለባቸው ብሎ የወረዳው ካቢኔ ካመነ ወደፊት በክፍለ ከተማው በካቢኔ ደረጃ በድጋሚ የሚታይ ይሆናል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2011
የትናየት ፈሩ