አዲስ አበባ፡- ኢህአዴግ የቀድሞ ጥምረቱ የሌለ የሚመስላቸው አራቱ ፓርቲዎች የልዩነት ሃሳቦች ሲኖሩዋቸው በውስጣዊ ውይይት ብቻ ይገድቡት የነበረውን አቋማቸውን በአደባባይ በመግለፃቸው መሆኑን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ፓርቲዎቹ ልዩነቶቻቸውን በአደባባይ መግለፃቸው በውስጣቸው መከፋፈል እንዳለ ግንዛቤ መውሰድ ስህተት እንደሆነና ይህንን አይነቱን አቋም በአደባባይ የመግለፅ አካሄድ ወደፊትም እንደሚቀጥል፤ ተግባራዊ የሚሆነውም በጋራ በሚወሰን ውሳኔ እንደሚሆን፤ የተጀመረው የመዋሐድ ሂደትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
« የፌዴራል መንግሥት ተዳክሟል ለማለት መለኪያው መሆን ያለበት አገር ስትወረር መመከት ሲያቅተው፣ ዲፕሎማሲያዊ ሥራዎችን በብቃት መመከት አልችል ሲል ነው፤ አሁን ግን በዚህ መልኩ የሚገለፅ አንዳችም ተግዳሮት አልገጠመንም፤ በክልሎች የሚፈጠሩ ችግሮች ላይ ጣልቃ የማንገባው ችግሮችን በራሳቸው መፍታት አለባቸው ብለን ስለምናምን ነው። ይህ ደግሞ ተገቢ ነው» ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ የበላይነትን አስመልክተው አሁን ሕዝቡ ዴሞክራሲን እየተለማመደ እንደሆነ፣ ነገር ግን በህብረተሰቡ በኩል ግዴታን የመወጣት ችግር መኖሩን፣ ባለፈው ሥርዓት መንግሥት አለ የሚባለው ጠጠር ያለ እርምጃ በመውሰዱ እንደነበርና አሁን ላይ መንግሥት ሆደ ሰፊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሆደ ሰፊ መሆን የሕግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ መግባቱን እንደማያሳይ፣ በሶማሌ 30ሺ ወታደር ይዘው በተደራጀ መንገድ ችግር ለመፍጠር የተሞከረው በመንግሥት መክሸፉንና 47 ሰዎች የፍርድ ሂደታቸው እየታየ መሆኑን እንደማሳያ ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቡራዩ በነበረው ችግር 108 ሰዎች፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ 2ሰዎች ጉዳያቸው በሕግ እየታየ መሆኑን፣ በሻሻመኔ ተከስቶ በነበረው ችግር ተሳትፎ ያደረጉ ሁለት ሰዎች የእድሜ ልክ እሥራት እንደተፈረደባቸው፣ የፍርድ ሂደቱም ከዚህ ቀደም እንደነበረው የጅምላ እሥራት ሳይሆን በማጣራት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ምዕራብ ወለጋ ከኦነግ ሽኔ ጋር መግባባት እንዳልነበር በመጥቀስ፤ ባልተገባ መንገድ የመንግሥት ቢሮዎችን ለሌላ ጉዳይ ማዋል፣ ማሰርና መግደል የመሳሰሉ ችግሮች እንደነበሩ፤ በክልሉ ጥያቄ መሠረት የፌዴራል መንግሥት ገብቶ ሠላም እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀደም ሲል በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች መካከል ከባድ ውጊያ መፈፀሙንና ሰው መሞቱን በማስታወስ፤ በግጭት ጥያቄን በዘላቂነት መመለስ እንደማይቻል ገልፀው፤ በአማራና በትግራይ የድንበር ይገባኛል ጥያቄ ቢኖርም እስካሁን ተኩስ እንዳልነበረ፤ ሁለቱ ክልሎች አንዱ አንዱን ቢወጋ አገርን እንደወጋ እንደሚቆጠርና ለዚህም የኢትጵያ ህዝብ ዝም ብሎ እንደማይመለከት ተናግረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ጉዳይን በተመለከተ አንዳንድ ኃይሎች በአልባሌ ጉዳይ ጊዜያችንን እንድናባክን እያደረጉን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አዲስ አበባ ከየትም አካባቢ የሚመጡትን ሕዝቦች የምታቅፍ ከተማ መሆኗን፤ ለአብነትም በግጭት ምክንያት ከኤርትራና ከሞቃዲሾ የመጡ ዜጎች እየኖሩባት እንደሆነ፤ የአዲስ አበባ አጀንዳ መሆን ያለበት ከተማዋ በልማት ልትቀየር በምትችልበት ጉዳይ ላይ ብቻ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በአዲስ አበባ ጉዳይ ሕገ መንግሥቱ ይከበር የሚለው ሃሳብ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበትና ከተማዋን የኢንዱስትሪ መዲና ማድረግ እንደሚገባ፣ አንዱ ሲጠቀም ሌላው መጎዳት እንደሌለበት፣ አዲስ አበባ ላይ የሚኖሩ በኦሮሚያ ላይ ችግር ሊፈጥሩ ነው ተብሎ የሚናፈሰው ወሬም መሠረት ቢስ እንደሆነና ወሰን የአስተዳደር እንጂ የድንበር ጉዳይ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብና ቤቶች ቆጠራ ሂደት ሲባል ኮሚሽን መቋቋሙን፣ ቆጠራውም በምክር ቤቱ እንዲራዘም መደረጉንና ቆጠራው ሲካሄድም አንዱን ህዝብ ከፍ ለማድረግ ሌላውን ለማሳነስ ተደርጎ መታሰብ እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣኑን በተረከቡበት ወቅት 20 ቢሊዮን ብር የደመወዝ ጥያቄ መኖሩንና በወቅቱ አገሪቷ ዕዳ መክፈል የማትችልበት ደረጃ ላይ እንደነበረች፣ በዓመት 400ቢሊዮን ዕዳ መክፍልም ይጠበቅባት እንደነበር ገልፀው፤ በመንግሥት ጥረት በረጅም ጊዜ የሚከፈልና በስጦታ መልክ ተጨማሪ ሦስት ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡
ከኤርትራ ጋር ያደረግነው ስምምነት መሰረት ያደረገው ሠላምን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በቀጣይ በኢኮኖሚ፣ በንግድን እና መሰል በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለመስማማት በሂደት ላይ መሆናቸውንና ከህዝብ የተደበቀ ሌላ ስምምነት እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
ዲያስፖራው አገሩን ለመደገፍ የጀመረውን መንገድ ሊገፋበት እንደሚገባ፤ ይሁን እንጂ በማህበራዊ ሚዲያ በሚወጡ መረጃዎች ተስፋ የመቁረጥ ነገር እንደሚታይና ይህ ተገቢ እንዳልሆነ፤ ሁሉም ነገር መግባባት በተደረገበት መልኩ እየሆነ እንዳለ፤ ወደኋላ ማለት እንደማያስፈልግም ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 20/2011
አዲሱ ገረመው