በስፖርቱ ዓለም ስፖርታዊ ጨዋነት ወርቃማው ህግ ነው። ይህ ስፖርታዊ ጨዋነት በተለያየ መልኩ የሚገለጽና የሚተረጎምም ነው። ተጋጣሚን ወይም ተፎካካሪን ፍትሃዊ ባልሆነ መልኩ ማሸነፍና ለማሸነፍ ሲባልም በስፖርታዊ ህጎች ባያስጠይቅ እንኳን በተለያየ መንገድ ፍትሃዊ ያልሆነ ጥቅምን(አድቫንቴጅ) በተጋጣሚ ላይ መውሰድ የአሸናፊዎች ባህሪ አይደለም። የራሳቸውን ጥቅም ብቻ የሚያባርሩ ሌላው ይውደቅ ይነሳ ደንታ የሌላቸው በበዙባት አለም ግን አንዱ የአንዱን ድክመት ተጠቅሞ አሸናፊ ሆኖ መገኘት እንጂ ለህሊና መቆም ዋጋ እያጣ መቷል። ያም ሆኖ ለህሊናቸውና ለፍትህ የቆሙ ጥቂቶች ባገኙት አጋጣሚ በሚሰሩት በጎ ነገር ለበርካቾች ምሳሌና ትምህርት ሲሆን ይስተዋላል።
የስፖርቱ አለም ህጎች ባያግዷቸውም በህሊናቸው ዳኝነት እየተመሩ ማሸነፍ እየቻሉ “ለእኔ አይገባም” ብለው ድልን ለተፎካካሪያቸው አሳልፈው የሚሰጡ በርካታ ምሳሌ የሆኑ የስፖርቱ አለም ሰዎችን በታሪክ አጋጣሚ ተመልክተናል። በእግር ኳስ ፍልሚያ ላይ ዳኛ በስህተት የሰጠውን ፍጹም ቅጣት ምት አስቆጥረው ማሸነፍ ሲችሉ ፍትሃዊ ባለመሆኑ ሆን ብለው የግብ እድሉን የሚያመክኑ በርካታ ተጫዋቾችን ተመልክተናል። አሸንፈው የተሸለሙትን ሜዳሊያ ከአንገታቸው አውልቀው ለተፎካካሪዬ ነው የሚገባው ብለው ለባላንጣቸው ያጠለቁም ጥቂት አይደሉም። ብዙ ጊዜ በተለያዩ ማህበራዊ ገጾች የሚዘዋወር አንድ ፎቶ ግራፍ ግን የስፖርታዊ ጨዋነት ጥግ ሆኖ ብዙዎች እንዲማሩበት አድርጓል።
ይህ ፎቶ ግራፍ እኤአ 2012 ላይ በስፔን በተካሄደ አንድ አገር አቋራጭ ውድድር ላይ የተነሳ ነው። ታሪኩም እንዲህ ነው። ኬንያዊው አትሌት አቤል ሙታይ በአድካሚው የአገር አቋራጭ ውድድር መገባደጃ ላይ እየመራ የድሉን ክር ለመበጠስ ይቃረባል። ውድድሩን አሸንፎ ሜዳሊያውን ለማጥለቅ ጥቂት ሜትሮች ሲቀሩ ግን ይህ አትሌት የውድድሩን መጠናቀቅ የሚያበስሩ ምልክቶች ያ ወ ዛ ግ ቡ ታ ል ። ውድድሩን ሳይጨርስ ያጠናቀቀ መስሎትም ይቆማል። በቅርብ ርቀት ሲከተለው የነበረው ስፔናዊው አትሌት ኢቫን ፈርናንዴዝ የተወዛገበውን ኬንያዊ አትሌት ሁኔታ ደርሶበት በተረዳ ጊዜ ጥሎት በማለፍ ለማሸነፍና ሽልማቱን ለመውሰድ አልጓጓም። ይልቁንም ኬንያዊው አትሌት መሳሳቱን ተረድቶ ውድድሩን እንዳልጨረሰና መሮጡን እንዲቀጥል ጮክ ብሎ ሊያስረዳው ሞከረ። ኬንያዊው አትሌት ግን ሰምቶ አልሰማውም በቆመበት ጸና፣ምክኒያቱም ተፎካካሪው የሚናገረውን የስፓኒሽ ቋንቋ መስማት ወይም መረዳት አይችልም ነበር።
ስፔናዊው አትሌት ፈርናንዴዝ አሁንም ግራ የገባውን ኬንያዊ አትሌት ጥሎት በመሮጥ ወርቅ የማጥለቅ እድሉ ከእጁ አልወጣም። ማሸነፍ እየቻለ አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶች ግራ አጋብተውት የቆመውን አትሌት ድል ለመንጠቅ ግን ህሊናው አልፈቀደለትም። ወደ ቆመበት ተጠግቶ ግራ የተጋባውን አትሌት እጅ ይዞ ወደ ፊት በማስቀደም እየመራው ውድድሩን በቀዳሚነት እንዲያጠናቅቅ ረዳው።
“ለምን እንዲህ አደረክ” ኢቫን ከውድድሩ በኋላ በአንድ ጋዜጠኛ የቀረበለት አጭር ጥያቄ ነበር። የስፖርታዊ ጨዋነትን ጥግ በዚህ ውድድር በተግባር ለአለም ሕዝብ ያሳየው አትሌት “ህልሜ አንድ ቀን ሌሎች አሸናፊ እንዲሆኑ የሚረዳ ማህበረሰብ ተፈጥሮ ማየት ነው” የኢቫን አጭርና አንጀት የሚበላ ምላሽ ነበር።
ጋዜጠኛው ጥያቄውን ቀጠለ “ግን ለምን ኬንያዊው አትሌት እንዲያሸንፍ ፈቀድክለት”? የኢቫን መልስ አሁንም አጭርና ግልጽ ነው “እንዲያሸንፍ አልፈቀድኩለትም፣ ውድድሩን ያሸንፍ ነበር፣ ይህ የእሱ ውድድርና ድል ነው”።
ጋዜጠኛው አሁንም ጥያቄውን አልጨረሰም ደግሞ ጠየቀው” ግን እኮ አንተ ማሸነፍ ትችል ነበር”። ኢቫን ጋዜጠኛውን ትክ ብሎ እየተመለከተው ጥያቄውን በጥያቄ መለሰ” የእኔ ማሸነፍ ትርጉሙ ምንድነው?፣የዚህ ድልና ሜዳሊያ ክብርስ ምኑ ላይ ነው?እናቴ ይህን ውድድር በዚህ መንገድ ባሸንፍ ምን ልታስብ ትችላለች?፣ ከዚህ ድል ይልቅ በጎ ተግባሮች ከትውልድ ወደ ትውልድ ተሸጋግረው አስተማሪ ይሆናሉ”።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን እሁድ ሐምሌ 17 ቀን 2014 ዓ.ም